Wednesday, February 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ብዙ ጊዜ ትኩረት የማንሰጠው ችግር በቤተሰብ ውስጥም ሆነ በሥራ አካባቢ እየገጠመን ነው፡፡ እኔም ከመኖሪያ ሠፈሬ ጀምሮ እስከ መሥሪያ ቤቴ ድረስ ግራ የሚያጋቡ ሰዎች ያጋጥሙኛል፡፡ በቅርቡ እንደተለመደው ከጓደኞቼ ጋር ምሳ ለመብላት ወደ ምናዘወትረው ምግብ ቤት እንሄዳለን፡፡ አስተናጋጁ ትዕዛዛችንን ተቀብሎ ከሄደ በኋላ እጄን ለመታጠብ ወደ ውስጠኛው ክፍል ስዘልቅ፣ እጅ መታጠቢያው አጠገብ ከቆመ አንድ ሰው ጋር ተገጣጠምን፡፡ ይህን ሰው ድሮ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስለማውቀው ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡ ከዚያም እንደተለመደው የት ጠፋህ ከተባባልን በኋላ እጃችንን ታጥበን ስንመለስ ጠጋ ብሎኝ፣ ‹‹ምሳህን በልተህ ስትጨርስ ቡና እየጠጣን እናወራለን…›› ብሎኝ ወደ በረንዳው ወጣ፡፡

እኔም ከጓደኞቼ ጋር ምሳዬን በልቼ ከጨረስኩ በኋላ ሰውዬውን ለማነጋገር ወደ በረንዳው ሄድኩ፡፡ አጠገቡ ደርሼ ወንበር ስቤ ከተቀመጥኩ በኋላ ቡና አዞልኝ ወሬ ጀመርን፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ የሰውዬው አነጋገር ተለወጠብኝ፡፡ እየተንጠራራ ወደ ምግብ ቤቱ ውስጥ እያየ፣ ‹‹አየህ ይከተሉኛል…›› አለኝ፡፡ እኔም ደንግጬ፣ ‹‹እነ ማን ናቸው?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ ‹‹ሞሳድና ሲአይኤ ናቸው የሚከታተሉኝ…›› ሲለኝ እኔው ራሴ በረገግኩኝ፡፡ ከእነሱ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት እንዳለው ጠየቅኩት፡፡ እሱ እንደሚለው ላለፉት ሦስት ዓመታት ሞሳድና ሲአይኤ እንደሚከታተሉት፣ ምክንያታቸው ደግሞ እሱ በምርምር ያገኘውን ሳይንሳዊ ዕውቀት አፍነውት በመውሰድ ሊቀሙት እንደሆነ ነው፡፡ የሆነ ነገር ጠረጠርኩ፡፡ ይህ ሰው የአዕምሮ ኹከት ደርሶበታል ማለት ነው፡፡

እንደ ምንም አባብዬና መክሬው ከተሰናበትኩት በኋላ የገጠመኝን ነገር ለጓደኞቼ ስነግራቸው ተገረሙ፡፡ አንደኛው ጓደኛችን ግን ምንም አልገረመውም፡፡ እንዲያውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተወሰኑ ሰዎች ይህንን ዓይነቱን በመንፈስ ጭንቀት የተሞላ ችግር እንደሚያንፀባርቁ ነገረን፡፡ እሱ እንደ ነገረን በአንድ ትልቅ ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ ደመወዝ ተከፋይ የሆነች የአጎቱ ልጅ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማንንም ሰው ትጠራጠራለች፡፡ ወንድምና እህቶቿ፣ ጓደኞቿና አብረዋት የሚሠሩ ሰዎች በእሷ ላይ እንደሚነጋገሩ፣ እንደሚዶልቱባትና ወንጀለኛ እንደሚያደርጓት ስለምታስብ ጠልታቸዋለች፡፡ ‹‹አሳልፈው ሊሰጡኝ ነው…›› እያለች በማስቸገሯ የአዕምሮ ሕክምናና ፀበል መጀመሯን ነገረን፡፡ በመጠኑ ሻል እያላት ቢሆንም አሁንም ሙሉ ለሙሉ ጤነኛ ናት ለማለት እንደማያስደፍር በሐዘን ሲነግረን ተገረምን፡፡

ከሌላ የሰማሁት በማለትም በአንድ ወቅት በተግባቢነቱና በተጫዋችነቱ የሚታወቅ ሰው ለጓደኞቹ መንግሥት ስልኩን እንደጠለፈበት፣ በሚንቀሳቀስበት ቦታ ሁሉ ካሜራ እንዳዘጋጀበት፣ በየሄደበት ሥፍራ ሁሉ የሚከተሉት እንዳሉ በመግለጽ ግራ አጋባቸው፡፡ አንተ ምን ስለሆንክ ነው ክትትል የሚደረግብህ ተብሎ ሲጠየቅ ምክንያቱን መናገር አይችልም፡፡ ብቻ የሚያውቀውም ሆነ የማያውቀው ሰው ሲመጣ በእሱ ላይ የተላከ ሰላይ፣ ወይም ተከታታይ እየመሰለው ሲደናበር ጨርሶ ለይቶ አበደ በማለት ነገረን፡፡ ይህ ሰው ፈጽሞ ሊሻለው ባለመቻሉ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን አከለልን፡፡ ጭንቀት ሰው እንደሚገድል ስለማውቅ የአዕምሮ መዛባት ያለባቸው ወገኖቻችን ጉዳይ በጣም ያሳስባል፡፡

ይህንን እየተነጋገርን ሳለ አንድ ጓደኛችን ምሳ ለመብላት መጥቶ ተቀላቀለን፡፡ ምሳውን እየበላ የውይይታችንን ርዕስ ሲረዳ እሱም በቅርቡ የገጠመውን ነገረን፡፡ ሰውየው ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነው፡፡ የራሱ የንግድ ድርጅት ሲኖረው በጣም ጥሩ የሚባል ኑሮ አለው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ቤተሰቡንም ሆነ በድርጅቱ ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞችን እየበጠበጠ ነው፡፡ ሥራ ላይ እያለ ድንገት ሾፌሩን ይጠራና በአስቸኳይ ቤት ሄዶ ከሚስቱ ጋር ማን እንዳለ እንዲያይ ይነግረዋል፡፡ በዚህ ትዕዛዝ የደነገጠው ሾፌር ቤት ሄዶ ስለጉዳዩ ለሚስትየው ይነግራታል፡፡ እሷም እዝን ብላ፣ ‹‹እሱ እኮ ታሟል፡፡ ታከም ወይም ፀበል ሂድ ስንለው ደግሞ ይቆጣል…›› ትለዋለች፡፡ የጨነቀው ሾፌር ቢሮ ተመልሶ ማንም ሰው እንደሌለ ሲናገር፣ ሰውየው ሽጉጡን አውጥቶ መጮህ ሲጀምር ቢሮው ተተራመሰ፡፡ በስንት እግዚኦታና ልመና እንዲረጋጋ ቢደረግም፣ የሰውየው ድርጊት አሁንም ቀጥሏል አለን፡፡ ይህ እኮ እጅግ በጣም አስደንጋጭ ነው፡፡

ይህ ጓደኛችን የአንዲት የቤት እመቤት ተመሳሳይ ድርጊትን እንዲህ በማለት ተረከልን፡፡ ሴትየዋ ባሏ በገባ ቁጥር ልብሱን ትፈትሻለች፡፡ ኮቱን፣ ሱሪውንና ሸሚዙን አገላብጣ ታያለች፡፡ የሰውነቱን ክፍሎች በጥንቃቄ ትመረምራለች፡፡ ይኼ የተለመደ የየዕለት ተግባሯ ነው፡፡ ከጀማመራትም ስድስት ወራት ሞልተዋል፡፡ ባልየው ለምን እንዲህ እንደምትሆን ደጋግሞ ቢጠይቃትም አትናገርም፡፡ አንድ ቀን ግን አባቷን፣ የገዛ ወንድሙንና እናቱን አስጠርቶ ሲጠይቃት፣ ‹‹በእህቶቼ ስለምጠረጥርህ ነው…›› ስትለው ሁሉም ደነገጡ፡፡ ይህ የጤና አይደለም በማለት ፀበል እንደወሰዷት ነገረን፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ሲያጋጥሙን ዘመዶቻቸው ወይ ፀበል አሊያም ወደ አዕምሮ ሕክምና ማዕከላት መውሰድ እንዳለባቸው መምከር እንዳለብን ተግባባን፡፡

እባካችሁ ይህ ዓይነቱ አሳዛኝ ነገር ሲያጋጥማችሁ ከመሳቅ ወይም ከመገረም ይልቅ፣ ለመፍትሔው እናስብ፡፡ ‹ክትትል እየተደረገብኝ ነው፣ በመኪና ያሳድዱኛል፣ በካሜራ ዙሪያዬን ተከብቤያለሁ፣ ስልኬ ተጠልፎብኛል፣ ባለቤቴ ከሌላ ሰው ጋር ይወጣል ወይም ትወጣለች፣ ሊያጠፉኝ የሚያሴሩ አሉ…› ወዘተ. በማለት የምናውቃቸው ሰዎች ሲነግሩን፣ ችግሩን ከሥነ ልቦና አንፃር በማየት ዕርዳታ የሚያገኙበትን መንገድ እናመቻች፡፡ ይኼ ችግር በጣም እየተበራከተ ነው፡፡ በሌላ በኩል አደንዛዥ ዕፅ የሚጠቀሙ ሰዎች በጣም ስለበዙ ችግሩ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን፣ መንግሥትና ማኀበረሰቡ በቅንጅት መሥራት አለባቸው፡፡

እኔማ አንዳንዴ ፖለቲካው ውስጥ ገብተው ችግር የሚፈጥሩ ሰዎች የዕብድ ባህሪ የሚያሳዩን አንድም አደንዛዥ ዕፅ እየተጠቀሙ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የማናውቀው የአዕምሮ ሁከት ሰለባ ሆነው ይመስለኛል፡፡ ሰው በጤናው መቼም አገር እየበጠበጠ ለሕዝብ ዕልቂት አይደግስም፡፡ አገር አማሾችን የጤናና የምስክር ወረቀታችሁን ካላመጣችሁ በስተቀር ፓርቲ መመሥረትም ሆነ አባል መሆን፣ ወይም በምርጫ ለመወዳደር ብቁ አትሆኑም ቢባል ምንኛ መልካም ነገር ነበር፡፡ ጤና አጥተው ጤና የሚነሱን እኮ ወደው ላይሆን ይችላል፡፡ የቸገረ ነገር ሲያጋጥም ምን ይባላል ታዲያ! 

(ናኦድ ፍቅሬ፣ ከለቡ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...

ንግድ ባንክ ከቪዛና ማስተር ካርድ ጋር ተደራድሮ ያስጀመረው የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂና ፋይዳው

ከውጭ ወደ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መጠን...

ይኼ አመላችን የት ያደርሰን ይሆን?

እነሆ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ። ‹‹አዳም ሆይ በግንባር ወዝ ትበላለህ››...