የ‹‹ኦነግ ሸኔ›› ጥቃትን በመሸሽ ከሚኖሩበት ኦሮሚያ ክልል ከምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ወደ ምሥራቅ ወለጋ ተፈናቅለው አርጆ ጉደቱ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች፣ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የመጠለያና የምግብ ዕርዳታ ማግኘት እንዳልቻሉ ገለጹ፡፡
ከአራት ወራት በፊት ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ጭፍጨፋ የተፈጸመበት ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ተፈናቃዮች፣ ከሁለት ሳምንታት በፊት ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ወደ ምሥራቅ ወለጋ የተሻገሩት የ‹‹ኦነግ ሸኔ›› ታጣቂዎች ወደ ቀበሌዋ በመቃረባቸው ምክንያት ነበር፡፡
ከ600 በላይ አባወራዎች በአጠቃላይ 1,183 ሰዎች ተፈናቅለው በምሥራቅ ወለጋ ዲጋ ወረዳ አርጆ ጉደቱ ከተማ እንደሚገኙ ለሪፖርተር የተናገሩት የቀበሌው ምክትል ሊቀመንበር አቶ አህመድ ዘይኑ፣ ‹‹በሁለት ሳምንት ውስጥ ምንም የተገኘ ነገር የለም፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም መጠለያና ምግብ ለማግኘት ለከተማው አስተዳደር ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱን ገልጸዋል፡፡
ተፈናቃዎቹ መኖሪያቸው የሆነችው ቶሌ ቀበሌን ከጊምቢ ከተማ ጋር የሚያገናኘው መንገድ በታጣቂዎች በመያዙ ምክንያት፣ ከስልክ ንግግር ውጪ ከወረዳው አመራሮች ጋር ለመገናኘት አለመቻላቸውን ምክትል ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡
አቶ መሐመድ ዓሊ የተባሉ የቀበሌው ነዋሪ ባለቤታቸውንና ልጆቻቸውን ጨምሮ ስድስት ቤተሰብ ይዘው ከቶሌ ቀበሌ መፈናቀላቸውን ተናግረው፣ ከቶሌ ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ የሚመገቡት ‹‹በልመና›› መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በተፈጸመው ጭፍጨፋ ሁለት ልጆቻቸው፣ አንድ የልጅ ልጅና የልጃቸው ባለቤት እንደሞቱባቸው የሚገልጹት አቶ መሐመድ፣ ‹‹ቶሌ እያለን ያረስነውን ሰሊጥ፣ በቆሎና ለውዝ ወደ ቤታችን እያስገባን ነበር፡፡ አሁን የለበስናትን ልብስ ብቻ ይዘን ነው የወጣነው፡፡ በብርድም በረሃብም ችግር ውስጥ ነው ያለነው፤›› ሲሉ በአርጆ ጉደታ ያሉበትን ሁኔታ ገልጸዋል፡፡
ቶሌ ቀበሌ የሚገኝበት የምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቡላ ደመራም ዕርዳታ እየቀረበ አለመሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ የተፈናቀሉት የቀበሌው ነዋሪዎች ዕርዳታ እንዲቀርብላቸው ቀይ መስቀልን ጨምሮ ለዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች መደወላቸውን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው፣ ‹‹እንደርሳለን ብለውኝ ነበር፣ እስካሁን ምንም የደረሰ ነገር የለም፤›› ብለዋል፡፡ ይሁንና በአካባቢው ያለው የፀጥታ ሁኔታ ዕርዳታ ለማቅረብ ‹‹የማያስችል›› መሆኑን ተናግረዋል፡፡
‹‹ወረዳው እስካሁን አልተረጋጋም፣ የፀጥታ ኃይል በሁሉም ቦታ አልገባም፤›› የሚሉት አቶ ቡላ፣‹‹ሸኔዎች የእነሱን (የቶሌ ቀበሌ ነዋሪዎች) በር መስኮት ሳይቀር ሁሉንም ነገር ዘርፈዋል፣ ሌላውም በሜዳ ተበትኗል፤›› ብለዋል፡፡
ነዋሪዎቹ ከቀበሌው ከወጡ ከሁለት ቀናት በኋላ ቅዳሜ ጥቅምት 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ታጣቂዎች ቀበሌዋን መቆጣጠራቸውን የሚገልጹት የቀበሌው ምክትል ሊቀመንበር አቶ አህመድ፣ ‹‹12 መስኪዶች›› መውደማቸውንና የነዋሪዎች ቤት መዘረፉን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ቤቶቹ በሙሉ በርና መስኮታቸው ሳይቀር ነው የተዘረፉት፡፡ መቶ ኩንታል ሰሊጥ የተዘረፈበት ነጋዴም አለ፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ሪፖርተር በክልሉ ለሚገኙ ተፈናቃዎች የሚደረግ የዕርዳታ አቅርቦትን አስመልክቶ ለኦሮሚያ ክልል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ገረመው ኦሊቃ ያደረጋቸው የስልክ ጥሪዎችና የጽሑፍ መልክዕክቶች ምላሽ አላገኙም፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (ኦቻ) በኦሮሚያ ክልል ያለውን የዕርዳታ አቅርቦት አስመልክቶ ኅዳር 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት፣ በምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያ አካባቢዎች የሚደርሰው ዕርዳታ በ50 በመቶ መቀነሱን አስታውቆ ነበር፡፡ በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ ያለው የፀጥታ ሥጋት በመባባሱ ዕርዳታ ሰጪ ተቋማት ሥራቸውን ማቋረጣቸውንም ገልጿል፡፡
በፀጥታ ችግርና በድርቅ ምክንያት በክልሉ 740 ሺሕ ነዋሪዎች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውን የሚያስረዳው የኦቻ ሪፖርት፣ የፀጥታ ሥጋት በክልሉ አብዛኛው ቦታዎች ዕርዳታ ለማቅረብ እንቅፋት መሆኑን አስታውቋል፡፡