Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የምግብ ዘይት አምራቾች ምርቶቻቸው ለገበያ ባለመቅረባቸው ተጨማሪ ለማምረት ተቸግረናል አሉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ፌቤላ ፋብሪካ ማምረት አቁሟል
  • ሸሙ ፋብሪካ 5.6 ሚሊዮን ሊትር ተከማችቶበታል
  • ፋብሪካዎች በየትኛውም ቦታ እንዲሸጡ በጊዜያዊነት ሊፈድ ነው

የአገሪቱ ትልልቅ የምግብ ዘይት አምራች ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ገበያ ወጥተው ባለመከፋፈላቸው ምክንያት፣ ተጨማሪ ለማምረት መቸገራቸውን አስታወቁ፡፡ ከአምራቾቹ እየተቀበሉ ለኅብረተሰቡ የሚያከፋፍሉት ማኅበራትም ምርጫቸውን በፍራንኮ ቫሉታ (Franco Valuta) የሚገቡ የምግብ ዘይት ዓይነቶች ላይ በማድረጋቸው፣ በአገር ውስጥ የሚመረቱት ዘይቶችን እያከፋፈሉ እንዳልሆኑ አምራቾችና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገልጸዋል፡፡

የዘይት አምራች ፋብሪካዎች ከመንግሥት የውጭ ምንዛሪ ተመድቦላቸው የፓልም ድፍድፍ ዘይት (Palm Crude Oil) ከውጭ በማስገባት በማጣራት ሥራ የተሰማሩ ሲሆን፣ ምርቶቻቸውን የሚሸጡት በተወሰኑና በተመደቡላቸው ቦታዎች ብቻ ነው። ለዚህም ሥራ በመንግሥት የተመደቡት አከፋፋይ ማኅበራት የተመረቱትን ምርቶች እያነሱላቸው እንዳልሆነ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊዎች ባለፈው ሳምንት ፓርላማ ቀርበው ተናግረዋል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የሚኒስቴሩ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ፋብሪካዎቹ በዓለም ገበያ ዋጋ በጨመረበት ጊዜ ባስገቡት ድፍድፍ ቢያመርቱም፣ ምርቶቻቸውን ማኅበራቱ ብቻ እንዲሸጡ በመንግሥት በመደረጉና ማኅበራቱ ባለመፈለጋቸው ነው፡፡ ከገዙበት የጥሬ ዕቃ ዋጋ አንፃር የሚሸጡበት ዋጋ ከፍ የሚል ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ነጋዴዎች በራሳቸው የውጭ ምንዛሪ በፍራንኮ ቫሉታ ከሚያስገቡት ከሱፍ አበባ ዘይት ጋር በዋጋ ብዙም ላይለይ ችሏል።

በሩሲያና በዩክሬን ጦርነት ምክንያት አንድ ቶን የፓልም ድፍድፍ ዘይት ካለፈው በጀት ዓመት አጋማሽ አካባቢ ጀምሮ እስከ 1,900 ዶላር ድረስ ይሸጥ የነበረ ሲሆን፣ አብዛኞቹም ፋብሪካዎች በዚህ ዋጋ ነበር ግብዓቶቻቸውን ያስገቡት። በአሁኑ ጊዜ ተመሳሳይ ይዘት ያለው የፓልም ድፍድፍ ዘይት ወደ 1,200 ዶላር በመውረድ እየተሸጠ ነው።

‹‹በአጋጣሚ አሁን የዓለም አቀፍ ዋጋው ወረደ፣ ነገር ግን ቀድሞ በውድ የገባውን ዘይት እኛ የገበያ ትስስር የሠራንላቸው ማኅበራት አከፋፋዮች አሁን ከፋብሪካዎቹ የመውሰድ ፍላጎት የላቸውም፤›› ሲሉ፣ አከፋፋዮቹ በፍራንኮ ቫሉታ የገባውን ዘይት ለደንበኞቻቸው የመሸጥ ፍላጎት እንዳላቸው ኃላፊው አስረድተዋል።

እንደ ጊዜያዊ መፍትሔ ፋብሪካዎቹ ምርቶቻቸውን በግዴታ በተሳሰሯቸው ማኅበራት ብቻና በተወሰነላቸው ቦታዎች ብቻ ሳይሆን፣ በፈለጉበት ቦታ እንዲሸጡ ለማድረግ መታቀዱን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኃላፊ ገልጸዋል። ‹‹በጊዜያዊነት ግዴታ መሆኑ ቀርቶ ምርታቸውን ተወዳዳሪ በሆነ ዋጋ በፈለጉበት ቦታ እንዲሸጡ ሊፈቀድላቸው ነው፤›› ሲሉ ኃላፊው አረጋግጠዋል።

በድሬዳዋ የሚገኘውና መንግሥት ለግብዓት ማስገቢያ የውጭ ምንዛሪ ከሚመድብላቸው አምስት ግዙፍ ፋብሪካዎች አንደኛው የሆነው ሸሙ የምግብ ዘይት ማምረቻ ከተጎዱት አንደኛው ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜም በጥቅምት ወር ተከፋፍሎ ማለቅ የነበረበት 5.6 ሚሊዮን ሊትር ዘይት በመጋዘኑ ተከማችቶ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት በግብዓት እጥረት ምክንያት የአቅሙን 30 በመቶ ብቻ ያመረተው ፋብሪካው፣ በአሁኑ ጊዜ ያመረተውን ዘይት ባለመከፋፈሉ ብቻ ከ20 በመቶ በታች እያመረተ እንደሚገኝ የፋብሪካው ኃላፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል።

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋ ሚካኤል ሚካኤል ጉዑሽ እንደሚሉት፣ ፋብሪካው የገጠመው ችግር ዋነኛ ምክንያት የግብዓት ውድ መሆንና በፍራንኮ ቫሉታ የሚገባ ዘይት የበለጠ ተመራጭ መሆኑ ነው፡፡ በራሳቸው የውጭ ምንዛሪ ዘይት የሚያስገቡ ነጋዴዎች ዋጋ እነ ሸሙ ፋብሪካ ግብዓት አስመጥተው፣ አምርተውና አጓጉዘው እስኪያደርሱ ድረስ ከሚሸጡበት ዋጋ ጋር ተመጣጣኝ መሆኑን ነው የገለጹት። ‹‹በእርግጥ ዋናው ለኅበረተሰቡ ዋጋ እንዲረጋጋለት ስለሆነ የሚፈለገው፣ መንግሥትም ተፈጥሮ የነበረውን ቀውስ ለመቅረፍ ነው የወሰነው፤›› ብለዋል፡፡

በፋብሪካው በአሁኑ ጊዜ ተመርቶና ተከፋፍሎ ማለቅ የነበረበት ድፍድፍ የፓልም ዘይት እንዳለ፣ ፋብሪካው ግቢ ውስጥ ለአከፋፋዮቹ በሊትር 120 ብር ዋጋ ባለ 20 ሊትር ጀሪካን ዘይት እንደሚሸጥ ኃላፊው ተናግረዋል።

ሌላው ግዙፉ በበላይነህ ክንዴ ግሩፕ ሥር የሚገኘው ፊቤላ ዘይት ፋብሪካ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ በፋብሪካው ተመርቶ ያልተከፋፈለ ዘይት መጋዘኑን ስለሞላ፣ ዘይት እያመረተ አለመሆኑን የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ እንየው ዋሴ ለሪፖርተር ተናግረዋል። ፋብሪካው ባለፈው ዓመት የአቅሙን 24 በመቶ ያመርት እንደነበር፣ በአሁኑ ጊዜ ግን ምርት ማቆሙን ዋና ሥራ አስኪያጁ ክለዋል።

‹‹አከፋፋዮቹ ሊወስዱልን ስላልቻሉ በእኛ በኩል ትልቅ ክምችት ነው ያለን። በፊት ተራ በተራ ወረፋ እየጠበቁ ነበር የሚወስዱት፡፡ አሁን ግን ሌላ የፍራንኮ ቫሉታ ምርጫ ስላላቸው ሊወስዱልን አልቻሉም። እኛ ደግሞ መንግሥት ዋጋ ተምኖልን እሱ ለመደባቸው አከፋፋዮች ስለምናስረክብ ተወዳድረን ለሕዝብ መሸጥ አንችልም፤›› ብለዋል።

ፊቤላ ፋብሪካም ዘይቱ በሊትር ከ125 እስከ 127 ብር የሚሸጥ መሆኑን፣ የአከፋፋዮቹ ትርፍ መንግሥት በወሰነላቸው መሠረት ሦስት በመቶ እንደሆነ፣ በፍራንኮ ቫሉታ የሚመጣውን ዘይት ትርፍ ነፃ ገበያ እንደመሆኑ መንግሥት የሚቆጣጠረው እንዳልሆነ ገልጸው፣ ‹‹ከእኛ ፋብሪካ አብዛኛው ክልል ዘይት ይወስድ ነበር፡፡ አሁን ግን በፊት የሚወስዱልን በአካባቢያቸው በፍራንኮ ቫሉታ የገባውን ዘይት ስለሚያገኙ ከእኛ የሚወስድ የለም፤›› ሲሉ አቶ እንየው አስረድተዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች