Sunday, April 21, 2024

የተወሳሰበው ሰላም የማስፈን ሒደት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት ተፈርሞ ብዙም ሳይዘገይ የኬንያው ቀጣይ ዙር ስምምነት መፈረሙ፣ ሒደቱ በፍጥነት ወደ መሬት የሚወርድ ያስመስለ አጋጣሚ ነበር፡፡ የትግራይ አማፂያን ትጥቅ መፍታትን ተከትሎ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ትግራይን የሚቆጣጠርበት ቀን በጉጉት ሲጠበቅም ነበር፡፡ ነገር ግን በቀናት ልዩነት የሰላም ስምምነቶቹን ገቢራዊነት የሚያወሳስቡ ጉዳዮች እየወጡ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ ደግሞ የሰሜኑ ጦርነት ዳግመኛ ሊያገረሽ ይችላል የሚል ሥጋትን እያጫረ ይገኛል፡፡

በተለይ የሰላም ስምምነቶቹን በተመለከተ ከትግራይ ክልል ይወጡ የነበሩ መግለጫዎች፣ ሒደቱ እንደሚወሳሰብ የመጀመርያው ጠቋሚ ምልክቶች ነበሩ፡፡ በትግራይ መንግሥት ስም የወጣው መግለጫ ደግሞ ከዋናው የፕሪቶሪያ ስምምነት ዋና ዋና አንቀጾች ጋር የሚጋጭ ይዘት ነበረው፡፡ መግለጫው በሕዝብ የተመረጠው የትግራይ መንግሥት ተወካዮች እንጂ፣ የሕወሓት ተወካዮች አይደሉም በሰላም ስምምነቱ የተፈራረሙት ብሎ መግለጹ ከስምምነቱ የተቃረነ ነበር፡፡

ስምምነቱ የሕወሓት አማፂያንና የኢትዮጵያ መንግሥት ብሎ በግልጽ አስቀምጦ ሳለ፣ የትግራይ መንግሥት ነው ተፈራራሚው ተብሎ መግለጫ መውጣቱ የሚያምታታ   መሆኑን የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀር ሲቃወሙት ታይተዋል፡፡ መግለጫው ግን ከዚህ አልፎ በትግራይ የጊዜያዊ የሽግግር ጊዜ አስተዳደር መቋቋም ሒደትንም ሲቃወም ነው የታየው፡፡

የትግራይ መንግሥት የሚፈርሰው በመረጠው በትግራይ ሕዝብ ድምፅ እንጂ በግጭት ማቆም ስምምነት አይደለም ያለው መግለጫው፣ የትግራይ አማፂያን ትጥቅ ፈትትው ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ጊዜያዊ አስተዳደር ይመሠረታል የሚለውን የስምምነት መርሆ ፍፁም የሚቃረን አቋም የሚያንፀባርቅ ነበር፡፡

በናይሮቢ የወታደራዊ መሪዎች ስምምነት በዋናነት በአንቀጽ 2 ‹‹Disarmament of Tigray Armed Combatant›› ተብሎ ስለአማፅያን ትጥቅ አፈታት የተቀመጠው መርህም በሒደት ያለ መግባባት ምንጭ ሲሆን እየታየ ነው፡፡ በተለይ በንዑስ አንቀጽ 2.1 በተራ ቁጥር D ላይ የተቀመጠው ሐሳብ ለመተግበር ትልቅ ፈተና እንደገጠመው እየተነገረ ነው፡፡

‹‹D Disarmament of heavy weapons will be done concurrently with the withdrawal of foreign & non ENDF forces from the Region.›› በሚል የተቀመጠው የስምምነት ማዕቀፍ ከትግራይ ክልል ሁሉም ዓይነት የታጠቁ ኃይሎች ወጥተው የኢፌዴሪ መከላከያ አካባቢውን ሲቆጣጠር ነው የትግራይ አማፅያን ትጥቅ የሚፈቱት የሚል ትርጉም እየተሰጠው ነው፡፡ ይህ የትግራይ አማፅያን በ15 ቀናት ቀላል መሣሪያዎችን፣ በአንድ ወር ጊዜ ደግሞ መላው ትጥቃቸውን ለመፍታት የገቡትን ቃል ገቢራዊ ለማድረግ በችግርነት እየቀረበ ነው፡፡

አሁን የኤርትራ ጦር እንዲሁም የአማራ ኃይሎችና በአጠቃላይ ከመከላከያ ውጪ ያሉ ታጣቂዎች ካልወጡ፣ የትግራይ አማፅያን ትጥቅ አይፈቱም የሚለው ሙግት ዋና የስምምነቱ ገቢራዊነት እንቅፋት ተደርጎ እየቀረበም ነው፡፡

ትግራይ ክልል በመከላከያ ሠራዊት እጅ በገባ ወቅት በተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ሥር የመቀሌ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ አታክልቲ ኃይለ ሥላሴ፣ የሕወሓት ነባር ባህሪ ለሰላም ዝግጁነት የማይታይበት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከሕወሓት ጋር መደራደር ችግሩን ማርዘም እንደሆነ ሲናገሩ መቆየታቸውን ያመለከቱት አቶ አታክልቲ፣ ነገር ግን በስምምነቱ ሰላም ከመጣ ሁሉም የሚፈልገው በመሆኑ እንደተቀበሉት ይጠቅሳሉ፡፡

‹‹ሲጀመር ወደ ድርድር ያመጣቸው ምን ስለሆኑ ነው? ጥቂት የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚዎች ምን ያመጣሉ ተብሎ ተፈርቶ ነው? ከእነሱ ጀርባ የታጠቀ ኃይል ስላለ አይደለም ወይ ወደ ድርድር የመጡት? ጦርነቱ መቆም ስላለበትና ለአገር ስለማይጠቅም ነው ይቁም ተብሎ ለድርድር የተቀመጡት፡፡ ታጣቂዎች የእነሱ ካልሆኑ ምን ስለሆኑ ነው ታዲያ መንግሥት የሚደራደራቸው? ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ተደራደሩ ብሎ የለመናቸው ለምን ነበር?›› በማለት የሚጠይቁት አቶ አታክልቲ፣ አሁን ሕወሓቶች የሰላም ስምምነቱን ለመተግበር ሆን ብለው መጓተት እየፈጠሩ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ሕወሓቶች የሰላም ስምምነቱን ለመተግበር እንቅፋት እየፈጠሩ ብቻ ሳይሆን፣ ዳግም የሰው ሕይወትን ወደ የሚያጠፋ ጦርነት ለመግባት እየተዘጋጁ መሆኑን ነው አቶ አታክልቲ ያስረዱት፡፡

‹‹አሁን ወጣቶች እየታደኑ በግዳጅ ወደ ጦር ካምፕ ለሥልጠና በመግባት ላይ ናቸው፡፡ ሰላም ተብሎ አገርና ሕዝብ ደስ ብሎታል፣ በሌላ በኩል ደግሞ በጉልበት ወጣቶችን እያስገደዱ ወደ ማሠልጠኛ በማስገባት ለጦርነት እየተዘጋጁ ነው፤›› በማለት፣ ሕወሓቶች ለሰላም ስምምነቱ መተግበር እንቅፋት እየፈጠሩ መሆኑን ነው አቶ አታክልቲ የተናገሩት፡፡

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ መስፍን ደሳለኝ ለሰላም ዝግጁነት ካለ ምክንያቶችን ማጥፋት ይቻላል ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ፡፡ የሰላም ስምምነቱ እስከተፈረመና ሁሉም ወገን የሰላም ስምምነቱን ለመተግበር ዝግጁ እስከሆነ ድረስ የኤርትራ ሠራዊት ሊወጣ ይገባል የሚል እምነት እንዳላቸው የተናገሩት አቶ መስፍን፣ ሆኖም ይህንን ጉዳይ ለግጭት ማዋል ተገቢነት እንደሌለው ይናገራሉ፡፡ 

‹‹ሕወሓት የኤርትራ ሠራዊት መውጣት ጉዳይን ለሌላ ዓላማ እንዳይጠቀምበት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በሕወሓትና በመንግሥት መካከል አለመተማመን ሊፈጠር አይገባም፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን ትጥቅ ላለመፍታት ጊዜ መግዣ እንዳያደርጉት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በግሌ የሰላም ስምምነቱን አተገባበር በጥብቅ የሚከታተል ጠንካራና ገለልተኛ የሆነ ሦስተኛ ወገን ያስፈልጋል፤›› በማለት ነው አቶ መስፍን የገለጹት፡፡

የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ሒደቱን አተገባበር እንደሚከታተል ከስምምነት መደረሱ የተነሳላቸው አቶ መስፍን ኅብረቱ ድርድሩን ለማፈራረም መብቃቱ በራሱ ትልቅ ነገር ቢሆንም፣ ነገር ግን እንደ ሌሎች ዓለም አቀፍ አካላት የማስገደድ አቅሙ አስተማማኝ ነው ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡

‹‹አድብቶ በመጠፋፋትና በመከዳዳት ሴራ የተጠለፈው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይህን የሰላም ስምምነት ወደፊትም እንዳይራመድ እያደረገው ነው፡፡ መንግሥትም ሆነ ሕወሓት የሰላም አማራጭ ነው የሚያዋጣን ብለው በድርድር የሰላም ስምምነቱን መፈረማቸውን መርሳት የለባቸውም፡፡ ስምምነቱ እዚህ ደረጃ ከደረሰ በኋላ ወደኋላ ለመመለስ የሚችሉበት አማራጭ የለም፡፡ በዚህ ላይ ብዙ የሕዝብ ሕይወት አደጋ ላይ ነው ያለው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ሌላ ዙር ግጭት የሚሸከምበት አቅም የለውም፤›› በማለት የተናገሩት አቶ መስፍን፣ የሰላም ስምምነቱን ያደናቀፈ ወገን ሕዝብ እንዲረግፍ የፈቀደ ነው ብለዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመና ግጭቱ ጋብ ካለ በኋላ ለጥቂት ሳምንታት የትግራይ ሕዝብ ዕፎይ ማለቱን የጠቀሱት አቶ መስፍን፣ ይህን ዕፎይታና የሰላም አየር ሕዝቡ ዳግም ማጣት እንደማይፈልግ እምነታቸውን ተናግረዋል፡፡

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ይህን ቢሉም፣ ነገር ግን ሕወሓት ለዳግም ዙር ጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን ከትግራይ እየወጡ ያሉ መረጃዎች በመጠቆም ላይ ናቸው፡፡ በአዲግራት፣ በራያ፣ በጨርጨር፣ በአላማጣ፣ በመሆኒ፣ በቢሶበር፣ በማይጨውና በሌሎችም አካባቢዎች ምሽግ የመቆፈርና ለጦርነት የመዘጋጀት እንቅስቃሴዎች እየታዩ መሆኑን ቅርብ የመረጃ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ዳግም ለመሰብሰብና ለመደራጀት የቻሉ አማፅያን መለስተኛ ቢሆኑም ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ግጭት መፍጠራቸው እየተነገረ ነው፡፡

ለድርድሩም ሆነ ለሰላም ስምምነቱ መፈረም ትልቅ ተፅዕኖ እንደነበራቸው የተነገረው እንደ አሜሪካ ያሉ ኃይሎች፣ በዚህ ጉዳይ ላይ እያራመዱት ያለው አቋም ደግሞ ሌላ ሥጋት እየፈጠረ ነው፡፡

ከሰሞኑ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ሰጡት በተባለ መግለጫ የኤርትራና የአማራ ኃይሎች ከትግራይ ለቀው ካልወጡ የአሜሪካ መንግሥት ማዕቀብ ለመጣል ዝግጁ መሆኑን መናገራቸው፣ የትግራይ ክልልን ብሎም የኢትዮጵያን አንፃራዊ ሰላም ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይከተው እየተፈራ ነው፡፡

በአንድ ሉዓላዊ አገር ግዛት ውስጥ ምን ዓይነት የታጠቀ ኃይል ምን ቦታ መሰማራት እንደሚችል ሉዓላዊ ሥልጣን ያለው የፌዴራል መንግሥት እያለ፣ ሕወሓቶችም ሆነ ከጀርባቸው ሆነው የሚዘውሯቸው የምዕራባውያን ኃይሎች እገሌ ካልወጣ የሚል ቅድመ ግዴታ ማስቀመጣቸው ጣልቃ ገብነት ነው በሚል እየተተቸ ነው፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ከሰሞኑ በፌስቡክ ገጻቸው ይፋ ባደረጉት መረጃ፣ የፕሪቶሪያውን ስምምነት መሠረት በማድረግ መንግሥት የሚጠበቅበትን እያደረገ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡

‹‹ይህ የመንግሥት ተጨባጭ የሰላም ጥረትና ፍላጎት በሌላኛውም ወገን በስምምነቱ መርህ መሠረት ይበልጥ ወደ ተግባር መቀየር ይኖርበታል፡፡ ለዘላቂና አዎንታዊ ሰላም የሁሉም ወገን ቅንነት የተሞላበት እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው፤›› በማለት የተናገሩት ለገሰ (ዶ/ር)፣ መንግሥታቸው ከሕወሓት ኃይሎች ምን እንደሚጠብቅ ለመጠቆም ሞክረዋል፡፡

የሕወሓት ደጋፊዎች የኤርትራና የሌሎች ኃይሎችን መውጣት ለትጥቅ መፍታትም ሆነ ለሰላም ሒደቱ ወደፊት መግፋት እንደ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠዋል፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ የሰላም ስምምነቱ ያስቀመጣቸው የተግባር ቅደም ተከተሎች ቀናት እየተቆጠሩ የጊዜ ገደባቸው እየደረሰ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከታሰበው በተቃራኒ የግጭት ምንጭ እንዳይሆን ሥጋት እየፈጠረ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -