Sunday, May 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በርካታ ባለሀብቶች በቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመግባት ፍላጎት ማሳየታቸው ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ዕጥረት ምክንያት በተጠበቀው ልክ ባለሀብቶች ሳይገቡበት የቆየው የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ከአንድ መቶ በላይ ባለሀብቶች ለመግባት ፍላጎት ማሳየታቸው ተገለጸ፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ከተቋቋሙት አራት አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለይም ከፍተኛ የግብርና ጥሬ ዕቃ አለባቸው ተብለው ከተለዩት ቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባር ቀደሙ መሆኑን፣ የቡሬ የተቀናጀ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳኛቸው አስረስ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ይህ መልካም አጋጣሚ እንደተጠበቀ ሆኖ የኃይል አቅርቦት ችግር ግን አስቀድመው በፓርኩ ውስጥ ለማልማት የገቡት የሪችላንድና ፌቤላ የመሳሰሉ ትልልቅ ፋብሪካዎች፣ ማምረት በጀመሩበት ወቅት የኃይል ችግር ማነቆ ሆኖባቸው መቆየቱን ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ለፓርኩ የሚያስፈልገውን 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማሠራጫና ማስተላለፊያ ግንባታ ማስጀመሩንና ከ14 ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ቃል መግባቱን አቶ ዳኛቸው ገልጸዋል፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኩ የኤሌክትሪክ ኃይል ችግር በዚህ ወቅት መልክ የያዘ በመሆኑ፣ ፓርኩ ውስጥ ገብተው ለማልማት ፍላጎት ያሳዩ ድርጅቶች በትንሹ ግንባታ አጠናቀው ለመጨረስ አንድ ዓመት ስለሚፈጅባቸው፣ የኃይል ማሠራጫውና ማስተላለፊያው ግንባታ የሚጠናቀቅና የኃይል ችግሩም ይቀረፋል ብለዋል፡፡

ሰሞኑን የቡሬ የተቀናጀ ኢንዱስትሪ ፓርክን ለማስተዋወቅ ያለመ የኢንቨስትመንት ፎረም በባህር ዳር የተካሄደ ሲሆን፣ በፎረሙ ከታደሙ ባለሀብቶች 103 ያህሉ ፓርኩ ውስጥ ገብተው ለማልማት ፍላጎት ማሳየታቸው ታውቋል፡፡

የቡሬ የተቀናጀ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአንድ ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ በሦስት ምዕራፎች ለማልማት ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት 264 ሔክታር መሬት ላይ ከመንግሥት የሚጠበቀው የተቀናጀ የመሠረተ ልማት ግንባታ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡

በመጀመርያው ምዕራፍ ይለማል ተብሎ ከታቀደው 264 ሔክታር መሬት ውስጥ ለኢንዱስትሪ (ማቀነባበሪያ) በማስተር ፕላኑ የተዘጋጀው 169 ሔክታር ሲሆን፣ ቀሪው ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ለመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች የሚሸፈን መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ እስካሁን ለባለሀብቶች ከተላለፈው 60 ሔክታር ውጪ የቀረውን 109 ሔክታር የለማ መሬት ለባለሀብቶች ለማስተላለፍ የኢንቨስትመንት ፎረምና ማስተዋወቂያ መድረክ መዘጋጀቱን፣ የቡሬ የተቀናጀ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ዳኛቸው ገለጻ፣ የተዘጋጀው መድረክ ውጤታማ ሊባል የሚችል ነው፡፡ ‹‹103 ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ ለመግባት ፍላጎት አሳይተው የስምምነት ፊርማ ተፈራርመዋል፡፡ እነዚህ ባለሀብቶች ፓርኩ ውስጥ ገብተው የሚያለሙ ከሆነ፣ ተጨማሪ መሬት ስለሚያስፈልግ ያንን ለማመቻቸት የኢንዱስትሪ ፓርኩ 105 ሔክታር መሬት ለመጨመር ከአርሶ አደሮች ጋር ውይይት ተደርጎ የካሳ ግምት እየተሠራ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ፓርኩ በ2013 ዓ.ም. ከተመረቀ ወዲህ ዓምናን ጨምሮ 23 ባለሀብቶች መግባታቸውን፣ ከእነዚህ ውስጥ 16 ያህሉ በ2014 ዓ.ም. ገብተው ለማልማት መሬት የተረከቡ መሆናቸውን ዋና ሥራ አስኪያጅ ተናግረዋል፡፡ ከተጠቀሱት ባለሀብቶች ውስጥ በአሁኑ ወቅት ማምረት የጀመሩ፣ እየገነቡ የሚገኙ፣ እንዲሁም በቅድመ ግንባታ ደረጃ (ሒደት) ላይ ያሉ መኖራቸው ተጠቅሷል፡፡

የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በዋናነት የምግብና መጠጥ ፋብሪካዎች የሚደራጁበት ሲሆን፣ ምናልባትም በሦስተኛው ምዕራፍ የፋርማስዩቲካልስ ኢንዱስትሪዎችን ሊያሳትፍ እንደሚችል ታውቋል፡፡ የቡሬ የተቀናጀ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተለያዩ የምግብ ኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉበት መሆኑን፣ ከተለዩት ውስጥ የቅባት እህሎች ማቀነባበር፣ የጥራጥሬ ሰብሎችን በመጠቀም የሚመረቱ ምርቶች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ማቀነባበር፣ እንዲሁም የሥጋና የወተት ማቀነባበሪያዎች እንደሚስተናገዱበት ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች