Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አሰልቺው ዘመቻ!

ከቦሌ ወደ ሳሪስ ልንጓዝ ነው። ፍጥረት እንደ ሰንበሌጥ ከወዲያ ወዲህ ሲወዛወዝ ቀልብ የለውም። ጎዳናው ግን ሚስጥሩ የተቋጠረው በአቅጣጫ ሳይሆን፣ በመፈጠር ዕዳ መሀል ላይ ብቻ ይመስላል። በሮጡበት መስክ ሁሉ ደፈንኩት ያሉት ቀደዳ ጎህ ሳይቀድ አፍስሶ የሚያድርባት ዓለም ናትና። ይህችን የሕይወት ሽንቁር ማድጋ በውኃ ለመሙላት ዕድሜውን ሁሉ ወንዝ የሚመላለስ ትውልድ ይመጣል፣ ይሄዳል። አንዳንድ የዘመኑ ተራቃቂዎች ይህን ቅስም ሰባሪ ወለምታ ‹‹ፍርጃ›› ይሉታል። ትውልድ ይመጣል ትውልድ ይሄዳል፡፡ ፀሐይና ጨረቃ ይፈራረቃሉ፣ ሌትና ቀን፣ በልግ፣ ሃጋይ፣ ፀደይና ክረምትም ይተካካሉ። ‘መላ ያጣ ነገር ቅጡ እየተዛባ፣ ሲዞር ሲዞር ኖሮ ልቤ ከአፈር ገባ’ ሲያሰኘው አንዳንዱን፣ ሌላውን ዙሩ ምንም ሳያደክመው ስንፍናውንና ግዴለሽነቱን ጠግቦ ይሸኛል። የሁለቱም ዕጣ አንድ አፈር ይሰኛል። አፈሩን ያቅልልንና!

ታክሲ ውስጥ ገብተናል። ጉዟችን ተጀምሯል። ‹‹አይ ዛሬ ቀን… አይ ዕድሌ…›› ያጉተመትማል አንድ ጎልማሳ። ‹‹ምንድነው እሱ? ምን ሆነህ ነው?›› ወያላው እሱን መስሎት ይጮህበታል። ‹‹ኧረ እባክህ አንተ ሰውዬ ተወኝ ወዲህ ነው። ኧረ! ኧረ ምን አደረግኩህ?›› ወደ ላይ አንጋጦ የዛቻ ያህል ከምስቅልቅሉ መነሻ ጋር በሐሳብ ይፋጠጣል። ‹‹ምን እህህ እያልክ ብቻህን ታምጠዋለህ? የሆንከውን ንገረንና መፍትሔ እንፈልግ፡፡ ካልሆነ ዝም በል…›› አለው ከአጠገቡ የተቀመጠ ወጣት ተሳፋሪ። ቀጠለና ደግሞ፣ ‹‹ከዚህ የበለጠ በሽታ አለ ግን? ሲሞላልንና ሲሳካልን የምንደነፋውን ያህል ምነው ሲያመን ብንናገር? ሁሉን በሆዳችን ይዘን፣ ሁሉን በሆዳችን ሰፍረን እንችላለን እንዴ?›› ይላል። ጋቢና የተሰየመች መለሎ፣ ‹‹ቆይ አንተ የሆድ ሐኪም ነህ? ወይስ ጆሮ ጠቢ? ምነው ይኼን ያህል የሰው ቁስል አሳከከህ?›› ትለዋለች ሳይሰማት። ይኼኔ ሰውየው ችግሩን ማውራት ይጀምራል።

‹‹እኔ አላመመኝም፣ ነገር ግን ‹ዲግሪ› ያለኝ ሰው ነኝ። ሥራ ልወዳደር ከክልል ነበር የመጣሁት። እዚህ ስደርስ ያመጣኝ ባለ ዶልፊን የመጣህበትን ካልከፈልከኝ ብሎ የዲግሪ ምስክር ወረቀቴን ወሰደብኝ። መላው ጠፍቶብኝ ነው እባካችሁ? እኔ ልመና አልችልበትም…›› አለና ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ ‹‹እባካችሁ እኔ ለአገሩ እንግዳ ነኝ። ክፈል የተባልኩት 600 ብር ስለሆነ ብታወጡልኝና አገሬ ብገባ? እንዲያው ሌላ አላስቸግርም…›› ብሎ አረፈው። ይኼኔ የሰማውን ሰምቶ አላስችል ያለው (ያላመነው) መተረብ ጀመረ። ‹‹ዝም አትበሉ እንጂ እሳት አደጋ ጥሩ፣ የፀሐይዋ ቃጠሎ ሳያንሰን ደግሞ በባለዲግሪ እንቃጠል? ወይ ዘመን?›› ሲል አንዱ ተራቢ ጎልማሳ፣ ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡ አንዲት አዛውንት ቀበል አድርገው፣ ‹‹እንደ ዘንድሮ የአለማመን ሥልት መራቀቅ ከሆነ 8100 ላይ ለህዳሴው ግድብ የምናዋጣው ገንዘብ ሳይቀር በ‘ሳይበር አታክ’ ባይዘረፍ ቢቀር አይግረማችሁ…›› አሉ። ወዲያው ለቀልድና ለተረብ ይራኮት የነበረው ተሳፋሪ ሁሉ በአዛውንቷ አስተያየት ከማግጠጥ ተቆጥቦ እንደ መደንገጥ ሲል ይታያል። ‹‹መንገድ ለመንገድ አልችለው ብለናል ልመናን ጭራሽ በቴክኖሎጂ ሊታገዝ? የለንማ…›› የሚለው ብቻውን ይስቃል፡፡ ዘመኑ እንዲህ ሆኖ ይረፈው?

አዛውንቷ ሳያስቡት የፈጠሩት ድንጋጤ ሰውዬው ላይ ከማሾፍ ይልቅ ቁጣ ፈጥሯል። ‹‹አንተ መጀመሪያም መሣፈሪያ ሳይኖርህ ነው ሰው መኪና ላይ የምትወጣው?›› ሲል አንዱ መጨረሻ ወንበር ላይ የተቀመጠ ወጣት ያፋጥጠዋል። ይኼን ሰምቶ ወያላው ሒሳብ ብሎ ቀድሞ ራሱኑ ጠየቀው። ‹‹ተቸግሬ እያየኸኝ ጭራሽ አንተም ሒሳብ ትለኛለህ? እኔ እየዋሸሁ አይደለም። እውነቱን ነገርኳችሁ እኮ፣ ያመጣኝ የዶልፊን ሾፌር ዲግሪዬን ይዞብኝ ጠፋ። እሺ በምን መረጃ ሥራ ልወዳደር? እባካችሁ የሰው አገር ሰው ነኝ…›› ተሳፋሪዎችን ለማሳመን ሲረባረብ ታክሲያችን ቆማለች። ፊቱን በደንብ ያላየነው ጋቢና የተሳፈረ ጎልማሳ፣ ‹‹ቆይ ግን ዲግሪው በግዥ ነው ወይስ ተለፍቶበት የተገኘ ነው? ዘንድሮ ዲግሪና ድርጊቱ አመራማሪ ሆኗል አሉ…›› ብሎ ሳይጨርስ ሾፌሩ፣ ‹‹አስወርደው ይኼን ቀጣፊ…›› ብሎ ጮኸ። ወያላው በክብር ከተቀመጠበት ሦስተኛው ረድፍ ጎትቶ ሰውዬን አስወረደው። ከመውረዱ የእርግማን ዶፍ ያዘንብብን ጀመር። ግን እውነቱን ቢሆንስ!

በቆመበት ጥለነው ጉዟችንን ስንቀጥል፣ ‹‹‹ይህን ሰውዬ እዚህ አውላላ ሜዳ ላይ አውርደነው በንዴት ራሱን ቢያጠፋ የለሁበትም…›› ይላል አንዱ ሥጋት የገባው። ‹‹እንዴ ካልጠፋ አራድነት ገና ለገና ለጫት አልሰጡኝም ብሎ የተቆጣ ራሱን ያጠፋል ብሎ ማሟረት ምንድነው? የዘመኑ ሰው እንደሆነ ከላይ እስከ ታች ሌብነት ላይ ሙጥኝ ብሎ እንኳንስ ፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ፣ ፈጣሪ ራሱ መሬት ወርዶ የፍርድ ችሎት ቢያቋቁም መስረቁን አያቆምም፡፡ ይኼም እዚህ ካልተሳካለት ሌላ ቦታ የጀመረውን ማታለል ይቀጥላል…››  ብላ ሂጃብ የጠመጠመች ከኋላችን የተቀመጠች ሴት ተናገረች። መጨረሻ ወንበር ደግሞ፣ ‹‹በቃ እኛ ሥራችን ዘመቻ ሆኖ ቀረ ማለት ነው፡፡ ለሌብነት ኮሚቴ፣ ለልማት ኮሚቴ፣ ለዕርዳታ ኮሚቴ…፣ አሁንስ በዛ…›› የምትለው ደግሞ አንዲት ቀዘባ ናት፡፡ በላይ በላይ ሳይበስሉ የሚከስሉብን ነገሮች ሳያንሱ አሁን እስኪ በትንሽ ትልቁ ነገር ትን ሲለን ምን ይባላል እናንተ? ወይስ እንደምትለው ጥሎብን ይሆን? ቅጥ ያጣ ነገር!

ጉዟችን ቀጥሏል። ወያላው፣ ‹‹ጫፍ ላይ ወራጅ አለ? ባይኖርም የኢንሹራንስ መብቴን ብነፈግ ነው…›› እያለ ከምንጊዜው 12 የነበርነውን 18 እንዳደረሰን አይታወቅም። አንዳንዶች የወያላውን ጮሌነት ሲያዳንቁና ሲተቹ አንዳንዶች፣ ‹እቅጩን የሚነግረን ሰው ስላጣን ነው እንጂ ቁጥራችን 120 ሚሊዮንን አልፏል…› እያሉ ባልተያዘ ነገር፣ ነገር ይማዘዛሉ። ‹‹በቃ እኔ ላስታርቃችሁ የመኪና አደጋ በየቀኑ የሚቀንሰውን ሕዝብ ካሰባችሁት ነው እንጂ 120 ሚሊዮንማ ምን አላት?›› ሲሉ አዛውንቷ ጣልቃ ገቡ። ከረር ያለው ጨዋታ ባለወግ በሆኑት አዛውንት ሰበብ መለዘብ ሲጀምር፣ ‹‹እውነትዎን እኮ ነው፡፡ እኔ በበኩሌ ከኢቦላ፣ ከኮቪድና ከመሳሰሉ ወረርሽኝ ልቤ የምትበረግገው ለትራፊክ አደጋ ሆኗል። መንገዱ የተወረረው እኮ መንዳት በማይችሉ ነገር ግን እንደ ቅድሙ ባለዲግሪ ‹‹ፌክ›› በሆነ መንጃ ፈቃድ ነው…›› ብላ ጋቢና ያለችው ተናገረች። አጠገቧ ያለው ተቀበለና ደግሞ፣ ‹‹ምን ይደረግ መንጃ ፈቃድ እንደ ቀበሌ መታወቂያ ያለ ማሽከርከር ብቃት አንስተው ያድሏቸዋል፡፡ 70 እና 80 ኩንታል ጭነው እንደ ንፋስ ሲበሩ እንደ አውቶሞቢል በአንድ እርግጫ ፍሬን የሚቆሙ ይመስላቸዋል። መቼም እኛ ሆነን አሥር ሲሞትብን መቶ ሺሕ እያረገዝን ባንወልድ ኖሮ፣ ምድሪቷ በግሪሳና በቁራዎች ‘ፓርቲ’ ትወረር ነበር…›› ይላል። ያሰኛል!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። የዕለት እንጀራውን ማግኘት ማጣቱ የወዘወዘው ተሳፈሪ በበኩሉ፣ ‹‹ተው ሳበው ሳበው መሸብኝ፣ የጆቢራ ራት ግብር አለብኝ፤››ን በኤፍኤም የሚጋብዝ ይመስል አሥር ጊዜ ስልኩን ይነካካል። አንዳንዱ ፍጥነትን ከድህነት ማምለጫ መሣሪያው አርጎ ሲቆጥር፣ ሌላው በአጭር እየቀረ መንገድ ይቀራል፡፡ አያድርስ እንጂ ሌላ ምን ይባላል? እንደ ግምጃ ቤት ሰው በሰው ላይ አነባብሮ አሳፍሮ ማመላለስ ከመለመዱ የተነሳ ሕጋዊ አድርገን ማሰብ መጀመራችንን ያወቅነው የትራፊክ ፖሊስ ሲያስቆመን ነው። ሾፌራችን መንጃ ፈቃድ እንዲያሳይ ሲጠየቅ እየተቅለሰለሰ ከመኪና ወርዶ ይለማመጥ ጀመር። ‹‹እንዲህ ተነባብረንም አልቀለለልን እንኳን በ’ቪአይፒ’ በምቾት ተጓጉዘን…›› ሲል አንዱ ጨዋታ ጀመረ። ሌላው ቀበል አድርጎ፣ ‹‹በሁለት ቢያጆ ያገኛታል ለምን ይለማመጠዋል?›› ይላል። የትራንስፖርት እንግልቱ ሕግና ሕጋዊነትን ያስረሳን ይመስላል። የትራፊክ ፖሊሱ መንጃ ፈቃድ የማያሳየው ከሆነ ሰሌዳውን እንደሚፈታና መኪናዋን እንደሚያስራት በትኅትና ለሾፌራችን ደጋግሞ ሲነግረው፣ የቅጣት ወረቀት ከኪሱ አውጥቶ አሳየ። የትራፊክ ፖሊሱ ሌላ የቅጣት ወረቀት ጽፎ ታርጋውን መፍታት ጀመረ። ወበቁ መፈጠሩን ያስጠላው በትዕግሥት ተቀምጦ ሲጠባበቅ፣ ያላስቻለው እየወረደ ቀሪውን መንገድ በእግሩ ተያያዘው። ምን ይደረግ ታዲያ!

ይህ ሁሉ ሲሆን ሕግና ሕጋዊነት በሁለት ጽንፍ ሊያባላን ደርሷል። አንዱ ከግል ጥቅሙ በመነሳት ይመስላል፣ ‹‹ሕግ ተለዋዋጭና አመዛዛኝ ካልሆነ ምን ዋጋ አለው?›› ይላል። በዚህ የማይያዝ የማይጨበጥ ሐሳብ አንጀታቸው ካረሩት ተሳፋሪዎች አንዱ ጎልማሳው ነው። ‹‹እኮ እንዳንተ አባባል ከሆነ ሕገወጥነት የሚስፋፋው እንዲህ እየታሰበ ነው፡፡ አገሩ ሁሉ የሌባ ሠራዊት የወረረው በእንዲህ ዓይነቱ ዓይን አውጣነት ወይም ግዴለሽነት ነው፡፡ ምድረ ሌባ አገሪቱን ቅርጥፍ አድርጎ ከበላ በኋላ ፀረ ሙስና ዘመቻ እንደሚጀመር ሰምተናል፡፡ ‹‹ከመቅረት መዘግየት›› ቢሻልም፣ አሁንም ቢሆን ከዘመቻ ሥራ ተላቀን ተቋማዊ አሠራር ካላመጣን የዘረፋው ኔትወርክ የሚቻል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ዘራፊው፣ ተባባሪው፣ ዓይቶ እንዳላየ የሚሆነው ግዴለሽና በጥቅም ኔትወርክ የተደራጀው ኃይል ለምንም ነገር ስለማይመለስ ነው፡፡ ለዚህም ነው ከዘመቻ መላቀቅ ያለብን…›› እያለ ሳሪስ ደረስን፡፡ እውነት ነው ሁልጊዜ ዘመቻ ይሰለቻል!  መልካም ጉዞ! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት