Saturday, December 3, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፖርትየጁዶና ጂጂትሱ ስፖርት ተስፈኛዋ እንስት ሕልፈት

  የጁዶና ጂጂትሱ ስፖርት ተስፈኛዋ እንስት ሕልፈት

  ቀን:

  የጁዶና ጂጂትሱ ስፖርት የጃፓን ተወዳጅ ባህላዊ ስፖርት ሲሆን፣ ሁለቱም በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ይዘወተራሉ፡፡ በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. 2007 ጀምሮ መዘውተር እንደጀመሩ የሚነገር ሲሆን፣ ስፖርቱ ተወዳጅ ቢሆንም በጥቂት ባለሙያዎች ብቻ እየታገዘ ቆይቷል፡፡

  ከእነዚህም መካከል በጂጂትሱ በኢትዮጵያ በተዘጋጁ የዓለም አቀፍ ውድድሮችና  በአፍሪካ ሻምፒዮናዎች ላይ መካፈል የቻለችው የመጀመሪያዋ ሴት ኢትዮጵያዊት የ26 ዓመቷ መስከረም ዓለማየሁ አንደኛዋ ነበረች፡፡

  አትሌቷ እ.ኤ.አ. በ2019 በሞሮኮ በተዘጋጀ ሻምፒዮና ላይ የአፍሪካ ምክትል ሻምፒዮን በመሆን የብርና የነሐስ ሜዳልያ የማግኘት ድልን መጎናፀፍ ችላለች፡፡ በ14 ዓመቷ የጁዱና የጂጂትሱ ስፖርት የጀመረችው መስከረም በግሏ ስፖንሰር በማፈላለግ ጭምር በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሻምፒዮናዎች ላይ ስትካፈል ቆይታለች፡፡ ምንም እንኳ ስፖርቱ በኢትዮጵያ በበርካቶች ተወዳጅ ስፖርት ቢሆንም፣ ትኩረት የተነፈገው በመሆኑ እንቅስቃሴ እንዲደረግ የመስከረም አስተዋፅዖ የጎላ እንደነበር ይነገራል፡፡

  መስከረም የዓለም አቀፍ ተሞክሮዋን ይዛ በኢትዮጵያ ስፖርቱን ለማስፋፋት ወጥና ስትንቀሳቀስ የነበረ ሲሆን፣ በግል ለሚሠለጥኑ ሠልጣኖች ሥልጠና ስትሰጥ ከመቆየቷ በዘለለ፣ በተለያዩ ቦታዎች ለማሠልጠን እንቅስቃሴ ጀምራ እንደነበረ ተገልጿል፡፡

  በቅርቡ 2022 የወርልድ ጌምስ ዕጩ ተመራጭ የነበረችው መስከረም፣ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአቡ ዳህቢ በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና ላይም በብቃት መሳተፍ ችላለች፡፡

  በዓለም አቀፍ ጁዶ ፌዴሬሽን የሴቶች ክፍል ባገኘችው ዕድል በርቀት የማኔጅመንት ሥልጠና ጀምራ ነበር። በኢትዮጵያ ስፖርቱ እንዲያድግና ዕውቅና እንዲያገኝ በከፍተኛ ሁኔታ ያለመታከት ስትሯሯጥና ስትደክም እንደነበረ የስፖርት አጋሯ የሆነችው እህቷ ፀሐይ ዓለማየሁ ለሪፖርተር አስረድታለች።

  በቅርቡም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ‹‹ጁዶ ለስደተኞች›› በሚል ፕሮግራም ሥልጠና ለመስጠት በቀረበው ፕሮግራም ላይ ሥልጠና ለመስጠትም እየተዘጋጀች እንደነበር እህቷ ፀሐይ ለሪፖርተር አስረድታለች።

  ከዚህም ባሻገር በተባበሩት መንግሥታት የስፖርት ለአካባቢ አየር እንቅስቃሴ ላይም ስፖርቷን በመወከል መሳተፏ ታውቋል፡፡

  ‹‹መስከረም ብሩህ አዕምሮ ያላት፣ ደግ፣ አበረታችና ታታሪ ሰው ነበረች። ከትምህርት ቤት ወደ ስፖርት፣ ከዚያም ከሥራ ወደ ስፖርት በስተቀር ሌላ የማታውቅ፣ ብዙ የማደግ ህልም የነበራት፣ በሄደችበት ቦታ በኩራት የኢትዮጵያን ባህል ያስተዋወቀች ነበረች፤›› በማለት ፀሐይ ትናገራለች፡፡ እሷን በመከተልም ታናሽ እህቷ ፀሐይ ጠንካራ አትሌት በመሆን በአፍሪካ ውድድሮችን ላይ በመካፈል የእህቷን ፈለግ የመከተል ሐሳብ እንዳላት ገልጻለች፡፡

  ከጥቂት ቀናት በፊት በአዲስ አበባ መጠነኛ ቀዶ ሕክምና አድርጋ በሰላም ወደ ቤቷ የተመለሰችው ወጣቷ፣ ከሕክምናው ሰባት ቀናት በኋላ ኅዳር 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡

  የቀብር ሥነ ሥርዓቷም ኅዳር 10 ቀን ኮተቤ በሚገኘው ሀና ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...