Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን ብር አዲስ ካፒታል በመጨመር አጠቃላይ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወስኗል።

የአዋሽ ባንክ ቦርድ በአምስት ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ የ43 ቢሊዮን ብር ካፒታል ለመጨመርና የባንኩን አጠቃላይ ካፒታል ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ በጠቅላላ ጉባዔው ምንም ዓይነት ተቃውሞ ሳይቀርብበት ፀድቋል፡፡ 

አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ከተወሰነው የተጨማሪ 43 ቢሊዮን ብር ካፒታል ውስጥ 38 ቢሊዮን ብር ዋጋ የሚያወጡትን አዲስ አክሲዮኖችን የባንኩ ባለአክሲዮኖች በድርሻቸው ልክ እንዲገዙት የተደለደለ ሲሆን፣ ቀሪው አምስት ቢሊዮን ብር ደግሞ ለባንኩ ሠራተኞችና የባንኩ ከፍተኛ አጋር ለሆኑ ኩባንያዎች እንዲሸጥ የቀረበውንም ሐሳብ ጠቅላላ ጉባዔው ተቀብሎታል። ይህ የባንኩ ውሳኔ በኢንዱስትሪው ከግል ባንኮች ከፍተኛ የካፒታል መጠን የያዘ ባንክ ያደርገዋል፡፡ ነገር ግን ባንኩ በዚህን ያህል መጠን ካፒታሉን ለማሳደግ ገፊ የሆነበት ምክንያት ምንድነው የሚለው በብዙዎች ዘንድ የሚመላለስ ጥያቄ ነው። ሪፖርተር በባንኩ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተገኝቶ የቦርድ አመራሮቹ ከሰጡት ማብራሪያ በዋናነት የተረዳውም ባንኩ ካፒታሉን የማሳደግ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ መግባቱን ነው።

የባንኩን ካፒታል በዚህን ያህል ደረጃ ለማሳደግ ቦርዱና ማኔጅመንቱ ብዙ ከመከሩበት በኋላ ለባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ እንዲቀርብ የተደረገበትን ምክንያት የአዋሽ ባንክ ቦርድ ሊቀመንበር እንዲሁም የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተውበታል፡፡ 

በተለይ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው፣ ባንኩ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ አስፈላጊ ካሏቸው ምክንያቶች አንዱ የባንኩን ፈጣን ዕድገት የሚመጥን ካፒታል ማፍራት የግድ አስፈላጊ መሆኑን ነው፡፡ ባንኩ በተለይ ባለፉት አሥር ዓመታት ፈጣን በሚባል ዕድገት እየተጓዘ መሆኑን፣ ለአብነትም ባለፉት አምስት ዓመታት በአማካይ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ በ37 በመቶ ማደጉን፣ የሰጠው የብድር መጠን ደግሞ በ42 በመቶ ማደጉን፣ አጠቃላይ የሀብት መጠኑም በ37 በመቶ ዕድገት የታየበት እንደሆነ በማስታወስ፣ ይህንን ዕድገት የሚመጥን ካፒታል መያዝ የግድ እንደሚል አስረድተዋል።

ከትርፍ አንፃርም የአምስት ዓመቱ አማካይ ዕድገት 41 በመቶ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ፀሐይ፣ ይህም አጠቃላይ የባንክ ዕድገት ከኢንዱስትሪው አማካይ ዕድገት በላይ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ይህንን ዕድገት የሚመጥን ካፒታል መያዝ በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ፣ የፋይናንስ ተቋማትን የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም የባንኮች የብድርና የሀብት መጠን ከካፒታላቸው ጋር የተጣጣመ መሆን እንዳለበት ያስገድዳል ብለዋል። በመሆኑም የአዋሽ ባንክ አጠቃላይ ብድርና ሀብት ካለው ካፒታል አንፃር ተገቢውን ምጣኔው ካልጠበቀ የብሔራዊ ባንክን መመርያ መተላለፍ በመሆኑ ካፒታሉን ማሳደግ ግድ እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡  

በብሔራዊ መመርያ መሠረት የብድርና የሀብት ዕድገት ከካፒታል ዕድገት ጋር የተመጣጠነ መሆን እንደሚኖርበትና የካፒታል ሀብት ሽፋን ምጣኔ (Capital Adequacy Ratio) ባንኩ ካስቀመጠው መጠን በታች መሆን ስለሌለበት አዲሱ የካፒታል ጭማሪው ለዚህ መመርያ ተፈጸሚነት አጋዥ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ ላይ የተቀመጠው ዝቅተኛ የካፒታል ሀብት ምጣኔ ስምንት በመቶ በመሆኑ፣ ይህንን ድንጋጌ ለማሟላት አዋሽ ባንክ ካፒታሉን የግድ ማሳደግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ባንኩ የዛሬ ስድስት ዓመት አጠቃላይ ሀብቱ ከካፒታሉ አንፃር ሲታይ፣ 17.4 በመቶ እንደነበር የገለጹት አቶ ፀሐይ፣ ይህ አኃዝ በአሁኑ ወቅት 8.2 በመቶ በመድረሱ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው ዝቅተኛ መጠን ጋር በመቀራረቡና መመርያውም አስገዳጅ በመሆኑ፣ አዋሽ ባንክ ካፒታሉን የማሳደግ ግዴታ እንዳለበት አመልክተዋል፡፡ በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት የካፒታል ሀብት ምጣኔው ከስምንት በመቶ ከወረደ አዋሽ ባንክ ካፒታሉን እንዲያሳድግ ብሔራዊ ባንክ ይገደዳል ገልጸዋል፡፡ ይህንን መመርያ መተላለፍ ባንኩ ብድር እንዳያበድርና ኢንቨስትንት እንዳያካሂድ ክልከላ ጭምር የሚያስከትል በመሆኑ የካፒታል ማሳደጉ ውሳኔ አስፈላጊና አስገዳጅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡  

ስለዚህ ሀብት፣ የብድርና በሌሎች ዕድገቶች ከካፒታል ዕድገት ጋር በተመጣጠነ መልኩ እየሄደ ባለመሆኑ የባንኩን ዕድገት ለማስቀጠል ካፒታሉን ማሳደግ ያሻል ብለዋል፡፡ ‹‹አሁን የአዋሽ ባንክ የተከፈለ ካፒታል 18.3 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ በኢንዱስትሪው ትልቁ የተከፈለ ካፒታል ነው፡፡ ነገር ግን ከአዋሽ ባንክ ዕድገት ጋር የሚመጣጠን አይደለም፤›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ የባንኩን ካፒታል ማሳደግ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉትም አብራርተዋል፡፡ አንደኛው ባንኩን ተወዳዳሪነቱን አስጠብቆ እንዲቀጥል የሚያደርገው ሲሆን፣ ከዚህም ሌላ የባንኩን የሥጋት ደረጃ ዝቅተኛና ሥጋቶችን በራሱ መመለስና መቋቋም የሚችል ጠንካራ ባንክ መሆኑን ያረጋግጥለታል ብለዋል፡፡ ከዚህ ውጪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጣቸውን ዝቅተኛ መሥፈርቶች ባንኩ እንዲያሟላ ያግዘዋል፣ በተለይ ለአንድ ደንበኛ በአንድ ጊዜ ሊሰጥ የሚችለውን የገንዘብ መጠን ለማሳደግም ጥቅም እንደሚኖረው አብራርተዋል፡፡ ባንኩ እጁ ላይ ሊይዝ የሚችለውን የውጭ ምንዛሪ ከፍ ከማድረግ አንፃርም ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡ ስለዚህ የካፒል ዕድገቱ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት በማመን እንዲሁም በብሔራዊ ባንክ መመርያም የሚያስገድድ በመሆኑ የውሳኔ ሐሳቡ መቅረቡን አመልክተዋል፡፡ የባንኩ ካፒታል ዕድገት ያስፈለገበትን ተጨማሪ ምክንያቶች ያብራሩት የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ዲባባ አብደታ (ዶ/ር)፣ የባንኩን ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃና ሌሎች ሰፋፊ የቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንቶችን ለማካሄድ ካፒታሉን ማሳደግ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል። ከዚህም ሌላ መንግሥት የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ለማድረግ መወሰኑንና ከእነዚህ ዓለም አቀፍ ባንኮች ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን የካፒታል ዕድገቱ ወሳኝ ስለሆነ፣ እንዲሁም ካፒታል ማሳደግ ለሕዝብ የእምነት ምንጭ በመሆኑ የሚሉትን ምክንያቶች አቅርበዋል፡፡ 

እንደ አቶ ፀሐይ ገለጻ፣ ይህንን ካፒታል ለማሳደግ የባንኩ የአምስት ዓመት ስትራቴጂ እንዲሠራ ከተመረጠው ዓለም አቀፍ ማኪንዚ ኩባንያ ጋር ጭምር በመሆን በተሠራው ጥናት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት አዋሽ ባንክ በዚሁ ዕድገቱ እየቀጠለ ከሄደ ሚኒመም ካፒታል አድቮሲ ሬሾውን ለማሟላት ካፒታሉ ከእነ ረዘርቩ 78 ቢሊዮን ብር መድረስ አለበት፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የተከፈለ ካፒታሉ ወደ 55 ቢሊዮን ብር ማደግ መቻል አለበት የሚያመለክት በመሆኑ፣ በዚሁ አግባብ የቀረበ ሐሳብ እንደሆነው ከሰጡት ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡   

ባንኩ በአንድ ጊዜ በ43 ቢሊዮን ብር ካፒታል ዕድገት እንደኖረው ሲታሰብና ከዚህ ውስጥ 38 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች እንዴት ሊገዙ ይችላሉ የሚለው ጥያቄ ያስታወሱት አቶ ፀሐይ፣ በዚህም ላይም ሰፊ ጥናት ተደርጎ ባለአክሲዮኑ የተደለደለለትን አክሲዮን መግዛት የሚችል መሆኑን የማረጋገጥ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡  

ጉዳዩን በዝርዝር ማየታቸውን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ አሁን ባንኩ ለባለአክሲዮኖች እየከፈለ ባለው የትርፍ ክፍፍል በመነሳት በሚቀጥሉ አምስት ዓመታት ውስጥ ምን ያህል የትርፍ ክፍፍል ሊከፈል ይችላል የሚለውን በዝርዝር የተሠራበት በመሆኑ ባለአክሲዮኖች ከትርፍ ክፍፍሉ የተጠቀሰውን ካፒታል ማሟላት የሚችሉ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ 

ይህንንም ‹‹በሚቀጥለው አምስት ዓመታት ውስጥ ባንኩ አሁን የሄደበትን ዕድገት ካስቀጠለ ወደ 41 ቢሊዮን ብር መክፈል የሚችል በመሆኑ ከአዲሱ ሼር 38 ቢሊዮን ብር ለባለአክሲዮኖች መግዛት እንደሚችሉ የታመነ ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ 

ከዚህ ከካፒታል ዕድገት ጋር ተያይዞ ከሚጨመረው አዲስ ካፒታል ውስጥ ሁለት ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ሁለት ሚሊዮን አክሲዮኖች ለሠራተኛው ይከፋፈል የሚለው ሐሳብ ላይም አቶ ፀሐይ፣ የባንኩ ዕድገት የመጣው በሠራተኞቹ በመሆኑ አክሲዮን መስጠቱ ጠቃሚ በመሆኑ ነው፡፡ እንዲሁም ሠራተኞችን ይዞ መቆየት ከተፈለገ ይህ ማበረታቻ በማስፈለጉ እንደሆነ አቶ ፀሐይ አብራርተዋል፡፡ ‹‹ሠራተኛው የባንኩ አለኝታና ዋና ሞተር ነው፡፡ ሠራተኞች ሥለሠሩ ነው አዋሽ ባንክ በፍጥነት አደገ ብለን ልናወራ የቻልነው፤›› ብለው፣ የባንኩን ዕድገት ለማስቀጠልም የቀረበ ሐሳብ በመግለጽ ይህም ሒሳብ ከባለአክሲዮኖች ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርገዋል፡፡ ለባንኩ ደንበኞችና አጋር ኩባንያዎች በ50 በመቶ ፕሪሚየም ሦስት ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ይሸጥ በሚለው ሐሳብ ላይ አቶ ፀሐይ፣ ይህንን ማድረግ ባንኩን በእጅጉ የሚጠቅምበትን ምክንያትን ምሳሌ በመጥቀስ አብራርተዋል፡፡ ከጠቀሷቸው ምሳሌዎች ውስጥ አንዳንድ ኤክስፖርተሮች በየዓመቱ 30 እና 40 ሚሊዮን ዶላር በቋሚነት እያስገኙ ያሉ መኖራቸውን ነው፡፡ ስለዚህ ባንኩን ለዓመታት ሲያግዙ የነበሩ ደንበኞች ባለአክሲዮን ቢሆኑ ጥቅማቸው ስለሚልቅ ሐሳቡ ቀርቧል፡፡ ትልልቅ ተበዳሪዎችም አሉን፡፡ በአሁኑ ወቅት ሌሎች ባንኮች ባንኮችም ተመሳሳይ ዕርምጃ እየወሰዱ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባንኩ በመደበኛው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የ2014 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙ ቀርቧል፡፡ በዚህ ሪፖርቱ ባንኩ በተለያዩ አፈጻጸሞች አሁንም ከግል ባንኮች የመጀመርያውን ደረጃ ይዞ ማጠናቀቅ መቻሉን የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አመልተዋል፡፡ 

የባንኩ በ2014 የሒሳብ ዓመት የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን (ከወለድ ነፃ  ባንክ አገልግሎቱን ጨምሮ) 152 ቢሊዮን ብር መድረሱ በዋናነት ተጠቅሷል፡፡ ይህ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ 43.9 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ ባንኩ በ2013 ሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የነበረው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 108 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ 

የባንኩ አጠቃይ የብድር ክምችት መጠንም በ47.6 በመቶ በመጨመር በ2014 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ 129.2 ቢሊዮን ብር መድረሱንም የባንኩ ሪፖርት አመልክቷል፡፡ ዓመቱ መጀመርያ ጊዜ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማሰባሰብ መቻሉን ነው፡፡ 

በአጠቃላይ በሒሳብ ዓመቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ 1.25 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን የገለጸው አዋሽ ባንክ፣ በዚህን ያህል ደረጃ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ያገኘ አንድም ባንክ የለም በሚል በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ አዋሽ ባንክ የ2014 ሒሳብ ዓመት ገቢ በ50 በመቶ ጨምሮ 20.6 ቢሊዮን ብር መድረሱ ታውቋል፡፡ ባንኩ በ2013 ጠቅላላ ዓመታዊ ገቢ 13.7 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ወጪም በ48 በመቶ በመጨመር 13.19 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተጠቅሷል፡፡

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት 7.45 ቢሊዮን ብር ማትረፍ መቻሉን ገለጸ ሲሆን፣ ይህ የትርፍ ምጣኔው ከቀዳሚው ዓመት የ54.5 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበ መሆኑን ነው፡፡ ከታክስ በኋላ የባንኩ የተጣራ ትርፍ 5.34 ቢሊዮን ብር መድረሱ ታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት ባንኩ አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ላለው አንድ አክሲዮን 570 ብር ማስገኘት ችሏል፡፡ በ2013 አንድ አክሲዮን ያስገኘው 470 ብር እንደነበር አይዘነጋም፡፡ 

አዋሽ ባንክ በአሁኑ ወቅት ጠቅላላ የሀብት መጠኑ ከ183.3 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ይህ የሀብት መጠን ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ በ42.5 በመቶ ዕድገት ማስመዝገበ ነው፡፡ አዋሽ ባንክ እስከ 2014 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ድረስ በመላ ኢትዮጵያ ያሉት ቅርንጫፎች 725 ደርሰዋል፡፡ 17,393 ሠራተኞች አሉት፡፡. 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች