የገንዘብ ሚኒስቴር የኤክሳይዝ ታክስ የተጣለባቸው ዕቃዎች፣ ታክሱ እንደተከፈለባቸው ለማረጋገጫነት የሚያገለግል ‹‹የኤክሳይስ ቴምብር›› እንዲለጠፍባቸው የሚያስገድደውን ሥርዓት ሊያስጀምር ነው፡፡
ሚኒስቴሩ ሥርዓቱን የሚያስጀምረው ታክሱ በተጣለባቸው በአልኮልና በሲጋራ ምርቶች ላይ ሲሆን፣ ይህንን ሥርዓት ለመዘርጋትና ቴምብሩን ማቅረብ የሚችሉ ድርጅቶች ፍላጎታቸውን እንዲገልጹ ማስታወቂያ አውጥቷል፡፡
ማስታወቂያው እንደሚያስረዳው የኤክሳይስ ታክስ በተከፈለባቸው ዕቃዎች ላይ የሚለጠፈው የቴምብር ዓይነት በዕቃው ላይ የሚቀመጥ ልጥፍ፣ ማሸጊያ ማኅተም፣ ወይም ሌላ ዓይነት ማኅተም ሊሆን ይችላል፡፡ ፍላጎታቸውን ከገለጹ ድርጅቶች መካከል የሚመረጠው የቴክኖሎጂ አቅራቢ የኤክሳይዝ ቴምብሩን የማምረት፣ የማከማቸት፣ የማሠራጨትና የማረጋገጥ ኃላፊነትና ቴምብሩን በብቸኝነት የማከፋፈል መብት ይኖረዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ተግባራዊ ለማድረግ ያቀደው የኤክሳይስ ቴምብር ሥርዓት በ2012 ዓ.ም. በወጣው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ የተደነገገ ነው፡፡ በተመረጡ ዕቃዎች ላይ ቴምብር መለጠፍ ያስፈለገው የኤክሳይዝ ታክስ የተጣለባቸው ዕቃዎች በኮንትሮባንድ በብዛት ወደ አገር ውስጥ በመግባታቸው ምክንያት ከኤክሳይዝ ታክስ የሚሰበሰበው ገቢ ዝቅተኛ በመሆኑ እንደሆነ ከአዋጁ ጋር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የነበረው ማብራሪያ ይገልጻል፡፡ ታክሱ የተጣለባቸውን ምርቶች የሚያመርቱ ድርጅቶች ተገቢውን ታክስ አለመክፈላቸውም ለቴምብሩ አስፈላጊነት በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡
ከዚህም ባሻገር መንግሥት ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ ዕቃዎች ላይ ቴምብር በመለጠፍ፣ ከቀረጥ ነፃ ከገቡ በኋላ ለገበያ የሚቀርቡ ዕቃዎችን የመቆጣጠር ዕቅድ እንዳለው ማብራሪያው ያስረዳል፡፡
የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቴምብሩ ሊለጠፍባቸው የሚገቡ ኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸው ዕቃዎችን የመወሰን ኃላፊነት የገንዘብ ሚኒስቴር እንደሆነ የደነገገ ሲሆን፣ ከቴምብር ሥርዓቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ በሚኒስቴሩ መመርያ እንደሚወጣ ተመልክቷል፡፡
ገንዘብ ሚኒስቴር የቴምብር ሥርዓቱን በተመለከተ መመርያ እንዳዘጋጀና ቴምብር እንዲለጠፍባቸው የተመረጡት የአልኮልና የሲጋራ ምርቶች መሆናቸውን፣ ሪፖርተር በሚኒስቴሩ ውስጥ ከሚገኙ ምንጮች ሰምቷል፡፡
ከሦስት ዓመት በፊት የወጣው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ በቢራ ላይ 40 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ የጣለ ሲሆን፣ ቢራው ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ በበቀለ ገብስ የተመረተ ከሆነ ታክሱ ወደ 35 በመቶ ይቀንሳል፡፡ እንደ ውስኪ፣ ጂንና ቮድካ የመሳሰለ የአልኮም መጠጦች ደግሞ የተጣለባቸው ኤስሳይዝ ታክስ 80 በመቶ ነው፡፡
አዋጁ በሲጋራ ላይ የ30 በመቶና በእያንዳንዱ እሽግ ላይ ስምንት ብር ኤክሳይዝ ታክስ የጣለ ሲሆን፣ በፒፓ የሚጨሱና ሌሎች የትምባሆ ምርቶች ላይ ከ30 በመቶ በተጨማሪ፣ በግራም 250 ብር ታክስ ተጥሎባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሲጋራ ለማምረት ግብዓት የሚሆን የትምባሆ ቅጠልና ያልተፈበረከ ትምባሆ 20 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ተጥሎባቸዋል፡፡
መንግሥት በ2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ትምባሆ ድርጅትን በአንድ ቢሊዮን ዶላር ለግሉ ዘርፍ ሲሸጥ፣ በአገሪቱ ትምባሆ የማምረትና የመሸጥ የብቸኝነት መብትንም ለገዥዎቹ አብሮ ሸጧል፡፡ ይሁንና የድርጅቱን 70 በመቶ የያዘው የጃፓን ትምባሆ ኢንተርናሽናል ኩባንያ ድርጅቱ ከሚያመርታቸው የሲጋራ ዓይነቶች ውጪ፣ በኮንትሮባንድ ከ70 በላይ የሲጋራ ምርቶች ገበያው ውስጥ እንደሚገኙ ይገልጻል፡፡
ገንዘብ ሚኒስቴር ሊያስጀምር እየተዘጋጀ ያለው የኤክሳይዝ ታክስ ቴምብር ከኮንትሮባንድ ንግድ ጋር የተያያዙ እንዲህ ዓይነት ችግሮችን ይቀርፋል የሚል እምነት ተጥሎበታል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሚኒስቴሩ ምንጮች እንደሚያስረዱት፣ የአልኮልና የሲጋራ ምርቶች በፋብሪካ ተመርተው ከመውጣታቸው በፊት በእያንዳንዱ ምርት ቴምብር ይለጠፍባቸዋል፡፡ ቴምብር ሳይኖረው ገበያ ውስጥ የቀረበ የሲጋራና የአልኮል ምርት “በሕገወጥነት” እንደሚያዝም አክለዋል፡፡
ገንዘብ ሚኒስቴር ያወጣው የፍላጎት መግለጫ ማስታወቂ እንደሚገልጸው፣ የሚመረጠው ድርጅት የኤክሳይዝ ቴምብር ሥርዓቱን የመዘርጋትና ሥርዓቱን ለማስፈጸም የሚያገለግል ቴክኖሎጂ የማቅረብ ኃላፊነት ይወስዳል፡፡ የቴክኖሎጂ ሥርዓቱ ቴምብሩን ኦንላይን ለማዘዝ፣ ለማረጋገጥና ሪፖርት ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡
በተጨማሪም የሚመረጠው ድርጅት የኤክሳይዝ ታክስ ቴምብሩን ሥርጭት ለመከታተል (Track and Trace) የሚያስችል ሥርዓት የሚያቀርብ ከሆነ፣ ሚኒስቴሩ ፍላጎቱ እንደሆነ በማስታወቂያው ላይ ሠፍሯል፡፡