Sunday, May 26, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ ውጤት መጠበቅን ፉርሽ እያደረገ ነው፡፡ በዓለም እግር ኳስ ላይ እየታየ ያለው ለውጥና መዘመን ድንገተኛ ክስተቶችን ከማሳየት ባሻገር፣ ወደፊት በታላላቅ ውድድሮች ላይ ለማመን የሚከብዱ ትዕይንቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ከወዲሁ አመላካች እየሆነ ነው፡፡ ከእግር ኳስ ውድድሩ መንደር ወጣ ስንልም ዘመኑን አስደማሚ ያደረጉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች፣ የሰው ልጅ የደረሰበትን የአስተሳሰብ ዕድገት ደረጃ ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ፡፡ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በአቪዬሽን፣ በትራንስፖርት፣ በንግድና በሌሎች ዘርፎች እየታዩ ያሉ ዕመርታዎች የሰው አስተሳሰብ በከፍተኛ ለውጥ ውስጥ እየተጓዘ መሆኑን ያስገነዝባሉ፡፡ በማያቋርጥ ለውጥ ውስጥ ያለችው ዓለም በተለያዩ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ችግሮች ብትከበብም፣ ነገን ዓላሚ በሆኑ የለውጥ አቀንቃኞች ለማመን የሚከብዱ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማስተናገድ ላይ ናት፡፡ አርቆ አሳቢዎችም የለውጡን ባቡር ተሳፍረው ከሚገኘው በረከት እየተቋደሱ ነው፡፡

የዚህ ዘመን ትውልድ ኢትዮጵያውያን አገራቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ መለወጥ እንዳለባት መገንዘብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከውጭ በሚገቡ አልባሳት፣ መጫሚያዎች፣ ስማርት ስልኮች፣ ተሽከርካሪዎችና ሌሎች የመገልገያ ዕቃዎች ከማጌጥና ከመኩራራት ስሜት ውስጥ በመውጣት፣ አገራቸው ኢትዮጵያ የሰው ኃይሏንና የተፈጥሮ ፀጋዎቿን ተጠቅማ ከመራሩ ድህነት እንድትገላገል በአንድነት ይነሱ፡፡ አንድ ችግር ሲያጋጥም እሱን ይዞ ከማስታመም ይልቅ፣ ጥርስን ነክሶ ታግሎ ከችግሩ ውስጥ ተጠቃሚነትን ለማግኘት አስተሳሰብን ማዘመን የግድ መሆን አለበት፡፡ ዓለም እየተለወጠ ከለውጡ በተቃራኒ ራስንና አገርን መዘወር፣ ከተረጅነትና ከተወራጅነት በስተቀር የሚፈይደው የለም፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ነገር ለለውጥ ዝግጁ ሊሆን ይገባል፡፡ የሰዎች አስተሳሰብ ዘመኑ ከሚፈልገው አኳያ አብሮ መዘመን ካልቻለ፣ ሌላው ቀርቶ ልዩነቶችን በሠለጠነ መንገድ ማስተናገድ እያቃተ በዓለም ፊት መሳቂያ የሚያደርግ ጦርነት ውስጥ ይገባል፡፡ የእስካሁን የኢትዮጵያ ችግሮች ዋነኛ ምክንያት በሕዝቡ ውስጥ የሚታወቁ ጠቃሚ ማኅበራዊ እሴቶችን ማጣጣል፣ እንዲሁም እየተለወጠ ካለው ዓለም ጋር የሚጣጣም የዳበረ አስተሳሰብ አለማበልፀግ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ለውጥ ሲባል እንዳለ ከውጭ ገልብጦ ማምጣት ሳይሆን፣ ከሕዝባችን ነባር ጠቃሚ እሴቶችና አገር በቀል ዕውቀቶች ጋር ማጣጣም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአራቱም ማዕዘናት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ መስኮች ያዳበሯቸውን አገር በቀል ዕውቀቶች፣ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ወለድ ዕውቀቶች ጋር በማቆራኘት የተፈጥሮ ፀጋዎችን ማልማት አያቅትም፡፡ በአገር በቀል ዕውቀቶች አማካይነት ችግሮችን ለመፍታት መነጋገርና መግባባት መፍጠር እየታቻለ፣ ልዩነትን በቅጡ የማስተናገድ አርቆ አሳቢነት በመጥፋቱ የደረሰውንና እየደረሰ ያለውን ዕልቂትና ውድመት ማንም አይስተውም፡፡ ዕልቂቱና ውድመቱ ከመድረሱ በፊት በአገር ሽማግሌዎችና በእምነት መሪዎች ችግሮችን ለመፍታት ሙከራዎች ቢደረጉም፣ ለማመን የሚከብድ ጥፋት ከደረሰ በኋላ በውጭ ገላጋዮች ለመሸማገል የተደረሰበት ውሳኔ ሲታሰብ ልብ ሰባሪ ነው፡፡ የዘመኑን አስተሳሰብ በማይመጥን ጀብደኝነት የተገባበት ጦርነት ካደረሰው ዕልቂትና ውድመት በተጨማሪ፣ በወደፊቱ ትውልድ ላይ ሊጥለው የሚችለው ጠባሳ ከባድ ዋጋ የሚያስከፍል ነው፡፡ ለዚህና ለሌሎች መሰል ምክንያቶች ሲባል ከእንደዚያ ዓይነቱ አስተሳሰብ መገላገል ያስፈልጋል፡፡ ከዘመኑ ጋር መራመድ የሚቻለው ለአገር የማይጠቅም አስተሳሰብ ሲወገድ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ከፖለቲካው ቀውስ በማይተናነስ ሁኔታ የኑሮ ውድነት የዜጎችን ሕይወት እያመሰቃቀለ ነው፡፡ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ መንግሥት የተለያዩ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ ሙከራ ቢያደርግም፣ እንደሚታየው እንዲህ በቀላሉ ሊሳካለት እንደማይችል ይታወቃል፡፡ በመስኩ ያሉ ባለሙያዎች እንደሚሉት የኑሮ ውድነትን ጫና ለመቋቋም የሚቻለው፣ ወጪን በመቀነስ ወይም ገቢን በመጨመር ነው፡፡ እንደ ቅንጦት ሊታዩ የሚችሉ ጥቂት ነገሮችን መቀነስ ቢቻልም ምግብን፣ ልብስን፣ የቤት ኪራይን፣ የልጆች ትምህርት ቤትን፣ የተለያዩ አገልግሎቶች ክፍያዎችንና ሌሎች መሠረታዊ ነገሮችን እንዴት መሸፈን ይቻላል የሚለው የብዙዎች ራስ ምታት ነው፡፡ ስለዚህ ከወጪ ቅነሳው በበለጠ የራስን ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ግን ራስን በአካልም በአዕምሮም ዝግጁ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ከመደበኛው ገቢ የበለጠ መስዋዕትነት ለመክፈል ሊዳርግ ይችላል፡፡ ለዚህም ነው በራስም ሆነ በቤተሰብ ላይ ለውጥ ማምጣት የሚያስፈልገው፡፡ ቤተሰብ ሲለወጥ ማኅበረሰብም መለወጥ ይጀምራል፡፡ ከማኅበረሰብ በመቀጠል አገራዊ መሆን ይጀምራል፡፡ ለዚህ ደግሞ ትምህርትና ሥልጠና ትልቅ ሚና አለው፡፡  

አገርን የማስተዳደር ኃላፊነት በሕዝብ ድምፅ ያገኘ መንግሥት ትልቁ ግዴታ የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት ከማስጠበቅ ባሻገር፣ ኑሮውን የማሳደግና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ፣ በሥነ ምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ ማገዝ፣ የተለያዩ አገልግሎቶችን ያለ ምንም አድልኦ የሚያገኙባቸው አሠራሮችን ማስፈን፣ ለሕግ የበላይነት ተግቶ መሥራት፣ ለሌብነትና ለዝርፊያ የሚያመቹ ብልሹ አሠራሮችን ማስወገድ፣ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማስከበር፣ ከአድልኦና ከአግላይነት የፀዳ የፖለቲካ ምኅዳር መፍጠር፣ ለሰላምና ለመረጋጋት መጥፋት ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ አላስፈላጊ ድርጊቶችን ማስቆምና መሰል ተግባራትን ማከናወን የመንግሥት ኃላፊነት መሆን ይኖርበታል፡፡ ሌቦችንና ዘራፊዎችን አቅፎ ጣትን ሌላ ቦታ መቀሰር ትክክል እንዳልሆነው ሁሉ፣ ብቃት አልባዎችንና ሥነ ምግባር የሌላቸውን በብሔር መሳሳብ እየሾሙ በአገር ላይ መቀለድ መቆም አለበት፡፡ አዲሱ ትውልድ ዘመኑን የሚመጥን ዕውቀት እየቀሰመ በሥነ ምግባር እንዲያድግ ሲደረግ፣ ኢትዮጵያ ሁሉንም ልጆቿን በእኩልነት የምታስተናግድ ሀብታም አገር ትሆናለች፡፡ ለዚህ ዕውን መሆን ደግሞ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ መቅረት ካለባቸው መካከል አንዱ ከውጭ በግዥ በተገኙ ቁሳቁሶች መኩራትና የራስን ማናናቅ ነው፡፡ ይልቁንም አገር በቀሉን ዕውቀት ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በማቀናጀት፣ የራስን ሠርቶ መከበር ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊ ለም መሬት፣ መጠኑ የበዛ ውኃ፣ በአፍሪካ ግንባር ቀደም የእንስሳት ሀብት፣ ተዝቀው የማያልቁ ማዕድናት፣ በርካታ የቱሪዝም መስህቦችና ሌሎች የተፈጥሮ ፀጋዎችን ታቅፋ ለምን በድህነት ትማቅቃለች ተብሎ ቁጭት መፈጠር አለበት፡፡ ዝንተ ዓለም ከዘመኑ ጋር ለመራመድ አለመሞከር የፈየደው የለም፡፡ ይህ ዓይነቱ ባህሪ የፈጠረው ረሃብና መታረዝ፣ በወሳኝ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ አለመስማማት፣ ልዩነትን ማስተናገድ አቅቶ መፋጀትና ለትውልድ የሚተርፍ ቂምና በቀል መዝራት ነው፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሆነ የአገር ጉዳይ የሚመለከታቸው ወገኖች፣ ኢትዮጵያን ከተዘፈቀችበት ማጥ ውስጥ ለማውጣት አስተሳሰባቸውን ማዘመን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወጣቱ ትውልድ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን ቁመና ላይ እንዲገኝ መትጋት አለባቸው፡፡ ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ያቀረቡት መልቀቂያ ተቀባይነት ማግኘቱ ተሰማ

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት የቀድሞው የውኃ ሀብት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለዘመኑ በማይመጥን ዕሳቤ አገር ማተራመስ ይብቃ!

ዘመኑ እጅግ ድንቅ የሚባሉ የሥልጣኔ ትሩፋቶችን በረቀቁ ቴክኖሎጂዎች እያቋደሰ ነው፡፡ ለልማትና ለዕድገት የሚማስኑ የኑሮን ጫና ቀለል የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን በብዛትና በስፋት ሲጠቀሙ፣ ያላደላቸው ደግሞ እርስ...

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...