Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በመንግሥትና በግል አጋርነት የመኖሪያ ቤቶችንና ሱቆችን ሊያስገነባ ነው

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በመንግሥትና በግል አጋርነት የመኖሪያ ቤቶችንና ሱቆችን ሊያስገነባ ነው

ቀን:

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ይዞታዎቹ በሆኑ ስድስት ቦታዎች ላይ፣ በመንግሥትና በግል አጋርነት 998 የመኖሪያ ቤቶችንና 696 ሱቆችን ሊያስገነባ ነው፡፡

ሕንፃዎቹን ለመገንባት የሚያስፈልገው በጀት አምስት ቢሊዮን ብር እንደሆነ የተገመተ ሲሆን፣ ለግንባታው የአዋጪነት ጥናት ተጠናቆ የገንዘብ ሚኒስቴር የፍላጎት መግለጫ እንዲያወጣ እየተጠበቀ መሆኑን፣ በኮርፖሬሽኑ የቤት ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሚኪያስ ገዛኸኝ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ቤቶችንና ሱቆችን የሚይዙት ሕንፃዎች የሚገነቡት አዲሱ ገበያ፣ አብነት፣ ፓስተር፣ ጃን ሜዳ፣ ቦሌ ሳንጋምና ጆሳንሰን በተባሉት ሳይቶች ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ ሚኪያስ፣ ቦታዎቹ ከሁለት እስከ አምስት ሺሕ ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡ የስድስቱ ቦታዎች አጠቃላይ ስፋት 19,995 ካሬ ሜትር ወይም ሁለት ሔክታር ገደማ መሆኑን አክለዋል፡፡

እንደ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፣ ቤቶቹ የሚገነቡት ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎችን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር በቀጠራቸው ዓለም አቀፍ አማካሪዎች የተሠራው የአዋጪነት ጥናት፣ ቤቶቹ ተገንብተው በተመጣጣኝ ዋጋ ሊከራዩ እንደሚችሉ ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡

የአዋጭት ጥናቱ በገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ በሚገኘው የመንግሥትና የግል አጋርነት ቦርድ ቀርቦ ተቀባይነት ማግኘቱን ለሪፖርተር የተናገሩት የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይለ ብርሃን ዜና፣ ‹‹ቦርዱ በእኛ ኮርፖሬሽን አማካይነት ከውጪ ፍላጎት ኖሮት ከሚመጣ አጋር ጋር መቀጠል ይችላል በሚል ተቀብሎታል፤›› ብለዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በመንግሥትና በግል አጋርነት ሕንፃዎችን ለመገንባት ዕቅድ ሲይዝ ይኼ የመጀመሪያው ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ላስገነባቸውንና ሊያስገነባ በዕቅድ ለያዛቸው ፕሮጀክቶች በጀት ሲያገኝ የነበረው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሚወስደው ብድር ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ በተያዘው በጀት ዓመት በአራት ቢሊዮን ብር ወጪ 1,600 ቤቶችን ለመገንባት ዲዛይን አዘጋጅቶ በጀት ለማግኘት እየተጠባበቀ ነው፡፡

የቤት ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ሚኪያስ እንደሚስረዱት፣ ከግል ዘርፍ ጋር በሚደረግ አጋርነት ሊሠሩ ለታሰቡት ቤቶች ሙሉ ወጪውን የሚፍነውና ግንባታውን የሚያከናውነው አጋርነት የሚገባው የግል ኩባንያ ነው፡፡ ሕንፃዎቹ ከተገነቡ በኋላ ከቤቶቹ ኪራይና ከሱቆቹ ሽያጭ ወጪውን ከእነ ትርፉ ለኩባንያው መመለስ እንደሚቻል የአዋጪነት ጥናቱ ማመላከቱን የሚናገሩት አቶ ሚኪያስ፣ ‹‹እስከዚያው እኛ እናስተዳድራለን፣ እነሱ ገንዘቡን ይሰበስባሉ፣ ሲጨርሱ ንብረቱን አስረክበውን የሕዝብ ይሆናል፤›› ሲሉ የኮርፖሬሽን ዕቅድ ገልጸዋል፡፡

‹‹[ሊገነቡ የታሰቡት] ሕንፃዎቹ ከ20 በላይ ወለል ያላቸው ናቸው፤›› ያሉት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በዚህም ምክንያት የግንባታ ወጪው እስከ አምስት ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ መገመቱን አክለዋል፡፡

ቤትን በባለቤትነት ይዞ ለነዋሪዎች የማቅረብ ኃላፊነት የኮርፖሬሽኑ እንደሆነ ጠቅሰው፣ በአጋርነት የሚገባው ኩባንያ ከሚገነቡት አንድ ሺሕ ገደማ ቤቶች ውስጥ በቋሚነት የሚወስዳቸው ቤቶች እንደማይኖሩ አስረድተዋል፡፡ ከቤቶቹ ጋር የሚገነቡት 700 አካባቢ ሱቆች ለሽያጭ የሚቀርቡትም ከሽያጩ የሚገኘው ገቢ ለኩባንያው ውጪና ትርፉን ለመክፈል እንደሚያግዝ፣ የአዋጪነት ጥናቱ በማመላከቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአጋርነት የሚገባው ኩባንያው ትርፍ በምን ያህል እንደሚሆንና ወጪና ትርፉን በምን ያህል ጊዜ ውስጥ እንደሚወስድ የሚወሰነው፣ የፍላጎት መግለጫ ወጥቶ አጋርነት የሚገባ ኩባንያ ሲመረጥ መሆኑን አክለዋል፡፡

በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች 18,456 ቤቶች የሚያስተዳድረው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በ33.1 ቢሊዮን ብር ካፒታል እንደ አዲስ የተቋቋመው በ2009 ዓ.ም. ነበር፡፡ የኮርፖሬሽኑ የሀብት መጠን ለማወቅ የቤቶች ትመና (Housing Valuation) በገለልተኛ አካል ተሠርቶ የኮርፖሬሽኑ የሀብት መጠን 71 ቢሊዮን ብር እንደሆነ መተመኑን፣ በሰኔ 2014 ዓ.ም. ገልጾ ነበር፡፡ ኮርፖሬሽኑ በ2010 ዓ.ም. ሲያገኝ የነበረው ዓመታዊ ገቢ 300 ሚሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን ገቢው 2.2 ቢሊዮን ብር መድረሱንም አስታውቋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ለ28 ዓመታት ቤቶችን መገንባት አቁሞ ስለነበረ፣ በመጀመርያ ጊዜ ግንባታ በአዲስ አበባ በአምስት ሳይቶች ለመኖሪያና ለንግድ አገልግሎት ያስገነባቸውን ስምንት ብሎኮች ሰኔ ቀን 2013 ዓ.ም. ማስመረቁ ይታወሳል፡፡

ከአንድ ዓመት በኋላ ሰኔ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ደግሞ በ18 ወራት ውስጥ ገንብቶ ያጠናቀቀውን የገርጂ መኖሪያ መንደር ሰኔ 2014 ዓ.ም. አስመርቋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በ3.06 ቢሊዮን ብር አስገንብቶ ያስመረቀው ዘመናዊ የገርጂ መኖሪያ መንደር ገና ለነዋሪዎች ሳይተላለፍ፣ ከተገነባበት ዋጋ በአሥር ቢሊዮን ብር ጨምሮ 13 ቢሊዮን ብር እንደተገመተ በመንደሩ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ተነግሮ ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...