Thursday, February 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልእሸትና የቀመሳው በዓል

እሸትና የቀመሳው በዓል

ቀን:

በአብዛኛው ክፍለ ኢትዮጵያ  ክረምት ካለፈ በኋላ የመስከረምን መገባደጃ ተከትሎ አበባማውና ነፋሻማው ወቅት የሆነው መፀው ከገባ ከአንድ ወር በላይ ሆኖታል፡፡ የመስከረምን የመጨረሻ አምስት ቀናትን ጨምሮ ጥቅምትን፣ ኅዳርንና የታኅሣሥን ሦስት ሳምንታትን ይዞ የሚዘልቀው መፀው፣ በዋናነት የፍሬ ወቅት መሆኑ ይወሳል፡፡

አፈ ሊቅ አክሊሉ ገብረ ኪሮስ በአንድ ሐተታቸው እንደገለጹት፣ የክረምት ተረካቢው መፀው የተባለው ክፍለ ዘመን፣ እንደ ክረምት የውኃ ባህሪ ያፈላል፣ ይገናል፣ እንቡር እንቡር ይላል፣ ይዘላል፣ ይጨፍራል፡፡ ከዚህም የተነሳ ወንዞች ይሞላሉ፣ ምንጮች ይመነጫሉ፡፡ አዝርዕትና አትክልት ሐዲሳን [አዲሶች] ፍጥረታት ሆነው ይነሳሉ፣ ይበቅላሉ፣ ይለመልማሉ፡፡

ከሦስቱ የመፀው ወራት አንዱ የሆነው አሁን ያለንበት ወርኃ ኅዳር፣ ከአዝመራ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ መምህራኑ እንደሚሉት ከመሬት ብዙ ጥቅም የሚገኝበት፣ እህልና ተክሉ ሁሉ ፍሬ ሰጥቶ በኅዳር የሚያድርበት እሸት የሚቀመስበት ወር ያሰኛል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ማኅበረሰቦች ከአዝመራ ጋር ተያይዞ የሚከናወኑ ባህላዊና ትውፊታዊ ሥርዓቶች አሉ፡፡  ከነዚህም አንዱ  በወሎ የሚፈጸመው የእሸት መቅመስ በዓል ነው። 

በደቡብ ወሎ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሐተታ መሠረት፣ በዓሉ ‹‹ባዲገዝ››  ይባላል። ባዕድ ይገዝ፣ ዘመድ ያልሆነም ይርዳ እንደማለት።

ሐተታው ሲቀጥል ጥቅምትን የእሸት ወር ብሎ ነው። የመስከረም አበባ ፍሬ የሚሰጥበት፣ ወተት በገፍ የሚታለብበት፣ ለመድኃኒት የሚሆን ማር የሚቆረጥበት ወር ነው ጥቅምት። በተለይ የጥቅምት መጨረሻ ሳምንት በወሎ ኮምቦልቻ፣ ወረባቦ፣ ቃሉ፣ በተሁለደሬ፣ ኩታበርና በአጎራባች  ወረዳዎች ልዩው የበዓል ጊዜ ባዲገዝ ይባላል ሲል ያክላል።

ባዲገዝ ምርት የመሰብሰብና እሸት የመቅመስ በዓል ነው። ለበዓሉ እሸት ያለው እሸት፣ ወተት ያለው ወተት፣ ጥንቅሽ ያለው ጥንቅሽ፣ እንጀራ፣ ቂጣ፣ በቆሎ፣ ቃሪያ ወዘተ. እያመጣ ሕዝቡ ተሰባስቦ በአብሮነት የሚያከብረው በዓል ነው።

ባዲገዝ ማሳ የሌላቸውና ያላረሱ ሰዎች ሁሉ እሸት የሚቀምሱበት፣ የመተሳሰብ፣ የመተዛዘንና የመዋደድ በዓል ነው።

ሌላኛ ስያሜው  ‹‹ዲልበት››  ይባላል፡፡  አዝመራው ቃሪያ፣ ጥንቅሽ፣ በቆሎ፣… ሊሆን ይችላል፡፡  ባዲገዝ ማሳ  የሌላቸውና  ያላረሱ  ሰዎች  ሁሉ  እሸት  የሚቀምሱበት፣  የመተሳሰብ፣  የመተዛዘንና  የመዋደድ  በዓል  ነው፡፡  ከየማሳው  ያለው  የእሸት  ዓይነት  ሁሉ ቀርቦ እየተበላ እስከ ምሽት ድረስ ጨዋታና ምርቃቱ ይቀጥላል፡፡

በበዓሉ ዕለት ከየማሳው ያለው የእሸት ዓይነት ሁሉ ቀርቦ እየተበላ እስከ ምሽት ድረስ ጨዋታና ምርቃቱ ይቀጥላል።

‹‹ለዚህ የእሸት ወቅት ያደረስከን ተመስገን! አዝመራውን ለጎተራ አብቃልን!  ከርሞም ከዚህ የተሻለ አዝመራ ስጠን!›› ተብሎ ይመረቃል፤ ሃይማኖታዊ ፀሎት (ዱዓ) ይካሄዳል።

ትልልቅ ሰዎች ስለአካባቢውና ስለአገር ታሪክ፣ ስለባህልና መረዳዳት፣ ፖለቲካና የሕዝብ አስተዳደር በእሸት በዓሉ ባዲገዝ ላይ ያስተምሩበታል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚታደሙት የአካባቢው ሽማግሌዎች ‹‹ተላይ አልጋውን ከታች ለጋውን ጠብቅልን! አዝመራውን አብዛልን!›› እያሉ በዝማሬ ጭምር ይጸልያሉ፤ ‹‹አልጋ›› የሚሉት መንግሥትን ሲሆን ‹‹ለጋ›› የሚሉት ደግሞ ሕዝቡን ነው።

በሌሎች አካባቢዎችም ትውፊታዊ ሥርዓቶች አሉ።

‹‹የጉሙዝ ብሔረሰብ ባህላዊ ክንዋኔዎች›› በሚል ርዕስ ያጠኑት የፎክሎር ባለሙያው አቶ አበበ ኃይሉ እንደሚገልጹት፣ ከእርሻ ሥራ ጋር በተያያዘ በዓመት ሦስት ጊዜ የሚከናወኑ ሥርዓተ ክንዋኔዎች (Rituals) አሉ፡፡ እነዚህም ኬግዴራ (በዘር ጊዜ)፣ ኬግንድም (የእሸት ቀመሳ) እና ኬኳጫ (የተሰበሰበው እህል  ጎተራ  ከመግባቱ በፊት የሚከናወን) በመባል ይታወቃሉ፡፡

ስለ ቅምሻ ባተቱበት በዚሁ ጽሑፋቸው ይኸን ብለዋል።

‹‹የቅምሻ ሥነ ሥርዓት ሲካሄድ ሴቶች፣ ሕፃናት ወጣቶችና አዋቂዎች ከደጅ ሆነው ሽማግሌዎች ወይም ኤትምሳ ድግሳ ደግሞ ከቤቱ በራፍ ላይ ቆመው ዘመኑ የተባረከ፣ አዝመራቸው ያማረ ላደረገላቸውና የአዲሱን ዓመት እሸት ለመቅመስ ላበቃቸው ፈጣሪ አምላቸውና የኬግንድዋ መንፈስ ጸሎትና ምሥጋና ያቀርባሉ፡፡ ዘመኑ የሰላምና የፍቅር፣ የደረሰው አዝመራም የጤና እንዲሆንላቸው የምረቃ ሥነ ሥርዓትም ይካሄዳል፡፡

‹‹ይህ ሥነ ሥርዓት ሲከናወን ሁሉም ከተቀመጠበት ተነስቶ ሒደቱን በተመስጦና በጥሞና ይከታተላል፡፡ በመቀጠል አስተባባሪው ከቤቱ ምሰሶ ሥር ከተቀመጠ የእሸት ዓይነት ይቀምስና እየፈለፈለ በቤቱ ዙሪያ ይፈነጥቃል፡፡ የሚፈነጠቀው ለኬግንድዋ መንፈስ ድርሻ በሚል ነው፡፡ አስተባባሪው ከቀመሰ በኋላ ታዳሚዎች እንዲቀምሱ ይደረጋሉ፡፡ የወር አበባ ላይ ያሉ ሴቶች ግን የአዲስ ዓመት እሸት እንዲቀምሱ በባህሉ አይፈቀድላቸውም፡፡ ምክንያቱም ከቀመሰች የኬግንድዋ መንፈስ ይቆጣል፣ ምርቱም የተባረከ አይሆንም ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ ሥነ ሥርዓቱ ከተከናወነ በኋላ ገበሬዎች ከየማሳቸው የደረሰ ሰብላቸውን ለምግብነት መጠቀም ይችላሉ፡፡

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ምዝገባ ሰነዱ ላይ እንደተጻፈው፣ የጎፋ ብሔረሰብ ቀደም ሲል የደረሰ እሸት የመቅመስ ሥርዓት አለው፡፡ እሸት ለመቅመስ በቅድሚያ ቡና ይፈላል፣ ቀጥሎም በቆሎው ይጠበስና ለአባወራው ይሰጠዋል፡፡ ከተሰጠው በቆሎ የተወሰነ ፈልፍሎ ከረጨ በኋላ አንድ አንድ ፍሬ ለሚስቱና ለልጆቹ ያቀምሳቸዋል፡፡ እማወራዋም ‹‹እንኳን አደረሰን›› በማለት መሬቱን ትስማለች፡፡ ቀጥሎ ቡናውን ጠጥተው የእሸት መቅመሱ ሥርዓት ይጠናቀቃል፡፡ ከዛ በኋላ እሸት እየተቆረጠ በማንኛውም ጊዜ ይበላል፡፡ የክርስትናን እምነት የተቀበሉት የብሔረሰቡ አባላት እሸቱ እንደደረሰ ቆርጠው ባሉበት አጥቢያ ለሚገኘው ቤተ ክርስቲያን ይሰጣሉ፡፡ ከዛ በኋላ እሸቱን መብላት ይጀምራሉ፣ በመቀጠል በቆሎው እንደተሰበሰበ በአሥራት መልክ ለቤተ ክርስቲያን ይሰጣሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ የካቤኔ አባል የሆኑት አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሚያቀርቡትን ቅሬታ እያዳመጡ ነው] 

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር በእጅጉ ስላሳሰበኝ ነው በአካል...

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የፈጠሩት አምቧጓሮ

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው...

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ የፈጠራቸው አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖች

የአገሪቱ ንግድ ባንኮች በዓመት የሚሰጡት የብድር መጠን ላይ የኢትዮጵያ...

ቱግ ቱግ!

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለመታደም የመጡ እንግዶችን ሸኝተን ከፒያሳ ወደ...