ቱፍ – በል! ማሙሽ ቱ!
አለችው እናቱ
እሷው ናት አባቱ
ወንድምና እህቱ
ነፍስና አካላቱ፡፡
ማሙሽ ብቻ – ብቻውን
እያዩ መምጫ – መምጫውን
ያለምንም ከልካይ
ከጐጆው በራፍ ላይ
አፈር አድበልብሎ
ሲቅም እንደቆሎ….
እናት በችኮላ
እንስራዋን አዝላ
ልጄ! … ልጄን! … ብላ
አሳብራ መንገዷን
ዘንግታ ድካሟን
ስትደርስ ከደጃፉ
ሆኖ ስታገኘው አፈር ቅሞ ባፉ
ብድግ አ‘ረገችው
ቱፍ – በል!!! እያለችው፡፡
ጭቃ ባፉ ሞልቶ …
መላ – አካሉ ቦክቶ … ሆኖ ስላየችው፤
መታ አ‘ረገችው
ቱፍ – በል! እያለችው፡፡
እንባውን ስታየው
ቱ – በል! እያለችው
እየዳበሰችው
እያባበለችው
አቅፋ እየሳመችው
አዝላ እያስተኛችው
እሷም እንደማሙሽ ጭቃውን ቃመችው፡፡
- አሰፋ ጉያ ‹‹የከንፈር ወዳጅ››(1984)