Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

ቀን:

ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት ማሠራት ቅንጦት ከመሰለ ሰነባብቷል፡፡ ከዕድሳትና ከግንባታ ፈቃድ ጀምሮ ያለው የተቋማት ቢሮክራሲ ዜጎችን አንገሽግሿል፡፡ በተለይም ሰዎች የገዛ ቤታቸውንና የግቢ አጥራቸውን ለማደስ ከቀበሌ ፈቃድ ማግኘት ጀምሮ ሲፈተኑ ይታያል፡፡

የግንባታና የማደስ ፈቃድ ቢገኝም በግለሰብ ደረጃ ሲሚንቶ በገበያ ላይ ማግኘት ሌላ ጭንቀት ሆኗል፡፡ በሰሚ ሰሚ ‹‹ሲሚንቶ እከሌ ማከፋፈያ (ሱቅ) ይገኛል›› እየተባለ የደላላ መጫወቻ የሆኑ ዜጎች ምሬታቸውን በተለያዩ ጊዜያት ሲገልጹ ተስተውሏል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ሲሚንቶን ገበያ ላይ እግር እስኪቀጥን ሲጓዙ ቢውሉ ማግኘት የሚከብድ ቢሆንም፣ ለአንዳንዶቹ ደግሞ አስማት በሚመስል በእጃቸው ሲያስገቡ ይታያል፡፡ በተለይ ዘርፉ ላይ ደላሎች መብዛታቸው የሲሚንቶ ፈላጊዎችን አቅም ፈትኗል፡፡

- Advertisement -

ችግሩ አቅማቸውን ከፈተነው መካከል አቶ ይበልጣል ወንደወሰን ይገኙበታል፡፡ አቶ ይበልጣል የመኖሪያ ግቢ አጥራቸው ፈርሶ እንደ አዲስ ለመገንባት ከቀበሌ ፈቃድ ቢያገኙም፣ ሲሚንቶ ባለማግኘታቸው የተነሳ አጥራቸውን ሳያድሱ መቅረታቸውን አስረድተዋል፡፡

በተለያየ ጊዜ ወደ ሲሚንቶ ማከፋፈያ ሱቆች ሄደው ሲጠይቁም ሲሚንቶ አለማግኘታቸውን፣ በአሁኑ ወቅትም የቤታቸው አጥር እንጥልጥል ላይ መቅረቱን ገልጸዋል፡፡

ለቤታቸው አጥር ግንባታ የሚውል ሲሚንቶ አራት ኩንታል ብቻ እንደሚፈልጉ፣ ነገር ግን ሳያገኙ በመቅረታቸው የተነሳ ፈቃዳቸው ሊቃጠል እንደሚችልም አብራርተዋል፡፡ አብዛኛውን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች በዚህ የተነሳ ፈተና ውስጥ እያለፉ መሆኑን እሳቸውም የዚህ ችግር ገፈት ቀማሽ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

ከአጥር ግንባታ በዘለለም በቅርቡ የመፀዳጃ ቤታቸው መፈንዳቱን፣ የፈነዳውን የመፀዳጃ ቤት ለመገንባት ሲሚንቶ እንደሚፈልጉና ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ እንደሆነባቸው ይገልጻሉ፡፡

መንግሥት ሲሚንቶን በየማከፋፈያው በማሠራጨት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሰዎች መፍትሔ ማስቀመጥ ይኖርበታል የሚሉት አቶ ይበልጣል፣ ይህ ካልሆነ አዲስ ቤት ለመገንባት ቀርቶ በእንዲህ ዓይነት ችግር ውስጥ የወደቁ ወገኖች የዕለት ከዕለት ምሬት ሳይፈታ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በዚህ ችግር እየተፈተኑ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን፣ ከእሳቸው በተጨማሪም ጎረቤቶቻቸው ትንንሽ ዕድሳቶችን ለመፈጸም ቢፈልጉም፣ ሲሚንቶ ሳያገኙ መቅረታቸውን አስረድተዋል፡፡

በተለይ የመኖሪያ ቤቶቻቸው በላያቸው ላይ ወድቆ የሚኖሩ ሰዎች መኖራቸውን፣ እነዚህም ሰዎች ቤቶቻቸውን ለማደስ ላይና ታች ቢሉም ሲሚንቶ አለማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

የዮሴፍ ዘላቂ ማረፊያ የቀብር ማስፈጸም ማኅበር ሰብሳቢ አቶ ኃይሉ ሰለሞን ለሪፖርተር እንደገለጹትም በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ላይ የቀብር ሥርዓት የሚያስፈጽሙ ማኅበሮች የሲሚንቶ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወደደባቸው በመምጣቱ ቀብር ሥርዓት ለመፈጸም ችግር ውስጥ ወድቀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም አንዱ ኩንታል ሲሚንቶ 900 ብር በነበረ ሰዓት ለአጠቃላይ የቀብር ሥነ ሥርዓት 3,470 ብር እንዲያስከፍሉ መንግሥት የራሱ የሆነ መመርያ እንዳወጣላቸው፣ ነገር ግን አሁን ላይ ሲሚንቶ ዋጋ በመጨመሩ የተነሳ ችግር ውስጥ መወደቃቸውን አቶ ኃይሉ አብራርተዋል፡፡

በየጊዜው የሲሚንቶ ዋጋ መጨመር ብቻ ሳይሆን አቅርቦት ላይ ትልቅ ችግር መኖሩን፣ በዚህም የተነሳ የሐውልት ሥራ ማቆማቸውንና ሲሚንቶ ለሚያመጡ ሰዎች ብቻ የእጅ በማስከፈል አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡

ለቀብር ሥርዓት የሚሆን ሲሚንቶ አንዳንዴ የሚያጡበት ጊዜ እንዳለ፣ በአሁኑ ወቅትም በደላላ አማካይነት ሲሚንቶ እያገኙ አገልግሎት እንደሚሰጡ አስረድተዋል፡፡

ሲሚንቶ በቀጥታ ለቀብር አስፈጻሚ ማኅበሮች እንዲሰጥ ለንፋስ ስክል ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለወረዳ 08 ጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም ለአረንጓዴ ልማት ተፋሰስ ጥያቄ ማቅረባቸውን፣ ነገር ግን ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳልተሰጣቸው አቶ ኃይሉ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

በዮሴፍ ዘላቂ ማረፊያ የቀብር ሥነ ሥርዓት የሚፈጸሙ ማኅበሮች ሰባት መሆናቸውን፣ ማኅበሮቹም ለመንግሥት ጥያቄ ማቅረባቸውንና ሲሚንቶ ተደራሽ እንዲሆን በር ማንኳኳታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን በቀን ቢያንስ የሦስት ሰዎች ሥርዓተ ቀብር ሥርዓት እንደሚፈጸም፣ ይህንንም ተፈጻሚ ለማድረግ ሦስት ከረጢት ሲሚንቶ እንደሚያስፈል ጠቁመዋል፡፡

የቀብር ሥርዓት የሚቆምና እንደ ሌሎች ግንባታዎች የሚቋረጥ ባለመሆኑ፣ መንግሥት የሲሚንቶ አቅርቦትን ችግርን መቅረፍ ይኖርበታል የሚሉት አቶ ኃይሉ፣ ይህ ችግር ካልተቀረፈ አብዛኛውን የቀብር አስፈጻሚ ማኅበሮች ሥራቸውን እንዲያቆሙ ይገደዳሉ ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ሥርዓተ ቀብር ከተከናወነ በኋላ ራስጌ ላይ እምነ በረድ ሲደረግ 7,000 ብር እንደሚያስከፍሉ፣ አሁን ላይ የዋጋ ንረት በመከሰቱ መወደዱን ተናግረዋል፡፡

መንግሥት የሲሚንቶ አቅርቦት ችግርን ከቀረፈ ቀጣይነት ያለው ሥራ ለመሥራት ዕቅድ እንዳላቸውና ማኅበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዕለት ተዕለት የሚሠራ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

የሲሚንቶ አቅርቦትንም ሆነ ዋጋን መንግሥት በፍጥነት በማሻሻል በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችንና መቃብር አስፈጻሚ ማኅበሮችን ችግር ሊቀርፍ ይገባል ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ሪፖርተር የግንባታ ግብዓቶች የሚሸጡ ማከፋፈያና ሱቆች ላይ ሄዶ እንደተመለከተው ከሆነ፣ አብዛኛዎቹ ሱቆች ሲሚንቶ እየሸጡ አይደለም፡፡

የንግድ ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እከተለዋለሁ ያለውን የሲሚንቶ ዋጋ ንረት ለመግታት የሲሚንቶ ግብዓት መመርያ ቁጥር 908/2014 መሠረት በመላው አገሪቱ ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የዚህም መመርያ ዓላማም በረዥም የግብዓት ሰንሰለት አማካይነት ያላግብብ እየናረ የመጣውን የሲሚንቶ ዋጋ ለማስቀረት ብሎም በአገራዊና ማኅበረሰባዊ ዕድገት ላይ ፋይዳ ያላቸው የግንባታ ፕሮጀክቶች እንዳይስተጓጎሉና ቅድሚያ እንዲያገኙ ለማድረግ ታስቦ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ መመርያ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ጭምር ያማከለ ባለመሆኑ በርካታ ዜጎች በሲሚንቶ አቅርቦትና ተደራሽ ላይ ቅሬቸውን ያሰማሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...