Friday, July 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሰሜኑ ጦርነት በፈጠረው የግንኙነት መስተጓጎል ካሳ መጠየቅ ላልቻሉ ዕድል እንደሚሰጥ መድን ድርጅት አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በትግራይ ክልልና ሌሎች ጦርነት በተካሄደባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ከጦርነቱ ጋር ያልተያያዘ ጉዳት ገጥሟቸው ነገር ግን በመገናኛ ዘዴዎች መስተጓጎል ጉዳታቸውን አሳውቀው ካሳ መጠየቅ ላልቻሉ ደንበኞቹ ዕድል እንደሚሰጥ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት አስታወቀ።

በጦርነት ለሚደርስ ጉዳት የመድን ሽፋን ውል የገቡና በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው ደንበኞች ካሉም የሚስተናገዱበት ዕድል እንደሚኖር ድርጅቱ ገልጿል።

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነፃነት ለሜሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት በመቀሌ ከተማ የሚገኘው የድርጅቱ ዋና ቅርንጫፍን ጨምሮ ስድስት ቅርንጫፎች ሥራ አቋርጠዋል።

በእነዚህ ቅርንጫፎች በኩል የዋስትና ሽፋን በመስጠት ድርጅቱ ያገኝ የነበረውን ገቢ ከማጣቱም በላይ ደንበኞቹ ዋስትና የገቡላቸውን ንብረቶች የተመለከተ ምንም ዓይነት መረጃ ለማግኘት እንዳልተቻለ ጠቅሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከጦርነቱ በፊት በመቀሌው ዲስትሪክት ብቻ በዓመት ከ87 ሚሊዮን ብር በላይ ዓረቦን ገቢ ያገኝ እንደነበርም ከሥራ አስፈጻሚው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የድርጅቱ ቅርንጫፎች አገልግሎት ሳይሰጡ ቆይተዋልና ከጦርነቱ በፊት ዋስትና ተገብቶላቸው ጉዳት የደረሰባቸው ንብረቶች ቢኖሩ እንዴት እንደሚስተናገዱ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ለጦርነት የተሰጠ የመድን ሽፋን ሳይኖር በጦርነቱ ጉዳት ላደረሰባቸው ደንበኞች የንብረት ካሳ ሊከፈል አይችልም ብለዋል።

‹‹ጉዳት የደረሰው በጦርነት ነው፡፡ ጦርነት ደግሞ በውላችን የሚሸፈን አይደለም፤›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነገር ግን ከጦርነት በዘለለ የደረሱ አደጋዎች ኖረው አደጋውን በወቅቱ ለማሳወቅ ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ያጋጠማቸው አሳማኝ ማስረጃ ካቀረቡ ማስተናገድ የሚቻልበት ዕድል እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በትክክል የደረሰው አደጋ በውላችን መሠረት ሽፋን የሰጠንበት እስከሆነ ድረስ ውሉ ፅኑ በነበረበት ጊዜ ለደረሰው ኢንሹራንስ ነክ አደጋ የምናስተናግድበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፤›› ብለዋል፡፡ ምክንያቱም አንድ ደንበኛ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት አደጋውን ማሳወቅ ካልቻለ ያንን ግምት ውስጥ ማስገባት መስተናገድ ይኖርበታል ተብሎ ስለሚታሰብ ከጦርነቱ ውጭ ባለ አደጋ ለተሰጠ ሽፋን ካሳ ሊከፈልበት እንደሚቻል አመልክተዋል፡፡

ይህንንም ጉዳይ በምሳሌ ያስረዱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ‹‹ለምሳሌ አንድ ሰው የሕይወት ዋስትና ተሰጥቶት በሕመም ምክንያት ሲሞት ይህ መረጃ በሚገባ ተጠናክሮ ተቀምጦ ከሆነ እኛ ታሞ መሞቱን የማረጋገጥ ሥራ ነው እንጂ ተገቢውን ካሳ እንከፍለዋለን፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ አደጋው በደረሰ ጊዜ በወቅቱ አደጋውን ሪፖርት ያላደረገው መንገድ ዝግ በመሆኑ፣ ጦርነት ስላለ ወይም በየትኛውም የመገናኛ ዘዴ መገናኘት የማይቻልበት ሁኔታ ከተፈጠረ አስገዳጅ ሁኔታው ታይቶ ወይም የተፈጠረውን አስገዳጅ ሁኔታ ማረጋግጥ ከተቻለ ካሳ የሚከፈልበት ዕድል ሊኖር እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡ 

ስለዚህ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ጦርነት ዋስትና የተገባለት ንብረት ጦርነት ኢንሹራንስ የሚሸፍን ውል ካለ በዚያ የሚስተናግድ ሲሆን፣ ጦርነትን የሚሸፍን ውል ከሌለ ግን ካሳ መክፈል እንደማይቻል አመልክተዋል፡፡ ከጦርነት መለስ ላሉና መድን ድርጅት በሰጠው ሽፋን መረጃ እስከቀረበ ድረስ  ተገቢው ካሳ ይከፈላል ብለዋል፡፡ 

ድርጅቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ተዘግተው የቆዩ ቅርንጫፎቹን ሥራ ለማስጀመር የብሔራዊ ባንክ ይሁንታና የባንኮች ሥራ መጀመርን እየተጠባበቀ እንደሆነ አስታወቋል፡፡

ድርጅቱ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በመቀሌ ዲስትሪክት ሥር የነበሩ ስድስት ቅርንጫፎች አገልግሎት ያቋረጡ ሲሆን፣ በእነዚህ ቅርንጫፎች ለሰጠው የመድን ሽፋን ያገኝ የነበረው የዓረቦን ገቢ ተቋርጦ ቆይቷል፡፡ አሁን ግን በመንግሥትና በሕወሓት መካከል የሰላም ስምምነት ከተደረገ በኋላ አገልግሎቱን መልሶ ለማስጀመር ስለመዘጋጀቱ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሥራ እንዲጀመር ካሳወቀና ባንኮች ሥራ ሲጀምሩ የኢትዮጵያ መድን ድርጅትም አገልግሎቱን እንደሚጀምር የገለጹት ኃላፊው፣ ሥራውን የሚጀምረው በቅርንጫፎቹ ላይ ኦዲት ካደረገ በኋላ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

ሌሎች የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ውሳኔን እየጠበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ካነጋገርናቸው መካከል የኅብረት ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ መሠረት በዛብህ በጦርነቱ ምክንያት የተዘጉ ቅርንጫፎችን መልሶ ማስጀመር የሚሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች