Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚመራና የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ ተቋም የመመሥረት ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢንሹራንስ (መድን) ዘርፍን የመቆጣጠርና የመከታተል ኃላፊነት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወጥቶ ራሱን በቻለ አዲስ ተቋም እንዲመራ ላለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ ሲቀርብ የነበረው የዘርፉ ተዋናዮች ጥያቄ በመጨረሻ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተቀባይነት ማግኘቱ ተሰማ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቦርድ በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ፣ የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ውጪ ሆኖ፣ ራሱን በቻለ ኮሚሽን ወይም መሰል አደረጃጀት እንዲመራ የሚለውን ሐሳብ በመቀበል ውሳኔ ማሳለፉን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል።

የኢንሹራንስ ዘርፉን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ሥር ወጥቶ ራሱን በቻለ ተቋም እንዲመራ ተቀባይነት ያገኘ ቢሆንም፣ ዝርዝር ሕጋዊ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራ እንደሚቀር ምንጮቹ አክለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበር፣ እንዲሁም የመድን ዘርፍ ባለሙያዎች የኢትዮጵያ የመድን ኢንዱስትሪን የመከታተልና የመቆጣጠር ተግባር እስካሁን በብሔራዊ ባንክ ሥር ሆኖ መቆየቱ አግባብ አለመሆኑን ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡

ከዓለም አቀፍ አሠራር ውጪ የኢንሹራንስ ዘርፍ የፋይናንስ ተቋም ነው በሚል ብቻ ከባንክና ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ጋር አብሮ በብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር እንዲደረግበት፣ እንዲሁም እንዲመራ ማድረጉ ኢንዱስትሪውን ጎድቶታል የሚል ክርክርና አቤቱታ ለዓመታት ሲቀርብበት እንደነበር ይታወሳል፡፡ አሁን ግን ጥያቄው አዎንታዊ ምላሽ ማግኘቱ ለኢንዱስትሪው እጅግ ጠቀሜታ የሚሰጥ መሆኑን ያነጋገርናቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡ 

የመድን ዘርፉ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ውጪ ሆኖ በሚመሠረት ሌላ አዲስ ተቋም እንዲመራ ተፈቅዷል ከመባሉ ውጪ ተጨማሪ ዝርዝር ጉዳዩ አለመወሰኑን የሚገልጹት ምንጮቹ፣ ጥያቄው ተቀባይነት ማግኘቱ በራሱ ትልቅ ዕርምጃ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡  

የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ በሚገባው ደረጃ እንዳያድግ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ፣ ዘርፉ ብሔራዊ ባንክ ውስጥ በተቋቋመ አንድ የሥራ ክፍል (ዲፓርትመንት) ሲመራ መቆየቱ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። በዚህም ምክንያት ዘርፉ የሚገባውን ትኩረት እንዳያገኝ አድርጎታል ይላሉ።

በቅርቡ የኢትዮጵያ የመድን ሰጪዎች ማኅበር ለመንግሥት በአስቸኳይ ሊመልሱና ሊፈጸሙ ይገባቸዋል ብሎ ካቀረባቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ ይሄው የመድን ኢንዱስትሪው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወጥቶ ራሱን በቻለ ተቋም እንዲመራ የሚጠይቅ ነበር፡፡ 

የኢንሹራንስ ዘርፉን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወጥቶ ራሱን በቻለ ተቋም እንዲመራ ተወስኗል መባሉ፣ ኢንዱስትሪውን በተሻለ ወደፊት ለማራመድ የሚያስችል ስለመሆኑ የገለጹት የኢንሹራንስ ባለሙያው አቶ ፍቅሩ ፀጋዬ፣ ውሳኔው የሚጠበቅና ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ የሌሎች አገሮች የኢንሹራንስ ዘርፍ ራሱን በቻለና ከተለያዩ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በሚወከሉ ባለሙያዎች በሚዋቀር፣ ቦርድ ወይም ኮሚሽን የሚመራ መሆኑን የጠቀሱት ባለሙያው፣ በኢትዮጵያም ይህ ዓይነቱ አሠራር መከተል ተመራጭ እንደሆነ አስረድተዋል።

የኢንሹራንስ ዘርፉ ራሱን ችሎ መውጣቱ ዘርፉን በሚገባ በሚያውቁ የኢንሹራንስ ባለሙያዎች እንዲመራ ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ በእጅጉ ይጠቅማል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ከዓለም አቀፍ የዘርፉ መለኪያዎች አንፃር ሲመዘን ያላደገ መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ ፍቅሩ፣ ኢንሹራንሱ ካላደገባቸው ምክንያቶች አንዱ ደግሞ ዘርፉ ራሱን ችሎ በነፃነት እንዲመራና እንዲሠራ ማድረግ አለመቻሉ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ይህንንም በተደጋጋሚ የዘርፉ ባለሙያዎች ሲገልጹት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አሁን ግን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወጥቶ እንዲሠራ ከተደረገ፣ አጠቃላይ ኢንዱስትሪውን ሊቀይር የሚችልና ውጤት ሊያስገኝ ይችላል የሚል አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ 

ኢንዱስትሪው እንዲያድግ የኢንዱስትሪውን የልብ ትርታ በማዳመጥ፣ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጉ አዳዲስ ፖሊሲዎችን ከመቅረፅና የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ዘርፍ ፖሊሲ ኖሮት በዚያ እንዲመራ ለማድረግም ዘርፉ ራሱን ችሎ እንዲንቀሳቀስ መደረጉ አግባብ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ 

አሁን ላይ ያሉትን ኢንዱስትሪው ተግዳሮቶች በጥናትና በምርምር ላይ የተመሠረቱ መፍትሔዎችን ለመስጠት ጭምር ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ ኢንዱስትሪውን ሊለውጥ ይችላል ብለዋል።

በዓለም ላይ ኢንሹራንስ ራሱን ችሎ የባለሙያዎችና የባለድርሻ አካላት በተካተቱበት ቦርድ የሚመራ ስለመሆኑ ያስታወሱት አቶ ፍቅሩ፣ አሁንም ኢንሹራንስ ዘርፉ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይውጣ ሲባል ሊከተል የሚገባውም ይህንኑ የዓለም አቀፍ ልምድ መሆን እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡

ባንክና ኢንሹራንስን አጣምሮ ማስተዳደርና መቆጣጠር ተገቢ እንዳልነበረ የገለጹት አቶ ፍቅሩ፣ ኢንሹራንስ በባህርይው የተለየ በመሆኑ ቀድሞም ቢሆን በአንድ ጥላ ሥር ማድረግ ትክክል አልነበረም ብለዋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ቦርድ ውሳኔ ሰጠበት የተባለው ዘርፍ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወጥቶ ራሱን ችሎ ይውጣ የሚል ብቻ በመሆኑ፣ ከዚህ በኋላ ይህ ውሳኔም ሳይዘገይ ሊተገበር እንደሚባም አቶ ፍቅሩ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ከብሔራዊ ባንክ ወጥቶ ራሱን ይቻል ሲባል ምን ማለት ነው ለሚለው ጥያቄ አቶ ፍቅሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የተካተቱበት በይበልጥ በባለሙያዎች የሚመራ ቦርድ ይቋቋም ማለት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የሌሎች አገሮች ልምድ የሚያሳየው ዘርፉ በኢንሹራንስ ባለሙያዎች፣ ከዘርፉ ጋር የተያያዙ አካላት፣ ምሁራን፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ማኅበርና የመሳሰሉት በቦርድ አባልነት ተካተው የሚመሩት በመሆኑ፣ በኢትዮጵያም ይህንኑ ዓለም አቀፍ ልምድ ወስዶ በመቀመር ተግባራዊ ማድረግ ተመራጭ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያም ዘርፉን ከሚመለከቱ አካላት የሚውጣጡ ምሁራንን ያካተተ ቦርድ መሰየም እንደሚቻል የሚያስረዱት ባለሙያው፣ በዚህ ቦርድ ውስጥ እንደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና የገንዘብ ሚኒስቴር ያሉ ተቋማት መንግሥትን ወክለው የሚገቡበት አደረጃጀት መፍጠር እንደሚቻል አስረድተዋል። ባለሙያው አቶ ፍቅሩ እንደሚሉት፣ ይህ ዓይነቱ አወቃቀር ሥራውን ለማቀላጠፍ፣ እንዲሁም ወደሚፈለገው የዕድገት ግብ ለመድረስ የሚያግዝ ነው፡፡ ቦርዱን ገለልተኛ ሆኖ በማዋቀር የቁጥጥር ሥራው ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ በሚረዳ መልኩ ለማከናወን እንደሚያስችል አመልክተዋል፡፡  

ኢትዮጵያ ራሱን የቻለ የኢንሹራንስ ፖሊሲ የሌላት መሆኑ ራሱ ለዘርፉ ትኩረት መነፈጉን የሚያሳይ በመሆኑ፣ እንደተባለው ዘርፉ በራሱ ቦርድ ከተመራ ኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ፖሊሲ ኖሯት ግብ ተቀምጦ እንዲሠራ ዘርፉም ትኩረት እንዲያገኝ የተወሰነው ውሳኔ አጋዥ ይሆናል ብለዋል፡፡ ነገር ግን ውሳኔውን ተከትሎ ለዚህ የሚሆን ሕግ የማዘጋጀቱ ሥራ በቶሎ መጀመር እንዳለበት ጠቅሰዋል፡፡ 

በዚህ በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተውም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስፈላጊነት በማመን ይሁንታ የሰጠ ሲሆን፣ ዝርዝር ጉዳዩ ላይ ግን ተጨማሪ ውሳኔ የሚሰጥበት እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ 18 የሚሆኑ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ያሉ ሲሆን፣ እነዚህ ኩባንያዎች ዓመታዊ የዓረቦን ገቢያቸውን ከ16 ቢሊዮን በላይ አድርሰዋል፡፡ ሆኖም ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች አንፃር ሲታይ፣ የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለ ሲሆን፣ ለአገራዊ ምርት ዕድገት ያለው አስተዋጽኦም ከአንድ በመቶ በታች መሆኑ እየተጠቀሰ ቆይቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች