Sunday, April 14, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የኢትዮጵያ ፈርጀ ብዙ የኢኮኖሚ ችግሮች ምክንያቶቻቸውና መፍትሔዎቻቸው (ክፍል ሁለት)

በአመሃ ዳኘው ተሰማ

በክፍል አንድ እንደተመለከተው ባለፉት ከሠላሳ ዓመታት በላይ ለሆነ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የገባው መጠኑ ከፍ ያለ የውጭ ብድርና ዕርዳታ በአቻነት ከፍተኛ የሆነ የአገር ውስጥ ገንዘብን በተከታታይ ማተምን በማስከተሉ፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለከፍተኛ የዋጋ ንረትና ተያያዥ ለሆነው የኑሮ ውድነት እንዲሁም፣ እየተስፋፋ ከሄደው ምዝበራ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ፍልሰትን በማስከተሉ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ለከፍተኛ መናጋት ተጋልጧል፡፡

የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የመዋዕለ ነዋይ ፍላጎት ክፍተት ለማሟላት በሕወሓትም ሆነ በኦሕዴድ/ብልፅግና የአገዛዝ ዘመን የውጭ ብድርንና በየጊዜው ገንዘብን በከፍተኛ መጠን ማተምን እንደ ዓይነተኛ መፍትሔ አድርገው መውሰዳቸው ይታወቃል፡፡ ችግሩ በከፍተኛ የውጭ ብድርና በከፍተኛ የአገር ውስጥ ገንዘብ ኅትመት ሊተገበሩ የታቀዱ ብዙዎቹ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ከነገድ ፖለቲካው ጋር በተያያዘና የኪራይ ሰብሳቢነትን መሠረት ላደረገ የነገድ ፖለቲከኞች አገራዊ ምዝበራ እንዲሁም፣ በሙያዊ የፕሮጀክት የአመራር ዕጦት ምክንያቶች ፕሮጀክቶቹ የሚጠናቀቁበት ደረጃ ላይ ደርሰው የወጣባቸውን የውጭ ዕዳና የአገር ውስጥ ብድር ለመመለስ ሳይችሉ፣ የብድር መክፈያ ጊዜያቸው መድረሱ፣ ኢኮኖሚውን በከፍተኛ የዕዳ ክፍያ ጫና ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎታል።

የኦሕዴድ/ብልፅግና መንግሥት የተኩስ አቁም ስምምነት ከመድረሱ በፊት ያልተሳካለትን አገሪቱ ያለባትን የውጭ ዕዳ የብድር ክፍያ ጊዜውና የአከፋፈሉ ሁኔታ እንዲታይለትና አስተያየት እንዲደረግለት ምዕራባውያን አበዳሪ አገሮችንና መሣሪያዎቻቸው የሆኑትን የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ድርጅቶች ተለማምጦ ያልተሳካለትን፣ አሁን ከስምምነቱ በኋላ አዎንታዊ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኝነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህ ሃቅ የሚያስረዳው ጭብጥ ምዕራባውያን ኃያላን አገሮች የፋይናንስ አቅማቸውን በመጠቀም  የብልፅግና መንግሥት በሕወሓት ላይ እየወሰደ ያለውን የተሳካ ወታደራዊ ዕርምጃ በአስቸኳይ ተኩስ አቁም ስም እንዲያቋርጥ ማድረግ መቻላቸውን ነው።

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ የአገራችንን ኢኮኖሚ ቀፍድደው የያዙ ችግሮች የላይ ላይ የገፅታ ምክንያቶች የብልፅግና መንግሥት እከተላለሁ የሚለው “የነፃ” ገበያ ፖሊሲዎች (Liberal Economic Polices) ሲሆኑ፣ እውነተኛ (Real) ምክንያቱ ግን ሕወሓትም ሆነ የኦሮሙማው የብልፅግና መንግሥታት አገርን ሳይሆን፣ ነገድን መሠረት በማድረግ የያዙትን የፖለቲካ ሥልጣን ለማጠናከር፣ የውጭ ብድርና ከፍተኛ የአገር ውስጥ የገንዘብ ኅትመት ዋንኛ መሣሪያዎቻቸው ሆነው በመገኘታቸው ነው፡፡ ለውጭ ምዕራባውያን የበለፀጉ አገሮች እንጂ ለሕዝቦቻቸው ተጠሪ ያልሆኑ እንደ እነዚህ ያሉ መንግሥታት የሕዝቦቻቸውን ጥቅም ሊያራምዱ ከሚችሉ በአገራዊ ብሔርተኝነት ላይ ከተመሠረቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ይልቅ፣ የሥልጣን ቆይታቸውን ሊያራዝሙ ይችላሉ ብለው በማሰብ፣ የበለፀጉ ምዕራባውያን አገሮች የሚጭኑባቸውን “የነፃ ገበያ” የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በፀጋ መቀበልን ስለሚመርጡ ነው፡፡

በመሠረቱ እንኳን አሁን የዓለም ኢኮኖሚ በጥቂት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በሞኖፖል ተይዞ በሚገኝበት ዓለም ቀርቶ፣ የካፒታሊስት ሥርዓት ገና እያቆጠቆጠ በነበረበት ዘመን ‹‹ነፃ ገበያ›› የሚባል ኢኮኖሚ ኑሮ አያውቅም፡፡ በሶሻሊዝም ላይ የካፒታሊስቱ ሥርዓት የበላይነትን ከተጎናፀፈ ከ1990ዎቹ የመጀመርያዎቹ ዓመታት ጀምሮም ሆነ የአፍሪካና የእስያ አገሮች ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጡባቸው ከ1950ዎቹና ስልሳዎቹ ዓመታት ጀምሮ ተግባራዊ የተደረጉ አገራዊ የኢኮኖሚ ሞዴሎች ደግሞ የገበያ ኢኮኖሚና የልማታዊ ኢኮኖሚ ሞዴሎች በመባል የሚታወቁ ናቸው፡፡

የምዕራቡ ዓለም የበለፀጉ አገሮችና በእነሱ የሚደገፉት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በአሁኑ ጊዜ በታዳጊ አገሮች ላይ በነፃ ገበያ ሞዴል (ሊበራል ኢኮኖሚ) ሽፋን፣ እነሱ የኢንዱስትሪ አብዮት ካደረጉበት ጊዜ ጀምሮ ያልተከተሉት የኢኮኖሚ ሞዴል ነው፡፡ ኢኮኖሚያችሁን ለውጭ ውድድር ክፈቱ፣ ‹‹የግሎባላይዜሽን›› ዓለም አቀፍ ሒደትን ተቀላቀሉ” እያሉ የሚወተውቱት፣ ታዳጊ አገሮችን የእነሱ ጥገኛ አድርገው ለማስቀረት ነው፡፡ እንደ ቻይና፣ ህንድና ደቡብ ኮሪያ ወዘተ. ያሉ በአገራዊ ብሔርተኝነት ላይ የተመሠረተ የልማታዊ ኢኮኖሚ ሞዴል የሚከተሉ አገሮች በአጭር ጊዜ ምዕራባውያን አገሮች የደረሱበት የልማት ደረጃ ላይ ያደረሳቸውን የልማታዊ የኢኮኖሚ ሞዴል የምዕራቡ ዓለም ማጥላላቱ ተወዳዳሪ ሊሆኑ የሚችሉ የአፍሪካ አገሮች ብቅ እንዲሉ ካለመፈለግ የመነጨ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

በዚህ ጽሑፍ በክፍል አንድ ለማቅረብ በተሞከሩት ትንተናዎች መሠረት በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አገራችን ያጋጠማት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር መንግሥት የሚከተላቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ውጤት መሆኑ አጨቃጫቂ አይደለም። የኦሕዴድ/ብልፅግና መንግሥት ለአገርና ለሕዝብ ጠቃሚ ያልሆኑ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ለመተውና ለሕዝብና ለአገር በሚጠቅሙ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ለመተካት የማይፈልገው ይህን ቢያደርግ፣ አገራዊ ሳይሆን የነገድ ድጋፍንና የምዕራባውንን የበጀት ድጎማና የኢንቨስትመንት ብድር መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ሥልጣኑ የቆመባቸውን ሁለት እግሮቹን እንደሚያጣ ስለሚቆጥረው ነው፡፡

ከዚህ ሁኔታ ጋር በተዛመደ መልኩ ሌላ ቁምነገር መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ምዕራባውያን የበለፀጉ አገሮች በተለይም አሜሪካ፣ ኢትዮጵያ እንድትበታተን ወይም ፖለቲካዋ እንዳይረጋጋ አይፈልጉም። አለመፈለጋቸው ከራሳቸው እስትራቴጅያዊ ጥቅም አንፃር አሥልተው ነው። ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር ቻይናና ሩሲያ እጃቸውን ወደ አፍሪካ ቀንድ አስረዝመው ያስገባሉ የሚል ሥጋት አላቸው። ጦርነቱ በአስቸኳይ በድርድር ይፈታ እያሉ በብልፅግና መንግሥት ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ ያሉትም ለዚህ ነው።  ለዚህም ነው በአሁኑ ጊዜ ሕወሓትና የኦሕዴድ/ብልፅግና ተቻችለው፣ በኢትዮጵያ አገራዊ ብሔርተኝነት ኪሳራ የነገድ ፖለቲካን አስፍነው ኢትዮጵያን አብረው እንዲገዙ፣ በመካከላቸው መጠፋፋት ሳይሆን ዕርቅ እንዲሰፍን፣ በብልፅግና መንግሥት ላይ የኢኮኖሚ ጫና፣ በሕወሓት ላይ ደግሞ የዕርዳታና ዲፕሎማሲያዊ ጫናና ተፅዕኖ በማድረግ ዕርቅ እንዲፈጥሩ ለማድረግ የቻሉት።

በጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩትን ወገኖች ሁሉ ሳያሳትፍ፣ በሕወሓትና በኦሕዴድ/ብልፅግና መካከል በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ ተደረገ የተባለው ስምምነት የትግራይ ታጣቂዎችን የቡድንና ቀላል መሣሪያዎቻቸውን የሚያስፈታና የክልሉን ልዩ ኃይል የሚበትን እንደሆነ ከሚዲያ ሪፖርቶች ለመገንዘብ ተችሏል። ከሕወሓት ተፈጥሮ አንፃር ይህ ዓይነት ስምምነት ላይ መደረሱ ሕወሓት የሽብርተኝነት ምድቡ ተነስቶለት፣ በሕጋዊነት ሽፋን ለመቀጠል የቀየሰው ሥልት ሊሆን እንደሚችል ቢገመትም፣ ለጊዜውም ቢሆን ጦርነቱ መቆሙ ዕውንና ዘለቄታዊ ከሆነ፣ በአገራችን ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ጫና እንደሚቀንስ ስለሚታመን፣ ከዚህ አንፃር በአዎንታዊ መልኩ መቀበል ይቻላል።

የመፍትሔ ሐሳቦች

ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአስከፊ የኑሮ ውድነት እየተለበለበና በከፍተኛ የከተማና የገጠር ሥራ አጥነት እየተቸገረ ይገኛል፡፡ ይህን አስከፊ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የብልፅግና መንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎቹ የተቀመሩበትን የፖለቲካ አመለካከት መቀየር ይኖርበታል። እንደሚታወቀው 50 በመቶ የሆነውን ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የሚያስገኘው፣ 83 በመቶ የሆነውን የወጭ ንግድ ምርት የሚያቀርበው፣ 80 በመቶ ለሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሥራ የፈጠረው የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ነው፡፡ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ምርትና ምርታማነት ሳይሻሻል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከመዋቅራዊ የኋላ ቀርነት አዙሪት ቀለበት ሊላቀቅ የሚችልበት ሁኔታ የለም፡፡ የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዳያድግ ጠፍሮ የያዘው ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ሕወሓትና የኦሮሙማው የኦሕዴድ/የብልፅግና መንግሥታት ሞተን እንገኛለን እንጂ አንቀይርም የሚሏቸውን መሬትን ለዜጋ ሳይሆን በቡድን መብት ስም ለነገድ የሰጠ፣ መንግሥትን ጂኦግራፊያዊ/አካባቢያዊ በሆነ መልክ ሳይሆን ቋንቋን ዋነኛ መመዘኛ ላደረገ አወቃቀር የዳረገ የፖለቲካ ፖሊሲን፣ ብሎም እነዚህ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች መዋቅራዊ ሆነው እንዲቀጥሉ ያስቻላቸውን ሕገ መንግሥት  መቀየር የግድ ይላል፡፡ የሕገ መንግሥቱ መቀየር ከሚያስከትለው የተመቻቸ የፖለቲካ መደላደል ውጪ አሁን በሕገ መንግሥቱ የፖለቲካ ቅኝት የተነደፉ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን መቅረፅም ሆነ ተግባራዊ ማድረግም አይቻልም፡፡

ከመሬት ፖሊሲው እንጀምር

በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላጋጠመው ከፍተኛ ቀውስና ለዋጋ ንረቱ መባባስ ቀደም ሲል ከተገለጹ ለአገርና ለሕዝብ የማይጠቅሙ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በተጨማሪ የመሬት አቅርቦትና በመሬት የመጠቀም መብት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መሄድ ዓይነተኛ ምክንያት ሊሆን በቅቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2013 የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማኅበር ባካሄደው ጥናት  96  በመቶ የነበረው መሬትን የማቅረብና በመሬት የመጠቀም መብት በ2021 ወደ 21 በመቶ ዝቅ ብሏል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግር ሊቀረፍ ያልቻለው፣ ለግብርናና ከግብርና ጋር ለተሳሰረው አግሮ – ኢንዱስትሪ ዘርፍ ዕድገት ወሳኝ የሆነው መሬትን በአግባቡ የመጠቀም መብት እየተሻሻለ ሳይሆን፣ እየዘቀጠ በመሄዱ፣ በኢኮኖሚው ላይ እያሳደረ ያለው ጫና በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት ነው። ይህም ሊሆን የቻለው ቀደም ሲል ሕወሓት አሁን ደግሞ የኦሕዴድ/የብልፅግና መንግሥት ከሚከተለው የነገድ ፖለቲካ አንፃር፣ መሬትን በአሁኑ ጊዜ ማግኘት የሚቻለው አንድም በሙስና አለበለዚያም ደግሞ በወረራ በመሆኑ ነው፡፡ ትልቁ የአገራችን ሀብት መሬት ሲሆን፣ መንግሥት ፖለቲካን መነሻ በማድረግ በሚከተለው የመሬት ፖሊሲ ምክንያት ይህ ትልቁ የአገራችን ሀብት ታንቆ እየመከነ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ መሬት ብቻ ሳይሆን በመሬቱ ላይ የሚገኘው ብዛት ያለው የሰው ጉልበት በተገቢው ሁኔታ ጥቅም ላይ ሳይውል፣ ኢኮኖሚው ለከፍተኛ ሥራ አጥነትና የተደበቀ ሥራ አጥነት (Disguised Unemployment)፣ ለከፍተኛ የዋጋ ንረት እየተጋለጠ መሆኑን የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ አባል የሆነበት የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር እንዲካሄዱ ያስደረጋቸው ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡

መሬት የኢኮኖሚ መሣሪያ ሳይሆን የፖለቲካ መሣሪያ እንዲሆን በመደረጉ፣ ሰፊ ምርታማ ሊሆን ይችል የነበረ የመሬት ሀብት እየባከነ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በሕወሓትና በብልፅግና ዘመን መሬትን የመሸጥ የመለወጥ መብት ለባለሥልጣናት እንጂ ለገበሬው የተሰጠ ባለመሆኑ፣ ባለሥልጣናት እየከበሩ ገበሬው የሚደኸይበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ዋጋ ከሆንግ ኮንግ፣ ከሲንጋፖር፣ ከሻንጋይ፣ ከኒውዮርክና ቶኪዮ ከተሞች የመሬት ዋጋ ጋር ተነፃፃሪ እንዲሆን ያደረገው በመሬትና በመሬት ነክ አገልግሎቶች ሙስናና ብልሹ አሠራር በመስፈኑ ነው፡፡ መሬትን በሊዝ ጨረታ የማቅረቡ ሒደት  በከተማው ውስጥ ያለውን የመሬት ፍላጎት ያላገናዘበ፣ በቁጥቁጥና በተራዘመ ጊዜ የሚካሄደው በጨረታ የሚሰጥ የመሬት አቅርቦትን በከተማው ካለው መሬትን የማልማት ፍላጎት በእጅጉ ያነሰ በመሆኑ፣ መሬት ደግሞ ለግብርናም ሆነ ለኢንዱስትሪ ምርቶች ለአገልግሎት ዘርፍ ዋንኛ ግብዓት በመሆኑ፣ መንግሥት የተከተለው የከተማ የመሬት ፖሊሲ ለአጠቃላዩ የዋጋ ንረት እየጨመረ መሄድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ጥናት ያመለክታል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ከመላው አፍሪካ አራሹ ገበሬ ለሚያርሰው መሬት ባለቤት ያልሆነባት ብቸኛዋ አገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ በኢትዮጵያ ሰማንያ በመቶ የሚሆነው በገጠር የሚኖረው ሕዝብ ሃያ በመቶ የሚሆነውን በከተማ የሚኖር ሕዝብ መቀለብ አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ በአገሪቱ ባለው የመሬት ፖሊሲ ምክንያት ለራሱ የሚሆን በቂ ምርት ለማምረት አልቻለም፡፡ በአንፃሩ የገበሬው የመሬት ባለቤትነት በተረጋገጠባቸው የዳበሩ አገሮች አምስት በመቶና ከዚያ በታች የሆነ በገጠር የሚኖር አራሽ 95 እና ከዚያ በላይ የሆነውን የከተማ ሕዝብ በበቂ ሁኔታ ይቀልባል፡፡ በኢትዮጵያ የመሬትን ፖሊሲ በመለወጥ ብቻ ረሃብና ዕርዛትን ብቻ ሳይሆን፣ የምግብ እጥረትን ከነአካቴው በማስወገድ  የኑሮ ውድነትን መቀነስ እንደሚቻል በርካታ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡

ለዚህ ተጨባጭ ምሳሌ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣ መስከረም 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው ዕትሙ ላይ ይህን ርዕስ በተመለከተ አንድ በገጠር ይኖሩ የነበሩ እናቱን ለመቅበር ከውጭ አገር የመጣ ዳያስፖራ ወደ ገጠር ሄዶ ያጋጠመውን ተሞክሮ በሚከተለው አኳኋን አትቶ አቅርቦታል፡፡ የእናቱን ለቅሶ ለመድረስ ወደ ገጠር የሄደው ሰው በሄደበት ጊዜ እህል ተሰብስቦ ያለቀበት ወቅት ስለነበረ፣ የእርሻ መሬቱ ሁላ ሳይታረስ ባዶ ሆኖ ይመለከታል፡፡ ከተመለከታቸው የእርሻ መሬቶች መካከል አንደኛው ከሌሎች እርሻ መሬቶች በተለየ ሁኔታ በመሀሉ አንድ አነስተኛ ምንጭ ያልፍበታል። ይህ ከውጭ የመጣ ሰው ለምንድነው የምንጩን ውኃ በመጠቀም የመሬቱ ባለቤት በበጋ ወቅት የተለያዩ ምርቶችን የማያመርተው? ብሎ ራሱን ይጠይቃል፡፡

ለጥያቄው መልስ ለማግኘት የነበረው ጉጉት ዘመዶቹ የመሬቱ ባለቤት ቤት  እንዲወስዱት እንዲጠይቅ ይገፋፋዋል፡፡ የመሬቱ ባለቤት (ይቅርታ ትክክል የሚሆነው ተገልጋይ ቢባል ነው) ቤት ደርሶ ሰላምታ ከተለዋወጠ በኋላ አባወራውን ሊጠይቅ የፈለገውን ጥያቄ ያነሳባቸዋል፡፡ መሬቱን ሰንጥቆ በሚያቋርጠው ምንጭ በመጠቀም በበጋ ቢያንስ ሁለት ጊዜ ለምን ማምረት እንዳልቻሉ ይጠይቃቸዋል፡፡ የገበሬው አባወራ ጥያቄው ከፈረንጅ አገር የእናቱን ሐዘን ለመድረስ የመጣ መሆኑን በመገንዘብ ‹‹አየህ ልጄ አንተ እንዳልከው ይህን የያዝኩትን መሬት አቋርጦ የሚያልፈውን የምንጭ ውኃ ተጠቅሜ በበጋ የተለያዩ ምርቶች ባመርት፣ የወረዳው ኃላፊዎች (የገዥ ፓርቲ ካድሬዎች) በመስኖ የምታለማ ከሆነ ይህ ሁሉ መሬት ላንተ ይበዛብሃል ብለው መሬቱን ቆርሰው ይወስዱብኛል፡፡ በመሆኑም ክረምት ሲመጣ ብቻ ነው ጠብቄ የማርሰው፤›› ብለው ይመልሱለታል፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አገር መገንጠልን በመብትነት ሲፈቅድ መሬትን የሚያርስ ገበሬ ምርታማነቱን ሁለትና ሦስት እጥፍ በመጨመር ራሱን ጠቅሞ አገሩን አንዳያለማ፣ ላቡን አንጠፍጥፎ  በሚያርሰው መሬት ላይ የተሟላ የባለቤትነት መብት እንዳይኖረው አድርጎታል፡፡ ከደርግ ጊዜ ጀምሮ በተለይም ደግሞ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት  “የነፃ ገብያ ፖሊሲ” እንከተላለን በሚሉት በሕወሓትና በብልፅግና የአገዛዝ ዘመኖች፣ ገዥ ፓርቲዎቹ በሚያራምዱት የመሬት ፖሊሲ ምክንያት ገበሬዎች የሚያርሱትን መሬት አቅማቸውና የመሬቱ ለምነት በሚፈቅደው መጠን የእርሻ መሬታቸውን አልምተው፣ ራሳቸውንም ሆነ አገራቸውን እንዳይጠቅሙ የተሟላ የመሬት ባለቤትነት መብት አለመከበሩ የመሬት ምርትና ምርታማነት እንዳይጨምር ዋንኛ ደንቃራ መሆኑ በግልጽ ሊታወቅ ይገባል፡፡

የሕወሓትም ሆነ የብልፅግና ፓርቲ መሬትን ለብሔረሰብ እንጂ የግል ገበሬ ይዞታ እንዲሆን አንፈቅድም የሚሉበት ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ነው፡፡ የመሬት ባለቤት የሆኑት የክልል መንግሥታት ጢሰኛ ሆኖ ለሚገኘው ገበሬ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር የሚያቀርቡት የፓርቲ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ምርጫ ሊደርስ አካባቢ መሬትን እናከፋፍላለን ብለው የሚነሱት ቀደም ሲል የሕወሓት አሁን ደግሞ የብልፅግና የወረዳና ቀበሌ አስተዳዳሪዎች/ካድሬዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የወረዳ ካድሬዎች ገዥ ፓርቲውን ካልመረጥህ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር አታገኝም፣ መሬቱንም በገጠር ከሚገኘው ከፍተኛ የሥራ አጥነት ቁጥር አንፃር እናሸጋሽጋለን በሚል የሚነሱት ምርጫ ሊደርስ አካባቢ ስለሆነ፣ የነገድ ፖለቲካን መመርያው አርጎ ለሚከተል ገዥ ፓርቲ መሬት የፖለቲካ እንጂ የኢኮኖሚ መሣሪያ ሊሆን አይችልም።

ከዚህም በተጨማሪ መሬት ለነገድ ተከልሎ መሰጠቱ በአሁኑ ጊዜ በስፋት እንደሚስተዋለው ለግድያና ለዘር ማጥፋት እንዲሁም፣ ለተለያየ ዓይነት በሰብዓዊነት ላይ ለሚፈጸም ጥቃት ዋንኛ መንስዔ መሆኑ በገሃድ እየታየ ነው፡፡ የነገድ ፖለቲካ አራማጅ ፖለቲከኞች የኢትዮጵያ ሕዝብን መሬት በቋንቋ ለሚዛመዷቸው ብቻ በመደልደል፣ በየክልሉ ለዘመናት በሰላም አብረው ሲኖሩ የቆዩ ሌሎች ማኅበረሰቦችን በማፅዳት፣ የፖለቲካ ድጋፍ የሚሸምቱበትና የሥልጣን ዘመናቸውን የሚያራዝሙበት የፖለቲካ ሥልት በአገራችን ግጭት፣ ጦርነትና የዘር ማፅዳት ዘመቻዎች እንዲከናወኑ በግልጽ የሚታይ ምክንያት መሆኑን መካድ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማንነትን መሠረት ካደረገና መዋቅራዊ ከሆነ የኋላ ቀርነት አዙሪት ቀለበት (Poverty Cycle) ለማላቀቅ፣ በወል ከተያዙ የከብት አርቢ ይዞታዎች ውጭ ያለው የሚታረስ መሬት የግለሰብ ዜጋ መብት ሆኖ መሬትን የማልማት የማከራየት፣ የመሸጥና የመለወጥ ውሳኔ የገበሬውና የገበሬው ውሳኔ ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የግብርና ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግና የዋጋ ንረትን ለመከላከል ብሎም የኑሮ ውድነትን ለማቅለል የሚቻለው የኢትዮጵያ የመሬት ፖሊሲ ሲለወጥ ብቻ ነው፡፡

የነዳጅ ዋጋ አተማመንና የነዳጅ ድጎማን ማስቀረትን በተመለከተ

የኑሮ ውድነትን በከፍተኛ ደረጃ በማባባስ ላይ የሚገኘው ሌላው ምክንያት መንግሥት ድጎማን በማስቀረት የነዳጅ ዋጋ በየጊዜው እንዲጨምር የማድረጉ የፖሊሲ አቅጣጫ ነው፡፡ የኢኮኖሚ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የማምረቻና የማከፋፈያ ወጭን በመጨመር የዋጋ ንረትን በማባባስ የኑሮ ውድነት በተፋጠነና ቀጥተኛ በሆነ ሁኔታ እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑን ያመለክታል፡፡ መንግሥት የበጀት ጉድለቱን ገንዘብ በማተም የሚያካክስ እስከሆነ ድረስ፣ የነዳጅ ድጎማን  ከማንሳት ቢቆጠብ የተሻለ እንደሚሆን አንዳንድ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

የነዳጅ ድጎማን በማስቀረት የሕዝቡ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ከማድረግ ይልቅ፣ በነዳጅ ግዥ አቅርቦትና ነዳጅን በማከፋፈል ረገድ ከነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ጀምሮ አሁን ወደ አርባ የተጠጉ ዋና ዋና የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎችን የትርፍ ህዳግ መርምሮ ማስተካከያ ማድረጉ፣ የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋን ጭማሪ ተመርኩዞ እየተከሰተ ያለውን የኑሮ ውድነት ለማስታገስ ይቻላል የሚሉ ከዘርፉ ባለሙያዎች በተገኙ መረጃዎች ላይ የተመረኮዙ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ይሰማል፡፡ በዘርፉ ላይ ጥናት ያካሄዱ ባለሙያዎች ተገዝቶ ወደ አገር ለገባው ነዳጅ በተገቢው ሁኔታ አለመሠራጨት በኢትዮጵያ ያሉ የነዳጅ ማደያዎች ቁጥር አነስተኛ መሆን በምክንያትነት ይነሳል፡፡ አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር ካላቸው ኬንያ (1‚900 ማደያዎች) እና ኡጋንዳ (2‚900 ማደያዎች) ጋር ሲነፃፀር 120 ሚሊዮን ሕዝብ ባለበት አገራችን ያሉት የነዳጅ ማደያዎች 1,200 ብቻ መሆናቸውና የእነዚህም ጂኦግራፊያዊ ሥርጭት በተለይ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በጣም በተራራቀ ቦታ መሆኑ፣ ነዳጅ ለኮንትሮባንድ ንግድ እንዲጋለጥ ያደረገ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል፡፡ አብዛኞቹ የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ዴፖዎች የሌሏቸው መሆኑ ለኮንትሮባንድ ንግድ ሌላው ምክንያት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከተቆጣጣሪው መሥሪያ ቤት የቁጥጥር መላላት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በነዳጅ ግዥ፣ ክፍፍልና ሥርጭት ሒደት የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት በሊትር 0.25 ሳንቲም የትርፍ ህዳግ እንዲኖረው ሲደረግ፣ የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች በሊትር 19 ሳንቲም፣ ቸርቻሪዎቹ የነዳጅ ማደያዎች በሊትር የ23 ሳንቲም የትርፍ ህዳግ እንዲይዙ መደረጉ ይታወቃል፡፡

ለነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ከኩባንያ የትርፍ ህዳግ (Company Profit Margin) በተጨማሪ ለወጭ መሸፈኛ (Cost Recovery) በሚል መልክ የተመደበ፣ በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያደርግ ህዳግ እንዳለ የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት ከቤንዚን የ22 ሳንቲም ትርፍ ሲወስድ፣ የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ከቤንዚን የ42 ሳንቲም፣ ከነጭ ጋዝ 38 ሳንቲም፣ ከናፍጣ 38 ሳንቲም ማርጅን አላቸው፡፡ ይህ ህዳግ አከፋፋይ ኩባንያዎች በወጪ መሸፈኛ መልክ ከሚያገኙት በሊትር 0.42 ሳንቲም በተጨማሪ የሚሰጥ የኩባንያ የትርፍ ህዳግ ነው፡፡ ይህ የዋጋ ቀመር የነዳጅ ዋጋ መጠን እየጨመረ እንዲሄድ በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ፣ በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ካለው የኑሮ ጫና አንፃር ተገምግሞ በከፍተኛ ደረጃ ሊስተካከል ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ከአከፋፋዮችና ከቸርቻሪዎች የበለጠ የትርፍ ህዳግ እንዲይዝ መደረጉም  አግባብ አይደለም፡፡ መንግሥታዊ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ የገንዘብ ማስገኛ (ዕንቁላል ጣይ ዶሮ) ድርጅት እንዲሆን ከመፈለግ አንፃር ታይቶ ከሆነም፣ በሕዝብ ላይ እያሳደረ ያለውን የኑሮ ጫና ከግምት ውስጥ በማስገባት አሠራርን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ የነዳጅ ድርጅት የነዳጅ ዋጋን የማረጋጋት ተልዕኮ የተሰጠው የልማት ድርጅት ሆኖ እያለ፣ ከግል የነዳጅ ማደያዎች በላይ እንዲያተርፍ መደረጉ ከኅብረተሰቡ ጉሮሮ በመንጠቅ የኑሮ ውድነትን የሚያባብስ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሕወሓት ዘመን የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዓለም አቀፍ የነዳጅ ግዥ ጨረታ አውጥቶ የገዛበትን ዋጋ ብሔራዊ ባንክ ቢያውቀውም ይፋ የማድረግ አሠራር ባለመከተሉ፣ ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ሽሽት የተጋለጠ እንደነበር ይደመጥ ነበር፡፡ ያ ዓይነት አሠራር በኦሕዴድ/ብልፅግና መንግሥት ዘመን መቀጠል አለመቀጠሉ ሊፈተሽ ይገባል።

የኢንዱስትሪው ባለሙያዎች እንደሚጠቁሙት የነዳጅ ወጪን መቀነስ ብቻ ሳይሆን ከድፍድፍ ዘይት ነዳጅን በማጣራት ሒደት የሚገኙ ተዛማጅ የሆኑ እንደ ተሽከርካሪ ሞተር ዘይት፣ የሞተር ቅባቶች እንዲሁም ሬንጅን የመሳሰሉ ተረፈ ምርቶችን በቀነሰ ዋጋ ለማቅረብ በአገር ውስጥ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ መገንባት አስፈላጊነቱ በዘርፉ ባለሙያዎች የታመነበት ነው፡፡

የብልፅግና መንግሥት እስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ የፖሊሲ ዕይታ ቢኖረው ለከተማ ውበት የገጽታ ግንባታ እንዲሁም ለቢሮዎች ዕድሳት የሚያወጣውን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለነዳጅ ማጣሪያ ግንባታ ቅድሚያ በመስጠት ቢያውለው፣ የኑሮ ውድነትን ከማቅለል በተጨማሪ ነዳጅን በተመለከተ ድንገተኛና ያልታሰቡ አደጋዎች ቢያጋጥሙ፣ ለተወሰነ ጊዜ ችግርን ለመቋቋም ይረዳ ነበር፡፡

የነዳጅ ዋጋን ተከታታይ ጭማሪ ተከትሎ በሕዝቡ ላይ እየከበደ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማቅለል የመፍትሔ ሐሳብ ማቅረብን በተመለከተ ለዘለቄታው የውኃ፣ የንፋስ፣ የፀሐይና የመሬት ውስጥ እንፋሎት (ጂኦተርማል) የኃይል ምንጭ አማራጮች ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራቱ አስፈላጊ ነው። የአጭር ጊዜ መፍትሔዎችን በተመለከተ ግን ነዳጅን በአገር ውስጥ ፈልጎ ከማግኘት በተጨማሪ፣ በኢትዮጵያ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ማቋቋም፣ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የመሸጫ ዋጋ ህዳግን፣ እንዲሁም አከፋፋይ ኩባንያዎች የተመደበላቸውን ሁለት ዓይነት የዋጋ ህዳግ ቀንሶ ወደ አንድ ዓይነት ማውረድን ማጠቃለል ይኖርበታል፡፡

እነዚህን ሁለቱን ማለትም የኩባንያ የትርፍ ህዳግና የኩባንያ ወጪ ማካካሻን ህዳግ ለነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች መስጠት አግባብ አይደለም። ከሁለቱ አንዱን በመተው የሚገኘውን ቅናሽ ለነዳጅ ማደያ ባለቤቶች እንዲጨመር ማድረግ ያስፈልጋል። ለነዳጅ ማደያ ባለቤቶች በጭማሪነት የሚመደብላቸውም የትርፍ ህዳግ ተጨማሪ ነዳጅ ማደያዎች እንዲከፈቱ የሚያበረታታ ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚህ የሚተርፈው የትርፍ ህዳግ ወደ ድጎማ ፈንድ ተመላሽ እንዲሆን ተደርጎ፣ ፈንዱ እንዲጠራቀምና ድጎማ የማንሳቱ ሁኔታ በተቀራረበ ጊዜና በአንድ ጊዜ በከፍተኛ መጠን እንዳይሆን ቢደረግ፣ ነዳጅ በዋጋ ንረት ላይ የሚያሳድረውን ከባድ ተፅዕኖ ያስታግሳል፡፡ በተጨማሪም የነዳጅ ሥርጭትን በማስተካከል የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው እንዲበረታታ ስለሚያደርግ የኑሮ ውድነትን ለማቅለል ይረዳል፡፡

የብሔራዊ ባንክ አሠራርን በተመለከተ

የዳበረ ኢኮኖሚ ባላቸው አገሮች የየአገሮቹ ብሔራዊ ባንኮች በአደረጃጀትም ሆነ የፋይናንስ ፖሊሲን በማውጣትና በማስፈጸም ረገድ ከአስፈጻሚው መንግሥታዊ አካል የአሠራርም ሆነ የፖሊሲ ነፃነታቸው ሊደፈር በማይችልበት ሕጋዊ ማዕቀፍ ሥር የተቋቋሙና የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ የበለፀገ ኢኮኖሚ ባላቸው አገሮች ከአስፈጻሚው የመንግሥታዊ አካል ይልቅ በሚከተሉት የፋይናንስ ፖሊሲ አማካይነት ቁልፍ የሆነውን ኢኮኖሚን የማነቃቃትና ዋጋን የማረጋጋት ሚና የሚጫወቱት ብሔራዊ ባንኮች ናቸው፡፡ በእነዚህ አገሮች የፋይናንስ ፖሊሲዎችን የማውጣትና የመቆጣጠር ኃላፊነታቸውን የአገር መሪዎች ሳይቀሩ ሊዳፈሩና ጣልቃ ሊገቡባቸው አይችሉም፡፡

የገበያ ኢኮኖሚን በተከተሉ አገሮች ብሔራዊ ባንኮች የገንዘብ አቅርቦትንም ሆነ የወለድ ምጣኔን በመወሰን ረገድ ብቸኛ ባለቤት በመሆናቸው፣ ተልዕኮአቸውን በመወጣት ረገድ ጣልቃ የሚገባባቸው ባለመኖሩ፣ የገንዘብ አቅርቦትንና የወለድ ምጣኔን በመወሰን ኃላፊነታቸው ዋጋን ከማረጋጋት ጀምሮ የኢንቨስትመንት ካፒታል እንዲበረታታ በማድረግ፣ የሥራ አጥነት ሊቀንስ የሚችልባቸውን ፖሊሲዎች አፍላቂዎች በመሆናቸው፣ ብሔራዊ ባንኮች የየአገሩን ኢኮኖሚ በማነቃቃትና በማረጋጋት ረገድ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ ናቸው፡፡ ይህን የሚያደርጉትም የፖለቲካ ገጽታን ከግምት ውስጥ በማስገባት በሚፈበረኩ ኢኮኖሚ ነክ መረጃዎች ሳይሆን፣ እውነትን መሠረት አድርገው በሚነሱና ተጨባጭ በሆኑ የአገራዊ ኢኮኖሚ መረጃዎች ጥናትና ትንተና ላይ ተመርኩዘው ነው፡፡

በንጉሠ ነገሥቱም ሆነ በደርግ ዘመን እንደ ሕወሓት/ኢሕአዴግ በተለይም ደግሞ እንደ አሁኑ የኦሕዴድ/ብልፅግና ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ ከፍተኛ በሆነ የዋጋ ንረት ምክንያት ታይቶ ለማይታወቅ የኑሮ መጎሳቆል አልተዳረገም ነበር። በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ብሔራዊ ባንኩ የገንዘብ አቅርቦትንና (Money Supply) የወለድ ምጣኔን (Interest Rate) መጠን መወሰንን በተመለከተ ጣልቃ የሚገባበት የበላይ አካል ባለመኖሩ፣ እነዚያ መንግሥታት ይከተሉ የነበሩት የፋይናንስ ፖሊሲም ወግ አጥባቂ ስለነበር፣ የብድር አስተዳደሩም ከሙስና የፀዳ ስለነበር፣ የዋጋ ንረት የሚታወቅ አልነበረም። በደርግ ዘመንም ቢሆን ገንዘብ ሚኒስቴር በሚሾማቸው የቦርድ አባላቱ አማካይነት መንግሥት በብሔራዊ ባንክ ላይ የተወሰነ ተፅዕኖ ቢኖረውም፣ ደርግ ይከተል ከነበረው ሁሉንም የኢኮኖሚ ተቋሞች በሥሩ ያደረገ የሶሺያሊዝም የኢኮኖሚ ፍልስፍና አንፃር መንግሥት ከግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ጋር በሙስና የመተሳሰር አጋጣሚ አልነበረውም።

በደርግ ዘመን የአገሪቱ ብሔራዊ ባንክ እንደአሁኑ ዘመን ቀልቡን የተገፈፈና በመንግሥት የገንዘብ አታሚነት ሚና ላይ ያተኮረ ስላልነበረ፣ ይከተል የነበረው የፋይናንስ ፖሊሲም ከመንግሥት አንፃራዊ የሆነ ነፃነት ነበረው። ስለሆነም በደርግም ዘመን በተለይ በመጨረሻዎቹ አሥር ዓመታት (ከ1972 እስከ 1982) ይካሄድ የነበረው የእርስ በርስ ጦርነት እየተባባሰ በመጣበትና የመከላከያ ወጪ ከመንግሥት ገቢ አንፃር ሰማይ ነካ በተባለባቸው ዓመታት እንኳ፣ የዋጋ ንረቱ በአማካይ ከ5.2 በመቶ በላይ ሆኖ አያውቅም ነበር። በመሆኑም አንደአሁኑ የብልፅግና ዘመን የዋጋ ንረቱ ከ40 በመቶ በላይ ደርሶ ሕዝብን ያስጨነቀና የሕዝብ የቀን ተቀን መወያያ ርዕስ አልነበረም።

በአገራችን ብሔራዊ ባንክ የአደረጃጀትና የፋይናንስ ፖሊስ አመንጭነቱን በአስፈጻሚው መንግሥታዊ አካል የተነጠቀ፣ የአሠራር ነፃነቱን የተገፈፈ፣ የመንግሥት የገንዘብ አታሚ ድርጅት ከመሆን ያልዘለለ ተቋም መሆኑ፣ ሌላው ኢኮኖሚው አሁን የደረሰበት አዘቅት ውስጥ እንዲወድቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ምክንያት ነው፡፡ ኢኮኖሚው ወደ ተሃድሶ ጎዳና እንዲያመራ ከተፈለገ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአደረጃጀት፣ የአሠራርና የፋይናንስ ፖሊሲ አመንጭነትና አስፈጻሚነት ሙሉ ነፃነት እንዲከበር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የአገራችንን ኢኮኖሚ አሁን ከገባበት አዘቅት ውስጥ እንዲወጣ የተመቻቸ ሁኔታ ለመፍጠር አይቻልም።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውንና የፓርቲያቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles