Friday, May 24, 2024

ከመሬት ለአራሹ ወደ ደላላ የዞረው የመሬት ፖለቲካ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ለመጀመርያ ጊዜ የጻፈውና ያቀነቀነው ባሮ ቱምሳ ነው ብለው ‹‹የመሬት ለአራሹ›› ጥያቄን አነሳስ ቢናገሩም፣ በተማሪዎች ንቅናቄ የተነሳ መሆኑን ታሪክ ያስረዳል፡፡

በ1958 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ‹‹መሬት ለአራሹ›› ያሉ ተማሪዎች በንጉሡ ላይ በአደባባይ ተቃውሞ አሰሙ፡፡ ተማሪዎቹ በአንዳንዶች ዘንድ ያልበሰሉ፣ በግብታዊነትና በውጭ ተፅዕኖ የሚነዱ ተብለው  ተወገዙ፡፡ ይህ ውግዘት ዛሬም ሲከተላቸው ይታያል፡፡

ይሁን እንጂ ብዙዎች እንደሚስማሙበት እነዚያ ‹‹ያልበሰሉ›› የተባሉ ተማሪዎች ለብዙ ሺሕ ዘመናት የሰፈነውን ፊውዳላዊ ሥርዓት ከሥር ከመሠረቱ መንግሎ የሚጥል ከባድ የፖለቲካ ጥያቄ ነበር ያነሱት፡፡ ተማሪዎቹ የቱንም ያህል ግብታዊ ቢባሉ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ሥር የሰደደና መሠረታዊ የሆነውን የፖለቲካ ጥያቄ (የመሬት ጥያቄ) አንስተው ነበር፡፡

የታሪክ ምሁሩና የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተሩ አቶ አበባው አያሌው እንደሚናገሩት፣ የንጉሡ አገዛዝ በተማሪዎቹ ጥያቄ ደንግጦ በመሬት ይዞታ ሚኒስቴር ሥር ጉዳዩን የሚያጠና ትልቅ ኮሚቴ አዋቀረ፡፡ ትልልቅ ሚኒስትሮችን ያቀፈው ኮሚቴም የኢትዮጵያን የመሬት ሥሪት አጥንቶ የማሻሻያ ሐሳቦች አዘጋጀ፡፡

የንጉሡ ሥርዓተ መንግሥት የመሬት ሥሪቱን ማሻሻል እንዳለበት በጊዜው ቢረዳም፣ ነገር ግን ዕርምጃ ለመውሰድ እጅግ አረፈደ፡፡ የመሬት ሥሪቱን ለማሻሻል ተጠንቶ የቀረበው ጥናት ለዘጠኝ ዓመታት አንዴ ፓርላማ አንዴ ሚኒስትሮች ምክር ቤት እየተባለ ሳይፀድቅም ሆነ ሳይተገበር ተቀምጦ ቀረ፡፡

‹‹የመሬት ለአራሹ›› ጥያቄ ተንከባሎ በስተመጨረሻ የ1967 ዓ.ም. አብዮትን ይዞ መጣ፡፡ አብዮቱ ደግሞ ‹‹አብዮት የፈነዳባቸውን ብቻ ሳይሆን አብዮት አፈንጂዎቹንም አጥረግርጎ የሚወስድ ሆነ፤›› ብለው ባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር) እንደጻፉት ሁሉ ከባድ የፖለቲካ ማዕበል ያስነሳ ጎርፍ ሆነ፡፡

ደርግ በቦታው ሲተካም የመሬት ለአራሹ ጥያቄ ሌላ መልክ ያዘ፡፡ አቶ አበባው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ሥር ነቀል ለውጥ ያስከተለውን ‹የገጠር መሬት አዋጅ› ለማፅደቅ የተቻለው የደርግ አመራሮች በቀጥታ ስለገቡበት እንደነበረ ይናገራሉ፡፡ አዋጁን ለማፅደቅ ብዙ ሙግትና ፍጭት ቢደረግም የደርግ ሰዎች ግን ደፈር ያለ ዕርምጃ በመውሰዳቸው ነበር ወደ መፅደቅ የገባው ሲሉ ታሪኩን ያወሳሉ፡፡

የገጠር መሬት አዋጅ የመሬት ለአራሹ ጥያቄ የመለሰ ተባለ፡፡ አዋጁ በፀደቀ በማግሥቱም ወደ 800 ሺሕ ሰዎች በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በመውጣት ከፍተኛ ድጋፋቸውን አሳዩ፡፡ የመሬት ለአራሹ ጥያቄን ብቻ ሳይሆን ባላገሩን ከዕዳና ከግብር ነፃ ያደረገ ነበር አዋጁ፡፡ ባላባትነትን እንዲሁም ፊውዳላዊ ሥርዓቱን በማስቀረት የሀብት ክፍፍል ላይም መሠረታዊ ለውጥ አመጣ በማለት አቶ አበባው ይናገራሉ፡፡

ይህ ትልቅ ለውጥ ያመጣ አዋጅ ግን በ1971 ዓ.ም. በተጀመረው የኅበረት ሥራ ማኅበራት ማቋቋም ፕሮጀክት ተመልሶ ተወሰደ ይላሉ ምሁሩ ሲቀጥሉ፡፡ ገበሬው በራሱ መሬት የፈለገውን ማምረትና ማግኘት አቃተው፡፡ በኅብረት ሥራ ማኅበር ስም መደራጀትና ምርትን መጋራት ግዴታ ሆነ፡፡ ምርታማነት አሽቆለቆለ ገበሬው በራሱ መሬት የሚያመርተውን መወሰን አቃተው፡፡

በ1981 ዓ.ም. ቅይጥ ኢኮኖሚ ሲታወጅ ደግሞ በገበሬ ማኅበርና በኅብረት ሥራ ማኅበራት ተደራጅ የተባለው ገበሬ ንብረት በመካፈል ሒደት ብዙ ቀውስ ያጋጥመው ጀመር ይላሉ አቶ አበባው ሲናገሩ፡፡ በአዋጅ የተሰጠው የመሬት ባለቤትነት በአሠራር ሒደት ግን ምላሽ አልባ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይህ ሁሉ አልፎ ኢሕአዴግ በደርግ እግርም ሲተካ መሬት የሕዝብ የሚሆንበት ዕድል ሳይመለስ እንደተንከባለለ መቅረቱን የታሪክ ምሁሩ ያስረዳሉ፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ የመሬት ባለቤትነት ያለው አካል የኢትዮጵያን ፖለቲካ የመዘወር የበላይነት አለው በሚል ዕሳቤ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በኢሕአዴግ ዘመን በታወጀውና አሁንም በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 40 ላይ የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ተደነገገ፡፡ በንዑስ አንቀጽ 3 ላይ የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው፣ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው ተብሎ ተቀምጧል፡፡ ንኙስ አንቀጽ 4 ላይ ደግሞ አርሶ አደሮች መሬት በነፃ የማግኘትና ከመሬታቸው ያለመነቀል መብታቸው የተከበረ ነው ተብሎ ተደነገገ፡፡

ኢሕአዴጎች ይህ ሕገ መንግሥታዊ አዋጅ ‹‹የሚሻሻለውም ሆነ የሚቀየረው በመቃብራችን ላይ ነው›› አስከሚሉ ድረስ ላለፉት 30 ዓመታት ንክች ሳይደረግ በሥራ ላይ ውሎ ዘለቀ፡፡ ድንጋጌው ሌላው ቀርቶ የደርግን የገጠር መሬት አዋጅ የቀለበሰና የመሬት ለአራሹ ጥያቄንም እጅግ ወደ ኋላ የመለሰ ነው ቢባልም ሰሚ አላገኘም፡፡ ኢሕአዴግ በመቃብሬ ላይ ያለለት ይህ ድንጋጌ ግን ዞሮ ዞሮ በተግባር ሲፈተንና በማሻሻያ ጥያቄ ሲወጠር ነበር የኖረው፡፡

ይህ የመሬት ድንጋጌ ማሻሻያ ጥያቄ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከፍተኛ ክርክርና ውዝግብ ሲያስነሳ ነው የዘለቀው፡፡ በተለይ የምርጫ ፉክክር ሲመጣ ጎልቶ የሚነሳው የመሬት ፖሊሲ ማሻሻል ጥያቄ፣ በመንግሥትና በተቃዋሚዎች ዘንድ የልዩነት መሠረት ሆኖ ነበር፡፡ ለረዥም ጊዜ መሬት አይሸጥም አይለወጥም ሲል የቆየው መንግሥት፣ አሁን አሁን ግን ራሱም በፖሊሲው ጉድለት መፈተን መጀመሩን ከመንግሥት ባለሥልጣናት የሚሰነዘሩ አስተያየቶች እየጠቆሙ ነው፡፡

በቅርቡ ፓርላማ ተገኝተው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) የመሬት ጉዳይ መንግሥታቸውን እንዳስመረረው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ በተለይ የከተማ መሬት ላይ አተኩረው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹መሬት የመንግሥትም የሕዝብም አይደለም የደላላ ነው፤›› ሲሉ መናገራቸው አስገራሚ ነበር፡፡

ለረዥም ጊዜ በዘርፉ ምሁራን፣ በተቃዋሚዎችና በታዛቢዎች መንግሥት መሬትን የብሔር ብሔረሰብ ነው ብሎ ባለቤት አልባ አድርጎታል የሚለውን ትችት  አሁን መንግሥት የተቀበለው ይመስላል፡፡

የመሬት ፖሊሲው የዜጎችን የመሬት ባለቤትነት የነፈገ ብቻ ሳይሆን፣ መሬት የሀብት ምንጭ እንዳይሆን አግቶ የያዘ ነው የሚለው ትችትን መንግሥትም እየተጋራው ያለ ይመስላል፡፡ መሬት አይሸጥም አይለወጥም እየተባለ በሕገወጥ መንገድ ይቸበቸባል፣ የምዝበራና ሌብነት ምንጭም እየሆነ ይገኛል የሚለውን ወቀሳ መንግሥት በራሱ ሰዓት የተቀበለው ይመስላል፡፡

ይህ ሁኔታ ደግሞ የመሬት ሥሪቱን ለመቀየር እንደ አንድ አመቺ አጋጣሚ እየተቆጠረ ነው፡፡ ለረዥም ዘመናት የፖለቲካ ትግል መሣሪያ፣ እንዲሁም የሥርዓት ለውጦች መነሻ ሆኖ የዘለቀው የመሬት ጥያቄ በምን መንገድ ቢሻሻል ይበጃል? በሚለው ላይ ደግሞ የተለያዩ ባለሙያዎች የተለያዩ ሐሳቦችን እያቀረቡ ነው፡፡

‹‹ዓብይ (ዶ/ር) ስለመሬት ፖሊሲ ቢያንስ በዛ ደረጃ ሲናገሩ ስሰማ ቆሜ ነው ያጨበጨብኩት፤›› የሚሉት የግብርና ኢኮኖሚ ምሁሩ ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር)፣ የመሬት ፖሊሲ ማሻሻል ጉዳይን ለረዥም ጊዜ ሲያጠኑና ምክረ ሐሳብ ሲሰጡ መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡

እንዲህ ዓይነት የፖሊሲ ማሻሻያ ጥያቄዎች ሊደረጉ ከተፈለገ ግን፣ ‹‹ፖሊሲ ከስትራቴጂ፣ ስትራቴጂ ከፕሮግራም፣ ፕሮግራም ከተቋማት ተለይቶ መታየት›› እንደሌለበትም ይመክራሉ፡፡ ‹‹በኢኮኖሚ ሦስቱ ፖለቲከኞችና ፖሊሲ›› በሚለው ጥናታዊ መጽሐፋቸው የመሬት ፖሊሲና ስትራቴጂ ልዩ ቦታ ተሰጥቶት ራሱን በቻለ ምዕራፍ መቀመጡን ደምስ (ዶ/ር) ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህ ምዕራፍ አሁን ያለው የመሬት ፖሊሲና አሠራር ጠንካራም ደካማ ጎኖቹ መፈተሻቸውን ያወሳሉ፡፡

‹‹መሬት በግልም፣ በመንግሥትም፣ በጋራና በወልም ባለቤትነቱ መያዙ በብዙ የዓለም አገሮች የተለመደ ውጤታማ አሠራር ነው፡፡ እኛ አገር ግን መሬት የግል መሆን አለበት የሚለው ከዚህ ውስጥ ተዘሏል፤›› በማለት ነው የፖሊሲውን መሠረታዊ ጉድለት ያሉትን ያስቀመጡት፡፡ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የከተማ መሬት አሠራር ላይ ቢያተኩሩም፣ ከማንም ፖለቲከኛ ደፈር ብለው በአደባባይ ስለመሬት ፖሊሲ መሻሻል በጥቂቱም መናገራቸው ትልቅ እመርታ ሆኖ እንዳገኙት አክለዋል፡፡

ከሦስት ዓመታት በፊት የግብርና ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ የነበሩት አንተነህ ግርማ (ዶ/ር)፣ በአሥር ዓመቱ አገር በቀል የኢኮኖሚ ዕቅድ የግብርና ልማት ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረው ነበር፡፡ ለዚህ ሲባል ስምንት የግብርና ዘርፍ ማነቆ ችግሮች ተለይተው መቅረባቸውንና የማሻሻያ ዕቅዶችም መነደፋቸውን አመልክተዋል፡፡ ለግብርና ዘርፍ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ሲያስቀምጡም የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ሥርዓቱ፣ ያልተቀናጀና ያልዘመነ መሆኑን እንደ ዋና ተግዳሮት አስቀምጠውታል፡፡

‹‹ለግብርና መዋል ያለበት መሬት ለሌላ አገልግሎት፣ ለሌላ አገልግሎት መዋል  የሚገባው ለግብርና እየዋለ›› አካባቢ ለጉዳት እየተዳረገ መሆኑን ያመለከቱት አንተነህ (ዶ/ር)፣ ይህ ደግሞ የመሬት አጠቃቀሙ ችግር መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በተበጣጠሰ መሬት ላይ በማረስ ዘርፉንም ሆነ አገር ማሳደግ እንደማይቻል ጠቁመው፣ ‹‹በዘርፉ የአስተሳሰብ፣ የሥርዓትና የአሠራር ለውጥ›› ማምጣት ይጠይቃል ብለዋል፡፡ የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ፖሊሲ ማሻሻያ ከማድረግ ባለፈም የመሬት አጠቃቀምን የሚመራ ተቋም መገንባትም ያስፈልጋል ብለው ነበር፡፡

አንተነህ (ዶ/ር) መንግሥት የመሬት መጠቀምና ማስተላለፍን በተመለከተ፣ እንዲሁም ኪራይና በውርስ ማስተላለፍን በተመለከተ ለውጦች እንደሚያስፈልግ እንደሚያምን ጠቅሰው ነበር፡፡ የአገሪቱ የተበጣጠሰ የእርሻ ልማትም ቴክኖሎጂ እንዲስብ የሕግና ፖሊሲ ማዕቀፍ ማሻሻያ በማድረግ የኩታ ገጠም እርሻ በሰፊው እንደሚሠራ ተናግረውም ነበር፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት ይኸው የኩታ ገጠም እርሻ ልማት በሰፊው መካሄድ ቀጥሏል፡፡ ነገር ግን የአሁኑ መንግሥት ዋና የትኩረት አቅጣጫ የሆነው ይህ የኩታ ገጠም እርሻ ልማትም ቢሆን፣ የመሬት ሥሪቱ ላይ መሠረታዊ ለውጦች እስካልተደረጉ ድረስ እንቅፋት እንደሚገጥመው የዘርፉ ባለሙያዎች እያሳሰቡ ነው፡፡

ኩታ ገጠም የተባለው የወቅቱ የእርሻ ልማት ሽፋን መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የመንግሥትና ሕዝብ ንብረት ነው ከሚለው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ጋር እየተጋጨ መሆኑን አንዳንድ ባለሙያዎች እያሳሰቡ ነው፡፡ እስካሁን ከ2.8 ሚሊዮን ሔክታር በላይ፣ እንዲሁም ከ3.8 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደር በኩታ ገጠም እርሻ ልማት መታቀፉ ይነገርለታል፡፡ እነዚህ በኩታ ገጠም የታቀፉ አርሶ አደሮች ቴክኖሎጂና ግብዓት እየቀረበላቸው ራሳቸውን እንደሚያሳድጉም ተቀምጧል፡፡ እያደጉ ሲሄዱ ደግሞ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ (ፒኤልሲ) በመመሥረት በግብርና ማቀነባበር ወደ ኢንዱስትሪ እንዲሸጋገሩ ነው ግብ የተቀመጠው፡፡ ይሁን እንጂ መሬታቸውን የካፒታል ምንጭ በማድረግ ራሳቸውን ማሳደግ እንዲችሉ የሚደግፍ የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ፣ የኩታ ገጠም እርሻ ልማት ማነቆ እንደሚያጋጥመው እየተናገሩ ያሉ ባለሙያዎች በርካታ ናቸው፡፡

ኢሕአዴግ ግብርና መር የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ (ADLI) መከተሉ ላይ ከአነሳሱ ብዙዎች የደገፉት ቢሆንም፣ በሒደት ግን ከመሬት ሥሪቱ ጋር ሲጋጭ ነው የታየው፡፡ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ሚዛነ ክርስቶስ ዮሐንስ ፖሊሲው ግብርናና ኢንዱስትሪ ወይም ገጠርና ከተማ ልማቶች እንዴት እንደሚተሳሰሩ ተገቢ በሆነ መንገድ ያላስቀመጠ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የእንስሳት ልማት፣ ደንና የተፈጥሮ ልማት፣ እንዲሁም ከግብርና ውጭ ባሉ ዘርፎች የተሰማራው ማኅበረሰብ በፖሊሲው ትኩረት እንደተነፈጋቸውም ያስረዳሉ፡፡

በከተማ ልማት በተለይም በኮንስትራክሽን ዘርፍ ብዙ ሀብት፣ ቴክኖሎጂና ዕውቀት እንደሚፈስ የጠቀሱት አቶ ሚዛነ ክርስቶስ ይህም የኮንስትራክሽን ዘርፉን በእጅጉ እንዳሳደገው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ግብርናንም ልክ እንደዚሁ ብዙ ዕውቀት፣ ሀብትና ቴክኖሎጂ እንዲስብ ማድረግና ማሳደግ ይቻላል፤›› ይላሉ፡፡ ይህ ደግሞ የሚሆነው መሬትን ዋና የሀብት ምንጭ በማድረግ ነው ሲሉ ያክላሉ፡፡

መሬት መሸጥና መለወጥ የማይቻል የመንግሥትና የሕዝብ ንብረት ነው የሚለው የመሬት ፖሊሲ፣ አሁን ካለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታና ዕድገት ጋር አብሮ እንደማይሄድ የሚተቹ ወገኖቸ በርካታ ናቸው፡፡ ራሱ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ የመሬት ሥሪቱ መሻሻል አለበት የሚሉ ድምፆች እየበረከቱ ነው፡፡

መሬት ለኢኮኖሚው ምን ማለት ነው? የሚለው ጥያቄ ቀድሞ ይነሳል፡፡ መሬትን ከፖለቲካ የሚያገናኘውስ ምንድነው? የሚለውም ጉዳይ ከፍ ብሎ ይመደጣል፡፡ ዛሬ  እንደቀደመው ጊዜ ‹መሬት ለአራሹ› ብሎ ለተቃውሞ አደባባይ የሚወጣ ባይኖርም፣ ነገር ግን መንግሥት የመሬት ባለቤትነትን ጠቅልሎ ገበሬውን የራሱ ፖለቲካ ጭሰኛ አድርጎታል የሚለው ክስ በተደጋጋሚ ይሰማል፡፡ መንግሥት መሬትን የፖለቲካ መሣሪያ በማድረጉ የተነሳም፣ አገሪቱ ብዙ ማደግ እየቻለች ነገር ግን ወደ ኋላ ቀርታለች የሚለው ትችትም በተደጋጋሚ ይሰማል፡፡

በመሬት ነክ ጉዳዮች ላይ ያጠኑት በፖለቲካና ኢኮኖሚ ተንታኝነታቸው የሚታወቁት አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን፣ ‹‹መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው ተብሎ በመደንገጉ ምን አተረፍን?›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹በፊትም ድህነትና ረሃብ ነበር፣ ዛሬም ከመሬቴ ውጣልኝ የሚል ዕልቂት ነው የተረፈን፤›› ሲሉም ምልከታቸውን ያጋራሉ፡፡

በዚህ ዙሪያ ብዙ ማጥናታቸውንና መፍትሔ ያሉትን ሐሳብ ያሰፈረ መጽሐፍ ያዘጋጁት አቶ ሸዋፈራሁ፣ በደርግ ዘመን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሥልጣን የነበሩትን አቶ ፋሲካ ሲደልልን ዋቢ በማድረግ ይበጃል የሚሉትን ሐሳብ ይናገራሉ፡፡

‹‹የዩጎዝላቪያ ባለሙያዎች፣ አቶ ፋሲካ ሲደልል እንደጻፉትም መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው ብላችሁ ባለቤት አልባ እንዳታደርጉት ብለው መክረው ነበር፡፡ ለባለሀብቱ ስጡትና ስትራቴጂካዊ በሆኑ ምርቶች ላይ አተኩሩ በማለት የዩጎዝላቪያን ተሞክሮ አጋርተው ነበር፡፡ ነገር ግን ደርግ የዩጎዝላቪያን ስህተት በመድገም መሬትን የሕዝብና የመንግሥት ብሎ ደነገገ፡፡ ኢሕአዴግም ይህንኑ አሠራር ደገመ፡፡ ነገር ግን መሬት ባለቤት አልባና ጥቅም አልባ ሆኖ ነው የኖረው፤›› በማለትም አቶ ሸዋፈራሁ ያስረዳሉ፡፡

በክልሎች ሕገ መንግሥቶች ላይ ደግሞ በባሰ ሁኔታ፣ ‹‹መሬት የእከሌ ብሔረሰብ ነው እየተባለ፣ አሳፋሪ በሆነ መንገድ በዓለም ላይ በሌለ ፖሊሲ እንዲመራ ተደርጓል፤›› የሚሉት አቶ ሸዋፈራሁ፣ ይህ ደግሞ አገሪቱን ለማበልፀግ የማይታሰብ እንደሚያደርገው ይናገራሉ፡፡

ስለመሬት ሥሪቱ ከ15 ዓመታት በላይ ያጠኑት ዳንኤል በኃይሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው ጉዳዩ ብዙ ጥናቶችና ለውጦች እንደሚፈልግ ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹አገሪቱ የምትመራበት የመሬት ፖሊሲ የላትም፡፡ በዚህ ጉዳይ ኃላፊነት የሚወስድ ተቋም የለም፡፡ ሦስተኛው ደግሞ የመሬት ጉዳይ ሕገ መንግሥታዊ ውዝግብ ያለው ነው፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡

የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ዛሬ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) የደላላ ነው ብለው እስኪናገሩ ድረስ ብዙ ታሪካዊ ዳራን ያሳለፈ ስሜታዊ የፖለቲካ ጉዳይ እንደሆነም ዳንኤል (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡ ‹‹የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ሚና ተለይቶ አለመቀመጡ ግርታን የሚፈጥር ነው፡፡ መሬት ለአራሹ የሚለው መጀመርያ ለምን መጣ? ከዚህ በኋላ ደግሞ የመንግሥት እንዴት ሆነ? ከዚያስ እንዴት የመንግሥትና የሕዝብ ተባለ? እውነት የመንግሥትና የሕዝብ ነውስ ወይ? ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደላላ ነው ያሉት ጠንከር ያለ ቢሆንም ነገር ግን ከእውነታው ብዙ የራቀ አይደለም፤›› የሚሉት ምሁሩ፣ መሬት በኢትዮጵያ በሕግም፣ በተቋምም ሆነ በአሠራር ብዙ የተሟላ ነገር እንደሌለው ነው ያስረዱት፡፡

የላንድ ፎር ኢትዮጵያ ተቋም የፕሮጀክትና ኮሙዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ ሙሉጌታ ጋዲሳም፣ ይህንኑ የሚያጠናክር አስተያየት ነው የሰጡት፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ አሠራሮችንና ተሞክሮዎችን በማጥናት የሚያቀርበው በመሬት ጉዳይ ላይ የሚሠራው ላንድ ፎር ኢትዮጵያ፣ ዘርፉ እንዲሻሻል ድጋፍ እንደሚያደርግም ይናገራሉ፡፡

‹‹መሬት ባለቤት የለውም፣ በኢትዮጵያ መሬትን በባለቤትነት የሚመራ ተቋም እንደሚያስፈልግ ሐሳብ እያቀረብን ነው፡፡ መሬትን የሚመራ ፖሊሲም አገሪቱ ያስፈልጋታል፡፡ በግብርና ሚኒስቴር ሥር የገጠር መሬት አስተዳደር ተብሎ ቢዋቀርም፣ ነገር ግን ዘርፉ ራሱን የቻለ ተቋም ያስፈልገዋል፡፡ በከተማ የመሬት ጉዳይን የኮንስትራክሽን ሚኒስቴርና የከተማ አስተዳደሩ ሲያዙበት ይታያል፡፡ ይህ ጥርት ባለ ተቋም ቢመራ ነው የምንለው፤›› ይላሉ፡፡

‹‹በአፍሪካ ኅብረት እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመሬት ባለቤትነትና አጠቃቀም ዙሪያ የተደነገጉ ማዕቀፎች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ የእነዚህ ድርጀቶች አባል አገር እንደ መሆኗ መጠን፣ እነዚህን ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች በቅጡ በመቀመር አገር አቀፍ ተስማሚ ሁኔታ በማዘጋጀት ወደ ተግባር እንድትገባ ነው ምክረ ሐሳብ የምናቀርበው፤›› ሲሉም አቶ ሙሉጌታ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -