Wednesday, April 17, 2024

የትጥቅ  መፍታት ሒደትና የሰላም እንቅፋቶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የትግራይ ተራሮች ከጦር መሣሪያ ጩኸት የተገላገሉ ይመስላል፡፡ በየምሽጉ አድፍጠው የቆዩ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ጥለው ሲወጡ መታየት ጀምሯል፡፡ የሕወሓት ኃይሎች የሰላም ስምምነቱን ቢፈርሙም፣ በተጨባጭ ትጥቃቸውን ፈተው ለስምምነቱ አይገዙም የሚለው ግምት በተቃራኒው ሲሆን እየታየ ይመስላል፡፡ የሕወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ ፈተው ለስምምነቱ እየተገዙ መምሰላቸው፣ በትግራይ ቴሌቪዥን ጣቢያና በተለያዩ የዜና አውታሮች በምሥል ተደግፎ ከሰሞኑ መዘገቡ ትልቅ ዜና ሆኗል፡፡

ይህ ትጥቅ የመፍታት ጅማሮ የሰላም ስምምነቱን በተግባር የመተርጎሙን ጥረት ከዳር ያደርሰው ይሆን ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች በመነሳት ላይ ናቸው፡፡ የሕወሓት አማፂያን እንዴት ትጥቅ ሊፈቱ ወሰኑ በማለት ጉዳዮን በጥርጣሬ የሚመለከቱ እንዳሉ ሁሉ፣ ዕርምጃውን ትልቅ የሰላም ድል አድርገው የተቀበሉም አሉ፡፡

በሌላ በኩል የትጥቅ መፍታት ሒደት መጀመሩ ለሰላም ሒደቱ የሚፈይደው ነገር የለም የሚሉም አሉ፡፡ የሰላም ሒደቱን ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር እንቅፋት የሆኑ ችግሮች ባልተነኩበት፣ ትጥቅ መፍታት ትርጉም እንደማይኖረው እነዚህ ወገኖች እየተናገሩ ነው፡፡

የወልቃይትና የራያ አካባቢዎች ጥያቄ፣ ከመከላከያ ውጪ ያሉ የታጠቁ ኃይሎች ከትግራይ ክልል ሊወጡ እንደሚገባ የሚነሳው ጥያቄ፣ እንዲሁም የኤርትራ ጦር ከትግራይ ክልል ሊወጣ ይገባል የሚለው ጥያቄ ትጥቅ የመፍታት ሒደቱን ሊቀድም ይገባል በማለት የሚሞግቱ አሉ፡፡

ከዚህ በተቃራኒው ግን የሰላም ስምምነቱ ያለ ቅድመ ሁኔታ ወደ ትጥቅ መፍታት ምዕራፍ መሸጋገሩ፣ ለትግራይ ክልል ሕዝብም ሆነ ሰላምን ለሚናፍቁ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ትልቅ ተስፋን የሚሰጥ ዕርምጃ መሆኑን ብዙዎች እየገለጹ ነው፡፡

የሕወሓት መሪ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ ‹‹የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን እንፈልጋለን›› በማለት መናገራቸው ከሰሞኑ ተዘግቧል፡፡ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹የትግራይ መንግሥትና ሠራዊት ለስምምነቱ ተግባራዊነት በርካታ ሥራዎች እየሠሩ ነው፤›› ብለው መናገራቸው ተዘግቧል፡፡ የሚፈጠሩ ችግሮችም ካሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱና ሁሉም ኃይል ኃላፊነቱን እንዲወጣ  መጠየቃቸውም ተነግሯል፡፡

በኬንያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጄኔራል ባጫ ደበሌ ከሰሞኑ በዙም ስብሰባ ላይ ተናገሩት የተባለው መረጃ ደግሞ፣ የሰላም ስምምነቱ ወሳኝ ዕርምጃ ትጥቅ የመፍታት ሒደት በአግባቡ እየተካሄደ ስለመሆኑ ትልቅ ተስፋ የሰጠ ነበር፡፡

‹‹በሰባት ቀናት ውስጥ የሕወሓት ተዋጊዎች ከባድ መሣሪያዎችን ያስረክባሉ፤›› ያሉት ጄኔራል ባጫ (አምባሳደር)፣ የኤርትራ ሠራዊትም ከትግራይ ክልል እንደሚወጣ ማረጋገጫ ሰጥተው ነበር፡፡

በፖለቲካና በሚዲያ እንቅስቃሴያቸው የሚታወቁት አቶ ነአምን ዘለቀ ከሰሞኑ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ‹‹የሰላም ስምምነቱ ለኢትዮጵያም ሆነ ለቀጣናው ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ መሆን አለመሆኑን በሒደት የሚታይ ነው፤›› በማለት ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡ የሕወሓት አመራሮች በተለይ እንደ አቶ ጌታቸው ረዳና ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ (ሌተና ጄኔራል) የመሳሰሉት አመራሮች፣ ስምምነቱን በአስገዳጅ ሁኔታ የፈረሙት አድርገው ያቀርቡታል ሲሉ አቶ ነአምን ተችተዋል፡፡ ‹‹የሕወሓት አመራሮች ስለጦርነቱ አጀማመር የሚሰጡት ትርክት አለ፡፡ ከስምምነቱ ውጪ ስምምነቱን የሚያፋልሱ መረጃዎች መስጠታቸው፣ ከእነዚህ ሰዎች ጋር የተደረሰ ስምምነት በተጨባጭ ተግባራዊ ይሆናል ወይ የሚለውን ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፤›› በማለትም አቶ ነአምን ጥርጣሬያቸውን ተናግረው ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ ይህን ጥርጣሬ ውድቅ የሚያደርግ መረጃ ነበር የሰጡት፡፡ ‹‹ይህንን ስምምነት ማንም እየተነሳ የሚጥለውና የሚያነሳው ጉዳይ አይደለም፤›› ሲሉ ነበር በሕወሓት በኩል አለ ያሉትን ተግባራዊ ቁርጠኝነት የተናገሩት፡፡

ከግራም ከቀኝም የሚሰጠው በተቃርኖ የተሞላ አስተያየት የቀጠለ ቢሆንም፣ በተጨባጭ በመሬት ላይ እየታየ ያለው ትጥቅ የመፍታት እንቅስቃሴ እንደ ትልቅ ውጤት በመነሳት ላይ ነው፡፡

በትግራይ ክልል ስለሚታየው ተጨባጭ ዕርምጃ በቅርበት የሚከታተሉት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ መስተዳድር ሲቋቋም የመቀሌ ከንቲባ የነበሩት አቶ አታክልቲ ኃይለ ሥላሴ፣ ትጥቅ የመፍታት ዕርምጃው ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን ገለጸዋል፡፡

‹‹እንደ አንድ ስለትግራይ የሚመለከተው ሰውና ጉዳዩንም በቅርበት እንደሚከታተል ግለሰብ፣ በተወሰኑ ቦታዎች በርካታ ወጣቶች መሣሪያቸውን አስቀምጠው በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ውስጥ እየገቡ መሆኑን ለማወቅ ችያለሁ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ከምንም በላይ ሕዝቡ ለሰላም ስምምነቱ መተግበር ያሳየው ፍላጎትና ድጋፍ የሚበረታታ ነው፡፡ ሕዝቡ ጦርነቱ እንዳይቀጥል እንደሚፈልግ ከሰሞኑ በትግራይ እየሆኑ ካሉ ሁነቶች መገንዘብ ይቻላል፤›› በማለት ነው አቶ አታክልቲ የተናገሩት፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ግን፣ ‹‹አሜሪካኖች ዋስትና መስጠታቸው የትጥቅ ማስፈታቱን ዕርምጃ ከሁሉ በላይ አፋጥኖታል፤›› ሲሉ ነበር ምልከታቸውን ያጋሩት፡፡

ሕወሓት በኦፊሴላዊ የፌስቡክ ገጹ ይፋ እንዳደረገው ከሆነ፣ ተዋጊዎቹ ከነበሩባቸው ግንባሮች ለቀው መውጣት ጀምረዋል፡፡ ከደቡባዊ ግንባሮች ማለትም ማይ ቅነጣል፣ ዛላምበሳ፣ ነበለት፣ ጨርጨር፣ ኩኩፍቶ፣ ህጉምብርዳ፣ በሪተኸላይ እና አበርገለ ግንባሮች የሕወሓት ታጣቂዎች ለቀው ወጥተዋል ይላል የሕወሓት መግለጫ፡፡

የአፍሪካ ኅብረት በበኩሉ ኅዳር 22 ቀን 2015 ቀን በሽሬ ከተማ የሕወሓትና የመንግሥት የጋራ ኮሚቴ ስብሰባ መደረጉን በመግለጫው ይፋ አድርጓል፡፡ ከኅዳር 23 ጀምሮም የሕወሓት ኃይሎች ቀላል መሣሪያ ማስረከብ እንደሚጀምሩ የገለጸው የኅብረቱ መግለጫ፣ የሰላም ስምምነቱ የሁለቱ ወገኖች ወታደራዊ መሪዎች በፈረሙት ስምምነት መሠረት ደረጃ በደረጃ ይተገበራል ሲል አመልክቷል፡፡

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና የሽሬ ተወላጅ አቶ ሙሉብርሃን ኃይሌ ግን፣ የሰላም ስምምነቱን ወደ ተግባር እንዲወርድ ያደረገው ሕዝቡ ነው ይላሉ፡፡

‹‹ትጥቅ መፍታት የተጀመረውም ሆነ የሰላም ስምምነቱ እንዲተገበር አስገዳጅ ተፅዕኖ ያሳደረው የሕዝቡ ፍላጎት ነው፡፡ መከላከያ በተቶጣጠራቸው የትግራይ አካባቢዎች ከሕዝቡ ጋር የፈጠረው መግባባት የሰፈነበት ግንኙነት፣ እንዲሁም የተራዘመው ግጭት ያደረሰው ሰቆቃ ሕዝቡ ሰላም እንዲሰፍንና ስምምነቱ በቶሎ እንዲተገበር እጅግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዲያሳይ አድርጎታል፤›› ሲሉ ነው አቶ ሙሉብርሃን የተናገሩት፡፡

ዘንድሮ የአክሱም ጽዮን በዓል በታላቅ ድምቀት መከበሩን እንደ ምሳሌ ያወሱት አቶ ሙሉብርሃን፣ ‹‹ይህ ደግሞ የሰላሙ አንድ ፍሬ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሕዝቡ በሰላሙ እፎይታ እያገኘ በመሆኑ የታጠቁትን ወደ ሰላም ተመለሱ በማለት አስገዳጅ ጫና እየፈጠረ እንደሚገኝ አክለው ተናግረዋል፡፡

የሕወሓት አማፂያን ቀላል መሣሪያዎችን ማስረከብ ጀመሩ እንጂ፣ ትጥቅ ወደ መፍታት ሒደቱ ሙሉ ለሙሉ አልገቡም የሚሉ መረጃዎች አሁንም እየተሰሙ ነው፡፡ ከመከላከያ ሠራዊት ውጪ ያሉ ሌሎች ኃይሎች የኤርትራ ጦርን ጨምሮ ከአካባቢው እስኪወጡ ድረስ፣ አማፂያኑ ትጥቅ ፈተው ወደ ተሃድሶ ማሠልጠኛዎች ሙሉ ለሙሉ እንደማይገቡ የሚናገሩ አሉ፡፡

የሕወሓት ዋና ተደራዳሪና ስምምነት ፈራሚ አቶ ጌታቸው ረዳ ከሰሞኑ ለቢቢሲ ሃርድ ቶክ፣ የትጥቅ መፍታት ሒደቱ (የሰላም ስምምነቱ ትግበራ) እስከ አንድ ዓመትም ሊወስድ እንደሚችል ተናግረው ነበር፡፡ ይህን የሚጋሩ አንዳንድ ሃያሲያን ነገሮች ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረው ምዕራፍ እስኪመለሱ፣ ከመከላከያ ውጪ ያሉ የታጠቁ ኃይሎች ትግራይን ለቀው እስኪወጡ፣ እንዲሁም ችግሮች ሕገ መንግሥታዊ በሆነ አግባብ ዕልባት እስኪያገኙ የሕወሓት ተዋጊዎች ትጥቃቸውን ሙሉ በሙሉ ይፈታሉ ብሎ ለመገመት እንደሚቸገሩ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡

ይህን የሚቃወሙት አቶ አታክልቲ ግን፣ ‹‹ለሰላም ስምምነቱ መተግበር ከምንም በላይ ወሳኝነት ያለው ሕዝቡ ለሰላም እያሳየ ያለው ፍላጎት ነው፤›› ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ በቅርብ ከሚከታተሉት እንዲሁም በትግራይ ክልል እየሆነ ካለው በመነሳት፣ ‹‹ሕዝቡ በስምምነቱ የሠፈሩ ውሎች በፍጥነት እንዲተገበሩ ከፍተኛ ፍላጎት እያሳየ ነው፡፡ እኛ እዚህ አንድ ቀን እንኳን ለማጣት የማንፈልጋቸውን የመብራት፣ የስልክ፣ የባንክ፣ የውኃና ሌሎችም የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች ከሁለት ዓመት በላይ አጥቶ የቆየው የትግራይ ሕዝብ፣ ከፍተኛ የሰላም ፍላጎት አለው፡፡ ግጭትና ዕልቂት ማየት ሰልችቶታል፤›› በማለትም አክለዋል፡፡

አቶ አታክልቲ ይህን ቢሉም ግን አሁንም ቢሆን የሰላም ስምምነቱን መተግበር የማይፈልጉ ኃይሎች መኖራቸውን ከመናገር ወደኋላ አላሉም፡፡ ‹‹በዓለም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጦርነቱ ለምን ቆመ ብሎ ለተቃውሞ ሠልፍ የወጣ ዳያስፖራ የታየበት ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ትጥቅ የመፍታት ዕርምጃውን ቅድመ ሁኔታ በመደርደር የሚቃወመው ብዙ ነው፤›› በማለት ነው የተናገሩት፡፡

የአቶ አታክልቲን ሐሳብ ያጠናከሩት አቶ ሙሉ ብርሃንም፣ ‹‹ጦርነቱ የተመቻቸው፣ በግጭቱ ትርፍ ለማጋበስ የሚጥሩና የሰላም ስምምነቱ ወደፊት እንዳይራመድ የሚሹ ብዙ ኃይሎች ተሠልፈዋል፤›› ብለዋል፡፡

ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተለያዩ ሐሳቦች ቢሰነዘሩም ታጣቂዎቹ መሣሪያቸውን ጥለው ወደ ተሃድሶ ማዕከላት መግባታቸው፣ አሁን ተጨባጭ መስሏል፡፡ በትግራይ ቴሌቪዥን ቀርበው አስተያየት ከሰጡ ታጣቂዎች አንደበትም ‹‹ሰላም ነው የሚያዋጣው›› የሚሉ ቃላት ደጋግመው ተደምጠዋል፡፡

ይሁን እንጂ የዓለም ሀቅ ደጋግሞ እንዳሳየው ጦርነትን ለመጀመር፣ ለመቀጠልም ሆነ ለማቆም ከተዋጊዎች ይልቅ የአዋጊዎች ፍላጎትና ሚና ነው ወሳኙ ጉዳይ፡፡ አሁን ላይ ከሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች የሚደመጠው ለሰላም ስምምነቱ የመገዛት ፍላጎት በጎና አበረታች ቢሆንም፣ በዚህ መሀል የሚፈጠሩ የቅድመ ሁኔታ ድርደራዎችና አንዳንድ ዳተኝነቶች ሒደቱን እንዳያሰናክሉት ሥጋት ሲፈጥሩ ይታያል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -