- ሄሎ… ማን ልበል?
- ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ጤና ይስጥልኝ… ማን ልበል?
- የእርስዎ ትይዩ ነኝ፡፡
- አቤት?
- ያው ፓርቲዬን ወክዬ የፍትሕ ሚኒስትሩ ትይዩ ነኝ ማለቴ ነው፡፡
- ኦ… ገባኝ… ገባኝ…
- ትንሽ ግራ አገባሁዎት አይደል?
- ትይዩ ስትል መጠሪያ ስምህ መስሎኝ ማነው ብዬ እኮ ነው ትንሽ ግር ያለኝ።
- ገብቶኛል… ያው በስም አያውቁኝም ብዬ ነው…
- አሁንማ አወቅኩህ… አቻዬ ነህ…
- ኪኪኪ… ያው የደወልኩት አንድም አድናቆቴን ለመግለጽ፣ አንድም ያልገቡኝ ጉዳዮችን እንዲያብራሩልኝ ነው።
- መልካም፣ ደስ ይለኛል፡፡
- በመጀመሪያ ሙሰኞችን ለመመንጠር ሰሞኑን ያሳለፋችሁትን ውሳኔ ፓርቲያችን እንደሚያደንቀውና በእጅጉ እንደሚደግፈው ልገልጽልዎት እወዳለሁ።
- አመሠግናለሁ፣ ያው እንደምታውቀው ትግሉ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ሳይሆን የጋራ ኃላፊነታችን መሆን አለበት።
- እስማማለሁ ክቡር ሚኒስትር፣ ነገር ግን አንዳንድ ግልጽ ያልሆኑልኝ ጉዳዮች አሉ።
- ጥሩ፣ ምንድነው ግልጽ ያልሆነልህ?
- ክቡር ሚኒስትር ሙስናን ለመዋጋትም ሆነ በሙሰኞች ላይ ዕርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት የተሰጣቸው ተቋማት እያሉ፣ ለምን ጉዳዩን በኮሚቴ ለመሥራት እንደፈለጋችሁ ግልጽ አልሆነልኝም፡፡
- ልክ ነው፣ ከተቋቋመ ረዥም ዓመታትን ያስቆጠረ የፀረ ሙስና ኮሚሽን አለን፣ በተጨማሪም እንዲህ ዓይነት ወንጀሎችን ተከታትሎ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን የዓቃቤ ሕግ ክፍል በፍትሕ ሚኒስቴር ውስጥ አለ።
- እኮ ለዚህ ነው እኔም በኮሚቴ መሥራት ለምን ተፈለገ የሚል ጥያቄ የጫረብኝ።
- ጥያቄው መናሳቱ ተገቢ ነው፣ ግን ኮሚቴው የተቋቋመው ድጋፍ ለማድረግ እንጂ የሕግ ማስከበር ሥራው ሕጋዊ ሥልጣን በተሰጣቸው ተቋማት ነው።
- ኮሚቴው የምን ድጋፍ ነው የሚሰጠው?
- እንምታውቀው የሙስና ወንጀል በረቀቀ መንገድ ነው የሚፈጸመው፣ የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎችና የፋይናንስ ተቋማት የመሳሰሉት ይሳተፉበታል።
- አዎ፣ ልክ ነው።
- ስለዚህ ኮሚቴው በየዘርፉ ሙያዊ ድጋፍ እንዲያደርግ ታስቦ ነው የተቋቋመው፣ የኮሚቴ አባላቱን ስብጥርን ብትመለከትም ይህንኑ ነው የሚጠቁምህ።
- አሃ… አሁን ግልጽ ሆኖልኛል፣ ቢሆንም ግን ኮሚቴው ሌላ ተልዕኮ እንደሌለው የምንከታተለው ይሆናል።
- የምን ተልዕኮ?
- በሕግ መጠየቅ ያለባቸውን ሙሰኞችን የማመጣጠን ተልዕኮ፡፡
- የምን ምጥጥን?
- የብሔር፡፡
- አይ… እንዲያ እንኳ አይደለም፣ ግን…
- ግን ምን ክቡር ሚኒስትር?
- እንደምታውቀው ሙሰኞች ልትነካቸው መሆኑን ሲያውቁ ብሔራቸውን መሸሸጊያ ያደርጋሉ።
- ሊሆን ይችላል።
- ሊሆን ይችላል ሳይሆን እንደዚያ ነው የሚያደርጉት።
- ስለዚህ?
- አንድን ሕገወጥ ድርጊት እናስቆማለን ብለን የባሰ ችግር እንዳንፈጥር ጥንቃቄ ማድረግ አለብን ለማለት ነው።
- በጥንቃቄ መፈጸሙን ማነው የሚያረጋግጠው?
- ኮሚቴው!
[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ገብተው ገና አረፍ እንዳሉ ባለቤታቸው በአግራሞት እየታዘቧቸው መሆኑን አስተዋለው ምን ተፈጠረ ሲሉ ጠየቁ]
- ምነው? ምን ተፈጠረ?
- በቴሌቪዥኑ የሰማሁት አንድ ዜና አስደንግጦኝ ነው፡፡
- በመንግሥት ቴሌቪዥን ነው?
- አዎ።
- በመንግሥት ቴሌቪዥን የሚያስደነግጥ ዜና?
- ለማስደንገጥ ብለው ላይሆን ይችላል ግን…
- ግን ምን?
- እኔን አስደንግጦኛል፣ እንዲሁም አስገርሞኛል…
- ዜናው ሰለምን ጉዳይ ነው?
- የእናንተው ጉድ ነው፣ እናንተ የማታመጡብን ነገር ምን አለ?
- ለምን በግልጽ አትነግሪኝም?
- ወጣቶችን ወደ ብሔራዊ ውትድር ልታስገቡ ስለመሆኑ ነዋ፡፡
- ታዲያ ምኑ ነው የሚያስደነግጠው?
- እንዴት አያስደነግጥም? በደርግ ዘመን በነበረው ብሔራዊ ውትድርና ስንት ቤተሰብ እንደተንገላታ ዘንግተኸው ነው?
- ይኼኛው እኮ ለየት ያለ ነው።
- ምኑ ነው የሚለየው?
- አንደኛ ስያሜው የተለየ ነው።
- ስያሜው ምንድነው ታዲያ?
- ብሔራዊ አገልግሎት ነው።
- ሁለተኛስ?
- ሁለተኛ በዓላማው ይለያል፣ ሦስተኛ…
- እሺ ሦስተኛስ?
- ሦስተኛ አስገዳጅ አይደለም።
- እሺ እኔ በተራዬ ልጠይቅህ?
- ስያሜው ብሔራዊ አገልግሎት ነው ስትል ምን ማለትህ ነው? ለምን አገልግሎት ነው የሚመለመሉት?
- እሱማ ለውትድርና አገልግሎት ነው።
- ታዲያ ምኑ ነው የሚለየው?
- የውትድርና አገልግሎት ቢሆንም ለውጊያ ተፈልገው አይደለም።
- እሱንማ ዛሬ አትገልጹትም።
- እንዴት? እና መቼ ነው የምንገልጸው?
- ጦርነት ሲመጣ ነዋ፡፡
- እንደ ተቃዋሚ ፓርቲ መጠራጠር አይለቅሽም፡፡
- እሱን ተወውና ጥያቄዬን መልስ፡፡
- መቼ አልመልስም አልኩኝ? ጠይቂኝ?
- ዓላማው የተለየ ነው ብለሃል።
- አዎ፣ ዓላማው የተለየ ነው።
- በምንድነው የሚለየው?
- ዓላማው ወጣቶችን ማነፅ ነው፣ አገራቸውን እንዲወዱ ማድረግ፣ አገራቸውን እንዲያውቁ ማድረግና ጥሩ ሥነ ምግባር የተለባሱ ዜጎችን ማፍራት ነው።
- እሱ እንኳ ጥሩ ነገር ነው ግን…
- ግን ምን?
- በውትድርና ካልሆነ በሌላ መንገድ ማነፅ አይቻልም?
- ይቻላል ነገር ግን ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች የሚያሳዩት በውትድርና ቤት ሲሆን በተሻለ ፍጥነት ጥሩ ዲሲፕሊን ያለው አገሩን የሚወድ ትውልድ መቅረፅ እንደሚቻል ነው።
- በተሻለ ፍጥነት ስትል በምን ያህል ጊዜ ነው?
- እኛ ያሰብነው የሁለት ዓመት አገልግሎት እንዲሰጡ ነው።
- ሁለት ዓመት?
- አዎ፣ ሁለተኛ ደረጃ የጨረሱ ወይም ዩኒቨርሲቲ ያጠናቀቁ ወጣቶች ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ብሔራዊ አግልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል።
- ሁለት ዓመት በጣም አልበዛም? የቀለም ትምህርቱን አይዘነጉትም?
- አይዘነጉትም፣ እንዲያውም የበለጠ ያዳብሩታል።
- ወይ ጉድ፡፡
- ለምን ወይ ጉድ?
- አንድ ጥሩ ነገር ያለው አስገዳጅ አለመሆኑ ብቻ ነው፣ አስገዳጅ አይደለም ብለሃል አይደል?
- አዎ፣ አስገዳጅ አይደለም፣ ግን…
- ግን ካልክማ አስገዳጅ ነው ማለት ነው።
- አይ አስገዳጅ አይደለም፡፡
- ታዲያ ለምን ግን አልክ? ምን ልትል ነበር?
- ግን ትምህርቱን የጨረሰ ወጣት ብሔራዊ አገልግሎት ወስዶ አገሩን ካላወቀ በመንግሥት ተቋም ውስጥ ሥራ አይቀጠርም፡፡
- ስለዚህ አስገዳጅ አይደለም?
- አስገዳጅ አይደለም!