Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ይጨንቃል እኮ!

ሰላም! ሰላም! እንዴት ነው ዘመኑና ኑሮ? እኛ ኑሮ ከብዶን በዚያ ላይ እየተናጀስን ዓለም ጥሎን እየኮበለለ መሆኑን ሳስብ ውስጤ ያዝናል፡፡ እኔማ ማንም የሚቀልድበትን ዲግሪ ብይዝ ኖሮ የማንም መጫወቻ አልሆንም ነበር ብዬም እናደዳለሁ፡፡ ለምን ብትሉ በቋንቋ ችግር ምክንያት ብዙ የዓለም መረጃ እያመለጠኝ ነው፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ሰሞን፣ ‹‹ኤሎን መስክ የተባለ የዓለም ቱጃር የዶናልድ ትራምፕን የትዊተር አካውንት በትዊተር ተዋንያን ድምፅ አሰጥቶ አስመለሰለት…›› ያለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ ትራምፕን ባውቀውም ኤሎን መስክ የተባለው ቱጃር ማን እንደሆነ ባለማወቄ ከፋኝ፡፡ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ዶላር እያጠመደ ያስተነትናል ብላችሁ ስታሙኝ፣ የዓለማችንን ታዋቂና ዝነኛ ቱጃር አለማወቄ ከነከነኝ። በመሀል ግን ነገረኛው ስልኬ አዲስ መልዕክት ደርሶት አስነጠሰችላችሁ። አውጥቼ ሳይ መልዕክቱ፣ ‹‹አፋልጉኝ!›› ይላል። ‘ማን ምን ጠፍቶት ይሆን?’ አላልኩም። እንዴት እላለሁ? ወገኔ በየአቅጣጫው  የትስስርና የፍቅር ብርሃን ጠፍቶበት ዓይኑ በቁጭት ዕንባ እያደር እያነሰ እያየሁ እንዴት ብዬ። በየቦታው የእናቶች ዕንባ እየፈሰሰ ዋይታው በዝቶ፣ በገዛ አገሩ በፍቅርና በመተሳሰብ የመኖር ፀጋው ተገፎ፣ ልጆቹን የሚያስተምርባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ከዕውቀት ማዕድነት ወደ ጋለ ምድጃነት ተቀይረው፣ ከትናንት ዛሬ አልሻል እያለ ተስፋው ደብዝዞ፣ መልካሞች ወደ ጎን ተገፍተው እኩዮች በድፍረት ደረታቸውን ገልብጠው ሲንጎማለሉበት እያየ አንገቱን ደፍቶ ይብሰለሰላል፡፡ ምን ይሁን ታዲያ ምድረ ደፋሪ በጥጋብ ያሻውን ሲያደርግ!

የስልኩን መልዕክት ወረድ እያልኩ ሳነብ፣ ‹‹ጤፍ፣ ዘይት፣ ስኳር፣ ኤሌክትሪክ፣ ውኃ፣ የቤት ኪራይ፣ የልጆች ትምህርት ቤት… ዋጋቸው ባለፉት ዓመታት ወጣ ገባ ከፍ ዝቅ ሲጫወት ከርሞ፣ አሁን ከእነ አካቴው ከተዳሳሽነት ወደ ምናባዊነት ተሸጋገረ። እናም ከምናባዊነት ወደ ተዳሳሽነት ለመለሰ ወሮታውን እንከፍላለን…›› ይላል። ገርሞኝ በቅሬታ ውስጥ ሆኜ ፈገግ አልኩ። ቢከፋኝም ቢያንስ ከተዳሳሽነት ወደ ምናባዊነት ያልተሸጋገረ ጥርስ አለኛ። ምን ማለታችሁ ነው። ለምሁሩ የባሻዬ ልጅ በስልኬ የደረሰኝን መልዕክት ስነግረው ምን እንዳለኝ ታውቃላችሁ? ‹‹ጥርስህ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ወይም በልተው በማይጠረቁ ስግብግብ ነጋዴዎች እጅ አለመሆኑ በጀህ…›› ነበር ያለኝ። ጎበዝ ምናችን በእነ ማን እጅ ነው የሚለውን አደራ እየተጠራጠራችሁ፡፡ እሺ? ‹ያልጠረጠረ ተመነጠረ› ይባል የነበረው እኮ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ አለበለዚያ እንደ ድንበር ድንጋይ አንድ ቦታ ተገትረን መተረቻ መሆናችን አይቀርም፡፡ መተረቻና መዘባበቻ ከመሆን ይሰውረን እንደ ማለት ያለ መልካም ምኞት ካላችሁ ወዲህ በሉ፡፡ እስቲ ወዲያ ወዲህ እንበል ጎበዝ!

እናላችሁ ሰሞኑን ከአንዲት ምስኪን እናት ጋር ሱዚኪ ዲዛየር ዋጋ ሳነፃፅር ነበር የሰነበትኩት። እሳቸው የዋጋ ነገር ግራ ገብቷቸዋል። ከዋጋ በላይ ግን የጥራት ጉዳይ ያሳሰባቸው ይመስላሉ። ‹‹እነዚህ ሲያዩዋቸው ጨርቅ የለበሱ የሚመስሉ መኪኖች ይሰነብታሉ ግን?›› ይሉኛል ዓይን ዓይኔን እያዩ። ‹‹አይ እማማ በጥሩ ሁኔታ ካልተያዘ ሰውስ መቼ ይሰነብታል?›› እላለሁ ‘ትቼዋለሁ’ እንዳይሉኝ ሠግቼ። ‹‹እሱስ ልክ ነው…›› ብለው ሲቆዝሙ ‘ለማንና ለምን’ መኪኖቹን እንደሚገዙ አወጣጣቸው ጀመር። ‹‹ይኼውልህ ትንሹ ልጄ ገና ኮሌጅ እንደገባ ‘ማሪዋና’ ነው የሚሉት?… ብቻ ጭሳጭስ ለምዶ ይህችን አከለ። ተው ብል ማን ሰምቶኝ? ሽቅብ ያዩሃል የዘንድሮ ልጆች። እያደር ስሜቱ ሁሉ ቀዘቀዘ። ትምህርቱን ተወው። ያልወሰድኩት ሐኪም ያልወሰድኩት ፀበል የለም። አሁን ምን እንደነካው ሳላውቅ ተለውጦ ሁለት ‘ዲዛየሮች’ ግዥልኝና እየሠራሁ ልደግ አለኝ። ድንግሊቷ ፀሎቴን ሰማች። ይኼው ውጭ ያሉ ወንድሞቹን ሙሉልኝ ብዬ ካንተ ጋር እንከራተታለሁ…›› ሲሉኝ የምለው ጠፋኝ። አይ የእናት ነገር፡፡ ልጃቸው ራሱን ብቻ ሳይሆን የሚወደውን አብሮ አደጉን ጭምር የሥራ ባለቤት ለማድረግ አቅዶ ነበር ለካ ሁለት ዲዛየሮች በውድ ዋጋ የሚገዙት፡፡ አያችሁ ወገኖቼ፣ ስንፋቀር እኮ ቂጣ ብቻ ሳይሆን ሥራም እንካፈላለን፡፡ ሳንፋቀር ስንቀር ደግሞ በከንቱ እየተጨካከንን እንጋደላለን፡፡ ለፀፀት እየተዳረግን ከሰው በታች እንሆናለን፡፡ ከሰው በታች ከመሆን ይሰውራችሁ!

‹‹አይ የወለደ…›› ብዬ ዝም ማለቱ ከበደኝ። ምን እንደምል ጠፍቶኝ ሳቀረቅር፣ ‹‹ምነው ግን ልጄ ካልጠፋ ነገር የትውልዱ መጠመጃ ጭሳጭስ ሆነ?›› ብለው አፈጠጡብኝ። ምን ብዬ ላስረዳቸው፣ ትውልዱ የራስ ወዳዶችና የግፈኞች ሰለባ የሆነው እኮ በጭሳጭሱ ብቻ ሳይሆን፣ በክፋት መርዝ በተለወሰ ፖለቲካ ጭምር ነው ልላቸው ብዬ አሳዝነውኝ ተውኩት፡፡ እናትነት ምን ያህል ከባድ አደራና ኃላፊነት መሆኑን ስለማውቅ በሐዘኔታ እያየኋቸው ዝም አልኩ፡፡ የአቅሜን ያህል ተጣጥሬ ሻል ባለ ዋጋ ያልተጫሩና ያልተኮረኮሙ ሁለት ዲዛየሮች አጋዝቻቸው ስንለያይ አንጀቴ ተንቦጫቦጨ። ሄጄ ለአዛውንቱ ባሻዬ እንደ ወትሮው ውሎዬን ሳጫውታቸው፣ ‹‹በአገር የመጣ ነው አንበርብር…›› ብለው ይባስ ቅስሜን አያነክቱት መሰላችሁ? ‹‹ታዲያ ምነው አገር አልተሰማው? ምነው ጉዳዬ ብሎ አላወራው?›› ስላቸው፣ ‹‹ገመና እንዴት ይወራል አንበርብር? ያውም የልጅ? ምንም ቢሆን ልጅ እኮ ነው። ስንቱ ነው በልጁ ምክንያት የተሸነፈ? ነፃነትንና ልቅነትን መለየት እስኪያቅተን ድረስ ተቀላቅለውብን ስንቱ ነው ጥርሱን ነክሶ ልጁን በቁም የቀበረ? ስንቱ…›› እያሉ አላቆም አሉ። ይኼን ብሶት ማጠራቀም ትተን ‹ሳይቃጠል በቅጠል› እያልን የምንዘምትበት ጊዜ ቅርብ ይሆን? ምናለበት በሆነ፡፡ በመፈክር ሳይሆን በተግባር እናረጋግጠው!

በአዋዋሌ እንዲሁ ስገረም፣ ነፍሴ ስትገነዝ፣ ስቆጣ፣ ስለዝብ፣ ሳሻሽጥና ሳለዋውጥ እየዋልኩ ፀጉሬ ማደጉን አላስተዋልኩም። ውዴ ማንጠግቦሽ፣ ‹‹ኧረ ሽፍታ መሰልክ አሳጥረው…›› ስትለኝ እንደማያዋጣኝ ገባኝ። ይገርማችኋል ማንጠግቦሽ ፀጉሬና ፂሜ ከፍ ሲልና በጣም ሲያድግ ተመሳሳይ አነጋገር አትጠቀምም። እንደ ነገሩ መዘዝ ሲል፣ ‹‹ምነው አንበርብር ይኼን ፂምህን እኔ እያስታወስኩህ ባትላጨው?›› ነው የምትለው፡፡ በጣም ሲያስቀይማት ግን ‘ሽፍታ’ የሚለውን ቃል አውቃ ትጠቀማለች። እኔ ደግሞ በሽፍትነትና በዘራፊነት እንዳልታማ በእጅጉ የማደርገውን ጥንቃቄ አሳምራ ታውቃለች። መቼም በደካማ ጎናችሁ አንዴ አለመገኘት ነው። ነገሩን ካነሳሁት አይቀር ስስ ብልታችን በዝቶ እሱን እየነካኩ፣ እንዳሻቸው የሚቀልዱብን መብዛታቸውንም ልጠቁም። እኛም ታዲያ፣ ‹‹አንዱን በቴስታ አንዱንም በካልቾ ነበር ልማዳችን፣ ሚስት አገባንና ልጆች ወለድንና ፈሰሰ ሀሞታችን…›› ብለን እጅ ሰጠን። ታዲያ እንዳልኳችሁ ማንጠግቦሽ ‘ሽፍታ’ የሚባለውን የማልወደው ቃል ስለተጠቀመች እጅ ሰጥቼ የዘወትር ፀጉር ቆራጩ ዘንድ ስሄድ ‹‹መብራት የለም!›› ብሎ የገዛ ጥፍሩን ሲቆርጥ ደረስኩ። ምን ያድርግ ታዲያ!

ዛሬማ በመቀስም ቢሆን አስመድምጄው አድራለሁ እንጂ እንዲህ ሆኜ አልመለስም እያልኩ፣ በጄኔሬተር ኃይል ነፍስ ወደ ዘራ ‘ሞል’ ዘው ማለት። ምን እንደነካኝ አላውቅም። ፀጉር ቤት አፈላልጌ ሳገኝ፣  ‹‹ፓንክ!››  አልኩት ቆራጩን። በሦስት ቁጥር መድምዶኝ ሲያበቃ ጨርሻለሁ ብሎ ከየዓይነቱ ቅባት ቀባብቶ ውረድ አለኝ። የደንበኛዬ እጅ ይግደለኝ እያልኩ ማጠሩን ብቻ ዓይቼ ሒሳብ ስል፣ ‹‹አራት መቶ ብር!›› ተባልኩኝ፡፡ ‹‹የባህታዊ ፀጉርም ይኼን ያህል አይከፈልበት…›› ከማለቴ ‘ቶንዶሱ ሪል የጃፓን ሥሪት፣ ቅባቶቹን ቀጥታ ከአሜሪካ የምናስመጣቸው፣ ወንበሩ የጣሊያን’ ተባልኩ። እኔም እንደ ከፋኝ ምን አደርጋለሁ ብዬ ከፍዬ ወጥቼ ሄድኩ እላችኋለሁ። ከአካባቢያችን እያሳደደ የሚጫወትብን መብራት እንደሆነ መቼ አጣነው አትሉም? በነገራችን ላይ ለስደት የሚያነሳሱን ምክንያቶችን ለይተን አውቀን መፍትሔ ካልፈለግን፣ ወጣቱ ቀርቶ አዛውንቱም መነሳሳቱ የማይቀርበት ሁኔታ ውስጥ ያለን ይመስለኛል፡፡ እንደ እኔ የመሰላችሁ ካላችሁ ችላ ባትሉ ይመረጣል፡፡ ዋ ብያለሁ!

በቀደም ዕለት አንድ ባለተሳቢ ኢቬኮ ሳሻሽጥ ሻጩ ደንበኛዬ ትኩር ብሎ ቀለበቴን እየተመለከተ፣ ‹‹ትዳር እንዴት ነው?›› ብሎ ጠየቀኝ። ‹‹አሸወይና ነው፣ ወርቅ ሚስት አለችኝ…›› አልኩት። አንዳንዴ ከጥያቄው በፊት የተዘጋጁ መልሶች ችግር ይፈጥራሉ እኮ። ለካስ ዕድሜው ከእኔ ከጎልማሳው የማያንሰው ደንበኛዬ አራተኛ ጣት ባዶ ኖሯል። ምን ብዬ ጨዋታዬን ልቀጥል። ‹‹ይገርምሃል ከጓደኞቼ ሁሉ ሳላገባ የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ…›› አለኝ። ‘ግድ የለም ሁሉም በጊዜው ይሆናል’ ብዬ ሌላ የተዘጋጀ መልስ ከመመለስ ለጥቂት ተረፍኩ። አንዳንዱ ባለማግባቱ የሚበሳጨውን ያህል ሌላ በምንም ሲበሳጭ አላየሁማ። ‹‹ምነው አልክ?›› አልኩት ብዙም ያልደነቀኝ መስዬ። በዚህ ዘመን ስንትና ስንት የሚያስጨንቁና የሚገራርሙ ጉዳዮች እያሉብን የአንድ ሰው ማግባትና አለማግባት ምን ይደንቃል፡፡ ሰውየው ግን ምሬት ውስጥ ያለ ይመስል፣ ‹‹ዕድሜ ለጓደኞቼ መማሪያ ሆኑኛ። አንድ ሁለቱ ይሻላሉ እንጂ የሰባቱ ኑሮ ሲዖል በለው። ነጋ ጠባ ጭቅጭቅ ነው። ዘመኑ እንደምታየው ስለእኩልነት የሰበከውን ያህል ስላንተ ትብስ አንቺ አይሰብክም። እናም እኔ ይኼን እያየሁ ምን ተማምኜ ላግባ? ያውስ በመሸበት ማደር በቀለለበት ዘመን…›› ሲለኝ አሁን ትንሽ ገባኝ። በመጠኑ ማለቴ ነው!

በኋላ ሥራዬን ጨራርሼ ኮሚሽኔን ተቀብዬ ከባሻዬ ጋር ስንጫወት ይኼው ደንበኛዬ ያለኝን ብነግራቸው፣ ባሻዬ አንገታቸውን ወዝወዝ አድርገው ‘ዋ’ ብለው ቀሩ። ‹‹ምነው?›› ስላቸው፣ ‹‹ያለ ሙያቸውና ያለ ዕውቀታቸው ገብተው የተደናገሩ ከበሮ መቺዎችን እያየ ስንቱ ከበሮውን ትራስ አደረገው? ስንቱ ዛሬ ታይተው በነጋታው በፈረሱ ትዳሮች የወደፊት ተስፋው ፈረሰ? ለአገር ለወገኑ ስንት ዓላማና ዕቅድ ያለው ከእሱ በፊት የነበሩትን እያየ ስንቱ ሐሞቱ ፈሰሰ? ስንቱ ሰላማዊ ትግልን ሸሸ? ስንቱ ፖለቲካን እንደ ዓይነ ምድር ተፀየፈ?›› ሲሉኝ  አዝማቹን እየደጋገምኩ አጀብኳቸው። ነገር ግን በመሀል ሌላ ሐሳብ መጣልኝ፡፡ ከሌብነት ጋር አብረው ተወልደው ያደጉ የሚመስሉ ደግሞ፣ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም አገር እየዘረፈና እያዘረፈ በውስኪ ይራጫል፡፡ ለአገር ደንታ የለው፣ ለትውልዱ አያስብ፣ ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር አይራመድ፣ ብቻ እንደ አጋሰስ እየበላና እየጠጣ የሚያቀረሸው መብዛቱ ሲታሰበኝ ነገሩን ሁሉ ትቼ መጥፋት አማረኝ፡፡ ኧረ በስንቱ እንቃጠል!

በሉ እንሰነባበት። እንቅልፍም እንደ ዘመኑ ሰው ሰዓቱን ጠብቆ አልገኝ እያለ ሲያስቸግረኝ፣ ሁሌ እንደማደርገው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ዘንድ እደውላለሁ። ‹‹ለግሮሰሩ የምናጠፋው ብቻ ቢደመር አንድ የቢራ ፋብሪካ ያስከፍተን ነበር እኮ?›› እለዋለሁ ስንገናኝ፣ ‹‹በዘመነ ለውጥ መንደሮች ሁሉ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክነት በሚቀየሩበት በዚህ ጊዜ እንዴት የቢራ ፋብሪካ ትመኛለህ…›› አለኝ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ መጠጥ የሰው ልጅ ብቸኛ ጊዜ መግፊያ ከሆነ አገሩ በእንቅልፍ ዕጦት የዝንጀሮ መጫወቻ እንደሚሆን የሚታየኝ እኔ ብቻ ነኝ ማለት ነው? እውነቴን እኮ ነው። ‹‹የአሥር ሳንቲም ቆሎ ኮርሸም አደርግና፣ አንድ ጣሳ ውኃ ጭልጥ አደርግና ተመሥገን እላለሁ ኑሮ ይባልና…›› ብሎ የገጠመው ሰውዬ ዛሬ አግኝታችሁት ብትጠይቁት፣ እንኳን ለአንድ ጣሳ ውኃ ጥበቃ አንድ ጠርሙስ ቢራ ብሎ ቢያሻሽለው እንደሚመኝ ያስረዳችሁ ነበር። ሰውን በቁጥጥር ሥር ማዋል ብሎ ተዓምር ታዲያ ከዚህ በላይ ምን አለ? ተፈጥሮ የለገሰንን ውኃ የገብስ ጭማቂ ሲያስንቀው ማለቴ ነው። ለማንኛውም ይኼ በቀን የለመድነው መጠጥ ከዚህ መርዝ ፖለቲካ ጋር እየተሸረበ ምን እንምንደራረግ ሳስበው ክፍት ይለኛል፡፡ አይዞህ በሉኝ እንጂ!

እናም ከባሻዬ ልጅ ጋር የባጥ የቆጡን እያወራን በመሀል አንድ ተረት አመጣ። ከፍ ዝቅ ሄድ መለስ የሚለውን ነገረ ሥራችንን አስታኮ፣ ‹‹የሾተላይን ልጅ የገበታ ውኃ ይወስደዋል…›› ብሎ ተከዘ። ተረቱ ተመቸኝ። የተመቸኝ ከዚህ ሁሉ የልማትና የዕድገት ልፍለፋ በኋላ ለገበታ ውኃ መቸገራችን ብቻ ሳይሆን፣ የገበታ ውኃ የኢንዶኔዥያ ማዕበል አንገላቶ የማይገለውን ነፍስ እዚህ ፀጥ እያደረገው ማየቴ ነው። በቀላል አባባል ነገር ሳላንዛዛ ‹እኛ› እና ‹እናንተ› የሚለው ክፉ ነገር ውስጤ ገባ። ማመሳሰል ለምትወዱ ደግሞ ‘በግል ወይስ በጋራ?’ በሚል ዜማ መጫወት መብታችሁ ነው እያልኩ ስብሰለሰል፣ ከውስጤ የሆነ ድምፅ ተሰማኝ፡፡ ቅዥት ሳይሆን ጭንቀት የያዘው የሚመስል ግን የሚሰማ ድምፅ፡፡ ምንድነው አትሉኝም? ነገራችን ሁሉ ‘ቀልቀሎ ስልቻ፣ ስልቻ ቀልቀሎ’ ስለሆነ የግላችንና የጋራችን አልለይ አለ እኮ? ማን ነበር ሞኝ ሲሰምጥ ብልጥ ይንሳፈፋል ያለው? ለማንኛውም ከያዘን የዕብደት አባዜ መለስ ብለን ለነገው የጋራ ጉዳያችን እንጨነቅ እላለሁ፡፡ እየዞርኩ በማየው ሁሉ ደስተኛ አይደለሁም፡፡ ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬ ነገ አልሻል ካለን ፅኑ ደዌ ለክፎናል ማለት ነው፡፡ መድኃኒት ሳይኖረን በሽታ ማስታመም እንደማይቻለው ሁሉ አገር ሳይኖረን መኖር አይቻለንም፡፡ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ጨነቀኝ ስላችሁ አዳምጡኝ፡፡ ይጨንቃል እኮ! መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት