Saturday, May 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹ከገበሬው እስከ ሸማቹ ያለውን የንግድ ቅብብሎሽ አመቻቻለሁ›› ያለው ፐርፐዝ ብላክ ውጥኑ ከምን ደረሰ?

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚሰማ አንድ ርዕሰ ጉዳይ የኑሮ ውድነት ነው፡፡ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ እንዲሁም ከሁሉም በገዘፈ መልኩ በማዕከላዊ የአገሪቱ ክፍል የሚገኘው ነዋሪ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሲያነሳ የሚደመጠው ጉዳይ የዋጋ ንረትን ተከትሎ ስለተንሰራፋው የኑሮ መክበድ ነው፡፡

ሪፖርተር በተለያየ ጊዜና አጋጣሚ ያነጋገራቸው ሸማቾች ‹‹ነጋዴው ይራራልን!፤ መንግሥት ገበያውን ሃይ ይበልልን!›› ሲሉ ሐሳባቸውን አስተጋብተዋል፡፡ መንግሥት የእሑድ ገበያን ጨምሮ፣ የትምህርት ቤት ምገባ፣ ማዕድ ማጋራትንና የመሳሰሉ ፕሮጀክቶችን መተግበሩ ሥጋት የነበረውን የምግብ ዋጋ መናር፣ እንዲሁም መዘዙን ቢያንስ ባለበት ለማስቆም እንዳስቻለ የሚገልጽ ቢሆንም፣ የዋጋ ግሽበት አሁንም በማክሮ ኢኮኖሚው ዕቅድ ላይ ግቡን ያልመታ ርዕሰ ጉዳይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጭምር ያረጋገጡት ሃቅ ነው፡፡ 

በአገሪቱ በተለይም በመሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች ላይ የሚታየው ከፍተኛ የዋጋ ንረት መንስዔ የምርት እጥረት እንደሆነ ቢታወቅም፣ ችግሩን የበለጠ ያወሳሰበው ግን የገበያ ሥርዓቱ እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በአንድ አካባቢ ያለ በቂ ምርት ችግር ወዳለበት አካባቢ መድረስ አለመቻሉ፣ እንዲሁም የገበያ ተዋናዮች ምርቶችን በመያዝ የሚፈጽሙት ደባና የተራዘመ የገበያ ሰንሰለት ለዋጋ ንረቱ መባባስ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ይነገራል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ በመንግሥት በኩል የሸማቾች ማኅበራትን የማደራጀትና የገበያ ሰንሰለቱን ለመቁረጥ ጥረቶች ቢደረጉም ውጤቱ እዚህ ግባ ይሚባል አልሆነም። 

እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ የአገሪቱን የገበያ ችግርና መዛባት ለማረም የበኩላቸውን አሻራ ለማኖር የተሰባሰቡ ግለሰቦች ከዓመት ከሦስት ወር በፊት የጀመሩት ጥረት አሁንም እየገፉበት ይገኛሉ። የግለሰቦቹ ትጋት አምራችና ሸማቹን በተሻለ ለማቀራረብ ያለመ ነው።

ይህንን ትልም ይዘው የመሠረቱት ፐርፐዝ ብላክ አክሲዮን ማኅበር፣ ‹‹ገበሬውን በቀጥታ ከሸማቹ ጋር በማገናኘት በመሃል ያለውን ነጋዴ በማስወጣት በተመጣጣኝ ዋጋ ምርት አቀርባለሁ፣ የእርሻ መሬት ተረክቤ በማልማት ምርት እሰብስባለሁ፣ ደግሞም ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን በመትከል አንድም ከድርጅቱ ድርሻ የገዙ ባለአክሲዮኖችን እንዲሁም ገበሬውንና ሸማቹን ትርፋማ አደርጋለሁ፤›› ብሎ ገበያውን ከተቀላቀለ ዓመት ከመንፈቅ ሊይዝ ጥቂት ቀርቶታል።

በወቅቱ በአክሲዮን ማኅበሩ የተወጠኑት ውጥኖች የተለጠጡ፣ ወደ ተግባር ሲቀየሩም አዳጋች ሊሆኑ የሚችሉ ስለመሆናቸው ሥጋታቸውን የሰነዘሩም በርካቶች ናቸው፡፡

ለመሆኑ ፐርፐዝ ብላክ ባለፉት 15 ወራት ውስጥ ምን ሠርቶ ይሆን? ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ገበያውን ለማረጋጋት አስተዋፅኦ እያደረገ ነው? አርሶ አደሮችን በቴክኖሎጂ በመደገፍ የተሻለ ምርት እንዲያመርቱ ያደረገው ነገር አለ? የገበያ ዕድልን ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ባመቻቸው ዕድል ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል? ምን ያህል ካፒታል ላይ ደረሰ? በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ገብቶ የትና ምን እያመረተ ነው? የሚሉት ጥያቄዎች መቃኘት አንባቢያንንም ሆነ ጉዳዩን በቅርበት ለሚከታተሉ ሁሉ ጠቃሚ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡

የፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሰሐ እሸቱ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ድርጅቱ ከተቋቋመ ዓመት ከሦስት ወራት ሆነውታል፡፡ በዚህም ድርጅቱ ሲመሠረት የነበሩትን ባለአክሲዮኖች ቁጥር ከ110 ወደ አሥር ሺሕ እና ከዚያ በላይ አሳድጓል፡፡ ከዚህም ውስጥ አብዛኛውን ድርሻ (ከሦስት ሺሕ በላይ) የሚይዙት ገበሬዎች ናቸው፡፡ በእርግጥ ባለአክሲዮን ለመሆን የተመዘገቡ ግለሰቦች ቁጥራቸው 30 ሺሕ ቢሆንም በትክክል የሚጠበቅባቸውን ከፍለው ያጠናቀቁት ግን አሥር ሺሕ መሆናቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ያስረዳሉ፡፡

አንድ ድርጅት ከምሥረታ አንስቶ ባለው የትግበራ ወቅት ምን ሠርቷል ተብሎ ከሚለካባቸው መሥፈርቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሹ መሆኑ ሁሉንም የሚያስማማ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ለሦስት ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሮ የተጀመረው ሥራ በዚህ ወቅት ለ2,500 በላይ ሰዎች የሥራ ዕድል መፈጠር ምክንያት እንደሆነ፣ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ አራት ሺሕ የሠራተኛ ቁጥርን ማስተዳደር የተቋሙ የቅርብ ውጥን እንደሆነ ፍሰሐ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡ ለዚህም ፐርፐዝ ብላክ ባሉት ፕሮጀክቶች የሠራተኛ ቅጥር እየፈጸመ እንደሆነና ሥራ ሲጀምር ከነበረው አንድ ቢሮ አሁን ላይ 14 ቅርንጫፎች ላይ መድረሱ እንዲሁ ይነሳል፡፡

ፐርፐዝ ብላክ በመላ አገሪቱ ውስጥ ካሉት ቢሮዎች ባሻገር ከ310 በላይ ወረዳዎች ላይ እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑ፣ ይህም የተቀናጀ የኤክስቴንሽን ፕሮጀክት በሚል የጀመረው ሥራ አካል እንደሆነ ይገልጻል፡፡

በዚህ ወቅት 2,200 ሄክታር መሬት በተለያየ የአገሪቱ ክፍሎች እያለማ እንደሚገኝ ያስታወቀው ድርጅቱ፣ ከበቆጂና ኦሞ የእርሻ መሬት ላይ ምርቶችን መሰብሰብ መጀመሩን ይገልጻል፡፡ አርባ ምንጭ ላይ መለስተኛ የባህላዊ ምርቶችን (ሽሮ፣ በርበሬ፣ ቅመማ ቅመም) የሚያቀነባብር ፋብሪካ ሼድ በመከራየት ሥራ አንደ ጀመረ አስታውቆ፣ በዚህ ወቅት 2.5 ሄክታር መሬት ከዞኑ ተረክቦ፣ የማቀነባበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ለመጀመር ጥናቶችንና ተያያዥ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አስታውቀዋል፡፡

ድርጅቱ ከምሥረታው አንስቶ ባሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ አንድ ሺሕ የችርቻሮ መሸጫ ሱቆችን፣ 50 የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን እንደሚያቋቁም ማስታወቁ ይታወሳል፣ እንዲሁም አምስት ሺሕ ሄክታር መሬትን በአንድ ዓመት ብቻ የማልማት ግብ ጥሎ ነበር፡፡ እነሆ ከዓመት በላይ በዘለቀው የድርጅቱ የሥራ ጊዜ የተከፈቱት የችርቻሮ ሱቆችና ማከፋፈያዎች ሰባት ከመሆናቸው አንፃር፣ የተቋቋመው የማቀነባበሪያ ፋብሪካ በቁጥር አንድ ከመሆኑ አኳያ እንዲሁም ተረክቦ እያለማ ከሚገኘው የእርሻ መሬት ስፋት አንፃር በተባለው ጊዜ ውስጥ ድርጅቱ ግቡን ለማሳካት እየሄደበት ያለው ፍጥነት እንዴት ነው? የሚል ጥያቄ ያጭራል፡፡

‹‹ከግብ አንፃር አንዳንዶቹን ማስተካከል ነበረብን፡፡ ግቡን ለመምታት ከመክበዱ አንፃር ብቻም ሳይሆን፣ ከአካሄድ አንፃር አንድ ሺሕ ሱቆችን ለመገንባት ነበር የታቀደው፣ እስካሁን ባለው ሰባት ሱቆችን የመክፈት ሒደት እንደታየው የችርቻሮ ሥራ (ሞዴሉ) ውድ ነው፡፡ ትንሹ ሱቅ አራት ሚሊዮን ብር ወጭ ጠይቆናል›› የሚሉት ፍሰሐ (ዶ/ር)፣ ከሰባት እስከ ስምንት ሚሊዮን ብር ወጪ የፈጁ ሱቆችም እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ በሸማቹ ላይ ተጨማሪ የዋጋ ጭማሪ ማድረግን ስለሚስያገድድ ከዚያ ይልቅ በተንቀሳቃሽ የምርት ማቅረብ ሥርዓቶች በየሰው ቤት ማዳረሱ ርካሽ ሆኖ መገኘቱን ይገልጻሉ (ከኢንቨስትመንት ወጪ አንፃር አዋጭ ነው)፡፡ 

እንደ ፍሰሐ (ዶ/ር) ገለጻ፣ ፐርፐዝ ብላክ የችርቻሮ ምርት ሽያጭ ሥርጭትን በሦስት ዓይነት መንገድ የሚያከናወን ሲሆን፣ የመጀመሪያው ቤት ለቤት ምርት ማቅረብ፣ ሁለተኛው ሱፐር ማርኬቶችን መክፈት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ሰባት ሱፐር ማርኬቶች የተከፈቱ ሲሆን፣ ስድስት የሚሆኑት አዲስ አበባ ላይ የተከፈቱ ናቸው፡፡ ሦስተኛ የበይነ መረብ ሽያጭ ተጠቅመው ለሚገለገሉ ደንበኞች ምርት የሚቀርብበት መንገድ ሲሆን፣ ተስፋ ሰጪ ከሚባሉት አማራጮች ተጠቃሹ መሆኑን ፍሰሐ (ዶ/ር) ይገልጻሉ፡፡

በተያዘው ወር በፓርላማ ቀርበው በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ብቸኛው አማራጭ ምርትን ማሳደግ ነው ያሉት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በዚህ ወቅት እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር ብክነትን መቀነስን፣ ማዕድ ማጋራትን፣ ባሉ ክፍት ቦታዎች ሁሉ ምርት በበቂ መጠን ማምረትን፣ ከሌብነትና ከስንፍና መታቀብ እንዲሁም ከግጭት ሰላምን፣ ከስንፍና ትጋትን፣ ከሌብነት ሐቀኝነትን መምረጥ ቁልፍ ጉዳዮች መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

የግሽበት አኃዙ ከነበረበት 30 ቤቶች ውስጥ ወርዷል የሚለው በሚገለጽበት አግባብ ሳይሆን ፐርፐዝ ብላክ አመራጭ በማቅረብ ኅብረተሰቡን በፍትሐዊ የገበያ ሥርዓት ተጠቃሚ እንዲሆን ልምምድ ዘርግቷል የሚል ሐሳብ የሚሰነዝሩት ፍሰሐ (ዶ/ር)፣ በተለምዶ የእሑድ ገበያ ተብሎ እየተሠራበት የሚገኘው አማራጭ ‹‹ለምን ለኅብረተሰቡ ተንቀሳቃሽ በሆነ መንገድ ምርት አይቀርብም?›› የሚለውን ፅንሰ ሐሳብ በፐርፐዝ ብላክ ከቀረበ በኋላ የተጀመረ መሆኑን በማስታወስ፣ መሰል ፋብሪካዎች መጥተው፣ በቀጥታ ወደ ግብርና ገብተው አሊያም ከገበሬው ጋር ቀጥታ ሠርተው ለኅብረተሰቡ ምርት ማድረሳቸው የገበያ ዋጋ ማረጋጋት እንደጀመረ፣ አማራጭ በመምጣቱ ከዚህ ቀደም የነበረውን በነጋዴ በኩል የዋጋ መቆለል እያስቆመ ይገኛል ይላሉ፡፡ ሆኖም የመሰል ድርጅቶት አቅም መጠናከር ግድ እንደሚል ሌሎች የኢኮኖሚ ባለሙያዎችም የሚሰነዝሩት ሐሳብ ነው፡፡

ፐርፐዝ ብላክ ወደ ሥራ ሲገባ ዕድልና ተግዳሮቶችን ይዞ እንደሆነ የሚገልጹት ሥራ አስፈጻሚው፣ ድርጅቱ የተሰማራበት የግብርና ምርት ልማትና ሥርጭት ፍላጎት አገሪቱ ላይ መኖሩ መልካም ዕድልነቱ የሚያሳይ እንደሆነ በአስረጅነት ያነሳሉ፡፡ ብዙኃኑ ኅብረተሰብ በኑሮ ውድነት እንደ መሰቃየቱ ከገበሬው የሚመረተው ምርት በሸማቹ ደጅ እንዲያገኝ ከፍተኛ ፍላጎት አለ፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አገሪቱ በተለይም አምና በጦርነት ውስጥ እንደነበረች፣ ይህ ደግሞ ፕሮጀክቱ በጀመረበት ወቅት መሆኑ ሰው በአክሲዮን ገበያው (ሽያጭ) ኢንቨስት የማድረግ መተማመንን ጥያቄ ውስጥ የከተተበት ጊዜ እንደነበር ሌላ የሚገለጽ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ድርጅቱ ይዞ የመጣው የቢዝነስ ሐሳብ ዘወትራዊ ከሆኑ የአክሲዮን ቢዝነሶች ይልቅ ያልተዘወተረ መሆኑ ግንዛቤ ላይ ክፍተቶች መኖራቸው ድርጅቱ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከገጠሙት አንቅፋቶች ተጠቃሹ መሆኑን ያስታውቃል፡፡

ከሁሉም በላይ ግን የደላላው ሥርዓት እንደፈተናቸው የሚናገሩት ፍሰሐ (ዶ/ር)፣ ያንን ሥርዓት ተጋፍቶ፣ ገበሬውን አሳምኖ ምክንያታዊ በሆነ ዋጋ ምርት እንዲያቀርብ ማድረግና ያንን ደግሞ ለኅብረተሰቡ ማቅረብ በራሱ ፈተና መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ሙስና ሌላኛው ሥራውን የፈተነው ተግዳሮት ስለመሆኑ ተቋሙ ያስረዳል፡፡ ‹‹ሥራዎችን ለመሥራት ይህንን ካላመጣችሁ የሚባል ነገር አለ፤›› የሚሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች የሚባሉት በተለይ ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጋር ተያይዞ ያለው ችግር በራሱ እንደ አንድ ተፅዕኖ እንደሚወሰድ ይገለጻል፡፡

ከላይ የተገለጹት ሳንካዎች እንደተጠበቁ ሆነው ‹‹ወደ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተን ስንሠራ የነበረንን ግምት (ኤክስፔክቴሽን) ቀነስ (ዝቅ) አድርገን መግባታችን የገጠሙን ፈተናዎች በጣም እንቅፋት ሆነው አላገኘናቸውም፤›› የሚሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ‹‹አንሞክራለን ብለን መጥተን ለዚህን ያህል ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራችን ከጠበቅነው በላይ አግኝተናል ለዚያም ፈጣሪን እናመሰግናለን፣ ያ ማለት ግን አስቸጋሪ አልነበረም ማለት አይደለም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ፐርፐዝ ብላክ በሥራው ላይ ውጤታማ ሆኖ እንዲቆይ ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ የልዩ ጥቅም አክሲዮን (ፍራንቻይዝ ሼር) ዋነኛው ነው የሚሉት ፍሰሐ (ዶ/ር)፣ አክሲዮን ማኅበሩ ትንንሽ አክሲኖችን በመሸጥ እንደማይቀጥል በማስታወስ፣ ትልልቅ ኢንቨስተሮችን በማምጣት በዚህ አማራጭ አክሲኖችን ከዓመታዊ ትርፍ ክፍፍል 50 በመቶ ጥቅም እንዲያገኙ በማድረግ ከ90 በመቶ በላይ ካፒታሉን በዚህ መልኩ ማንቀሳቀሱን ይገልጻሉ፡፡ በዚህ አማራጭ 350 ሚሊዮን ብር አክሲዮን የሸጠው ፐርፐዝ ብላክ፣ ብዙኃኑ ፕሮጀክቶቹን የሚያንቀሳቅሰው በልዩ ጥቅም አክሲዮን አማራጭ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በረዥም ጊዜ ሒደት ካፒታሉን አሥር ቢሊዮን ለማድረሰ ግብ የጣለው ይህ ድርጅት በዚህ ወቅት 400 ሚሊዮን ብር ካፒታል እንደሚያንቀሳቅስ ይገልጻል፡፡

በቅርቡ ‹‹ሃሽታግ ኖ ሞር ሃንገር›› የሚል ትልቅ ፕሮጀክት ነድፌያለሁ የሚለው ፐርፐዝ ብላክ፣ ዘላቂ የገጠር ልማት ዘመቻ የሚል ሐሳብ ያነገበው ፕሮጀክት አርሶ አደሩን እያንዳንዱን በአንድ ሺሕ ክላስተር እያደረገ አርሻ ብቻ ሳይሆን የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው አንድ ቦታ ላይ ሰፍረው እንዲኖሩ ለማድረግ ነው፡፡ ድርጅቱን ይህን ዓይነት አንድ ሺሕ የሚደርስ ግንባታዎችን የመገንባት ዕቅድ ያለው ሲሆን፣ ለዚያ የሚሆነው ዘመቻ እንደተጀመረ ፍሰሐ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡

ፐርፐዝ ብላክ ያቀረበው የኩታገጠም እርሻ (ክላስተሪንግ) በመንግሥት ከሚተገበረው አሠራር የሚለየው በሁለት ዓይነት አማራጭ ወደ ሥራ የሚገባ መሆኑ ሲሆን፣ አንደኛው ድርጅቱ በራሱ የሚመሠርተው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አርሶ አደሩ ራሱ ተደራጅቶ በድርጅቱ ማዕቀፍ ሥር ለመሆን የሚመጣበት ነው ተብሏል፡፡

በመንግሥት ከሚደራጁት ይልቅ በፐርፐዝ ብላክ የሚሰባሰቡት ገበሬዎች የድርጅቱ ባለድርሻ ሆነው ከምርት እስከ ሽያጭ ባለው የድርጅቱ የቢዝነስ ሰንሰለት ውስጥ የሚገኘውን ጥቅም የሚካፈሉበት አማራጭ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ሥራ አስፈጻሚው ያስረዳሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ድርጅቱ በክላስተር ሥራው ለገበሬው መንግሥት የማያቀርበውን ፋይናንስ፣ ኢንሹራንስ፣ የግብዓት አቅርቦት በዱቤ አማራጭም ሆነ አሊያም ምርት አምርተው ከሸጡ በኋላ ብሩን የሚከፍሉበት አማራጭ እንደሚያቀርብ ይናገራል፡፡

ፐርፐዝ ብላክ በግብርና ኢንቨስትመንት ተሰማርቶ ከገበሬው እስከ ሸማቹ ድረስ ያለውን የንግድ ቅብብሎሽ በማመቻቸት የዋጋና ትርፍ ህዳግ ፍትሐዊነትን ያረጋገጠ የገበያ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያደርገው ጥረት የሄደበት ርቀት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ባለ ድርሻዎቹ የሚፈልጉትን የትርፍ ክፍፍል እንዴትና መቼ ያስተላልፋል? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡

ፍሰሐ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ‹‹ማንኛውም ኩባንያ የመጀመሪያ ዓመት ሥራው ኢንቨስትመንት ነው፡፡ በተያዘው ዓመት ሼር ሆልደሮቻችን ትርፍ ይጠብቃሉ ብለን አናስብም፡፡ በዕቅዳችን መሠረት በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ወጪያችንን ሸፍነን ትርፍ ወደ ማግኘት እንሄዳለን፣ እርግጠኛ ነኝ በሚቀጥለው ዓመት ፐርፐዝ ብላክ ጠቅላላ ጉባዔውን ሲጠራ እስከ 25 በመቶ ትርፍ ለመስጠት (ሪተርን) አቅዷል፣ ቃል የገባነው ነገር አለ፣ በአራት ዓመት ውስጥ ኢንቨስትመንታችሁን ትመልሳላችሁ ብለን ነው እየሠራን ያለነው፡፡››

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች