Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አጉል መንፈራገጥ!

ሰላም! ሰላም! እህ? እንዴት ነው ጃል? ‹ማግኘት ያበጃጃል ማጣት ያገረጅፋል› አትሉም እንዴ? ሁሉም ነገር በማግኘትና በማጣት መረብ ላይ የተዘረጋ በመሆኑ እኮ ነው፣ መወጣጠር በዝቶ ዓለም ለመፈንዳት ቋፍ ላይ ያለችው። በአንድ በኩል ሲታጨድ በሌላው መበተን እየተለመደ ነው ዓለም መስማማት አቅቶት እርስ በርስ ሲጓተት የውድመት ሰለባ እየሆነ ያለው። እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ባልማርም ይኼ እንደማይጠፋኝ በእርግጠኝነት እናገራለሁ፡፡ ‹‹አፈር ናችሁና ወደ አፈር ትመለሳላችሁ›› ስንባል ራሱ በመገኘትና በመታጣት ንድፈ ሐሳብ ላይ ተመሥርቶ መሆኑንም እረዳለሁ። ‹‹ማግኘትም አልከፋ ማጣቱም አልከፋ፣ እኔን የጨነቀኝ መኖር ነው በተስፋ›› ብሎ አንድ ደላላ ወዳጄ አንጎራጎረ። ‹‹ምነው ትዝታ ውስጥ የገባህ ትመስላለህ?›› ብለው፣ ‹‹እንዴት ቢሆን ነው ማግኘትና ማጣት ጥግ ድረስ እየሄዱ የማይበላ የተስፋ ዳቦ ሲያሳዩን የሚኖሩት?›› ብሎ መልሶ ጠየቀኝ። መጠያየቅ ከጀመርንማ አንላቀቅም!

እኔ ትዝታን በተመለከተ ከዘፈን ጀምሮ ብዙ ትውስታዎች አሉኝ፡፡ ሁሌም የማልረሳው ግን፣ ‹‹ሰው ማርጀቱን የሚያውቀው በተስፋ መኖር ትቶ በትዝታ መኖር ሲጀምር ነው…›› የሚለውን ዘመን ተሻጋሪ ጥቅስ ነው፡፡ ‹‹ትዝታሽ ዘወትር ወደ እኔ እየመጣ፣ ዕፎይ የሚልበት ሕይወቴ ጊዜ አጣ…›› ማለት ስጀምር ማንጠግቦሽ ወጣትነቷ እየታሰባት ነው መሰል በንዴት፣ ‹‹በቃህ!›› ስትለኝ እደነግጣለሁ፡፡ ማን ማርጀትን በዋዛ ይቀበላል? ወገብ ሲንቀጠቀጥ እግር መራመድ ሲያቅተው ይታያችሁ፡፡ ለዚህ መስሎኝ በስተርጅና ፖለቲከኞቻችን እንደ ሠፈር ጎረምሳ ይዋጣልን እያሉ የሚውረገረጉት፡፡ አሁን ደግሞ ከፈንጣጣ፣ ከትክትክ፣ ከኮሌራ፣ ከልጅነት ልምሻ፣ ከኤችአይቪ/ኤድስና ከበርካታ የዚያ ዘመን ወረርሽኞች በቅጡ ሳንገላገል እንደ ሱፐር ሶኒክ ጄት የሚወነጨፍ ኮሮና የሚሉት አተራምሶን ከርሞ፣ አውዳሚ ጦርነት ውስጥ መክረማችንን ሳስብ ያመኛል፡፡ አጠገቤ ያሉትን ስጠይቃቸው ወይ የምለው አይገባቸውም፣ ወይም ሁሉንም ነገር ለላይኛው ጌታ ሰጥተው ባላየ ባልሰማ ያልፉኛል፡፡ አሁንማ እሱው ይሁነን እንጂ አካሄዳችን ያስፈራል፡፡ እውነት ነው ያስፈራል!

በቀደም ፈራ ተባ እያልን የተለመደውን የፖለቲካ ጨዋታ ከጓደኛዬ ጋር አነሳነን። ያለ ውጤት እንደ መረብ ኳስ ጨዋታ ኳሱን አየር ላይ ስንቀባበለው 2015 ዓ.ም. ሊጋመስ ነው። ሕዝባዊ አጀንዳ በሰነቁና ድንፋታ በታጠቁ ፖለቲከኞች ምክንያት የአገራችን ችግር እየባሰበት ቢከርምም፣ አሁን ደግሞ ለሰላም በር የተከፈተ ይመስላል፡፡ ሰላሙ የተሟላ እንዲሆን ግን በሰሜን አቅጣጫ ጋብ ያለው ጦርነት በምዕራብ እንዳይስፋፋ መላ ያስፈልገናል፡፡ ችግራችንን በፅሞና ተነጋግረን ፍጅት ማስቆም አለብን፡፡ እስቲ ጠማማውን ፖለቲካ ለጊዜው ወደ ጎን ብለን ይህንን እንደ ሰደድ የሚንቀለቀል የኑሮ ውድነት አደብ ለማስገዛት ፊታችንን ወደ ሥራ እንመልስ። ‹‹አሁን አሁንማ ሰላምን ጭምር የፖለቲካ መቆመሪያ ለማድረግ የሚፈልጉ መዥገሮች እንደ ማፊያ አገር ማመሳቸው የሚቆም አይመስለኝም…›› አለኝ ጓደኛዬ። ‹‹ምን ያድርጉ ብላችሁ ነው ለነገሩ? እኛስ ከግዴታ ይልቅ መብትን ጠንቅቀን የምናውቀውን ያህል መቼ ዘመትንባቸው? ከጭቆና ተገላገልን ስንል ለባሰ ጭቆና ለመዳረግ የተነሱ አውሬዎችን መታገስ የለብንም…›› አለኝ ወዳጄ እየተብሰለሰለ፡፡ እውነት ነው ሰላም ይስፈን ሲባል እምቢ የሚሉትን በቃችሁ ማለት ይገባል፡፡ አሁንስ በዛ!

 እግረ መንገዴን አንድ ያጋጠመኝን ጉዳይ ላጫውታችሁ። በአንዱ ዕለት ማለዳ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ከቤቱ ወጥቶ ወደ ሥራ ሲጣደፍ አገኘኝ። ደህና አደርክ ሳይለኝ የለበጣ ሳቅ እየሳቀ፣ ‹‹አንበርብር እንደ ተዳከመ ቡድን በገዛ ሜዳዬ ነጥብ የመጣል አባዜ አስቸገረኝ እኮ…›› አለኝ ሁለት እጁን በኪሱ ከቶ አንገቱን እየነቀነቀ። በነገራችን ላይ የባሻዬ ልጅ ቀንደኛ የእግር ኳስ ተመልካች ነበር። ሊቨርፑልን እንደሚደግፍ ራሱን ቢደግፍ ይኼኔ የት በደረሰ ነበር ያስብላችሁ ነበር፡፡ ‹‹ምነው ሰላም አላደርክም? እንዴት አደርክ ማለት አይቀድምም?›› ስለው፣ ‹‹ደመወዝ በወር ኑሮ በዕለት ሆኖ መፈናፈኛ አጥተን እንዴት ሰላምታ ይቅደም?›› አለኝ። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ እጁን ተስሞ የሚፈለግ ልዩ ባለሙያ እንደሆነ ባውቅም፣ የገቢው ነገር ዘወትር ሲያሸማቅቀው አያለሁ። ‹‹ደመወዜ ከማነሱ ቀኑ እንደ ምጥ መርዘሙ ነው የሚገርመኝ…›› አለኝ፡፡ ‹‹እንዴት?›› ብዬ ስጠይቀው፣ ‹‹ቀኑ እንዴት እንደሚከንፍ፣ የደመወዝ ቀን ግን እንዴት ሰውን እንደሚያንቆራጥጠው አታይም? ከታክሲ ጥበቃ፣ ከፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና ዳኝነት ጥበቃ በተጨማሪ የመጣልንን ለውጥ መጠበቅ አቅቶን እየተናጀስን የደመወዝ ቀን ጥበቃ ሲጨመር አይጣል ነው…›› አለኝ ጭንቅ ብሎት። ‹‹አይዞህ ማጣትም ቢሆን ከልኩ አያልፍም…›› አልኩና በኮሚሽን ካገኘሁት ላይ 2‚000 ብር አውጥቼ ደመወዝ ስትቀበል ትሰጠኛለህ በሚል ሸጎጥኩለት። ጥሩ አይደል? ታዲያ ወገን ለወገኑ መቼ ነው የሚደርሰው? ተግባር የማያውቅ ባዶ የተስፋ ቃል መስማት አልሰለቻችሁም? በትንሽ በትልቁ ተጋግዘን አገር እናቀናለን ስንል የሥልጣን ጥም ያቃጠላቸው አስመሳይ ፖለቲከኞች ሲያወናብዱን ይነደኛል፡፡ ወይ ነዶ!

እንግዲህ እኔ ይኼን ሁሉ በሩጫዬ መካከል በትዝብት ስከታተል ወሬ በየአቅጣጫው ይሰማል፡፡ የአገር ጉዳይ ሲነሳ የነጋዴዎቻችን ነገር ትልቁን ቦታ ይይዛል፡፡ አንዱ፣ ‹‹የዘንድሮ ነጋዴ የተነሳበትን በመርሳት ጨካኝ ለመሆን የሚቀድመው የለም…›› ሲል ሌላው ተቀብሎ፣ ‹‹አገር የሚጠቅም ስንት ተግባር ማከናወን ሲገባቸው፣ አልጠግብ ባይ ሆነው ዝርፊያና ግብር ማጭበርበር ላይ ነው የሚራወጡት…›› ሲል እሰማዋለሁ። አዛውንቱ ባሻዬ በበኩላቸው፣ ‹‹አልጠግብ ባዮች እኮ ለማን እንደሚያከማቹት የሚያውቁ አይመስሉም። ከአቅማቸው በላይ ገንዘብ በኃጢያት እያግበሰበሱ ለማኅበረሰባቸው ውኃ፣ ክሊኒክ፣ መብራት፣ መንገድ ወይም ሌሎች ድጋፎች ለማድረግ ልብ የላቸውም፡፡ ፈጣሪ እነዚህን ነው እኔን ረስተው ገንዘብ እያመለኩ ነው የሚላቸው፡፡ ስስታም አንድም ያንቀው አንድም ይወድቀው ተብሎ የተተረተው ለእነሱ ነው…›› እያሉ በዕድሜ ዘመናቸው ስለሚያውቋቸው ስስታምና ክፉ ነጋዴዎች ሚስጥሮች ሲዘከዝኩልኝ ሰነበቱ። ሰው ከሰነበተ የማይሰማውና የማያሰማው የለም። አዳማጭ የለም እንጂ ብዙ ብሶቶች ይደመጣሉ፡፡ በተለይ ስግብግቦች እንዲህ ዓይነቱን ወቀሳ መስማት አይፈልጉም፡፡ ዓይናቸውም ጆሮአቸውም ዝግ ነው፡፡ ዝጋታም ሁሉ!

አብዛኛው የሰው ልጅ ዓለም በኑክሌር ሥጋት ውስጥ ሆና በድንጋጤ እንደ ሰጎን አንገቱን አሸዋ ውስጥ ለመቅበር የሚፈልግ ይመስላል። ጤናማ ፉክክር የዕድገት አንቀሳቃሽ እንደሆነ በእኔም ሕይወትና ሙያ ስለማስተውለው እጅግ እደግፈዋለሁ። ሆኖም የትናንት ታሪካቸውን እየረሱ ለወገን ባዕዳን የሚሆኑትን ሳይ ልቤ ይቆስላል። ለአገር ዕድገትና ልማት መረዳዳት፣ መተጋገዝና መተሳሰብ ሲገባን ለመበላላት መሯሯጥ ያስከፋል። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ይኼ ነው አንዱ የሥርዓተ አልበኝነት ጦስ…›› የሚለኝ ነገር ከቶውንም ባይገባኝም፣ በከፊል ግን የተወላገደው የዓለም የፖለቲካ ሥርዓት ለዚህ ያለውን አስተዋጽኦ አላጣውም። አሥር ሳንቲሞች ተጠራቅመው ሚሊዮኖችን እንዴት እንደሚታደጉ ማስረዳት እንደሚቻል አላውቅም። ‹‹ዋናው ጠላታችን የክፋት የጀርባ አጥንት የሆነው ራስ ወዳድነት ነው…›› ብለው የሚነግሩን እስኪወለዱ እንጠብቅ ይሆን? ደጅ መጥናት አይታክተን መጥኔ! 

መቼ ዕለት በጥድፊያዬ መሀል ውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ደወለችልኝ። ምን ገጥሟት ይሆን እያልኩ በጥድፊያ ስልኬን አነሳሁት። እንደ እኔ ስልካችሁ መጥራቱ በመቻሉ ብቻ ፈጠን ብላችሁ ማንሳት ይኖርባችኋል። ‹‹እንዴት?›› እንደማትሉ ተስፋ አደርጋለሁ። ምክንያቱም የአገራችን ዘርፈ ብዙ ችግር እንደ አዲስ የሚወራ አይደለምና ነው። ‹‹ሎተሪ ቢደርሰኝ ከሚሰማኝ የደስታ ስሜት እኩል ሲደወልልኝና የደወልኩት ስልክ ሲጠራ እደሰታለሁ…›› ያለኝ ደላላው ጓደኛዬ ነው። እውነቱን ነው የደላላ ስልክ ካልሰራ ገቢ የለም፡፡ ‹‹ኖ መኒ ኖ ፈኒ›› ሆነ ማለት ነው፡፡ ውዴን ስልኬን አንስቼ ሳነጋግራት፣ ‹‹በእጮኝነት ዘመናችን ታደርገው እንደነበረው ሲኒማ ቤት ይዘኸኝ ሂድ…›› አለችኝ። ወይ ማንጠግቦሽ? በስተርጅና ጭራሽ ሲኒማ ቤት? እኔም ተዘናግታ ይሆን እንዴ ብዬ ሲኒማ ቤትና ክለብ መሄድ የወጣቶች እንደሆነ ደጋግሜ አስረዳኋት። ዛሬ እርጅና እየመጣ ጉልበት እንደ ልጅነት አልሆን ሲልና ማስታወስ ሲቸግር ሰው ነንና ግራ ይገባናል። በአጉል አምሮት ውስጥ ደግሞ መሳቀቅ አለ። እናማ ማሳሰቢያው ሲደጋገምባት፣ ‹‹እንዲህ ከሆነ የዘመኑ ነገር በል ቅዳሜ ዕለት ዘመናዊ ልኳንዳ ቤት ወስደኸኝ እንዝናና…›› አለችኝ። የዘመኑ ነገር አቅል አሳጥቶኝ ይሆን እንዴ እኔ ስከላከል ውዴ ጭራሽ የሚብስባት? ለነገሩ ልክ ናት፡፡ በዘመኑ አነጋገር ፈታ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ወጣ ብሎ መብላትና መጠጣት፣ መናፈሻ ሄዶ መዝናናት፣ አሪፍ ሙዚቃና ቴአትር ማዳመጥና መመልከት፣ አስፈላጊ ሲሆንም ሲኒማ መመልከት አስፈላጊ ነው፡፡ ጎበዝ ፈታ እንበል!

አዕምሮዬ በአንድ በኩል በማንጠግቦሽ ሰሞነኛ የመዘንጋት አመል፣ በሌላ በኩል ለማሻሻጥ እየሮጥኩለት በነበረው አምስት ዓመት የሠራ ባለተጎታች ቦቴ ምክንያት ተወጥሮ ነበር። በዚህ መሀል ከኋላዬ ‹‹አንበርብር!›› የሚል ድምፅ ብሰማ ወዲያው ዞርኩ። በቅርቡ ከወንድሙ ጋር ተጋግዞ ሬስቶራንት የከፈተ የቀድሞ ደላላ ወዳጄ ድምፅ ነበር። ቤቱን አይቼለት ስለማላውቅ እግረ መንገዴን ጎራ እንድል ፈልጎ ስለሥራው እያጫወተኝ ሳለ ድንገት የመገረም ፈገግታ አሳይቶኝ፣ ‹‹‹ጤና ተቆጣጣሪዎች መጥተው መፀዳጃ ቤቱን ለማየት ገብተው ፅዱና ደረጃውን ያሟላ መሆኑን ዓይተው ሲያበቁ፣ ‹ይኼንን ባለሳህን መቀመጫ አንስተህ የመሬቱን ነው ማድረግ ያለብህ…› አይሉኝ መሰለህ? ለምን? ስላቸው ‹አዲስ የወጣ መመርያ ነው። በሁሉም ላይ ተግባራዊ እናደርገዋለን› አሉኝ። እኔም ደሜ ፈልቶ መመርያው የወጣው ለእኔ ብቻ ነው? ስላቸው እርስ በርሳቸው ይተያዩ ጀመር። እኔምለው አንበርብር ደንብና መመርያ የሚወጣው በደመነፍስ ነው እንዴ?›› በማለት አስደመመኝ። የአንዳንዱ መመርያ ‹‹ላም በሌለበት ኩበት ለቀማ››፣ የአንዳንዱ ደግሞ ‹‹ልፋ ያለው ገለባ ይወቃል›› ዓይነት ሲሆን ስናይ አግራሞታችን ያይላል፡፡ ‹‹ግራ ተጋብተው ግራ የሚያጋቡ ባይበዙ እኮ የጀመርነው የሰላም ፍለጋ ጉዞ ለምሥራቅ አፍሪካ ይተርፍ ነበር…›› ያለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ ድንቄም አመራር! 

በሉ እንሰነባበት። በለስ ቀንቶኝ ቦቴውን አሻሽጬ ጠቀም ያለ ገንዘብ ቆጠርኩ። ያሻሻጥኩለት ሰው የዕድሜውን ግማሽ ነዳጅ ሲያመላልስ ቢኖርም፣ ነዳጅ መፈለግ እንጂ በበቂ መጠን ማግኘት ያቃተን ምስኪኖች ስለሆንን ቅር እንዳይልህ ብሎ ያሰበልኝ ኮሚሽን ከበቂ በላይ ሆኖብኛል። አባባሉ የብዙዎቻችንን ምኞት ይወክል ይሆን ብዬ መብሰልሰሌ ግን አልቀረም። ይኼንን ጥያቄ ይዘን የተለመደችው ግሮሰሪያችን ቀዝቃዛ ቢራችንን እየተጎነጨን ነው፡፡ ‹‹በጦርነት፣ በድርቅና በረሃብ ምክንያት የጠቆረው ስማችን ሰሞኑን በሰላም መነሳት ጀምሯል፡፡ አሁን የቀረን አንድ ነገር ብቻ ነው…›› አለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፡፡ ቀና ብዬ፣ ‹‹ምንድነው እሱ?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ ‹‹በኢትዮጵያዊ ጨዋነት የታጀበ ብሔራዊ አንድነት፡፡ ከጥላቻና ከንቀት የተላቀቀ መከባበር፡፡ ሁሉም በእኩልነትና በባለቤትነት ስሜት የሚኖርባትን ዴሞክራሲያዊት አገር ዕውን ማድረግ፡፡ ከዚያ ዜጎች በአገራቸው አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲራመዱ ምኅዳሩን ማመቻቸት፡፡ ዋናው አንገትን አንዴ ቀና ማድረግ ነው። ከዚያ በኋላ ጉዞው አባጣ ጎርባጣ የሌለበት ሜዳ ነው…›› ብሎኝ ሲያበቃ፣ ‹‹…ፖለቲከኞችም ቂም በቀላቸውን ትተው የተወጠረው አየር ተንፈስ ብሎ እኛም ንፁህ አየር እንማግ፡፡  ስለዚህ የተኳረፍን፣ ጀርባ ለጀርባ የተሰጣጣን፣ በአሉባልታና በሐሜት የተለያየን፣ በጠመንጃ አገር ለማፍረስ የምንባዝንና ባልበሰለ አስተሳሰብ ታሪክ የምናዛባ ተቀራርበን ችግራችንን በሰላማዊ መንገድ እንፍታ፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው መንፈራገጥ አጉል መላላጥ ነው…›› እያለኝ ወጋችን ተቋጨ፡፡ አጉል መንፈራገጥ ለማንም አይጠቅምም፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት