Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየዓለም ዋንጫ አዳዲስ ክስተቶች

የዓለም ዋንጫ አዳዲስ ክስተቶች

ቀን:

በየዕለቱ አስደናቂ ክስተቶችን እያስመለከተ የሚገኘው የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ በኳታር ሦስተኛ ሳምንቱን ይዟል፡፡ ብሔራዊ ቡድኖች ሦስተኛ የምድብ ጨዋታቸውን ማድረግ የጀመሩ ሲሆን፣ ወደ ጥሎ ማለፍ መግባታቸውን ያረጋገጡ አገሮችም እየተለዩ ነው፡፡ ከውድድሩም በጠዋቱ የተሰናበቱ ብሔራዊ ቡድኖች እንዲሁ እየታወቁ ይገኛሉ፡፡

ገና ከጅማሬው ባልተገመቱ ውጤቶች ታጅቦ ቀጥሏል፡፡፡ ቀድመው ወደ ጥሎ ማለፍ የገቡትን ብሔራዊ ቡድኖችን ጨምሮ ቀሪ ጨዋታዎችን የሚያደርጉ ቡድኖች እስከ ዓርብ በሚያደርጉት ሦስተኛ የምድብ ጨዋታ ይለያሉ፡፡

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ ብራዚል፣ ፈረንሣይና ፖርቱጋል ወደ ጥሎ ማለፍ መግባታቸውን ያረጋገጡ ብሔራዊ ቡድኖች ሲሆኑ፣ አዘጋጇ ኳታርና ካናዳ ገና በጠዋቱ መሰናበታቸውን ያረጋገጡ ቡድኖች ሆነዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በሌላ በኩል በዓለም ዋንጫ ብዙ ይጓዛሉ ተብለው ግምት የተሰጣቸው ብሔራዊ ቡድኖች ገና በጠዋቱ ባልተገመቱ ጨዋታዎች ተረትተው አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል፡፡ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን በጃፓን መረታትና የአርጀንቲና በሳዑዲ ዓረቢያ መረታት በበርካቶች ዘንድ አግራሞትን የጫረ ውጤት ነበር፡፡

ከዚህም ባሻገር በዓለም እግር ኳስ ደረጃ ሁለተኛ ላይ የተቀመጠችው ቤልጂየም በሞሮኮ መረታቷን በአገሪቱ ረብሻ አስነስቷል፡፡

በምድብ ስድስት ከሞሮኮ፣ ክሮሺያና ካናዳ ጋር የተደለደለችው ቤልጂየም በምድብ አንድ ጨዋታ ካናዳን ብታሸንፍም፣ በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮ 2 ለ 0 በመረታቷ በቤልጂየም የተለያዩ ከተሞች በርካታ ረብሻዎች መቀስቀሱ ተገልጿል፡፡

በቤልጂየም ስምንት ከተሞች ላይ በተቀሰቀሰው ረብሻ ምክንያት የተለያዩ ንብረቶች የወደሙ ሲሆን፣ ፖሊስ የተቀሰቀሰውን ረብሻ ለማረጋጋት አስለቃሽ ጋዝና ውኃ የሚረጩ የፖሊስ መኪኖች የተሰማሩ ሲሆን በርካቶች መታሰራቸው ተነግሯል፡፡

የሞሮኮ ድል ማድረግን ተከትሎ በቤልጂየም የሚገኙ የሞሮኮ ስደተኞች ደስታቸውን የገለጹበት መንገድ ለብጥብጡ መባባስ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በተለይ የቤልጂየሙ አማካይ ተጫዋች ኪቨን ዴብሮይን ከጨዋታው በፊት በብሔራዊ ቡድን ውስጥ የተካተቱ ተጫዋቾች ዕድሜ ከ30 በላይ መሆናቸውንና ለዓለም ዋንጫን የሚመጥን ቡድን ይዘው አለመቅረባቸውን መነገሩ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ በዚህም በቡድኑ ውስጥ መኮራረፍ እንዳልቀረ እየተገለጸ ይገኛል፡፡

የካሜሮን ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ስንብት

አፍሪካን ከሚወክሉ አምስት አገሮች አንዱ የሆነው የካሜሮን ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ከቡድኑ ውስጥ መሰናበት በርካቶችን ያወዛገበ ውሳኔ ነው፡፡

በምድብ ሰባት ከኔዘርላንድ ብራዚልና ሰርቢያ ጋር የተደለደለችው ካሜሮን የቡድኑን ዋና ግብ ጠባቂ ከስብስቧ ውጪ አድርጋለች፡፡ ካሜሮን ከኔዘርላንድ ጋር ባደረገችው የምድብ አንድ ጨዋታ ቀን ለብሔራዊ ቡድኑ መሠለፍ የቻለው አንድሬ ኦናና፣ በሁለተኛ የምድብ ጨዋታ ከመሰናበቱም በላይ በተጠባባቂ ወንበር ላይ አለመኖሩ ሲያነጋገር ቆይቷል፡፡ በቀድሞዋ ተጫዋች ሮበርት ሶንግ እየተመራች የምትገኘው ካሜሮን ግብ ጠባቂው ከውድድር የመሰናበቱን ምክንያት በርካቶችን ሲያወዛግብ ቆይቷል፡፡ በዚህም ግብ ጠባቂ ከአሠልጣኙ በመጣ ትዕዛዝ ምክንያት ከስብስብ ውስጥ መቀነሱ የተገለጸ ሲሆን፣ ግብ ጠባቂው ከአሠልጣኙ ጋር ሲነጋገር መቆየቱና በዲሲፕሊን ጉዳይ ከቡድን ውስጥ መቀነሱን ገልጿል፡፡

የኢንተርሚላኑ ግብ ጠባቂ ኦናና አጨዋወት ያልተመቻቸው አሠልጣኙ፣ ‹‹የአጨዋወት ዘይቤህን ቀይር፤›› የሚል አስተያየት እንደሰጡትና በመጨረሻም መግባባት ላይ ባለመድረሳቸው ከቡድኑ ለመቀነሱ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡

ማርካ ጋዜጣ ከቅርብ ሰዎች አገኘሁት ባለው መረጃ መሠረት በጨዋታ ወቅት ግብ ጠባቂ ኳስን እግር ሥር እያሽሞነሞነ ራሱን አደጋ ውስጥ ይከታል የሚል አስተያየት ከአሠልጣኙ እንደቀረበለት ተጠቅሷል፡፡

እንደ ማርካ ዘገባ ከሆነ አሠልጣኙ ሶንግ ቅዳሜ ዕለት በነበረው ልምምድ ላይ ግብ ጠባቂ ላይ ሲጮህበት እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ ከልምምድ በኋላ አሠልጣኙና ግብ ጠባቂ ቁጭ ብለው ቢነጋገሩም ስምምነት ላይ አለመድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም አሠልጣኙ ተጫዋቹን በቀጥታ ከቡድን ውጪ ለማድረግ መወሰናቸው ተብራርተዋል፡፡

ሆኖም ካሜሮን ከሰርቢያ ባደረገችው የምድብ ሁለት ጨዋታ የመጀመርያው ግብ አስቆጥራ መምራት ብትችልም፣ በተከታታይ በተቆጠሩ ግቦች መርታት የምትችለውን ጨዋታ 3 ለ 3 በሆነ ውጤት ማጠናቀቋና የሁለተኛው ግብ ጠባቂ ስህተት ለጎሎች መቆጠር እንደ ምክንያት ተነስቷል፡፡ በዚህም ምክንያት አሠልጣኙ የወሰኑት ውሳኔ ስህተት ነው ብለው የሚከራከሩ አሉ፡፡

‹‹ሆኖም አሠልጣኝ ግብ ጠባቂው ወደ ቡድኑ መመለስ ከፈለገ፣ ይቅርታ መጠየቅ አለበት፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ ግብ ጠባቂው አሠልጣኙ ያቀረቡትን የመፍትሔ ሐሳብ ‹‹ይቀበላል? ወይስ አይቀበልም?›› የሚለው በቅርቡ ምላሽ የሚያገኝ ይሆናል፡፡

ካሜሮን የምድቧን ሦስተኛ ጨዋታ ዓርብ ኅዳር 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ከብራዚል ጋር ታደርጋለች፡፡

በኳታር ተስፋ የተጣለባቸው ታዳጊ ተጫዋቾች

 በዓለም ዋንጫ ከሚስተዋሉ ፉክክሮች ባሻገር፣ በመድረኩ ላይ ብቅ የሚሉ አዳዲስ ተጫዋቾች ስም መስማት የተለመደ ነው፡፡ በተለይ ተስፋ የሚጣልባቸው ወጣት ተጫዋቾች በመድረኩ የበርካታ ክለቦች ዕይታ ውስጥ ሲወድቁ ይስተዋላል፡፡ በዘንድሮ የዓለም ዋንጫ ከወዲሁ ዋጋ የመጣላቸው ወጣት ተጫዋቾችን ስም ተከትሎ ክለቦች ለማስፈረም ዋጋ ፉክክር ውስጥ ገብተዋል፡፡

የስፔኑ ፔደሪ፣ የእንግሊዙ ጁዲ ቤሊንገሃምና የጀመርኑ ጀማል መሰያላ ከወዲሁ የበርካታ ክለቦችን ቀልብ የገዙ ተጫዋች መሆን ችለዋል፡፡

የስፔኑ ፔደሪ 20 ዓመቱ ሲሆን፣ የእንግሊዙ ብሊንገሃምና ጀማል 20 ሊሞላቸው ጥቂት ወራት ይቀራቸዋል፡፡

ታዳጊዎቹ ገና በጥቂት ጨዋታዎች የበርካቶችን ቀልብ መሳብ ችለዋል፡፡ ምንም እንኳ እንደ ሜሲና ሮናልዶ የመጨረሻ ዓለም ዋንጫቸው የሆነ ተጫዋቾች በዓለም ዋንጫው የሚያሳዩት እንቅስቃሴ ቢጠበቅም፣ ተጠባቂ ታዳጊዎች ስምም የበርካቶችን ቀልብ እንደሚገዛ ይታመናል፡፡

ገና በጥቂት ጨዋታዎች እንቅስቃሴያቸውን ያሳዩት ሦስቱ ተጫዋቾች ከ100 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ዋጋ እንደሚያወጡ እየተነገረ ይገኛል፡፡

በተለይ ተጫዋቾቹ ተወክለው የመጡት ዓለም ዋንጫውን እንደሚያነሱ ግምት ከተሰጣቸው ብሔራዊ ቡድኖች ጋር መሆኑ የበለጠ ተፈላጊ አድርጓቸዋል፡፡

እነዚህ ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው ተጫዋቾች በባርሴሎናና በባየር ሙኒክ ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ሲሆኑ፣ በቀላሉ ክለቦቻቸው የሚለቋቸው አለመሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም የክሮሺያው ቾስኮ ጊቫርዲኦላና የአርጀንቲናው ኤንዞ ፈርናንዴዝ ተስፋ የተጣለባቸውና ለኳታር ዓለም ዋንጫ ድምቀት የሆኑ ወጣት ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

አዲሱ የፊፋ የባከኑ ሰዓት ተጨማሪ ሕግ

ፊፋ በዘንድሮ ዓለም ዋንጫ ላይ ተጨማሪ ደቂቃ ላይ አዲስ ሕግ አውጥቷል። እንግሊዝ 6 ለ 2 ኢራንን ያሸነፈችበት ጨዋታ 117 ደቂቃዎች ፈጅቷል። ፊፋ በዓለም ዋንጫ ጊዜ ማባከንን ለመቀነስ ያለመ ማሻሻያ እንደሆነ ገልጿል።

በኳታር የዓለም ዋንጫ መክፈቻ አራት ጨዋታዎች ላይ በአዲሱ ፊፋ ሕግ ምክንያት ተጨማሪ የ64 ደቂቃዎች ተጨምረዋል። የጨዋታ ጊዜን ከፍ ለማድረግና ጊዜ ማባከንን ለመቀነስ ሕጉ ማስፈለጉን የጠቀሰው ፊፋ፣ በመጀመሪያ አጋማሽ በአማካይ ስምንት ደቂቃዎች መጨመራቸውን አስረድቷል።

እንግሊዝ ኢራንን ባሸነፈችበት ጨዋታ 27 ደቂቃ ተጨምሮ፣ ጨዋታው ከሁለት ሰዓት በላይ ፈጅቷል። ይህም የሆነው በመጀመሪያው አጋማሽ የኢራን ግብ ጠባቂ አሊሬዛ ቤይራንቫንድ ባጋጠመው የጭንቅላት ጉዳት እንዲሁም በሁለተኛውም አጋማሽ በሃሪ ኬንና ሃሪ ማጉዌር መካከል በተፈጠረው መጋጨት ምክንያት ነበር።

በዚህም በጨዋታ ወቅት ቅጣቶች ከግብ በኋላ ተጫዋቾች ደስታቸውን ሲገልጹ የሚያባክኑትን ደቂቃ፣ የሕክምና አገልግሎት እንዲሁም በቫር ምክንያት የሚባክኑ ደቂቃዎችን ለማካካስ ታስቦ እንደሆነ ተብራርቷል። ሕጉ ተግባራዊ በሆነባቸው ጨዋታዎች፣ አንድም በጨዋታው ደቂቃዎች እንዳይባክኑ ከመሆኑም በላይ፣ ውጤት ሊቀይሩ የሚችሉ ግቦች በሽርፍራፊ ደቂቃዎች እንዲቆጠሩ ማስቻሉ ተጠቅሷል።

ኔዘርላንድ ሴኔጋልን 2ለ0 ስታሸንፍ፣ ሁለተኛውን ጎል የተቆጠረው በ99ኛው ደቂቃ ሲሆን፣ ኢራንም እንግሊዝ ላይ ቅጣት ምት ያስቆጠረችው ግብ 103ኛው ደቂቃ ላይ ነበር።

ብዙ አድናቂዎች ማፍራት የቻለው የ62 ዓመቱን ጣሊያናዊው ዳኛ ፒርሎጂ ኮሊና በርካቶች በደስታ ያስታውሱታል። እ.ኤ.አ. በ1998 እና 2003 መካከል ስድስት ጊዜ ሪከርድ በሆነው የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ታሪክ ፌዴሬሽን ከተመረጠ በኋላ በሁሉም ጊዜያት ታዋቂው ዳኛ መሆን ችሏል።

ኮሊና በሴሪ እ.ኤ.አ. በ1991 እና 2005 በመሀል ዳኝነት የመራ ሲሆን፣ በ1995 እና 2006 መካከል በፊፋ ውስጥ በኃላፊነት ካገለገሉ ዳኞች መካከል አንዱ ነው። ጣሊያናዊው በሥራው ወቅት ብዙ ታዋቂ ጨዋታዎችን መምራት የቻለ ሲሆን፣ የ1999 ሻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ፣ የ2002 የዓለም ዋንጫ ፍፃሜና የ2004 የአውሮፓ ዋንጫ ፍፃሜ መምራት ችሏል።  በአሁኑ ሰዓት በፊፋ ውስጥ ዳኝነቱን በበላይነት እየመራ ይገኛል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...