Sunday, February 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉዜጎችን አገር አልባ አድራጊው የከተማ መሬት ዘረፋ

ዜጎችን አገር አልባ አድራጊው የከተማ መሬት ዘረፋ

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

በእሑድ ኅዳር 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ዕትም፣ ‹‹ከመሬት ለአራሹ ወደ ደላላ የዞረው ፖለቲካ፤›› የሚል በታሪክ ድርሳናት፣ በዘርፉ ምሁራንና ትንታኔ የዳበረ ጽሑፍ ቀርቦ ተመልክቻለሁ፡፡ እንዲህ ያሉ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑና መሠረታዊ የሕዝብ ጥቅምን የሚነኩ አጀንዳዎች መነጋገሪያ እንዲሆኑ መደረጉ ይበል የሚሰኝ ነው፡፡ መንግሥትም በትኩረት ሊመለከታቸው ይገባል፡፡ እናም ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው የሚል የግል እምነት አለኝ፡፡

አሁን ባለው አገራዊ ሁኔታ (ግጭትን ከማስቆምና ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ዜጎችን የመታደግ ዕርምጃዎች አንፃር) ትኩረት ሳይሰጠው በመቆየቱ እንጂ፣ ሁለንተናዊውን አገራዊ ችግር ያባባሰው ይኸው የመሬት አስተዳደር ብልሽት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በተጠቀሰው ጽሑፍ ላይ እንደተቀመጠው ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሬት ‹‹የሕዝብም የመንግሥትም ሳይሆን፣ የደላላና የሌባ አመራሮች ሆኗል፤›› እስከማለት ያስደፈራቸው፣ ከመንግሥት ቁጥጥር በላይ የሆነ ችግር ስለሆነባቸው ነው፡፡ ፈጣንና ጠንካራ ማሻሻያ ካላገኘም ውጤቱ መክፋቱ አይቀርም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በመሠረቱ መሬት የከተማም ይባል የገጠር በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ ድርሻ ያለው ሀብት ነው፡፡ ዛሬ በቻ ሳይሆን ትናንትም ሆነ ነገ ይህ እውነታ በቀላሉ ሊቀየር እንደማይችልም የታመነ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያው ደግሞ ከፊውዳላዊው ሥርዓት ጥቅምን የማስከበር ፍልሚያ አንስቶ፣ በወታደራዊው የሶሻሊስት መንግሥት (የመሬት ለአራሹ) የመደብ ትግል የተፋፋመው በዋናነት መሬት ላይ ተንተርሶ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ባለፉት ሰላሳ ሦስት ዓመታት የተከተልነው ብሔር ተኮር ፌዴራላዊ ሥርዓትም ቢሆን በዋናነት የማንነት አጀንዳ አራማጅ ይምሰል እንጂ፣ ውስጣዊ ፍትጊያው በወሰንና በመሬት ላይ መሆኑን መካድ ያዳግታል፡፡

ለዚህም ነው ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የነበሩትና ያሉት መንግሥታት ላያድኑትና ምርታማም ላያደርጉት መዳፋቸውን ከመሬት ላይ የማያነሳ ፖሊሲ ሲከተሉ የቆዩት፡፡ ባለፉት ዓመታት በአገራችን በተካሄዱ የተለያዩ ምርጫዎችና የፖለቲካ ፓርቲ ክርክሮች ወቅትም፣ “መሬት የሕዝብና የመንግሥት” ወይም “የግል” ነው በሚለው ጭብጥ ላይ ሰፋፊ ሐሳቦች ሲሰነዘሩ ነበር የቆዩት፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን መሬት ዛሬም ቢሆን የግጭት፣ የዘረፋና የኢፍትሐዊነት መገለጫ እንጂ የብዙኃኑ መጠቀሚያ መሆኑን በውል ማረጋገጥ እየተቻለ አይደለም፡፡

እሱ ብቻ ሳይሆን አገሪቱን ለ27 ዓመታት የመራው ሕወሓት/ኢሕአዴግ ይከተል የነበረውን የመሬት ፖሊሲ (መሬት የሕዝብ ቢሆንም፣ በመንግሥት ባለቤትነት መተዳደር አለበት የሚለውን ዕሳቤ) ላለመቀየር “በመቃብሬ ላይ” ካልሆነ አልደራደርም እስከ ማለት ደርሶ ነበር፡፡ በገቢር ግን በተደራጀ መንገድ በፈጠራቸው ጥገኞች ሰፋፊ የእርሻ መሬትን በመቀራመት (በተለይ በጋምቤላ፣ በሶማሌ፣ በቤንሻንጉልና በኦሮሚያ ቆላማ አካባቢዎች) እዚህ ግባ የሚባል ውጤት ሳይታይ፣ ለልማት ባንክ ብድር ብክነትና ዘረፋ ምክንያት አድርጎት ቆይቷል፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ የከተሞች መሬትም ያለበቂ ካሳና ምትክ ጥገኛ ባለሀብት ተብዬ፣ አመራሩና ደላላው የሚመዘብረው ሀብት አድርጎት እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ወራሹ የብልፅግና ፓርቲም ቢሆን እንኳንስ በዋነኛው የመሬት ፖሊሲ ላይ ቀርቶ፣ በሌሎች አነስተኛ የሕገ መንግሥት አናቅጽት ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ቢያንስ ምክክር ባለመጀመሩ ችግሩ ተባብሶ ይገኛል፡፡ በአንድ በኩል በክልሎች በእርሻ ሥራ ላይ የተመሠረተ የግል ባለሀብቱ እንቅስቃሴ ከመዳከሙ ባሻገር (ከክልሌ ውጣ የሚለው ጫና ቀላል ነቀርሳ አልሆነምና)፣ የአርሶ አደሩ ምርታማነት ስለመጨመሩም አልተረጋገጠም፡፡ በሌላ በኩል አዲስ አበባን በመሰሉ ከተሞች መሬት ያለከልካይ በመዋቅሩና በደላላ አሻጥር ሲዘረፍ፣ ዜጋው ቤት ለመሥራት እንኳን የማያገኘው ህልም ሆኗል (ከ30 እና 40 ዓመታት በፊት በወል የተያዘ የሕዝብ መሬትስ ለግለሰቦች መልሶ ተሰጠ በሚል የሚታጠረው በየትኛው አሠራርና ሕግ መሠረት ነው?!)፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት የአገራችን ተቃዋሚዎች በተቀራራቢነትና በአንድ ድምፅ ‹‹መሬት የግለሰብ አርሶ አደሩ (የዜጎች) መሆን አለበት፡፡ የመሸጥ፣ የመለወጥ፣ የማከራየት፣ የማልማት ጉዳይ የገበሬው ብቻ መሆንም አለበት፡፡ መንግሥት በመሬት ጉዳይ እጁን ማስገባት ወይም ጣልቃ መግባት የለበትም…›› ይሉ ነበር፡፡ ለአባባሉ ምክንያታቸውም አሁን የሚታየውን መዋቅራዊ ዘረፋ ለማስቀረት ብቻ ሳይሆን፣ መንግሥት መሬት ሰጪና ከልካይ ሆኖ በዜጎች ላይ ፖለቲካዊ ጫና ማሳደሩን ለመግታት እንደነበር እናስታውሳለን፡፡

ገዥው ፓርቲ ከዚህ በፊት በቀረፀውና በተግባር እየታየ ባለው ሕገ መንግሥትና የመሬት ፖሊሲ መሠረት፣ ‹‹መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው፣ አይሸጥም… አይለወጥም…›› ብሎ ሲከራከር ሀብቱ የተደቀነበትን አሻጥርና የእጅ አዙር ብዝበዛ እንኳን ለማስታወስ አይሞክርም ነበር፡፡ ምንም እንኳን በ2010 ዓ.ም. የሕዝቡ ምሬትና ቁጣ ገፍቶ ሲመጣ በዕውር ድንብር የተሃድሶ ግምገማ ነጥብ ቢያደርገውም፡፡ እናም አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጉዳዩን ማንሳት ብቻ ሳይሆን፣ ፖለቲካዊና ሳይንሳዊ ዕርምት እንዲያገኝ ነው መትጋት ያለባቸው፡፡

ተፎካካሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ገለልተኛ ምሁራንም፣ ‹‹አሁንም ቢሆን መሬት በቀጥታና በእጅ አዙር እየተሸጠ ነው፡፡ ገበሬው አይሽጥ እንጂ መንግሥት መሬቱን እየሸጠ ነው…›› ሲሉ በማሳያ ይከራከሩ እንደነበር ወደኋላ ማስታወስ አይገደንም፡፡ የገዥው ፓርቲና የመንግሥት ሰዎችም ‹‹መሬት እየተሸጠ አይደለም፣ ይህ ፈጽሞ ሐሰት ነው፣ መሬት በኢትዮጵያ አይሸጥም አይለወጥም፣ በእኛ መንግሥት ፖሊሲ መሠረት መሬት በይዞታነት የሚተላለፈው በሊዝ ነው፤›› ብለው ሲከራከሩ የማይታዘብ አልነበረም፡፡ አሁን ደግሞ ጭራሽ ሊዙም ቀረና በብሔር ካባ አጭበርባሪ ግለሰቦች እየተደራጁ የሚቸረችሩትና የሚፋንኑበት ሆኖ በመታየት ላይ ነው፡፡

በክልሎችና በገጠር ሰፋፊ የእርሻ መሬት በመንግሥት ዕይታ ሥር ለአገር ውስጥ ባለሀብቶችም ሆነ ለውጭ ኢንቬስተሮች በሊዝ መሸጡ ክፋት ላይኖረው ይችላል፡፡ በእኛ አገር ብቻ ዕውን የሆነ አሠራር አለመሆኑን መገነዘብም ይገባል፡፡ በአንዳንድ አገሮች የእኛን አገር ጨምሮ መሬት የመንግሥት መሆኑና የማይሸጥና የማይለወጥ መሆኑ፣ በሕገ መንግሥታቸው ላይ መሥፈሩም የሚታወቅ ነው፡፡ ግን በምን ዓይነት ሥልትና ዘዴ፣ በእንዴት ያለ ቴክኖሎጂና ፍትሐዊነት ማረጋገጫ መሣሪያ ነው የሚፈጸመው ማለት ነው የሚበጀው፡፡

እዚህ ላይ የሚነሳው ቁምነገር በተለይ የአርሶ አደሩን መሬት በብጥስጣሽ አጠቃቀም ምርታማነቱን ከማዳከም ለማውጣት እየተወሰዱ የነበሩ ዕርምጃዎች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ አሁንም በአንዳንድ ክልሎች እየተሠራባቸው ነው፡፡ ለአብነት ያህል ግብርናና ገጠር ልማቱ ራሱን ከመቻል አልፎ ለአገሪቱ አጠቃላይ ዕድገትና ልማት የሚያደርገውን ግብዓት እንዲያመነጭ ለማድረግ፣ ኩታ ገጠም የሆነ መሬት ያላቸው ገበሬዎች ተቀናጅተው በዘመናዊ የግብርና ዘዴ እየተጠቀሙ እንዲያርሱ የማድረጉ ጅምር ነው፡፡ ተጠናክሮ መቀጠልም አለበት፡፡

የከተሞች መሬት ይዞታ ጉዳይ ግን መንግሥትንም እያሳሰበው እንደመጣው ለአደገኛ ኢፍትሐዊነት፣ አልቦ ዜግነት ተጠቃሚነትና ሙስና እየተጋለጠ ነው፡፡ ዛሬ አዲስ አበባን ጨምሮ በብሔር የተደራጁት ክልሎችና የፖለቲካ መሪዎቻቸው ዋነኛ የመሬት አዛዦች ናቸው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች በነፃ ገበያ አሠራር የሊዝ ጨረታ ቢካሄድም፣ በአብዛኛው ክልል ከተሞች በአስተዳደሩ ፈቃድ ለተሰጣቸው ለቤት ሥራ ማኅበራት ብቻ መሬት ተቆንጥሮ የሚሰጥበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በዚህ አሠራር ደግሞ ቀዳሚው መሥፈርት ብሔር እንጂ ዜግነት አይደለም፡፡

አደጋው ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በአዲስ አባባ ለሚኩራ በሚባለው ክፍለ ከተማ ብቻ እንደታየው፣ በመቶ ሺዎች ካሬ ሜትር የሚቆጠር የወልና የግል መሬት ላይ (ሕጋዊ የሚመስል የማጭበርበሪያ ካርታና ሰነዶች እየተዘጋጀ) ከፍተኛ ዘረፋ ተፈጽሟል፡፡ ለወራት ያህል በሕዝቡ ውስጥ ውስጡን ሲነገር እንደተደመጠው፣ ጥቂቶች በነባር ባለቤትነት ይዞታ ስም (መሬት ባንክ የገባና ካሳ የተከፈለበትን የወል መሬት ሁሉ) በመቶዎች ካርታ አስወጥተው በሚሊዮን ብር ቸብችበዋል፡፡ ሊዚህ ደግሞ በመሬት ዘርፍ  ላይ ያሉ ባለሙያዎችና አመራሮች ዋነኛ ሸሪኮቻቸው ነበሩ፡፡ በሁሉም ክፍላተ ከተሞች በመሬት ጉዳይ ያለእጅ መንሻ ሥራ መከናወኑን ማን በድፍረት ሊናገር ይችላል?

ከጥቂት ጊዜያት በፊት በወር ደመወዛቸው ውሎ ለማደር ሲቸገሩ የነበሩ አንዳንድ የመዋቅሩ ሰዎች (በተለይ ባለሙያዎች)፣ ዛሬ “ሪቮሊሽን”ን ጨምሮ በድፍረት የአራትና አምስት ተሽከርካሪ ባለቤት፣ ባለቪላና ሕንፃ ብቻ ሳይሆኑ፣ ማሽን አከራይ ብሎም በአንድ ምሽት ሃምሳና መቶ ሺሕ ብሮች የሚያጠፉ ቅንጡዎች ለመሆን የበቁት ያለጥርጥር በሕዝብ ገንዘብ ዘረፋ አይደለምን!? አስገራሚው ነገር ደግሞ እስካሁን ጥገኛውን ኃይል እንዴትና ከየት አመጣህ የሚለው ሃይ ባይ አለመታየቱ ነው (እዚህ ላይ የመሬት ሙስናን መታገል፣ ሲጎዳ የኖረውን የአካባቢው አርሶ አደር ጥቅም እንደ መጋፋት እያስመሰሉ የሚነዙት ፖለቲካዎችም ዘረፋውን ለማጧጧፍ እንደነበር ልብ ይሏል)፡፡

በእርግጥ መንግሥት ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በተጀመረው ለውጥ ሒደት ለመረጋጋትና ለልማት ትኩረት ለመስጠት የሚችልበት ዕድል በስፋት ባያገኝም፣ የለውጥ ኃይሉ የመሬት ፖሊሲን ለማስተካከልም ሆነ የሕዝብ ሀብትን ከዘረፋ ለመታደግ በቂ ጥረት ሲያደርግ አልታየም፡፡ እንዲያውም ሊዝና የቤት ግንባታን በመገደብ እጥረቱን ከማባባስ በስተቀር፡፡ እንዲያውም በነባሩ አካሄድ መሬት አይሸጥም አይለወጥም ስም፣ አንዳንዶች ባለሀብቶችና በመዋቅሩ ውስጥ የተሰገሰጉ ምንደኞች ጥፋት እንዲያደርሱ በማድረጉ ተፀፅቶ ሊያርም ይገባዋል፡፡

‹‹መሬት የሕዝብና የመንግሥት ብቻ መሆን አለበት››፣ ‹‹መሬት አይሸጥም አይለወጥም›› ይል የነበረው የቀድሞው መንግሥት፣ በሊዝ፣ በድርድርም ይባል መሬቱን በልማት ስም ነዋሪዎችን ተነሽ በማድረግ የሠራው ፍትሐዊነት የሌለው ተግባር፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የዲሞግራፊ ተፅዕኖ የጎላበት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በብዙ የኢንቨስትመንት መሬቶች ላይ ደግሞ የሥርዓቱ ሰዎች ብቻ በልማታዊ ባለሀብት ስም የተጠቀሙበት እንደነበርም ማስተባበል አልተቻለም፡፡ ይህ እውነታ ዛሬስ ምን ያህል ተቀይሯል? የመንግሥትስ የእርምት ዕርምጃ ምን ገጽታ አለው? በዘርፉ ሌብነትና ውንብድናስ ተባብሷል? ወይስ ቀንሷል? የሚለውን በጥናትና በሕዝብ አስተያየት ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

አሁን የምንገኝበት ጊዜ ከቆየንባቸው የፍጥጫ የዘረ ድምር እየወጣን፣ በፍትሐዊነትና በእኩልነት ሕዝቦች የሚኖሩባትን አገር ለመገንባት እንቅስቃሴ የሚጀመርበት ሊሆን ይገባል፡፡ መንግሥትም ምንም እንኳን ያጋጠመው የውስጥና የውጭ ተግዳሮት ከፍተኛ ቢሆንም፣ መላው የአገራችን ሕዝቦች በተለይም ምሁራንና ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በዋና ዋና ሕገ መንግሥታዊና የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ መክረው፣ በረጋና በሰከነ መንገድ ተደማምጠው የሚቀራረቡበትን ብሔራዊ መግባባት እንዲያመጡ ፍላጎት እንዳለው ይገመታል፡፡ የመሬት ሀብት ጉዳይም ምንም እንኳን ተነጥሎ የማይታይ ባይሆንም፣ ቀዳሚው ጭብጥ መሆኑ አይቀርም፡፡ የቸገረው ነገር ተግባራዊ ዕርምጃ መውሰዱ ይመስለኛል፡፡

በመሠረቱ መንግሥት የመሬት ሀብትን ጨምሮ ሁሉንም የአገሪቱ ሕዝቦች ሀብትና ንብረት ጠብቆና ተቆጣጥሮ ብቻ ሳይሆን፣ በፍትሐዊነት አልምቶና አስፋፍቶ ለትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ ነው ያለበት እንጂ፣ ማንም ዘራፊና ጥገኛ በተናጠልም ሆነ እየተደራጀ እንደ ግሪሳ እንዲዘምትበትና በኋላም ሕገወጡን ሀብት አገር ለማፍረስ ዓላማ እንዲያውለው መደረግ የለበትም፡፡ ከዚህ አንፃር ለወደፊቱ ብቻ ሳይሆን ባለፉት ዓመታትም በተፈጸሙ ወንጀሎች ላይ ምርመራ ተደርጎ ማስተካከል የሥርዓቱ ግዴታ መሆን አለበት፡፡

እውነት ለመናገር መንግሥት የምግብ እጥረትን ለማስወገድ፣ ሥራ አጥነትን ለመቀነስ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማስገኘት፣ ለአጠቃላዩ ዕድገትና ልማት የሚሆን የካፒታል አቅም ለማመንጨት፣ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን አቅርቦት ለመጨመር፣ ወዘተ በገጠር መሬትን ለአጭር ጊዜ በሊዝ ቢሰጥ መልካም ነበር፡፡ መበረታታትም አለበት፡፡ ምንም እሴት ሳይጨመር እንዴት አንድ ካሬ ሜትር ባዶ መሬት እስከ 35 ሺሕ እስከ 40 ሺሕ ብር ለሚሸጥበት የዋጋ ግሽበት ለዳረገን ተስፋ አስቆራጭ የመሬት ደካማ ቁጥጥር ያጋልጠን የሚለው ጩኸት የብዙዎች መሆኑ መደመጥ አለበት፡፡

በዚህ ዓይነት አካሄድስ መጪው ትውልድ እንደምን አድርጎ ቤት ሊሠራና ትውልድ ሊያስቀጥል ይቻለዋል የሚለው ጥያቄም አንገብጋቢ ሆኖ እየመጣ ነው፡፡ በመግቢያው ላይ የጠቀስኩት ጽሑፍ ከአምስት አሥርት ዓመታት በፊት የመሬት ለአራሹ ጥያቄ ሲነሳ ፊውዳሊዝምንና የዛገውን የባላባት ሥርዓት ምንኛ ከሥሩ እንደነቀለው ተጠቅሷል፡፡ ያኔ የሕዝቡ ግንዛቤ ባልዳበረበት ጊዜ ያንን መነሳሳት የፈጠረው ደግሞ ድህነቱና ኢፍትሐዊነቱ ነበር፡፡ አሁንም እንዲህ ያለ የትውልድ ተስፋ ቆራጭነት ሲስፋፋ የሚያመጣው ዳፋ ግን ሄዶ፣ ሄዶ ያው መሆኑ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ለውጥ መጀመር አለበት፡፡ የግድ ነው፡፡

ከከተማም በሆነ የገጠር መሬት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ወሳኝ ነጥብ መሬት ለባለሀብት በመሰጠቱ (በመሸጡ) ነዋሪው (ዜጋው) የሚነሳበት (የሚፈናቀልበት) ሁኔታ እንዳይባባስ ጥንቃቄ የሚያሻው ጉዳይ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በተለይ በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ሲታይ በጥብቅ ሊታሰብበት እንደሚገባ መዘንጋት ትናንትን አለማስታወስ ነው፡፡ በተለይ እስካሁንም ድረስ አዲስ አበባን ለመሰሉ የከተማ መሬት የአርሶ አደሩ፣ የከተማው ነዋሪና የባለሀብቱ ፍላጎትና አቅርቦትን የሚያስታርቅ ፍትሐዊ መንግሥታዊ መዋቅር መዘርጋት ወሳኝ ፖለቲካዊ ዕርምጃ ቢሆንም፣ ሥራውን በግልጽነትና በተጠያቂነት ስለማከናወኑ ሕዝቡ መረጃ እያገኘ አይደለም፡፡ ይህም እርምት ይፈልጋል፡፡

አሁን ባለው አሠራር ለልማት ዓላማ ሲባል ሰዎች ከኖሩበት አካባቢ የሚነሱባቸው በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይህም በዓለም መሬት አቅራቢዎች ዘንድ የሚሠራበት ነው፡፡ በውስጡ ጤነኛ ያልሆነ ሴራ ካልተጠነሰሰ በስተቀር፣ አገርን ለማልማት ሲባል ዜጎች የሚከፍሉት ዋጋ ነው እንጂ ማንኛውም መንግሥት የራሱን ዜጎች ለመጉዳት ሲል የሚያደርገው የማፈናቀል ሴራ ሊሆንም አይችልም፡፡ ትናንትም ሆነ ዛሬ የተፈናቀሉ ካሉም ጉዳዩ በዚህ መንፈስ ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባል፡፡ ይህ ነው ወደፊት በጥብቅ ሊታሰብበትና መግባባት ሊያዝበት የሚገባው ሌላው ቁምነገር፡፡

ይህን በማቃናት ስምና አጠቃላይ የመሬት ሥሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ማስተካከያ እስኪያገኝ ድረስ በሚሠራባቸው ነባር አካሄዶች ስም፣ በተለይ በከተሞች ያለውን የመሬት ዘርፍ አለማስቆም ግን በታሪክም የሚያስጠይቅ ነው፡፡ በእውነት ሕዝቡንስ ምን ሊጠቅመው ይችላል? ምንደኛ ግለሰቦችን ካልሆነ በስተቀር፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት የለሽ፣ በቡድን የሚፈጸም ዘረፋና ሙስና የተስፋፋበት፣ የሥርዓቱ ሰዎች በዋናነትም ጥቂት ቱባ ባለሀብቶችና ባለሥልጣናት ያሻቸውን የሚፈጽሙበት አደገኛ አካሄድ ከተስፋፋስ እንኳን ብልፅግና አገር በምን ሊቆም ይችላል? ይህ አንገብጋቢ ጥያቄ መሆን አለበት፡፡

እሱ ብቻ ሳይሆን በቅርቡ ከተማ አስተዳደሩ (በዋናነት መንግሥት ብሔራዊ ኮሜቴ ካቋቋመ ወዲህ) በጀመረው ማጥራት እንደተረጋገጠው በከተማ፣ በወረዳና ክፍለ ከተማ ደረጃ ያሉ አመራሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች፣ እንዲሁም ደላሎችና ጥገኞች በሚሊዮኖች የሕዝብ ሀብት የሚዘርፉበት መሬት፣ በተለይም የከተማ መሬት ነው፡፡ ይህንን አገር አዳካሚና ሕዝብ አቆርቋዥ አካሄድ በሕግና ሥርዓት ለማስቆም፣ በብሔራዊ መግባባት መንፈስ በአንድነት ተነስቶ መታገል ካልተቻለ የፖሊሲ ለውጥ ገና አንጋጦ መጠበቅ ብቻ መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል መታወቅ አለበት፡፡ ሕዝቡ በንቃት ከመንግሥት ጋር ተባብሮ አገር ማዳን ይጠበቅበታል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...