Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአገራዊ ጉዞው እንዲቃና ምን ይደረግ?

አገራዊ ጉዞው እንዲቃና ምን ይደረግ?

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው     

በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር የከፋ ቀውስ ሳይከተል አገራዊ ለውጥ ከመጣ አምስት ዓመታት ሊቆጠሩ ነው፡፡ ይህ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበረ ባህላዊ ለውጥ እንደሚንፀባረቅበት የታሰበው አዲስ ምዕራፍ፣ ኢሕአዴግ ረዥም ጊዜ ከወሰደ ተሃድሶው በኋላ ባካሄደው የአመራር ለውጥ ብቻ ሳይሆን የመጣው ብዙኃኑ ሕዝብ፣ የተለያዩ ተቃዋሚ ኃይሎች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎችና ሚዲያዎች ጭምር ለውጡን በማቀጣጠላቸውና ዕውን እንዲሆን በመታገላቸው ነበር፡፡

እናም በአንድም ይሁን በሌላ የእነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ትውልድና የአዲሱ የፖለቲካ ኃይል በኢሕአዴግ ውስጥ ያረጀውንና ወደ ጥላቻና መገፋፋት የተለጠጠውን አስተሳሰብ ለመቀየር መሪ ሲጨብጥ፣ ከጎኑ የነበረው ሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ ነበር፡፡ ለዚህ ቅቡልነት ዋነኛው ምክንያትም የለውጥ ኃይሉና አብዛኛው አመራር ምንም እንኳን ሲወቀስ በኖረው ኢሕአዴግ ውስጥ የቆየ ቢሆንም የአገራዊ አንድነትን፣ የፍቅርንና የይቅር መባባልን ዓርማ በማንሳቱ ነበር፣ ለውጥማ አለ የሚለው ወገን የበዛ የነበረው፡፡ አሁን የደበዘዘ መሆኑ ባይካድም፡፡

በአገር ደረጃ የኢኮኖሚውም ሆነ የማኅበራዊ ዘርፍ ጥያቄዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ለውጡ እንዲመጣ በቀዳሚነት በሕዝብ የተፈለገው የፖለቲካ ጥያቄዎችን እንዲፈታ ነበር፡፡ በተለይም የዴሞክራሲ ምኅዳሩ ላይ የወደቀው ጫና እንዲነሳ፣ ጠንካራ አገረ መንግሥትና የሕዝቦች አንድነትን ለመመለስም ሕዝቡ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በፆታና በአመለካከትም ሆነ በዕድሜ ያሉትን ተፈጥሯዊ ልዩነቶችን እንዲያጠብ የሚረዱ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ፣ በኢትዮጵያ የተጀመሩ የኢንቨስትመንት፣ የኢኮኖሚና የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች በፍትሐዊነት ሥርጭት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ፣ እንዲሁም እንደ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ብልሽቶች እንዲታረሙ ነበር፡፡

ለዚህም በሒደት በሕዝብ ቅቡልነት ያለው አካታች፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የተላበሰ መንግሥታዊ ሥርዓት መፍጠርን ሕዝብ በጉጉት ሲጠብቅ ነበር፡፡ በእርግጥም በለውጡ ጅማሬ ሰሞን የተስፋ ብርሃን መፈንጠቁና የሕዝቡም ተስፋና የጉጉት ከፍታ በቅርብ የምናስታውሰው ነበር፡፡ ዛሬም ያ ጅምር ተጠናክሮና ጎልብቶ እንዲመጣ የሚፈልገው እጅግ ብዙ ነው፡፡

ሲጀምር በአጭር ጊዜ ውስጥ የለውጡ ኃይል በአመለካከት ልዩነት ሰበብ የታሰሩ ዜጎችን መፈታቱ፣ ጋዜጠኞችና የማኅበራዊ አንቂዎች የሐሳብ ነፃነት እንዲያገኙ፣ የተጋጩና ጫፍና ጫፍ የቆሙ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ አገራቸው እንዲገቡና እንዲቀራረቡ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ ጉዳያቸው እየመከሩ፣ በልዩነታቸውም በነፃነት እየተንቀሳቀሱ በአገራቸው ጉዳይ ያገባኛል የሚሉበት ጊዜ እንዲመጣ፣ በሙስናና ብልሹ አሠራር አገርን የዘረፉ እንዲጠየቁና የሕዝብ ሀብትም እንዲመለስ ጥረቶች መደረጋቸው አዲስ የመነሳሳት አብዮት ቀስቅሶ ነበር፡፡

ሌላው ቀርቶ ከኤርትራ ሕዝብና መንግሥት ጋር የነበረውን ፍጥጫ በማስወገድ መቀራረብ መጀመሩ፣ ከሌሎች ጎረቤት አገሮች ጋርም በሰጥቶ መቀበል መርህና በመስማማት በጋራ ተጠቃሚ ለመሆን አዳዲስ ዕርምጃዎች ታይተው ነበር፡፡ ከዚያም አልፎ የለውጡ አመራር አኅጉራዊ ህልሙን በማንፀባረቅ ብቻ ሳይወሰን፣ ለመላው ዓለም ዜጋ ተኮርና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ የውጭ ግንኙነት አቅጣጫ እንደሚከተል አቋሙን ማንፀባረቁ ሕዝቡ ብቻ ሳይሆን፣ ሌላው ዓለምም አጋርነትና ዕውቅና እንዲሰጠው ገፋፍቶታል፡፡ ዋጋ ከፍሎም ቢሆን ማስቀጠል የሚያስፈልገው እንዲህ ዓይነት ጅምሮችን ነው፡፡

ያም ሆኖ ጅምሩ እንደታሰበው የለውጡ ጉዞ አልጋ በአልጋ መሆን አልቻለም፡፡ በሕዝብ ግፊትና በሥርዓቱ ውስጥ ባሉ ለውጥ ፈላጊዎች የተጀመረው አዲስ ዕርምጃ፣ ጥቅሙን ያሳጣውና ያልተዋጠለት ሕወሓት ዋነኛው ተገዳዳሪ ሆኖ፣ ሒደቱ ከፍተኛ እስከሚባል አውዳሚ ጦርነት ወስዷት ቆይቷል፡፡ ኦነግ ሸኔና ሌሎች ታጣቂዎችም ቀላል የማይባል ጉዳት እያደረሱ ነው፡፡ በዚህም ሺዎች ሞተዋል፣ ቆስለዋል፣ ተንገላተዋል፣ ሚሊዮኖች ተፈናቃይና ተረጅ ሆነዋል፡፡ በቢሊዮን የሚገመት የአገር ሀብት ለጦርነት ተማግዷል፡፡ ለስላሳና ሰላማዊ የተባለው ለውጥ ዛሬም ባልተረጋጋ አገራዊ ሁኔታ ውስጥ እንዲቃትት የሆነውም በዚሁ መዘዝ ነበር፡፡ አሁን ላይ ተንፈስ የማለት ምልክት እየታየ ቢመስልም፡፡

በእርግጥ ተስፋ የተጣለበት ለውጥ በድንገትና ያለ መስዋዕትነት የተገኘ እንዳልሆነ የተረጋጋጠ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት አምባገነናዊውን የደርግ ሥርዓት በተራዘመ የትጥቅ ትግል አሸንፎ በተለይም የብሔር መብቶችን በማስከበር፣ የኢኮኖሚ ለውጦችም እንዲመጡ ማድረጉም ካለ ጥርጥር የማይካድ ነው፡፡ ይሁንና ሥርዓቱ ዴሞክራሲን በማጥበቡና በማዳከሙ፣ ፌዴራሊዝም ትክክለኛ መፍትሔ ቢሆንም፣ ልዩነትንና ጎጠኝነትን በማባባሱ፣ ልማት ቢኖርም ኢፍትሐዊነት ሥር እየሰደደ በመሄዱ ነበር፡፡ አሁን ላይ ዘወር ብለን ስንመለከተው የቱ ተቀረፈ? የቱ አሁንም ተግዳሮት ገጠመው ብሎ መፈተሽ ብቻ ሳይሆን፣ ለዘለቄታው በምን ይታረቅ ነው ብሎ መጠየቅ፡፡

እንደ አለመታደል ሆኖ የተጀመረው ፖለቲካዊ ለውጥ ገና ተጠናክሮ በእግሩ እንዳይቆም ያደረጉት ሳንካዎች ምንድናቸው መባልም አለበት፡፡ ከሁሉ በላይ የሕዝቦች አብሮ የመኖር ባህል ተሸርሽሮ ጫፍ ላይ የደረሰው ቀደም ባሉት ዓመታት በተነዙት ትርክት ቢሆንም፣ ከለውጡ ወዲህ ቀላል የማይባሉ የሕዝብ መከራና ስቃዮች ተስተውለዋል፡፡ አንዱ ሕዝብ ከሌላው ጋር በጋራ አብሮ ለመኖር የተሳነው፣ እርስ በርሱ የሚገፋፋ፣ የአንድ አገር ልጆች በሐሳባዊ ክልል ታጥረው የሚሳደዱ፣ ዜጎችም ከማንነት ፍጥጫ ያልወጡበት አስከፊ ንፍቀ ክበብ እንዳረበበ እየታየብን ነው፡፡ አሁን የተጀመረው የሰላም ድርድር መፍትሔ ሊያመጣ የሚችል ቢሆንም፡፡

ይህን አስቸጋሪና አስከፊ ሁኔታ በማስወገድ አገር በተረጋጋና ዋስትና ባለው ሰላምና ዴሞክራሲ እንድትቀጥል የለውጥ ኃይሉ ብቻ አልነበረም ኃላፊነት ያለበት፡፡ እንደ ሕዝብም ከዛገውና የተጋነነው አስተሳሳብ ተላቆ፣ በሕግና በሥርዓት እየተመሩ መኖር በተገባ ነበር፡፡ ፖለቲከኞቻችንና የማኅበራዊ አንቂዎች የዘውግ ትርክትና የብሔር ፉክክርን በተለይም መጠራጠርን ከማጋጋል ይልቅ አብሮነትን፣ የግልጽነትና ተጠያቂነትን ብሎም የፍትሐዊነት አጀንዳን ማራመድ በጀመሩ ነበር፡፡ ምንም ተባለ ምን ግን፣ ይህ ድክመት ነው አሁን መወገድ መጀመር ያለበት፡፡

የመጣንበትን ክፉ ጊዜ ለመሻገር መንግሥትም ፈራ ተባ ሳይል ለሕዝቦች አብሮነት፣ ለብሔራዊ መግባባትና ለዕርቅ ብሎም ፍቅርና አንድነት መጎልበት አቅሙን አሟጦ መትጋት ይኖርበታል፡፡ ገና ሰፊ ግንዛቤና የጋራ እምነት ያልተያዘበትን የመደመር አስተሳሰብ በጥቂት መሪዎች አንደበት ብቻ ሳይሆን በመላው ገዥው ፓርቲ (ብልፅግና) ሰዎች አፍና ልብ ውስጥ ማስረፅና አለመሸርሸርም ያስልጋል፡፡ አልፎም ወደ ሕዝብ ለማውረድ ጥረት መደረግ አለበት፡፡ የመልካም አስተዳደር ጉዳይም ሊታሰብበት ግድ ይላል፡፡

ገና ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የለውጡንና የአገሪቱን መሪ ዓብይ (ዶ/ር)ን ‹‹ማኅተመ ጋንዲ››፣ ‹‹ዴዝሞንድ ቱቱ››፣ ‹‹ዳግማዊ ማንዴላ›› እስከ መባል ያደረሳቸው ጭብጥ የሕዝብ ተስፋ ማሳደር ነው፡፡ መነሻውም መድረሻውም ግፉአንን በማንሳታቸው፣ ያንዣበበውን አገራዊ የመነጣጣል ትርክት የሚቀርፍ ዕሳቤ በማራመዳቸውና የአገረ ኢትዮጵያን ታሪክና የሕዝቦች አንድነት በማውሳታቸው ነበር፡፡ የብሔር ብሔረሰቦችን ማንነትና መብት በመጠበቅ አዲስ የአብሮነት ዕሳቤ የመገንባቱ ህልም ከአገር ውስጥ አልፎ እስከ ቀጣናዊ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ውህደት የሚሻገር መሆኑን ከፍ ባለ ዕሳቤ በማራመዳቸውም ነበር፡፡ ዛሬስ ይህን ለማስቀጠል ምን ይቸግራል!?

ያኔ የተጀመረው ለውጥ እኮ! ተስፋ የተጣለበት ዕሳቤ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ከአገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተስተጋብቶ ነበር፡፡ አገሪቱን ሲመራ ከነበው ገዥው ፓርቲ የኖረና የሻገተ አስተሳሰብ የተለየ አንድነት፣ ፍቅርና ይቅር መባባልን በወርቃማ ቃላት መቀንቀናቸውም ብዙኃኑን ከማግባባቱ ባሻገር፣ ፈጠን ያለ ተግባራዊ ዕርምጃና ብሔራዊ ምክክር አጅቦት ቢሆን ኖሮ፣ እንደ አሁኑ ወደኋላ የሚመልስ የውስጥና የውጭ ተገዳዳሪ ባልበረከተ ነበር የሚሉ ተችዎች ግን ብዙ ናቸው፡፡ ትግሉ እንደ አዲስ መነቃቃት ያለበትም ለዚሁ ነው፡፡

እዚህ ላይ መታሰብ ያለበት ቁም ነገር በወቅቱ ሕዝቡ የሚያቀርባቸው ጥያቄዎች ብቻ ሳይሆኑ ከታሪክ፣ ከዓለም አቀፍና አገራዊ ፖሊተካችን አንፃር ተፈትሾ የተጣጣሙና ትዕግሥትን የተላበሱ ዕርምጃዎች እንደሚፈልጉ ጥርጥር የለውም፡፡ ከሁሉ በላይ በለውጡ ሥጋት የገባቸውን ወገኖች በፍትሐዊና ግልጽነት የተላበሰ አስተዳደር ማነፅ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ አሁን መንግሥት የጀመረው ለሰላም አማራጭ የመስጠት ሙከራና ፀረ ሙስና ትግል መጠናከር አለበት፡፡ የግድ!!

የሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ፍላጎት የሚያቀራርቡ ለጋ ዕሳቤዎችና ተግባራት እየተፈጸሙ፣ ይህ ሁሉ ሰላም አስከባሪና የፀጥታ ጠባቂ በፌዴራል ብቻ አይደለም በየክልሉ እየተዘጋጀ በነፃነትና በረጋ መንገድ ዜጎች ለመንቀሳቀስ ሊሠጉም አይገባም፡፡ የአገር ደኅንነትም በየጊዜው እየተፈተነ በሚሄድ ለውጥና የሕዝብ ተሳትፎ እንዲጠናከር መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ግን መንግሥት ብቻ ሳይሆን ምሁራን፣ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና ማኅበረሰብ አንቂዎች ኃላፊነት አለባቸው፡፡

ለውጡ ሲጀምር ሌላው ቀዳሚ አጀንዳ የነበረው አዲሱ ኃይል ብቻ ሳይሆን ራሱ ኢሕአዴግም በተሃድሶው ይል እንደነበረው የመልካም አስተዳደር ችግርን ቢያንስ መቀነስ ነበር፡፡ በተለይ በየአካባቢው ያለው ሥራ አጥነትና ድህነት ትልቁ አገራዊ ፈተና እንደመሆኑ ለመቅረፍ ጥረት ለማድረግም ታልሞ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን በእርስ በርስ ግጭቱና በኑሮ ውድነቱ ተባብሶ የቀጠለ ችግር መሆኑ ግን አይካድም፡፡ ይህንን ፈታኝ ሁኔታ መቀየር ነው የዚህ ትውልድ ሸክም ማለት ይቻላል፡፡

ዛሬ ከእነ ችግሩና ፈተናው አምስት ዓመታትን ተጉዘን፣ በአንድም ይሁን በሌላ እነዚህን ችግሮች አለመቀየር/አለመቀነስ ደግሞ ምንም ተባለ ምንም በአፋጣኝ መታረም ያለበት ነው፡፡ እዚህ ላይ የማይካደው እውነት፣ ዓለም አቀፋዊ ጫናዎችና የውስጥ ፖለቲካዊ ቀውሱ ጫና ያሳደረ መሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን የሕግና የአሠራር ማዕቀፎችን በማስተካከል፣ ደሃ ተኮር ተግባራትን በማጠናከርና ያፈጠጠውን የመልካም አስተዳዳር ብልሽት በማስተካከል ከውድቀቱ መዳን ይቻላል፡፡  

ይህ የአገር መቆም መሠረት ከተጣለ በኋላ/ወይም ጎን ለጎን ደግሞ በአገራችን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታውን ቢያንስ በሥራ ላይ ካለው ሕገ መንግሥት አንፃር አጠናክሮ መተግበር አስፈላጊ ነው፡፡ እርግጥ እዚህ ላይ አንዳንዶች እንደሚሉት የሽግግር መንግሥት ወይም ወደኋላ የመመለስ ሙከራ ሳይኖር በርከት ያሉ መልካም ጥረቶች ተደርገዋል (የዴሞክራሲ ተቋማት ገለልተኝነት፣ የሕግ ማሻሻያዎች፣ ከገዥው ፓርቲ ውጪ ያሉ የሥራ መሪዎች መመደብ…)፡፡ ያም ሆኖ ስለምን የተገዳዳሪ ፖለቲከኞች የተፎካካሪነት ሥነ ልቦናና ብቃት ተዳክሞ ቀረ የሚለው መጠየቅና መፈተሽ አለበት፡፡ ይህ ተግዳሮት አሁንም በተጀመረው ለውጥ ዘላቂ መፍትሔና ተቋማዊ መተማመኛ ማግኘት ይኖርበታል፡፡

እውነት ለመናገር በኢትዮጵያ በቀደሙት ሦስት አሠርቶች የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መንፈስ ቢቀነቀንም፣ ሁሉም ሕዝብ የሚተማመንበት የምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤቶችና ገለልተኛ የፀጥታ ተቋማት አልነበሩም፡፡ ገዥው ፓርቲ በሁሉም መስክና መንግሥታዊ ክንፍ እጁን በሰፊው ዘርግቶ ስለዴሞክራሲ ቢያወራም፣ ውጤት ሊመጣ እንዳልቻለ አይነገርም፡፡ አሁን የለውጥ ጅምር መታየቱ ባይካድም ካለፈው የተሻለ ጊዜ ለመምጣቱ የጋራ ጥረት መደረግ አለበት፡፡ በዘርፉ የሚታይ ጉድለት ታርሞ የተሻለ ውጤት የማምጣት ድርሻ ግን የመላው የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎችና የልሒቃኑ ሚናም ሊጎላ ይገባል፡፡

እስካሁን እንደ አገር ተቃዋሚ ፓርቲ ሲባል ጥቂት ጉምቱና ዕድሜ ጠገብ ምሁራንን ብቻ ወይም የፓርቲ አመራሮችን እንጂ፣ መዋቅራዊ ጥንካሬዎችን፣ የአባላት ብዛትና ቁርጠኝነትን፣ የጠራ የፓርቲ ስትራቴጂና ማኒፌስቶን ማግኘት እንደ ህልም የማይጨበጥ ሆኖ መቆየቱም መፈተሽ አለበት፡፡ በተለይ የተለጣፊና የብሔር ድርጅት ውልድ የሆኑ ፓርቲዎች (አሁን አሁን ደግሞ የአውራነት ስሜት የተጫናቸው ግለሰቦች) መብዛት ተቀይሮ ኅብረ ብሔራዊና ተጨባጭ አማራጮችን የሰነቀ የፖለቲካ ኃይል መፍጠር የአገሪቱ ወሳኝና አንገብጋቢ ተግባር ሆኖ መምጣት አለበት፡፡

በተለይ እንደምንገኝበት ወቅት ባሉ ፈታኝ ዘመኖች የተሟላ ቁመና ያለው የፖለቲካ ተገዳዳሪነት ክበብ አለመኖሩና ኅብረ ብሔራዊና አገራዊ ዓላማ የሰነቁ የፖለቲካ ድርጅቶች ተጠናክረው አለመውጣታቸውም እጅጉን የሚያስቆጭ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ከውስጥም ሆነ ከውጭ እየተሰባሰቡ ባሉ ኃይሎች ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡ ለነገሩ ራሱ ብልፅግና ፓርቲም ከግለሰቦች ትከሻ ላይ ወርዶ በጋራ አስተሳሰብ፣ በወል ፕሮግራም መተዳደሪያ ደንብ፣ ብሎም በአስተሳሰብ ውህደቱ አገር እየመራ ስለመሆኑ መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ 

በየትኛውም አገር የፖለቲካ ትግል ውስጥ እንደሚታየው ሕዝቡ በራሱ ተነሳሽነት የሚያደርገው ነገር የለም፡፡ ጠንካራ የፖለቲካ መሪዎችና ሁሉን ማሰባሰብ የሚችሉ ጠንካራ ድርጅቶች ያስፈልጋሉ፡፡ መንግሥትም ሆነ የፖለቲካ ተቋማት አንድነታቸውን፣ ፍቅርን፣ ራስ ወዳድ አለመሆናቸውን፣ ፍትሐዊነትና ለአገር ተቆርቋሪነትን ሳያሳዩ ወይም ይቅር መባባልን ሳይተገብሩ ከሕዝብ ያውም፣ በተንጋደደ መንገድ በመጣ ትውልድ ውስጥ እንዲተገበር ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ይህንን ማረቅ ያስፈልጋል፡፡

በእርግጥ አንድነት፣ ፍቅርና ዕርቅን በመስበክ፣ የተበታተነን አመለካከት ወደ አንድ ከማምጣትና ዴሞክራሲን በቁርጠኝነት ለማስፈን ከመነሳት አንፃር ኃላፊነቱ ቀላል አይደለም፡፡ ዜጎች ለሕግና ሥርዓት ተገዥ በመሆን፣ መብትና ግዴታዎቻቸውን በመወጣት፣ ሕገወጥነትን በመታገል፣ አገርን በማስቀደም የዳበረ ባህል ማዳበር ይኖርብናል፡፡ ከሠለጠነው ዓለም በመማር ጭምር፡፡ ለዚህ ደግሞ ትምህርት ቤቶች፣ ሲቪክ ማኅበራትና መገናኛ ብዙኃንም የተነቃቃ ጥረት ይጠበቅባቸዋል፡፡

እንደ አገር በችግር ውስጥ ለመቆየትም ሆነ ከችግር ለመውጣትና ለውጡን ለማራመድ አሁን ያለው ትውልድ ዋነኛ ባለድርሻ ነው፡፡ በተለይ ምሁራንና የፖለቲካ ኃይሎች ሚናቸው የጎላ መሆኑ ሳይሆን፣ በመንግሥት ኃላፊነትና በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ የሚገኙ ሙያተኞች ደግሞ የታሪክ አደራ ወድቆባቸዋል፡፡ ስለሆነም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ካለፈው ድክመት ተምረው ስለፍትሕ፣ ገለልተኛነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት መርሆዎች መከበር እንዲተጉ ግፊት መደረግ አለበት፡፡

በአጠቃላይ አሁን በተጀመረው መንገድ መንግሥት የሰላም፣ የመልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ ጉዳይን ማስቀደም መጀመሩ ትልቅ ተስፋ ነው፡፡ የሕዝቡን መብቴ ይከበርልኝ ጥያቄን ለመመለስ በር ከፋች ነው፡፡ የውስጥ ችግርንና አገራዊ ቀውስን ለመፍታት የሚያስፈልገው ውጫዊ ሰበብ መደርደር ብቻ ሳይሆን፣ በጥልቀት ወደ ውስጥ በመመልከት ዘላቂና ተከታታይ፣ እንዲሁም ትውልዱንና ወቅቱን የሚመጥን መፍትሔ ማፈላለግ ሊሆን ይገባል፡፡ ስለሆነም ለለውጥ ጅምሮች መጠናከር ሕዝብን ያሳተፉ ጠንካራ ዕርምጃዎችን መውሰድ ከመንግሥት ይጠበቃል፡፡

ተቃውሞ ተፈጥሯዊ ቢሆንም በጭፍኑ ከለውጡ ብቻ ሳይሆን፣ ከአገር መሻሻልና ሰላም በተቃራኒው ተሠልፈው በተደራጀም ሆነ ባልተደራጀ መንገድ በመገናኛ ብዙኃንና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ጭምር የሚደረጉ ዘመቻዎችን በንግግርም ሆነ በሥርዓት ለመቀነስም ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ በሰፊ ዘመቻ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨትና የጥላቻ ንግግር የመዝራት ከንቱ ሙከራዎች መምከን አለባቸው፡፡ ለዓመታት ከአንድነትና ከኅብረት ይልቅ ቀለል ያለ ንፋስ የሚያናውጣቸውን የልዩነት ሕንፃዎች በድቡሽት ላይ ለመገንባት የሚደረግ ቅዠት በሕዝብ ትግል መገታት ይኖርበታል፡፡ ለዚህ የተጋን ያድርገን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...