Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያ በብድርና ዕርዳታ የምታገኘው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ፓርላማው አሳሰበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በብድር የተገኘ ገንዘብ በሥልጠናና ውሎ አበል መልክ እንዳይባክን ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ኢትዮጵያ ከውጭ አገሮችና ድርጅቶች በብድርና በዕርዳታ መልክ የምታገኘው ገንዘብ ከስብሰባና ሥልጠና ክፍያ ወጥቶ ለታለመለት ዓላማ ሊውል ይገባል ሲል ጠየቀ፡፡

ፓርላማው ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ለሥርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚውል 0.75 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ የሚከፈልበትና በ38 ዓመት የሚከፈል የ400 ሚሊዮን ዶላር ብድር፣ የ200 ሚሊዮን ብር ዕርዳታ እንዲሁም፣ ከጣሊያን መንግሥት በ30 ዓመታት የሚከፈል የአሥር ሚሊዮን ዩሮ ብድር ላይ ተወያይቶ አፅድቋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን ተወካይ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ረቂቁ ከመፅደቁ በፊት በሰጡት አስተያየት፣ ገዘፍ ያሉ ብድሮች አገሪቱን ጫና ውስጥ የሚከቱ መሆኑን በመግለጽ፣ በብድር መልክ የሚመጡ ገንዘቦች የመጪውን ትውልድ ዕዳ ውስጥ የሚያስገቡ መሆን የለባቸውም ብለዋል፡፡

በመሆኑም ይህ ገንዘብ በሥልጠናና አቅም ግንባታ እንዲውል ተብሎ መቅረቡንና የሚመጣ ገንዘብ በሥልጠናና በአቅም ግንባታ መልክ ወጪ እየተደረገ እንደሚባክን  በመግለጽ፣ ለአቅመ ግንባታ ተብሎ አገሪቱ የምትበደረው ገንዘብ በአገር ውስጥ አቅም መሸፈን ለምን አልተቻለም? በማለት ጠይቀዋል፡፡

ወ/ሮ አስቴር በሽር የተባሉ የምክር ቤት አባል የቀረበው ብድር ላይ ተቃውሞ እንደሌላቸው በመግለጽ፣ ‹‹ነገር ግን ብዙውን ጊዜ በብድርና በዕርዳታ መልክ ገንዘቡ ይመጣና እዚያው በዚያው ባክኖ ይቀራል፣ ገንዘቡ ለታለመበት ዓላማ ሳይውል በውሎ አባል፣ በስብሰባና በሥልጠና፣ እንዲሁም መሰል ሰበብ አስባቦች እንደሚባክን በመጠቆም አደራ ብለዋል፡፡

አክለውም በብድርና በዕርዳታ መልክ የሚመጡ እነዚህ ገንዘቦች የሥነ ልቦና ጫና እንደሚያሳድሩ በመጠቆም፣ ገንዘቡን ለታሰበለት ዓላማ በማዋል አገሪቷ ማግኘት ያለባትን ጥቅም ማግኘት ይጠበቅባታል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ የፓርላማ ተወካይ አብርሃም በርታ (ዶ/ር) ከጣሊያን መንግሥት የቀረበውን የአሥር ሚሊዮን ዩሮ ብድር አስመልክተው ሲያብራሩ፣ ገንዘቡ በዓመት 0.5 በመቶ ወለድ እንደሚከፈልበት፣ የ12 ዓመት የችሮታ ጊዜ እንዳለውና በዚህ የወለድ ምጣኔ ብድሩ በየዓመቱ 50 ሺሕ ዩሮ እንደሚወልድና በአጠቃላይ በ30 ዓመታት ውስጥ ከዋናው አሥር ሚሊዮን ዩሮ ጋር ተዳምሮ የሚመጣው ገንዘብ 25 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚደርስ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ይህን 25 ሚሊዮን ዩሮ የአገር ሸክም እንዳይሆን ጥንቃቄ ተደርጎበት፣ ገንዘቡ ተግባራዊ የሚሆንበት መንገድ በአግባቡ እንዲቀረፅ ጠይቀዋል፡፡

ከዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር በብድርና ዕርዳታ የተገኘው ገንዘብ አገሪቱ በአገር በቀል ኢኮኖሚክስ ሪፎርም ማሻሻያ የተመላከተው ግብ ላይ ለመድረስ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የአርሶና አርብቶ አደሩን ገቢ ማሳደግና ከድህነት ማላቀቅ፣ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንዲሁም፣ እሴት የታከለበት የግብርና ግብዓት ለውጭ ገበያ ማቅረብና በገጠር በቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያለመና እ.ኤ.አ. ከ2022 እስከ 2029 የሚቆይ ገንዘብ ነው፡፡

በሌላ በኩል ከጣሊያን መንግሥት የተገኘው የአሥር ሚሊዮን ዩሮ የጤናውን ዘርፍ ዘላቂ ልማት ግቦች ለማሳካት ለሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የተደረገ ስምምነት ነው፡፡ ፓርላማው በሁለቱም ረቂቅ አዋጆች ላይ ከተወያየ በኋላ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋቸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች