Sunday, May 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቡና ኢንሹራንስ ካፒታሉን ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አሥረኛ ዓመቱን የያዘው ቡና ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር ካፒታሉን ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ፡፡ ከባለአክሲዮኖች የሚተርፉ አክሲዮኖችን ለአዲስ ገዥዎች እንዲሸጥም የኩባንያው ባለአክሲዮኖች ተስማምተዋል፡፡

ኩባንያው ካፒታሉን ለማሳደግ ውሳኔ ላይ የደረሰው በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ካፒታል 500 ሚሊዮን ብር መድረስ እንዳለበት መመሪያ በማውጣቱና ይህንን መመርያ ተፈጻሚ ለማድረግ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ የኩባንያውን ካፒታል ማሳደጉ የኩባንያውን አቅም ለማጎልበት የሚረዳ በመሆኑ ካፒታሉን ከ200 ሚሊዮን ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ከኩባንያው ቦርድ የቀረበውን ሐሳብ ባለአክሲዮኖች ተወያይተው ይሁንታ ሰጥተዋል፡፡

የተጨማሪውን ካፒታል አክሲዮን ሽያጭ በተመለከተም ሁሉም ባለአክሲዮኖች በየአክሲዮን ድርሻቸው መጠን የሚገዙት አክሲዮን የሚደለድልላቸው ሆኖ የተጨማሪውን ካፒታል ማሟያ እንዲገዙ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ተወስኗል፡፡ ሆኖም ለባለአክሲዮኖች ተደልድሎ የሚተርፈውን አዲስ አክሲዮን ለአዳዲስ ባለአክሲዮኖች ለመሸጥ ስምምነት ላይ መደረሱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኩባንያው ከዚህ ውሳኔው ባሻገር በመደበኛው ጠቅላላ ጉባዔው የ2014 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ ሪፖርት ላይም ተወያይቷል፡፡ በኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድ ተዘጋጅቶ የቀረበው ሪፖርት ኩባንያው ከቀደሙት ዓመታት የተሻለ አፈጻጸምና ትርፍ ያገኘበት ዓመት እንደነበር አመልክቷል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ሕይወት ነክ ካልሆነው የመድን ሽፋን 468.7 ሚሊዮን ብር ዓረቦን ማሰባሰብ የቻለ ሲሆን ይህ አፈጻጸም ከዕቅዱ 17 በመቶ፣ እንዲሁም ከቀዳሚው ዓመት ደግሞ በ40 በመቶ ብልጫ ያለው ነው ተብሏል፡፡

በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍም 11.36 ሚሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ ማሰባሰብ መቻሉን የገለጸው ኩባንያው ይህ አፈጻጸሙ ደግሞ ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ የ279 በመቶ ብልጫ ያለው እንደሆነ ገልጿል፡፡ ከሁለቱም የኢንሹራንስ ዘርፎች የተሰበሰበው የዓረቦን ገቢ መጠን በጥቅሉ 480.2 ሚሊዮን ብር እንደሆነ የሚያመለክተው ሪፖርቱ፣ የሒሳብ ዓመቱ የሥራ አፈጻጸም በአብዛኛው ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት እንደሆነም ይጠቅሳል፡፡

ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ 174.6 ሚሊዮን ብር ለካሳ ክፍያ ያዋለ ሲሆን በመጠባበቂያነት የተያዘ የካሳ ክፍያ መጠን ደግሞ 89.20 ሚሊዮን ብር መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት 45.8 ሚሊዮን ብር ያተረፈው ቡና ኢንሹራንስ፣ ያገኘው የትርፍ መጠን ከቀዳሚው ዓመት ትርፍ ጋር ሲነጻጸር የ24.36 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጿል፡፡

ኩባንያው በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት አጠቃላይ የሀብት መጠኑን ወደ 1.08 ቢሊዮን ብር ማሳደግ ችሏል፡፡ ይህም በአንድ ዓመት የሀብት መጠኑን በ41.12 በመቶ ማሳደግ መቻሉን የሚያመለክት ሆኗል፡፡ በ2013 መጨረሻ ላይ ኩባንያው የነበረው ጠቅላላ የሀብት መጠን 768.13 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ ቡና ኢንሹራንስ በአሁኑ ወቅት ከ209 በላይ ሠራተኞች አሉት፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች