Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቅባት እህልና የጥራጥሬ ምርቶች ያከማቹ ላኪዎች በፍጥነት እንዲሸጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባለፈው የምርት ዘመን ተመርቶ ላኪዎች ከውጭ ገዥዎች ጋር ውል ሳያስሩ የተከማቸውን የቅባት እህልና ጥራጥሬ ምርት፣ እስከ ኅዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ውል አስረው እንዲሸጡ ማስጠንቀቂያ ሰጠ፡፡

ሪፖርተር የተመለከተውና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ለላኪዎች ያወጣው ማስታወቂያ እንደሚያስረዳው፣ ምርቱን ለመላክ ውል የገቡም ሆነ ውል ያልገቡ ላኪ ድርጅቶች ያለፈውን የምርት ዘመን (2013/2014) በክምችት የሚገኙ የቅባትና የጥራጥሬ ምርቶችን በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከአገር እንዲያስወጡ ቀነ ገደብ ተሰጥቷቸዋል፡፡

የግብይት ሥርዓታቸው በአስገዳጅነት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚከናወን የጥራጥሬና የቅባት የወጪ እህሎች በተመረቱበት የምርት ዘመን ወደ ውጭ ሙሉ በሙሉ መላክ እንዳለባቸው ያስታወሰው ሚኒስቴሩ፣ ምርት በክምችት ይዘው የውጭ ውል ያልፈጸሙ ላኪዎች እስከ ኅዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ውል ፈጽመው ምርቱን ማስወጣት አለባቸው ብሏል፡፡ ማሳሰቢያውን ተግባራዊ በማያደርጉ ማናቸውም ላኪ ድርጅቶች ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣቸውን ደንቦች መሠረት በማድረግ ዕርምጃ የሚወሰድ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም ማናቸውም ላኪ ድርጅቶች ከምርት ገበያ የገዙትንም ሆነ  በኢንቨስትመንት እርሻ የለማ ያለፈው ዓመት የምርት ዘመን ምርት ክምችትን  የውጭ ውል ፈጽመው እስካሁን ካላኩ፣ ከኅዳር 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት 15 ቀናት ውስጥ ምርቱን መላክ እንዳለባቸው ተነግሯቸዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ባለፈው ወር ከላኪዎች ጋር ባደረገው ውይይት የጥራጥሬና የቅባት እህሎች አከማችተው የተገኙ ላኪዎች ምርቱን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ውጭ የማይልኩ ከሆነ፣ እስከ የሕግ ተጠያቂነት የሚያደርስ ዕርምጃ እንደሚወስድ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከመስከረም 13 ቀን 2015 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 2 ቀን 2015 ዓ.ም. በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ መጋዘኖች ባደረገው ቆጠራ፣ ወደ ውጭ መላክ የነበረበትን 944,023 ኩንታል ጥራጥሬና የቅባት እህል አከማችተው የተገኙ ላኪዎች ምርቱን ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ በተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር፡፡

ከዚህ ቀደም ሚኒስቴሩ ከላኪዎች ጋር አድርጎ በነበረ ውይይት የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመጥቀስ ላኪዎች እህል በማከማቸት የውጭ ምንዛሪ እንዳይገኝ ማድረጋቸውን አስታውቆ፣ በላኪዎቹ ላይ ወቀሳ ማቅረቡ አይዘነጋም፡፡ ላኪዎች በበኩላቸው ከገዥ ጋር ተስማምተው ምርቱን መላኪያ ፈቃድ ለማግኘት ወደ ሚኒስቴሩ ሲሄዱ ዋጋው ከተመኑ ያነሰ ነው የሚል ምላሽ እንደሚሰጣቸው፣ በተጨማሪም በዓለም ላይ ያለው የገበያ ፍላጎት መቀዛቀዝም ምርቱ ለመከማቸቱ ምክንያት ነው የሚል ሐሳብ ማንሳታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከምታገኝባቸው ዘርፎች ውስጥ የቅባትና የጥራጥሬ ምርቶች የወጪ ንግድ ተጠቃሽ መሆኑ በተደጋጋሚ የሚገለጽ ሲሆን፣ ዘርፉ በበርካታ ችግሮች ምክንያት ባለፉት ዓመታት ማስገኘት የሚገባውን ያህል የውጭ ምንዛሪ እንዳላስገኘ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ከግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከሚገኝባቸው ንዑሳን ክፍሎች ውስጥ ከጥራጥሬና ከቅባት እህሎች በ2014 በጀት ዓመት 477 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ የሚታወስ ሲሆን፣ በተያዘው በጀት ዓመት ከምርቶቹ ወጪ ንግድ 595.1 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች