Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በ2014 የሒሳብ ዓመት በማግኘት ለባንኩ ታሪካዊ የሆነና በኢንዱስትሪውም ከፍተኛ የሚባል ውጤት አስመዘገበ። 

ባንኩ ባለፈው ቅዳሜ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔው ላይ ባቀረበው ዓመታዊ ሪፖርት ይፋ እንዳደረገው በ2014 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 4.6 ቢሊዮን ብር አትርፏል።አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ይህ የትርፍ መጠን ከቀደመው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ሲሆን፣ በሒሳብ ዓመቱ የትርፍ ምጣኔውን በዚህን ያህል ደረጃ ያሳደገ የግል ባንክ እንደሌለም ተጠቁሟል፡፡

ባንኩ በ2013 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት አስመዝግቦ የነበረው የትርፍ መጠን 2.05 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ ይህም ባንኩ የትርፍ ምጣኔ ዕድገቱን በየዓመቱ ከፍ እያደረገ መምጣቱን ከማሳያቱ ባሻገር ባለአክሲዮኖቹ በአንድ አክሲዮን የሚያገኙትን የትርፍ ድርሻ መጠን አሳድጓል፡፡ 

ባንኩ ያገኘው ትርፍ በኢንዱስትሪው ከፍተኛ የትርፍ ዕድገት ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ ይህ የትርፍ ዕድገትም አቢሲኒያ ባንክን ከግል ባንኮች ከፍተኛው ሁለተኛ አትራፊ ባንክ እንዲሆንም አስችሎታል፡፡

በከፍተኛ አትራፊነትም ሆነ በተለያዩ መመዘኛዎች በአገሪቱ ከሚገኙ የግል ባንኮች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው አዋሽ ባንክ ነው። አዋሽ ባንክ የ2014 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለባለአክሲዮኖቹ ጉባዔ አቅርቦ የነበረ ሲሆን፣ በሪፖርቱም በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት 7.45 ቢሊዮን ብር ማትረፉን፣ የተጣራ ትርፉ ደግሞ 5.3 ቢሊዮን ብር መድረሱ አስታውቋል።

አቢሲኒያ ባንክ በኢንዱስትሪው ከፍተኛ የሚባለውን ትርፍ ከማስመዝገቡ ባሻገር የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ለመጀመርያ ጊዜ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ በማሻገር ለባንኩ ሌላ አዲስ ታሪክ ለመጻፍም ችሏል። ባንኩ በ2014 የሒሳብ ዓመት የተቀማጭ ገንዘቡ መጠኑን በ32.3 በመቶ በማሳደግ 122 ቢሊዮን ብር ማድረስ የቻለ ሲሆን፣ ይህም የተቀማጭ ገንዘብ መጠናቸውን ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ማድረስ ከቻሉ ሦስት የግል ባንኮች መካከል አንዱ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ አቢሲኒያ ባንክ በ2013 የሒሳብ ዓመት የነበረው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 88.9 ቢሊዮን ብር እንደነበር ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡ 

በተመሳሳይ አቢሲኒያ ባንክ አጠቃላይ የብድር ክምችቱንም ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ የቻለው በዚሁ የ2014 የሒሳብ ዓመት ሲሆን፣ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የባንኩ የብድር ክምችት 113.3 ቢሊዮን ብር መድረሱን የባንኩ ሪፖርት ያመለክታል። ይህም በአንድ ዓመት ውስጥ የ48 በመቶ ዕድገት ያለው ወይም የ36.7 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠቱን የሚያሳይ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የብድር ክምችት መጠናቸውን ከአንድ መቶ ቢሊዮን በላይ ማድረስ ከቻሉ የግል ባንኮች ሦስተኛው እንዲሆን አስችሎታል። 

አቢሲኒያ ባንክ አጠቃላይ የሀብት መጠኑም ከፍተኛ በሚባል ደረጃ መጨመሩ ተገልጿል፡፡ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ መኮንን ማንያዘዋል ባቀረቡ ዓመታዊ ሪፖርታቸው ላይ እንደጠቀሱት፣ የባንኩ አጠቃላይ የሀብት ክምችት በ43.6 በመቶ አድጎ 149.4 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

የአቢሲኒያ ባንክ ከቀደሙ ዓመታት ሁሉ በ2014 ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበበት ነው ተብሎ የተጠቀሰው አፈጻጸሙ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ነው፡፡ በባንኩ ሪፖርት መሠረት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ቁጥር ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ ችሏል፡፡ የቦርድ ሊቀ መንበሩ ባቀረቡት ሪፖርታቸው ላይ እንደገለጹትም ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ደንበኞቹ ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከ60 በመቶ በላይ ጭማሪ ማሳየቱን ነው፡፡

እነዚህ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ከባንኩ አጠቃላይ ደንበኞች ቁጥር አንፃር ሲታይ የ13.1 በመቶ ድርሻ መያዛቸውንና ከእነዚህም ደንበኞቹ የተሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 12 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

በ2014 የሒሳብ ዓመት ብቻ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ 3.7 ቢሊዮን ብር በመሆኑ ባንኩ በዚህ ዓመት ከፍተኛ የሚባል ዕድገት እያስመዘገበ መቀጠሉን አሳይቷል፡፡

ከጠቅላላ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥም 9.9 በመቶ የሚሆነው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበ ነው፡፡ ለብድር የዋለው የገንዘብ መጠን 1.5 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም የ174 በመቶ ዕድገት ያለው ነው ተብሏል፡፡ 

የአቢሲኒያ ባንክ የ2014 ጠቅላላ ገቢው በ6.39 በመቶ በማሳደግ 16.7 ቢሊዮን ብር ማድረስ የቻለ ሲሆን፣ ከፍተኛ ወጪ ደግሞ 12.1 ቢሊዮን ብር ሆኖ መመዝገቡን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት አንፃር ባንኩ ከቀዳሚው ዓመት ቅናሽ የታየበት 674.6 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቱን ሪፖርቱ ይጠቁማል። 

በሌላ በኩል የአቢሲኒያ ባንክ አስቸኳይ ጉባዔው የባንኩን ካፒታል ወደ 12.5 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ የ2.5 ቢሊዮን ብር የተጨማሪ ካፒታል ውሳኔ አሳልፏል፡፡ አቢሲኒያ ባንክ የባንኩን ካፒታል ለማሳደግ የፈለገበት ምክንያትም፣ ባንኩ እያስመዘገበ ያለውን ከፍተኛ ዕድገት የሚመጥን ካፒታል ማፍራት ተገቢና የግድ በመሆኑ ነው፡፡ የገበያ ድርሻውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ በመምጣቱ ካፒታሉን ከፍ ማድረግ ማስፈለጉን ባንኮ ለውሳኔ ያቀረበው አመክንዮ ያስረዳል።

የባንኩን ዕድገት ቀጣይነት እንዲኖረው እንዲሁም፣ ለቀጣይ ዓመታት ተወዳዳሪነቱንና የገበያ ድርሻውን አስጠብቆና አጠናክሮ ለመሄድ የባንኩን ካፒታል ማሳደግ አስፈላጊ እንደሆነ ተብራርቷል። በተጨማሪም ባንኩ አሁን ያለው ካፒታል ከአጠቃላይ ሀብቱ አንፃር ያለው ምጣኔ ያልተመጣጠነ በመሆኑ በሥራ ሒደቱ ላይ እንቅፋት የሚፈጥር በመሆኑ የ2.5 ቢሊዮን ብር ካፒታል እንዲጨምር የውሳኔ ሐሳብ ቀርቧል። 

በተለይ የባንኩ ካፒታል ከባንኩ አጠቃላይ ዕድገት ጋር ተመጣጣኝ አለመሆኑ ግንዛቤ ውስጥ መግባት እንዳለበት የሚያመለክተው የውሳኔ ሐሳብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በመመርያ ያስቀመጠውን አስገዳጅ ዝቅተኛ የስምንት በመቶ የካፒታል ሀብት ሽፋን ምጣኔ አሟልቶ ለመቀጠል ካፒታሉን ማሳደግ የግድ ያስፈልጋል ብሏል፡፡ በዚህም መሠረት የባንኩን ካፒታል በ2.5 ቢሊዮን ብር በማሳደግ 12.5 ቢሊዮን ብር እንዲሆን የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ተቀባይነት አግኝቶ ፀድቋል፡፡ 

በተጨማሪም ከባንኩ ምሥረታ ጀምሮ 25 ብር ሆኖ የቆየውን የአንድ አክሲዮን ዋጋ ወደ 1000 ብር ለማሳደግ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ጠቅላላ ጉባዓው ተቀብሎ አፅድቆታል፡፡ 

ባንኩ በአገሪቱ ረዥም የሚባለውን ባለ 60 ወለል ሕንፃ ለመገንባት የያዘውን ዕቅድ በተመለከተ የቦርድ ሊቀመንበሩ በሰጡት ማብራሪያ፣ ግንባታውን ለማካሄድ ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ ጨረታውን ካሸነፈው ተቋራጭ ጋር ውል ስምምነት ተደርጎ የቅድመ ግንባታ ሥራዎች መከናወን መጀመሩን አስረድተዋል፡፡ 

ይህ ሕንፃ ወደ 20 ቢሊዮን ብር ሊፈጅ እንደሚችል ከዚህ ቀደም መገለጹ አይዘነጋም፡፡ ይህ የባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ሜክሲኮ አደባባይ ሕንፃ ከዋቢ ሸበሌ ሆቴል ጎን አጠቃላይ ስፋቱ 9,660 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚገነባ ነው፡፡ 

አቢሲኒያ ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት 125 አዳዲስ ቅርንጫፎች በመክፈት አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ቁጥር ወደ 748 ከፍ አድርጓል፡፡ የባንኩ ሠራተኞች ቁጥርም በ18.8 በመቶ ጨምሮ 9,677 እንደደረሱ የባንኩ ሪፖርት አመልክቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች