Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የፀረ ሌብነት ዘመቻው ለነጋዴ የሚቸበችቡ የሸማቾች ማኅበራትን እንዳይዘነጋ!

መንግሥት ሰሞኑን ሌብነት ላይ ለመዝመት እየሠራ ስለመሆኑ በሰፊው እየተነገረ ነው፡፡ እንደተባለው ሌቦች የእጃቸውን እንዲያገኙ መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና የሕዝብን የዓመታት ብሶት ለማቃለል በመንግሥት በኩል ሥራ ተጀምሯል፡፡ ይህን ወደ ነቀርሳ ደረጃ የተሸጋገረ ያለ ብልሹነት ለማከም ይረዳ ዘንድ በአገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው ፀረ ሌብነት ኮሚቴ ሥራውን ከየት እንደጀመረ ባናውቅም ሥራ መጀመሩን የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ፡፡ በብልሹ ተግባራት የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ምርመራ ስለመጀመሩ የሚጠቁሙ ዜናዎች ከሌላው ጊዜ በየተለየ ከዚህም ከዚያ መሰማታቸው አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ፀረ ሙስና ኮሚሽንም ሰሞኑን መንግሥት ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴው መቋቋሙን እንደ ብርታት የሚያየው ስለመሆኑ ማሳወቁም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡  

ይህ ኮሚቴ እጅግ ሥር የሰደደውን ሌብነትና የመልካም አስተዳደር ችግር ወደ መስመር ለመመለስ በምን ያህል አቅም እንደሚጓዝና ውጤት እንደሚያመጣ ወደፊት የምናየው ጉዳይ ይሆናል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግሩና የሌብነት አድማሱ ከመስፋቱ አንፃር ይህ ኮሚቴ የሚጠብቀው ብርቱ ሥራ ስለመሆኑ ግን አያጠያይቅም፡፡

የችግሩ ፈጣሪዎችና አድራጊዎች እዚያው በመንግሥት ጉያ ሥር ያሉ ጭምር በመሆናቸው ነገሮችን ማወሳሰቡ አይቀርም፡፡ የኮሚቴው በአንፃሩ ዘው ብሎ ወደ ዕርምጃ ከመግባት ይልቅ በጥናት ላይ የተደገፈ እንቅስቃሴ ቢያደርግ ወደ ሚፈለገው ግብ ለመጓዝ ያግዛል፡፡

ፍተሻው ከላይ እስከ ታች ድረስ መሆን እንዳለበት ይታመናል፡፡ በተለይ ታች ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል በእጅጉ እያማረሩ ያሉ ተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ በፍጥነት በመቃኘት ያሻል። ለምሳሌ ለሕዝብ ምሬትና ብሶት መባባስ ምክንያት የሆኑ የሸማቾች ማኅበራትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የሸማቾች ማኅበራት በአግባቡና በትክክል የተቋቋመለትን ዓላማ ማሳካት ቢችሉ ዛሬ የተዘፈቅንበትን የዋጋ ንረት በእጅጉ ይታደጉ ነበር፡፡ ሆኖም እነዚህ የሸማች ማኅበራት ከሚደረግላቸው ድጋፍ አንፃር ሲታዩ ግብራቸው እየተንሻፈፈ ሄዷል ማለት ይቻላል፡፡ በአግባቡ ቁጥጥር የማይደረግባቸው በመሆኑ ሌብነት የሸማቾችን እሮሮ እያባባሰው ነው፡፡

የዋጋ ንረትን ለመከላከል በሚል በተለያዩ መንገዶች በብድር መልክ የሚሰጠው ገንዘብም በአግባቡ ስለመመለሱ ማረጋገጫ የለም፡፡ ይህ ደግሞ በመሀል ለብክነትና ለሌብነት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ተብሎ ይታመናል፡፡ 

ለሸማች ማኅበራት በተመጣጣኝ ዋጋ የተለያዩ ምርቶችን እንዲከፋፈሉ በድጎማ ጭምር ይቀርባል፣ አነስተኛ ገቢ ላለውም ሆነ ለሌላው ኅብረተሰብ በአግባቡ እየተሠራጨ ያለመሆኑ የችግሩ አንድ አካል ነው፡፡ እንዲህ ያለው የቆየ የሌብነት ችግር በተደጋጋሚ በአደባባይ ሲነገር የነበረ ቢሆንም አንድም መፍትሔ ሲሰጠው አይታይም፡፡ ከፍ ባለ ደረጃ ከሚታየው ሌብነት የበለጠ በብዛት ወደ ታች ባሉ እንደ ሸማቾች ማኅበራት ውስጥ ያለው ችግር ብዙዎችን የሚመለከት ከመሆኑ አንፃር አሁን የሚጀመረው ዘመቻ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን በጥንቃቄ መመልከት እንዳለበት ማስታወሱ ተገቢ ነው፡፡

ሌብነቱ ያልነካካው ዘርፍ የሌለ በመሆኑ በተለይ ብዙኃኑ ላይ ጉዳት እየደረሱ ያሉ ተቋማት ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል የሚባልበት ዋና ምክንያት ሌብነቱ ሳያንስ የግብይት ሥርዓቱን ብልሽት የነዋሪዎችን ችግር እያባባሰ በመሆኑ ነው፡፡

ዛሬ ጥቂት የማይባሉ የሸማች ማኅበራት ውስጥ የሚሠሩ ኃላፊዎች በድጎማ የሚመጡ ምርቶችን ሳይቀር በጎን ለነጋዴ ቸብችበው በስሙ ምርት የመጣለት ሸማች ምንም ሳያገኝ የሚቀርበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡

በእነዚህ ብልሹ የሸማች ማኅበራት ሠራተኞች በጎን ለነጋዴ የሚሰጡ ምርቶች ሸማቹ እጅ ያለመግባታቸው ብቻ ሳይሆን አሁን የሚታየውን የዋጋ ንረት በማባባሱ ረገድም የራሳቸው ሚና አላቸው፡፡

ስለዚህ ሌብነት ስንል በመንግሥት ቢሮ ቁጭ ብሎ በጉቦ ጉዳይ ‹‹የሚገድል›› ብቻ አይደለም፡፡ የከተሞችን መሬት ከደላሎች ጋር ሆኖ የሚቀራመተውን ብቻ ወደ ሕግ ማምጣት ብቻ አይደለም፡፡ በቀጥታ ከብዙኃን የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሚገናኝ እንደ ሸማች ማኅበራት ውስጥ ያሉ ተቋማት ውስጥ ያሉ ትናንሽ የሚመስሉ ግን ጉዳታቸው እጅግ የከፋ የሆኑ ህፀፆች መነቀል አለባቸው፡፡ 

በየወሩ በየሸማች ማኅበራት በኩል ለሕዝብ እንዲቀርቡ የሚደረጉ ምርቶች ለማን መቼ ተሰጠ? የሚባል ቁጥጥር በሌለበት ሁኔታ ምዝበራው የት ድረስ እንደሚሄድ ማወቅ ይገባል፡፡ ወደ ኋላ መለስ  ብሎ ይህ የት ሄዶ ማለትንም ይጠቃይል፡፡ 

የሸማቾች ማኅበራት ኦዲት አለመደረግ ኦዲት ቢደረጉም የሚገኘውን ጉድለት ያደረሱ አካላት በሕግ ሲጠየቁ የማይታዩ በመሆኑ ሌብነቱ ቅጥ እያጣ እንዲሆን ያደረገው ሌላው ቁልፍ ጉዳይ በሆነ አጋጣሚ ሲሰርቁ ተያዙ የተባሉ ሰዎች ወዲያው ተለቀው ወደ ተለመደ ተግባራት እንዲገቡ የሚደረግ መሆኑ ነው፡፡ እንዴት ወጡ? ለምንስ ወደ ሥራ ተመለሱ የሚለው ጥያቄ ለብዙዎች እንቆቅልሽ እንደሆነ አለ፡፡ 

በሸማች ማኅበራት ብቻ መገኘት ያለባቸው ምርቶች በገበያ ውስጥ የመገኘታቸው ምክንያት ሌላ ሳይሆን ለሸማች ይድረስ የተባለውን ምርት ለነጋዴ በማቀበላቸው ነው፡፡ በዚህ ቅብብሎሽ ስንት ደሃ እያለቀሰ እንደሆነ ቤት ይቁጠረው፡፡

ብዙ ሸማች በሸማቾች ማኅበራት ማግኘት ያለባቸውን ምርት በውድ ዋጋ ከአትራፊ መልሰው እንዲገዙ መገደዳቸው የሚያሳየን ሌብነት በሰንሰለት የተሳሰረ ጉዳቱም አስከፊ መሆኑን ነው፡፡ 

ለምሳሌ ‹‹ወደ እገሌ ሸማች ማኅበር መድረስ የነበረበት ዘይትና ስኳር የጫነ መኪና በሕገወጥ መንገድ ለነጋዴ ሊደረስ ሲል ተያዘ፤›› የሚሉና ተመሳሳይ ዜናዎችን እንሰማለን እንጂ ይንን የፈጸሙ የሸማቾች ማኅበራት መሪዎች እንዲሁም ምርቶቹን ሊገዛ ነበር የተባለው ወይም ደላላ ማንነት ሲገለጽ አይሰማም፡፡

እንደው ምናልባት ማንነታቸው ከታወቀ እንኳን ሕግ ፊት ቀርበው አይቀጡም? ከተያዙም ወዲያው የመለቀቃቸው ጉዳይ ምንድነው ካልን የሌብነቱ ኔትዎርክ  ከሸማቾች ማኅበራት ወጥቶ ከፍ ወዳለው አካል ጭምር የሚሄድ መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡

ስለዚህ ብሔራዊ ኮሚቴም ሆነ ሌላው አካል ሌብነት ላይ በትክክል ስለመዝመቱ የምናረጋግጠው ወደ ታች ወርዶ በሸማች ማኅበራት ውስጥ ያለውን አደገኛ ውንብድና ላይ ጭምር ዕርምጃ ሲወሰድ ነው፡፡

የቀበሌ መታወቂያ ለማግኘት በእጅጉ የማይገባቸው ወረዳዎች የቤት ኪራይና መሰል አገልግሎቶችን በቀላሉ ማግኘት ቢቻል ጉቦ እየወሰዱ በቡድን የሚከፋፍሉትን ሠራተኞች ጭምር ተግባራቸው ተጋልጦ ዕርምጃ ካልተወሰደ ነገሩ ሁሉ ቢወቅጡት እንቦጭ ነው የሚሆነው፡፡ በመሆኑም ሌብነትን ለመክፈት አሁን የተጀመረው ሥራ ለማለት ብቻ ያመሆኑን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ተነካክቶ የሚተው ከሆነም አደጋው እጅግ የከፋ ሊሆን እንደሚችል በማሰብ ሥራው ቀጣይነት ያለውና ተቋማዊም እንዲሆን ይመከራል፡፡

 

 

   

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት