Thursday, February 29, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የኢትዮጵያ ፈርጀ ብዙ የኢኮኖሚ ችግሮች ምክንያቶቻቸውና መፍትሔዎቻቸው

በአመሃ ዳኘው ተሰማ

የአገራችን ኢኮኖሚ ከኮቪድና ከእርስ በርስ ጦርነቱም በፊት የነበረበት ሁኔታ አስከፊ ነበር። አሁን የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ያስከተለው ተፅዕኖ ሲጨመርበት ኢኮኖሚውን ከድጡ ወደ ማጡ በማስገባት የከፋ የችግር አረንቋ ውስጥ ከቶታል፡፡ መንግሥት ለራሱ እንዲስማማ እያደረገ በሚያወጣው መረጃ መሠረት በ2014 ዓ.ም. የዋጋ ግሽበቱ 38.9 በመቶ እንደነበር ቢገለጽም፣ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ ከ50 በመቶ በላይ እንደሆነ ነው አንዳንድ መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡ የምግብ የዋጋ ግሽበት 57 በመቶ በላይ ሆኗል፡፡ ይህ የስታትስቲክስ መሥሪያ ቤት የሚያወጣው መረጃ ሲሆን፣ በተግባር ማንም ገብያ ወጥቶ አስቤዛ የሚሸምት ሰው እንደሚያውቀው የምግብ ዋጋም ሆነ ሌሎች ከአስቤዛ ጋር የሚሄዱ ሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ ባለፉት ዓመታት ከነበሩበት ከሦስት እስከ አምስት እጥፍ መጨመሩን በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል። የመንግሥት ገቢና ወጪ ብቻ ሳይሆን የአገራችን የንግድ ሚዛን መዛባት፣ የዕዳ ጫናው እየከበደ መምጣት ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የኢኮኖሚ ሁኔታውን አስፈሪና አሳሳቢ አድርጎታል፡፡

  በዚህ በያዝነው አዲስ ዓመት በኢትዮጵያ የተመዘገበው የዋጋ ንረት ምጣኔ ከሰሃራ በታች ካሉ አፍሪካ አገሮች በልጦ ተገኝቷል፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት በተለይም ለእርሻ ምርት መጨመር እንዲሁም፣ የግብርና ምርቶችን በግብዓትነት የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎችን ምርት ለመጨመር ዋነኛ ግብዓት የሆነው መሬት ከኢኮኖሚ አገልግሎት ይልቅ የኦሕዴድ/ብልፅግና መንግሥት በሚከተለው የነገድ ፖለቲካ ምክንያት የፖለቲካ መሣሪያነቱ አመዝኖ እንዲገኝ በመደረጉ ነው፡፡ የኢኮኖሚ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እ.ኤ.አ. በ1996 በኢትዮጵያ ለግብርና ምርት ሊውል ይችል የነበረው የመሬት አቅርቦትና አጠቃቀም 91 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ ይህ አኃዝ በ2022 ወደ 16 በመቶ ዝቅ ማለቱ ለዚህ አባባል ዋነኛ አመላካች ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ ከተከሰተ የቆየው የፖለቲካ አመለካከት ጽንፈኝነትና የነገድ ፖለቲካ እየተካረረ መምጣቱ የአገራችንን የፖለቲካ ምኅዳር አልፎ የኢኮኖሚውን ሁኔታ እያናጋ መምጣቱ አሌ ሊባል የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ በአገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ የመጣው የዋጋ ንረት፣ ንረቱን ተከትሎ የጨመረው የኑሮ ውድነትና ብልሹ የግብይት ሥርዓት ዋነኛው ምክንያት የመንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች የሚነደፉበትን ወይም የሚቀዱበትን ዘውጋዊ የሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ተመርኩዘው ተግባራዊ የሚደረጉ የኢኮኖሚ መርሐ ግብሮች በገበያ ሕግ ሳይሆን፣ አድሏዊ በሆነ የጥቅም ግንኙነት (Patronage Network) አማካይነት የሚመሩ እንዲሆኑ በመደረጋቸው ነው፡፡

 በአገራችን ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት እየጨመረ መምጣቱ ሕዝቡ እሮሮውን በየጊዜው የሚያሰማበት ጉዳይ ሆኗል። በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣው የኑሮ ውድነት እየተባባሰ እንዲሄድ ያደረጉ ምክንያቶች በርካታ ቢሆኑም፣ እንደ ዋና ዋና ሊቆጠሩ የሚገባቸው ስድስት እንደሆኑ ፓርቲያችን ባልደራስ ያምናል፡፡ እነርሱም፡-

 1. የግብርና ምርታማነት ከሕዝብ ቁጥር ዕድገት መጨመር ጋር አብሮ ሊሄድ አለመቻል አንዱ ነው፡፡ በአገራችን በአሁኑ ጊዜ ያለው ምርታማነት በንጉሡ ዘመን ከነበረው ምርታማነት እምብዛም የተራራቀ አይደለም፡፡ ይህም ከሕወሓት ዘመን ጀምሮ አሁንም የኦሕዴድ/የብልፅግና ፓርቲ ከሚከተለው የመሬት ፖሊሲ የመነጨ ነው፡፡ በንጉሡ ዘመን አማካይ የነበረው የግብርና ምርታማነት 9 በመቶ ሲሆን፣ በአሁኑ ዘመን ያለው አማካይ የግብርና ምርታማነት 12 በመቶ ነው፡፡ በአንፃሩ በንጉሡ ጊዜ የነበረው አማካይ የሕዝብ ቁጥር ከሠላሳ ሚሊዮን ያልበለጠ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ የአገራችን ሕዝብ ቁጥር ወደ አንድ መቶ ሃያ ሚሊዮን እንደሚጠጋ ይታመናል፡፡ ይህም የ400 በመቶ ዕድገት ነው፡፡
 2. የአገሪቱ የብር መጠን በየጊዜውና በተከታታይ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ምርትና አገልግሎት ለማዘዋወር ከሚያስፈልገው መጠን በላይ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ በሚወስደው ብድር መልክ እያሳተመ ገበያው ውስጥ እንዲገባ የሚያደርግበት አሠራር ሌላው ነው፡፡ ይህ የአጠቃላይ የኢኮኖሚውን ዕድገት ምጣኔ ያላገናዘበ (Excess Money Supply) የገንዘብ ፖሊሲ በሕወሓት ዘመን የተጀመረ ቢሆንም፣ በኦሕዴድ/ብልፅግና ዘመን በከፍተኛ ደረጃ ተባብሷል፡፡ መንግሥት ይህን የሚያደርገው የበጀት ጉድለቱን ለማሟላት ነው፡፡ መንግሥት የበጀት እጥረቱን ሲያሟላ የቆየው በአገር ውስጥ ብድር፣ ከውጭ በሚገኝ ብድርና ዕርዳታ ነው፡፡ በአገር ውስጥ የመንግሥት ብድር የሚሸፈነው ከንግድ ባንክ በሚገኝ ብድርና ቀሪው በብሔራዊ ባንክ አማካይነት አዲስ ገንዘብ ታትሞ ለመንግሥት የመደበኛ ወይም የካፒታል በጀት መሸፈኛ እንዲውል በማድረግ ነው፡፡

ለምሳሌ በአገራችን ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት ማለትም በ2000 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ውስጥ በሰው ኪስ፣ በትራስ ውስጥ የተደበቀው፣ በግልና በመንግሥት ድርጅቶች ሒሳብ ውስጥ የነበረው ጠቅላላ የብር መጠን 67 ቢሊዮን ብር ብቻ ሲሆን፣ ከአሥራ ሦስት ዓመታት በኋላ ማለትም 2013 ዓ.ም. በኢኮኖሚው ውስጥ ሲዘዋወር የነበረው ገንዘብ 870 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህም የገንዘብ አቅርቦቱ (Money Supply) 1,298 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን ያመለክታል፡፡ ባለፈው እ.ኤ.አ. በ2021 የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ ላይ መንግሥት ብሔራዊ ባንክን በማዘዝ በአዲስ እንዲታተም ያደረገው የብር መጠን 83.5 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ከ2020 ከነበረው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲያነፃፀር የ169.4 በመቶ ዕድገት እንደነበረው የብሔራዊ ባንክ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የገንዘብ አቅርቦቱ ከአጠቃላይ ብሔራዊ ምርት (GDP) ከ12 በመቶ በላይ ከሆነ ውጤቱ የዋጋ ንረትን መጨመር እንደሆነ የኢኮኖሚ ጥናቶች ይጠቁማሉ። በኢኮኖሚው ውስጥ እየናረ ለመጣው የዋጋ ንረት አንዱ ዓይነተኛ ምክንያት ይህ በየጊዜው እየታተመ ወደ ገበያ ውስጥ እንዲሠራጭ የሚደረገው በምርትና አገልግሎት ያልተደገፈ ሌጣ ብር ነው።

 1. ከሕወሓት ኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመን ጀምሮ እስከ ተተኪው የብልፅግና አገዛዝ ድረስ የቀጠለው የብርን የምንዛሪ ዋጋ የማርከስ (Devaluation) ፖሊሲ ለአገራችን ኢኮኖሚ ቀውስና ቀውሱን ላስከተሉት የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ሌላው ዓይነተኛ ምክንያት ነው፡፡ ሕወሓትም ሆነ ብልፅግና ለዚህ ፖሊሲያቸው የሚሰጡት ምክንያት የብር የምንዛሪን ዋጋ ማርከስ የአገሪቱን የወጪ ንግድ ያበረታታል የሚል ነው። ይህ የመንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላለፉት አሥራ አምስት ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየ ቢሆንም፣ እንደ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የምርትና የአገልግሎት አቅርቦት እጥረት (Supply Constraint) ባለበት ሁኔታ የብርን ዋጋ በማርከስ የውጭ ንግድን ማበረታት አይቻልም፡፡

በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ለውጭ ንግድ የሚላኩ ምርቶች አቅርቦት ከፍላጎት በላይ ሆኖ አያውቅም፡፡ እንዲያውም ለውጭ ንግድ የሚላኩ ምርቶች ሁሉም ለማለት በሚቻልበት ሁኔታ ከአገር ውስጥ ፍጆታ እየተቀነሱ እንጂ የአገር ውስጥ ፍላጎትን አሟልተው አያውቁም፡፡ ለምሳሌ ሥጋ፣ ፍራፍሬና ሰሊጥ እንዲሁም ሌሎች የአገር ውስጥ ምርቶች የአገር ውስጥ ዋጋቸው ለውጭ ገበያ ሲቀርቡ ከሚያስገኙት ዋጋ  የበለጠ ነው። ወደ ውጭ የሚላኩት የውጭ ምንዛሪ ስለሚያስፈልግ ብቻ ነው፡፡ የእነዚህ ምርቶች የአገር ውስጥ ፍጆታ ተቀንሶ ወደ ውጭ በሚላኩበት ጊዜ፣ የገበያ አቅርቦታቸው ከፍላጎት ያነሰ ስለሚሆን በአገር ውስጥ የሚኖራቸው ዋጋ እየጨመረ ይሄዳል፡፡

ባለፉት በርካታ ዓመታት ኢትዮጵያ ከውጭ ንግድ የምታስገኘው ገቢ በአማካይ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር እስከ 3.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሆኖ አያውቅም፡፡ ባለፈው ዓመት መጨረሻ አገራችን ከውጭ ንግድ ያገኘችው ገቢ 4.1 ቢሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት የሚላከው ምርት በማደጉ ሳይሆን፣ እንደ አጋጣሚ ሆኖ በ2014 ዓ.ም. በዓለም ገበያ ላይ የወርቅ ዋጋ በ700 በመቶ በመጨመሩና የቡናም ዋጋ ከበፊቱ ዓመት ጭማሪ በማሳየቱ ነው፡፡

ይህ ብር ከአሜሪካ ዶላር ጋር ያለውን የምንዛሪ ምጣኔ የማርከስ (Devaluation) ፖሊሲ መንግሥት የውጭ ንግድን ለማበረታታት የሚል ሽፋን ይስጠው እንጂ፣ ትክክለኛና እውነተኛ ምክንያቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ‹‹የእናት ጓዳ›› የሚሏቸው የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ለሚሰጧቸው ብድሮች፣ በአስገዳጅነት ከሚቀርቡት ቅድመ ሁኔታዎች መካከል አንዱ ቅደመ ሁኔታ (Conditionality) በመሆኑ ነው፡፡ መንግሥት የእነዚህን ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ብድርና ድጎማ እስከ ፈለገ ድረስ፣ በግዳጅነት የተጫነበት ፖሊሲ መሆኑን ለሕዝብ የማይገለጸው ምስጢሩ ነው፡፡ ሕወሓት ሥልጣን በያዘበት እ.ኤ.አ. በ1991 (1983 ዓ.ም.) እና ባለፈው ዓመት እ.ኤ.አ. በ2022 (2014 ዓ.ም.) መካከል የብር የምንዛሪ መጠን ከብር 2.07 ለአንድ አሜሪካ ዶላር ወደ 52 ብር ለአንድ የአሜሪካ ዶላር የረከሰ ሲሆን፣ ይህም በእነዚህ ዓመታት የኢትዮጵያ ብር የረከሰበት መጠን ከ2,426 በመቶ በላይ ሆኗል ማለት ነው፡፡ በኢኮኖሚው ውስጥ በእጅጉ እየናረ ለመጣው የዋጋ ንረት ሌላው ዓይነተኛ ምክንያት ይህ የብርን የምንዛሪ ምጣኔ የማርከስ ፖሊሲ ነው፡፡

 1. ከገበያ ኢኮኖሚ መርሆ ውጭ በነገድ ፖለቲካ ተፅዕኖ የተዋቀረውና የተበላሸው የግብይት ሥርዓት ሌላው ለዋጋ ንረት በከፍተኛ ደረጃ መጨመር ዓብይ ምክንያት ነው፡፡ የገበያ ኢኮኖሚ በሰፈነባቸው ምዕራባውያን አገሮች በንግድ ዘርፍ ያለው የትርፍ መጠን በአማካይ ከ15 እስከ 20 በመቶ ሲሆን፣ በአገራችን የነጋዴው የትርፍ መጠን ከ100 በመቶ እስከ 200 በመቶ፣ አንዳንድ ጊዜ ከዚህም በላይ እንደሆነ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ጥናት ያረጋግጣል፡፡

የአገራችን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ካዘጋጇቸው አንዳንድ ጥናቶች ለመገንዘብ እንደሚቻለው፣ በአሁኑ ጊዜ ከ500,000 በላይ በችርቻሮ የተሰማሩ ነጋዴዎች ሲኖሩ፣ ዋና ዋና ትልልቅ የጅምላ አስመጭዎችና አከፋፋዮች ከ30 እና 40 እንደማይበልጡ ይጠቁማሉ። ከሕወሓት ዘመን ጀምሮ በብልፅግና የአገዛዝ ዘመንም የቀጠለው መንግሥት ከእነዚህ ዋና የጅምላ አስመጭዎችና አከፋፋዮች ጋር ያለው ግንኙነት በኪራይ ሰብሳቢነት ግንኙነት ላይ የተመሠረተ መሆኑ፣ ሌላኛው ለዋጋ ንረት ምክንያት እንደሆነ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ያካሄዷቸው ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

በዚህ ግንኙነት ምክንያት የመንግሥት አግባብ ያላቸው ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቶች እነዚህን ዋና ዋና አስመጭና አከፋፋይ ድርጅቶች እንዲቆጣጠሯቸው አይፈለግም። በአንፃሩ እነሱ መሥሪያ ቤቶቹን ተቆጣጥረዋቸዋል ማለቱ ይቀላል፡፡ በፕሮፓጋንዳ ደረጃ መንግሥት ለዋጋ ንረቱ መጨመር አነስተኛ ነጋዴዎችን በስግብግብነት ቢወነጅልም፣ ለዋጋ ንረቱ ቅጥ ማጣት የጅምላ አስመጭዎችና አከፋፋዮች ለቸርቻሪዎች በምን ያህል ዋጋ እንደሚያከፋፍሉ ገበያን የመቆጣጠርና የማረጋጋት ሚና አለኝ የሚለው የንግድና የቀጣናዎች ትስስር ሚኒስቴር ሲተነፍስ አይሰማም፡፡ ገበያን ለማረጋጋት ኃላፊነት የተሰጣቸው መንግሥታዊ ተቋማት ተልዕኳቸውን በሚገባ አለመወጣታቸው ለዋጋ ንረቱ መባባስ አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩ የሚካድ አይደለም፡፡

 1. ተቋማዊ ሙስና፡- ከታች እስከ ላይ በመንግሥት ቢሮክራሲ ውስጥ የተንሰራፋው ሙስና በሰጪው ዘንድ እንደ መደበኛ ወጪ እየተቆጠረ፣ የዋጋ ንረቱን ወደ ተጠቃሚው ኅብረተሰብ ማስተላለፍ የተለመደ ክንውን ሆኗል። በሕዝቡ ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የዋጋ ንረት ተመርኩዞ ለሚከሰተው የኑሮ ውድነት አንዱ ዓይነተኛ ምክንያት ተቋማዊ ሙስና ነው፡፡ ይህን ምክንያት በተመለከተ ማስተዋል የሚያስፈልገው በአገራችን ያለው ሙስና በግለሰብ ባለሥልጣናት የሚፈጸም አስተዳደራዊ/ቢሮክራሲያዊ ሙስና ላይ ብቻ የተገደበ ሳይሆን፣ ወደ ተቋማዊ ሙስና (Institutional  Corruption) ደረጃ የተሸጋገረ የመሆኑ ገዳይ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ሙስና ከአስተዳደራዊ/ቢሮክራሲያዊ ሙስና ደረጃ አልፎ ተቋማዊ ሙስና ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አስተዳደራዊ ሙስና ማለት የመንግሥት ባለሥልጣኖች ለራሳቸው የግል ጥቅም ለማግኘት ሲሉ፣ በሥራ ላይ ያሉ ሕጎችን በማጣመም ወይም እንደሌሉ በመቁጠር የሚፈጽሙት ሕገወጥ የግል ብልፅግና የማግኘት ዘይቤ ነው፡፡ በአንፃሩ ተቋማዊ ሙስና የሚባለው ግን በሕወሓት/ኢሕአዴግ የአገዛዝ ዘመን በጉልህ እንደታየው ገዥ ፓርቲው በበላይነት የሚመራቸውን የመንግሥት ተቋማት ማለትም የሕግ አውጭውንና አስፈጻሚ ተቋማትን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር፣ በሥራ ላይ ያለውን ሕግ ለፓርቲውና ፓርቲው ቆሜለታለሁ ለሚለው የተወሰነ  የኅብረተሰብ ክፍል እንዲጠቅም በማድረግ ሕግ የመደንገግን፣ እንደ ብሔራዊና የንግድ ባንኮች ያሉ የፋይናንሰ ተቋማት ለገዥ ፓርቲው ኩባንያዎች መገልገያ መሣሪያ ማድረግን፣ ከአገሪቱ ሕግ ውጪ የፓርቲ ኩባንያዎች እንደ ግል የአክሲዮን ኩባንያዎች እንዲመዘገቡ በማስደረግ፣ በአገርና በሕዝብ ሀብት እንደፈለጉ እንዲጠቀሙበት ማድረግን ያጠቃልላል። በአጠቃላይ ‹‹መንግሥትን በምርኮ በመያዝ›› (State Capture) እና በመንግሥት ውስጥ ‹‹ሥውር መንግሥት›› (Shadow State) በማቋቋም፣ የገዥ ፓርቲው ጉምቱ አባላት ፓርቲው ሙሉ በሙሉ በሚቆጣጠራቸው ቁልፍ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ወሳኝ ባለሥልጣናት እንዲሆኑ በመመደብ ‹‹መንግሥትን የውንብድና ማስፈጸሚያ መሣሪያ›› (Criminalization of the State) ሲያደርጉት ነው፡፡

 በልማት ኢኮኖሚ ጥናት (Development Studies) ይህ ክስተት በዚሁ (Criminalization of the State) በተሰኘው ስያሜው የሚታወቅ ሲሆን፣ ይህ ክስተት ዕውን በሆነበት አገር መንግሥት የሚባለው ተቋም ከፊት ለፊት በሚታዩት ባለሥልጣናት ሳይሆን ‹‹ሥውር መንግሥቱን›› ተቧድነው በሚመሩት ለፓርቲው ታማኝ በሆኑ ከፍተኛ ካድሬዎች አማካይነት መንግሥታዊ ውንብድናን መፈጸም የመንግሥት ቋሚ ተግባር የሆነበት ሁኔታ ነው፡፡ ይህ ክስተት በአገር ሀብት አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ መዛባትን በመፍጠር የአገር ሀብት ከመካከለኛውና በስፋት ከሚገኘው ዝቅተኛ ገቢ ከሚያገኘው የኅብረተሰብ ክፍል ጉሮሮ ተነጥቆ ወደ ገዥ ፓርቲውና ለፓርቲው ተባባሪ ወደሆኑ ባለሀብቶች የሚሸጋገርበት ክስተት ነው፡፡

የኢትዮጵያን መንግሥት ከሌሎች ‹‹በምርኮ ከተያዙ መንግሥታት›› የሚለየው በኢኮኖሚው ውስጥ ለሚታየው ተቋማዊ ሙስና መሠረት የሆነው የነገድ ፖለቲካው  (Ethnic Politics) የመሆኑ ሁኔታ ነው፡፡ በነገድ አንድነት ላይ ተመርኩዞ የመንግሥት ሥልጣንን በመያዝ የአገር ሀብትን የመዝረፍ ባህል ልክ እንደ ሕወሓት/ኢሕአዴግ የአገዛዝ ዘመን አሁንም በኦሕዴድ/ብልፅግና አገዛዝ ዘመን ዳብሯል። በቅርቡ የብልፅግና መንግሥት የሀብት ምዝገባ መርሐ ግብር ተጠናቀቀ በተባለበት ጊዜ፣ ዋዜማ የዜና ምንጭ አጣራሁ ብሎ ባወጣው ዘገባ መሠረት፣ ከ2.3 ሚሊዮን የመንግሥት ሠራተኞች መካከል ሀብታቸውን ይፋ አድርገው ያስመዘገቡ 72 ሺሕ ብቻ መሆናቸው፣ በመንግሥታዊ ቢሮክራሲው ውስጥ ሙስና ምን ያህል ሥር እንደሰደደ ያመለክታል። ስለዚህ በአገሪቱ ውስጥ ለዚህ ዓይነት የተንሰራፋ ሙስና መሠረት የሆነው የነገድ ፖለቲካ በሕግ ሳይታደግ በኢኮኖሚው ውስጥ የተንሰራፋውን ተቋማዊ ሙስና ማስወገድ አይቻልም፡፡ ተቋማዊ ሙስና በተንሰራፋበት ሁኔታ ደግሞ በኅብረተሰብ ውስጥ ማኅበራዊ ፍትሕን የተመረኮዘ የሀብት ክፍፍል ሊኖር አይችልም።

 1. ባለፉት ሁለት ዓመታት በብልፅግናና በሕወሓት መካከል እየተካሄደ የነበረው ጦርነት በኢትዮጵያ አገራዊ ብሔርተኝነት ሁለገብ አሸናፊነት ሊጠናቀቅ የሚችልበት ሁኔታ ካልተፈጠረና፣ ለነገድ ፖለቲካው በመሣሪያነት እንዲያገለግል እስከተፈለገ ድረስ የተኩስ አቁሙ ስምምነት ዘላቂነት አጠራጣሪ ስለሚሆን፣ የኢኮኖሚ ቀውሱ እየባሰበት እንጂ እየተሻለው ሊሄድ አይችልም፡፡ እንደሚታወቀው ጦርነት የአገር ሀብትን ለልማት ሳይሆን ለጥፋት የሚያውል አውዳሚ ክስተት ነው፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ለመከላከያ የሚውለው የመንግሥት በጀት ባለፉት አራት ዓመታት በየዓመቱ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመምጣቱ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የበጀት ጉድለት እንዲከሰት አድርጓል፡፡

የኦሕዴድ/ብልፅግና መንግሥት ደግሞ ይህን በከፍተኛ መጠን እየጨመረ የመጣ የበጀት ጉድለት በአብዛኛው ሲያሟላ የቆየው መጠኑ ብዙ የሆነ ገንዘብ በማተምና ወደ ገበያው እንዲረጭ በማድረግ ነው፡፡ ስለሆነም ለዋጋ ንረቱ ሌላኛው ምክንያት አሁን የሰላም ስምምነት ተፈረመ እስከተባለበት ጊዜ ድረስ አላባራ ያለው ጦርነት ነው፡፡ ጦርነቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ገበሬዎች ከግብርና ሥራቸው እንዲፈናቀሉና የምግብ ዕርዳታ ፈላጊ እንዲሆኑ ማድረጉ፣ የምርት አቅርቦት ሳይጨምር ወይም እየቀነሰ ባለበት ሁኔታ የምርት ፍላጎት እየጨመረ ስለሚሄድ፣ በተለይ ለምግብ እህል ዋጋ መናር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። እንደሚታወቀው የኦሮሙማው የኦሕዴድ/ብልፅግና መንግሥት ደግሞ በነገድ ፖለቲካ አራማጅነትና በአማራ ጥላቻ አምሳያው የሆነው ሕወሓት የሥልጣን ተቀናቃኙ የማይሆንበት ሁኔታ እንዲፈጠር እንጂ፣ ሕወሓት ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ጨርሶ እንዲወገድ አይፈልግም፡፡ በአንደኛና ሁለተኛ ዙር ጦርነቶች ወቅት የብልፅግና መንግሥት ጦርነቱ እንዲራዘም ማድረጉ፣ ለአገሪቱ የኢኮኖሚ መዳሽቅ የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካ ቅኝት አስተዋጽኦ ማድረጉ የማይካድ ነው፡፡

ከእነዚህ ዋና ዋና ምክንያቶች በተጨማሪ በአገራችን ላለው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ተጨማሪ ተጓዳኝ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከእነሱም መካከል አንዱ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ የተፈቀደው ፍራንኮ ቫሉታ፣ ንግድ በባንክ ውጭ ምንዛሪ ተመንና በጥቁር ገበያው የውጭ ምንዛሪ ተመን መካከል ያለው ልዩነት እየሰፉ እንዲሄድ ማድረጉ እየታየ ነው፡፡ የዕቃዎች ዋጋ ከጥቁር ገበያው የምንዛሪ ተመን መጨመር ጋር የተገናዘበ እንደሆነ መገንዘብ አያዳግትም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በገበያ ውስጥ የዕቃዎች ዋጋ  እየተወሰነ ያለው በፍላጎትና አቅርቦት ብቻ ሳይሆን፣ በአብዛኛው የጥቁር ገበያን የምንዛሪ ዋጋ መሠረት እያደረገ በመሆኑ፣ ለዋጋ ንረት መባባስ ይህ በባንክ የብር/ዶላር የምንዛሪ ተመንና በጥቁር ገበያው የምንዛሪ ተመን መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መሄድ ለዋጋ ንረቱ መባባስ አስተዋጽኦው ጉልህ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በአገራችን ፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት የውጭ መዋዕለ ንዋይ እየቀነሰ መምጣትም ለምርትና አገልግሎት እጥረት ብሎም ለዋጋ ንረት መጨመር ሌላው ምክንያት ነው።

የኢኮኖሚ ችግሮች ማጠቃለያ

  ከ1997 ዓ.ም. የምርጫ ሽንፈት በኋላ ሕወሓት በልማታዊ ኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳብ ቅኝት ለተከታታይ ሁለት አሠርታት ከአፍሪካ አማካይ የኢኮኖሚ ዕድገት በላይ የሆነ ዕድገት ማስመዝገቡ አይካድም፡፡ የዚህ የዕድገት ምንጭ ኢኮኖሚውን ከመዋቅራዊ የኋላ ቀርነት አዙሪት ቀለበት በሚያወጣ መልኩ አምራች በሆኑት የግብርና፣ ኢንዱስትሪና የማዕድን ክፍላተ ኢኮኖሚዎች ዕድገት የተገኘ ሳይሆን፣ በመሠረተ ልማት (መንገድ ሥራ፣ በባቡር ሐዲድ መስመር ዝርጋታና የአየር ማረፊያዎች ግንባታ፣ በትምህርትና ጤና ተቋማት ግንባታ) እንዲሁም በከፍተኛ ፕሮጀክቶች ማለትም እንደ ትልልቅ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች፣ ተጠናቀው ባላለቁ የስኳር ፋብሪካዎች፣ ወዘተ…) ላይ በርካታ ገንዘብ በማፍሰስ የተገኘ ዕድገት ነው፡፡ ይህ ከፍተኛ ሊባል የሚችል የኢኮኖሚና የማኅበራዊ መሠረተ ልማት ግንባታ እጅግ ግዙፍ የውጭ ምንዛሪና የአገር ውስጥ ገንዘብን የጠየቀ ነበር፡፡

ይህ በውጭ ምንዛሪ የተገኘ ብድርና ዕርዳታ በንጉሡ ዘመንም ሆነ በደርግ የአገዛዝ ዘመን ሊገኝ ያልቻለ፣ የምዕራቡ ዓለም ለኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን ላበቃው ለሕወሓት/ኢሕአዴግ መንግሥት ሊሰጠው የቻለው፣ የወያኔ መንግሥት የምዕራቡ ዓለም ጉዳይ አስፈጻሚ ሆኖ በማገልገሉ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አገዛዝም ፀረ አሜሪካ አቋም እንደሌለው አሜሪካኖች ጠንቅቀው ያውቃሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በቅርቡ ለአንድ አሜሪካዊ መልዕክተኛ ‹‹እኔ ለአሜሪካ ልሞት የተዘጋጀሁ ነኝ›› ሲሉ መናገራቸው ይህንኑ ነጥብ የሚያጠናክር ነው።

የምዕራቡ ዓለም ሕወሓት/ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ መንግሥትን ሥልጣን ከተቆጣጠረ ጀምሮ በቆየባቸው 27 ዓመታት፣ የብልፅግናን ከአራት ዓመት በላይ የአገዛዝ ዘመን ጨምሮ ላለፉት ሰላሳ አንድ በላይ ዓመታት ከ110 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ በብድርና በዕርዳታ ወደ አገራችን እንዲገባ አድርጓል፡፡ በ2011 (እ.ኤ.አ. በ2019) ብቻ በአሜሪካ ይሁንታ የብልፅግና ፓርቲ ለሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት  ከአይኤምኤፍ፣ ከዓለም ባንክ እንዲሁም ከሁለትዮሽ ግንኙነት ዘጠኝ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ፈሰስ የተደረገ ሲሆን፣ በ2014 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. በ2021) ኢትዮጵያ ከግብፅ ቀጥላ በአፍሪካ ሁለተኛዋ የአሜሪካ የዕርዳታ ተቀባይ አገር መሆኗን መረጃዎች ያሳያሉ። ብዙም የውጭ ዕርዳታና ብድር ያልተገኘበትን ሃምሳ ዓመታት የሚጠጋውን የንጉሡ ዘመን ትተን፣ አሥራ ሰባት ዓመታት በቆየው የደርግ የአገዛዝ ዘመን ኢትዮጵያ ከምዕራቡ ዓለም በዕርዳታና በብድር መልክ በውጭ ምንዛሪ ያገኘችው ለልማት ሊውል የሚችል ገንዘብ (Official Development Assistance) ከ 7.3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚበልጥ  አልነበረም፡፡

እንደሚታወቀው የምዕራቡ ዓለም የሚሰጠው ዕርዳታና ብድር በሰብዓዊነት መመዘኛ ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ መንግሥት የካፒታልና የመደበኛ ባጀት ጉድለትን ለማካካስ እንዲውል የተመደበን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የሕወሓት/ኢሕአዴግ መንግሥትም ሆነ የእሱ ውላጅ የሆነው የኦሮሙማው የኦሕዴድ/የብልፅግና መንግሥት በግድ ማሟላት የነበረባቸው (Conditionalities) ነበሩ፣ አሁንም አሉ፡፡ ይህን የውጭ የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት ለማግኘት የሕወሓት/ኢሕአዴግም ሆነ የኦሕዴድ/ብልፅግና መንግሥት ማሟላት የነበሩባቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዕርምጃዎች የሚከተሉት ነበሩ፣ አሁንም ናቸው፡-

 1. ብር ከዶላር ጋር ያለውን የምንዛሪ ጥምረት እንዲረክስ ማድረግ (Devaluation)
 2. መንግሥት ለግሉ ዘርፍ አመች እንቅስቃሴ መሰናክል የሆኑ ደንቦችን፣ መመርያዎችንና አሠራሮችን መሰረዝና የሚሻሻሉትን ማሻሻል (Deregulation)፣
 3. መንግሥት በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን የቁጥጥር ሚና እንዲያለዝብ ማድረግ (Liberalization)፣
 4. የአገር ውስጥ ገበያን ላልተገደበ የውጭ ካፒታል ተሳትፎ ክፍት እንዲሆን ማድረግ ወዘተ… እና ከዚህ ተዛማጅ የሆኑ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ዘርፍ ዕርምጃዎችን መውሰድ (Opening the National Market to Foreign Competition in the Name of Globalization)፣
 5. የመንግሥት ትልልቅ የኢኮኖሚ ተቋማትን ማለትም እንደ ኢትዮ ቴሌኮም፣ አየር መንገድ፣ ባንኮች ያሉትን እንደ ምድር ባቡር፣ የመርከብ አገልግሎት ያሉ የሎጅስቲክ ተቋማትን፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አቅራቢ የሆነውን መብራት ኃይልን በከፊል ወይም በሙሉ ወደ ግል ይዞታ ማዛወር (Privatizatcon) ወይም በሌላ አነጋገር እነዚህን ትልልቅ የአገር ውስጥ መንግሥታዊ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ለውጭ ኩባንያዎች መሸጥን የሚያጠቃልሉ ናቸው።

 በሕወሓትና በብልፅግና መንግሥት መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ከመፈረሙ በፊት ብድር/ድጎማ አለቅም ብሎ የነበረው የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት አሁን ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ወዲያውኑ አስተናግዳለሁ ማለቱ፣ የጦርነት መቆም ሌላ ተጨማሪ አስገዳጅ ሁኔታ እንደነበር መገንዘብ አያዳግትም።

በአገራችን የኢኮኖሚ ሙያ ጠበብት በተለይም የኢኮኖሚ ፖሊሲ አጥኚ በሆኑ የልማት ፖሊስ ሐሳብ አመንጭዎች (Development Studies Experts) መካከል የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለዓለም ገበያ ብርግድ አድርጎ በመክፈት፣ ገርበብ አድርጎ በመክፈትና ጨርሶ አለመክፈትን በሚመለከት የተጧጧፈ ክርክር ሲካሄድ ቆይቷል፣ አሁንም በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ብርግድ አድርጎ በመክፈትና ባለመክፈት መካከል ተሟጋች የልማት ፖሊሲ አመንጪ ምሁራን ዘንድ እየቀረቡ ያሉ አስተያየቶች የራሳቸው ጠንካራና ደካማ ጎኖች እንዳላቸው የሚቀበሉ የልማት ፖሊሲ አመንጪዎች ሌላ ሦስተኛ ጎራ ፈጥረዋል፡፡ ሦስተኛው ጎራ የሁለቱንም ደካማ ጎኖች በመተው ጠንካራ ጎናቸውን በማቀናጀት ተግባር ላይ ማዋል ይቻላል ብሎ ያምናል። ኢኮኖሚውን ለውጭ ውድድር የመክፈቱ ፖሊሲ ከውጭ ተፅዕኖ ነፃ በሆነ መልኩ መከናወን አለበት፡፡ በሩን  በአንድ ጊዜ ብርግድ አድርጎ መክፈት ሳይሆን፣ ተለቅ ተልቅ ያሉ የአገር ውስጥ መንግሥታዊም  ሆኑ የግል ድርጅቶች/ኩባንያዎች ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን አቅም ከገነቡ በኋላ ቢከፈት ይሻላል የሚል ነው፡፡ የአገራችን ኢኮኖሚ ከተተበተበበት የኋላቀርነት አዙሪት ቀለበት ሊያስወጣ የሚችለው የዕድገት ጓዳና ይህን ዓይነት ኢኮኖሚውን ለውጭ ውድድር የማዘጋጀት ፖሊሲ የተከተለ ሊሆን ይገባል የሚል ነው፡፡

 ሦስተኛው ጎራ በአገራችን በመንግሥትም ሆነ በግሉ ዘርፍ ያሉ ኩባንያዎች አብዛኛዎቹ በካፒታል፣ በሥራ አመራር ልምድና በገበያ ትስስር እንዲሁም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ገና ባልዳበሩበት ሁኔታ፣ ኢኮኖሚውን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ማድረግ፣ ተወዳዳሪ ያልሆኑ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች በውጭ ኩባንያዎች እንዲዋጡ፣ ወይም ከገበያው እንዲወጡ የማድረግ ውጤት ስለሚኖረው፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በውጭ ኩባንያዎች ተፅዕኖ ብቻ ሳይሆን፣ ሙሉ ቁጥጥር ሥር እንዲወድቅ ያደርጋል ብሎ ያምናል። በዚህ ሒደት የሚገኘው ውጤት ሚዛን ያልጠበቀ የኢኮኖሚ ዕድገት (Economic Gronth) ሊሆን ቢችልም፣ ዕድገትን (Growth) ከማኅበራዊ ፍትሕ (Social Equity) ጋር ያቀናጀ የኢኮኖሚ ልማት (Econoimic Development) አያስገኝም የሚል እምነት አለው፡፡

በተለይ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የተለጠጠ አደረጃጀታቸው ወጪ ቆጣቢ እንዲሆኑ አላደረጋቸውም፡፡ የአስተዳደርና የአመራር ነፃነት ስለሌላቸው አትራፊም ሆነ ተወዳዳሪ ሲሆኑ አልታየም፡፡ በመሆኑም ትልልቅ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከተፈለገ የተሟላ የአስተዳደርና የአመራር ነፃነት (Management  Autonony) ሊኖሯቸው የግድ ይላል፡፡ ይህም ማለት የመንግሥት የልማትና የአገልግሎት ድርጅቶች የነገድ የፖለቲካ ድርጅቶች ካድሬዎች የሚፈነጩባቸው ሊሆኑ አይገባም ማለት ነው። የኃላፊዎች ምደባም ሆነ በተዋረድ የሚደረግ ምደባ፣ ዕድገት ወዘተ. ከሙያ ብቃት አንፃር ብቻ እንጂ ከነገድ ማንነት ጋር ጨርሶ ሊገናኝ አይገባም ማለት ነው፡፡

ሁለተኛውን አማራጭ የሚያራምዱት ደግሞ አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ከዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ጋር በአንድም ሆነ በሌላ መልክ ያልተሳሰረ ዝግ የሆነ አገራዊ ኢኮኖሚ ስለሌለ፣ ፍፁም ዝግ የሆነ፣ የውጭ ውድድርን የማያስተናግድ የኢኮኖሚ ሞዴል እንከተል ማለቱ ትክክል ስለማይሆን፣ የአገራችን ኢኮኖሚ ለውጭ ውድድር ክፍት መሆን አለበት ይላሉ፡፡ ሦስተኛውን የፖሊሲ አቅጣጫ የሚደግፉ የኢኮኖሚ ምሁራን ደግሞ በውድድር አለንጋ የማይሸነቆጡ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ምንጊዜም ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ተወዳዳሪ ሊሆኑ ስለማይችሉ፣ ኢኮኖሚው ለውጭ ውድድር ክፍት መሆኑ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ጠንክረው ተወዳዳሪ ሆነው እንዲወጡ ይረዳል የሚል አመለካከትን ያራምዳሉ። የሁለተኛውና የሦስተኛው ጎራ ልዩነት ኢኮኖሚው ለውጭ ውድድር የሚከፈትበት ጊዜ መችና ምን ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው በሚሉ ነጥቦች ብቻ ነው የሚለያዩት፡፡

ሦስተኛው ጎራ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ወደ አገር ውስጥ መጋበዝ የሚኖርባቸው ተለቅ ተለቅ ያሉ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ትክክለኛ በሆነ የመንግሥት የፖሊሲ ድጋፍ ከውጭ ኩባንያዎች የሚያጋጥማቸውን ውድድር በብቃት መቋቋምና አትራፊ ሆኖ መቀጠል የሚችሉበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ከተደረጉ በኋላ፣ መንግሥት የውጭ ኩባንያዎችን የረቀቀ አሠራር ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅሙን በአስተማማኝ ደረጃ ከገነባ በኋላ ቢሆን ይመረጣል የሚል አቋም ያራምዳል። ከዚህ በኋላ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ለውጭ ውድድር ቢጋለጡ፣ ተወዳዳሪነታቸው ለውጤታማነታቸው መንደርደሪያ ሆኖ ይበልጥ ጎልብተው ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱና ለተገልጋዩ ኅብረተሰብ ዕርካታን ሊያስገኙ ይችላሉ የሚል የፖሊሲ ሐሳብ ያራምዳል፡፡

ካለፉት በርካታ ዓመታት ተግባራዊ ክንውን እንደታየው ደግሞ ሁሉም የግል ድርጅቶች ውጤታማ፣ ሁሉም በመንግሥት ይዞታ ሥር ያሉ ድርጅቶች ደካማ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ በመንግሥት ይዞታ ሥር ሁነው በአንፃራዊ መልኩ የአመራርና የአስተዳደር ነፃነት የተጎናፀፉት በተለይ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም  ኢትዮ ቴሌኮም ያሉት ውጤታማ ሁነው ከመገኘታቸውም ባሻገር ለአገራችን ኩራት ሆነዋል፡፡ ይህ አባባል መብራት ኃይልንም ይጨምራል። እነዚህ መንግሥታዊ የአገልግሎት ዘርፍ ድርጅቶች ላለፉት ከሰላሳ በላይ ዓመታት የአስተዳደር ነፃነታቸው በገዥ ፓርቲዎች ጣልቃገብነት ተነጥቆ በነበረበት ሁኔታ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ከቻሉ፣ አግባብነት የሌለው መንግሥታዊ ጣልቃገብነት ከእነአካቴው ቢወገድላቸውና ሙያን መሠረት ያደረገ (Meritocracy) አሠራርን ተከትለው ቢሆን ኖሮ፣ አሁን ካስመዘገቡት የላቀ ውጤት ማስመዝገብ ይችሉ እንደነበር መገንዘብ አያዳግትም፡፡

እነዚህን ኩባንያዎች መንግሥት ራሱ አላግባብ ጣልቃ እየገባ ሲያውካቸው ከከረመ በኋላ ይህንንም ጣልቃገብነት ተቋቁመው ለአገር ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የመንግሥት ኩባንያዎችን ለውጭ ኩባንያዎች በከፊልም ሆነ በሙሉ እንዲሸጡ የብልፅግና መንግሥት የሚያራምደው ፖሊሲ የዓለም የፋይናንስ ድርጅቶች ያሳደሩበትን ተፅዕኖ መቋቋም ካለመቻል ወይም ካለመፈለግ የመነጨ ነው። ለጊዜያዊ የበጀት ችግር ማስተንፈሻ ሲባል የኢትዮጵያን ብሔራዊ ሀብት ለዘለቄታው ለባዕዳን አሳልፎ መስጠት፣ እስትራቴጃዊ ዕይታ የጎደለው ፖሊሲ መሆኑ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚህ ካለፈ ደግሞ የአገር ኩራት የሆኑ ኢትዮጵያዊ ተቋማትን ለውጭ አገሮች ኩባንያዎች መሸጥ፣ ከአገራዊ ብሔርተኝነት ይልቅ ለነገድ ማንነት ቅድሚያ ከሚሰጥ የጠበበ የፖለቲካ አመለካከት ሊመነጭ እንደሚችል መጠርጠርም ይቻላል። 

እነዚህ የአገር ኩራት የሆኑ ድርጅቶች በውጭ ኩባንያዎች እንዲገዙ ከመፍቀድ ይልቅ ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በአቻነት እንዳይወዳደሩ የሚያደርጓቸውን መንግሥት በውስጥ የአስተዳደር ሥራቸው የሚያደርገውን ጣልቃገብነት በማቆምና የተሟላ የውስጥ አስተዳደር ነፃነት እንዲኖራቸው በማድረግ፣ መሥሪያቤቶች በገዥ ፓርቲ ካድሬዎች ሳይሆን፣ ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ በሆኑ ባለሙያዎች እንዲመሩ፣ ቅጥርም ሆነ ዕድገት ሙያን ብቻ መሠረት አድርጎ እንዲከናወን በማድረግ፣ በአጠቃላይ  እነዚህ ድርጅቶች ከመንግሥት የሚደርስባቸው ተፅዕኖ እንዲቋረጥ በማድረግ ብቻ ውጤታማነታቸውንና ተወዳዳሪነታቸውን በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምሩ ለማድረግ ይቻላል፡፡ እነዚህን የአገር ሀብት የሆኑ የመንግሥት አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች መሸጥ ሳይሆን፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሥርፀት፣ በዓለም አቀፍ የገበያ ትስስር በመሳሰሉት ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በበቂ ሁኔታ ለመወዳደር የሚያስፈልጓቸውን ግብዓቶች እንዲያገኙ በቂ ድጋፍ በማድረግ፣ የውጭ ተወዳዳሪ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው እንዲወዳደሯቸው የሚያደርግ ፖሊሲን መከተል፣ ውድድሩን ይበልጥ ውጤታማ በማድረግ የአገራችንን ኢኮኖሚ ልማት ሊያፋጥን ይችላል፡፡ 

በተጨማሪም ውድድሩ ፍትሐዊ እንዲሆን የውጭ ኩባንያዎች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ከመጋበዛቸው በፊት፣ ቀደም ሲል እንደ ተጠቀሰው የዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን  የውጭ ምንዛሪን ከደንብ ውጭ ወደ እናት ኩባንያዎቻቸው የማሸሽ የረቀቀ አሠራር ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅምን መገንባት ያስፈልጋል፡፡ መደገፍ ያለበት ይህን ዓይነት የአገራችንን የመንግሥትም ሆነ የግል ኩባንያዎች ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ተወዳዳሪ ሊያደርግ የሚችል በገበያ ኢኮኖሚ መርሆዎች ላይ የተመሠረተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውንና የፓርቲያቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles