Tuesday, April 16, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

አፍሪካን እንደ አንድ አገር የማዋቀሩ ሒደት

በያሬድ ነጋሽ

የአፍሪካውያን የነፃነትና የአንድነት ጉዞ ስድስት የታሪክ ይዘቶች በያዙና እ.ኤ.አ. 1963ን ድንበር አድርገው ወደ ኋላና ወደፊት በተቀመጡ ሁለት የዘመን ምዕራፎች የተከፈለ ነው፡፡

 የመጀመርያው የታሪክ ምዕራፍ ከ1963 በፊት የነበረው ሆኖ ሦስት የታሪክ ይዘቶችን የያዘ፣ አፍሪካውያን በምድራቸውና በግዞት በሄዱበት አዲሱ ዓለም ለነፃነት ያደርጉት የነበረውን ተጋድሎ የሚዘክር ነው፡፡

ከመጀመርያው የታሪክ ምዕራፍ፣ አንደኛው የታሪክ ይዘት አፍሪካውያን ከቅኝ ገዥዎች ጋር እየታገሉ የሕይወት መስዕዋትነት ይከፍሉ የነበረበት ወቅት ነው፡፡ ለዚህ እንደ ምሳሌ መሆን የሚችሉ፣ የሸንቁጥ ልጆችና የሶሊቱድ ዓይነት ታሪኮችን እናንሳ፡፡

የሸንቁጥ ልጆች

በ1930ዎቹ ተሾመ፣ ኃይሌ፣ አበበ፣ ይነሱና ጥላሁን ለአንድ ጉዳይ በጋራ ተሰባስበዋል፡፡ ስብስቡ ኢትዮጵያ ውስጥ በከተማና በአንዳንድ ሥፍራ ተወስኖ አገሪቷን የተቆጣጠረውን የፋሺስት ጣሊያን ጦር መፍትሔ እስኪቸግረው ድረስ መቆሚያ መቀመጫ ያሳጡ አርበኞች ነበሩ፡፡ ‹‹ታዲያስ አርበኛው ስሙ አልተነሳሳ እንደሆን እንጂ አያሌ አይደለም ወይ?›› ያልን እንደሆነ ይህ ስብስብ በልዩነት የሚያስቀምጠው ነገር ቢኖር ከቀኛዝማች ሸንቁጥና ከወ/ሮ ማሚቴ ሙሉነህ የተወለዱ ወንድማማቾች መሆናቸው ነበር፡፡ አባታቸው ሸንቁጥ በዓድዋ ጦርነት ላይ ጀብዱ የሠሩ ጀግና ኢትየጵያዊ ነበሩ፡፡

ዋዜማ ሬዲዮ የሸንቁጥ ቤተሰቦች በሚል ርዕስ በሠራው ዝግጅት ‹‹ሁሉም አገር አንድ ጀግና ሊወልድ ይችላል፡፡ አንድ ቤተሰብ እንዴት ሙሉ ጀግና ይወልዳል? የሸንቁጥ ቤተሰብ የሚገርመን ለዚህ ነው፤›› በሚል ይገልጻቸዋል። ከጄኔራል ናዚና ከዱካ ደ አውስታ ጋር የነበረው ጁሴፒ ማረሊዮ የተባለ ጣሊያናዊ የታሪክ ጸሐፊ  ‹‹ፍራቴሊ ሸንቁጥ›› (ወንድማማቾቹ የሸንቁጥ ልጆች) በሚል ርዕስ በጻፈው ጽሑፍ ላይ ‹‹በመርሐ ቤቴ ተመሳሳይና ተወዳዳሪ ከማይገኘላቸው ጥቂት የጦር ሰዎች መካከል በላይኛው መስመር ላይ ይገኛሉ፤›› ሲል ያደንቃቸዋል፡፡

እኔ ደሞ ‹‹በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ለአርበኝነት የሚውል ልጅ እንዳለ ሁሉ፣ ሌላው ቢሞት በአንዱ ለመጽናናት፣ ዘር እንዲቀጥል፣  ቤተሰብ እንዲጦር  ወይም ለእርሻ እንዲጠቅም እቤት የሚቀር ወንድ ልጅ ይኖራል፡፡ በሙሉ ለአርበኝነት ሲውሉ ማየት ግን በእጅጉ ያስደንቃል፤›› እላለሁ፡፡ ምክንያቱም በዘመናዊ የወታደር ምልመላ ከቤተሰብ ከአንድ በላይ ለመመልመል ስለማይሞከር ነው፡፡ (ከወንድማማቾቹ መካከል ከመንግሥት ኃላፊነታቸው ሳይቀር ተነስተው ወደ አርበኝነቱ የተቀላቀሉም ይገኛሉ)፡፡

ኮላሽ ምሽግ በሸንቁጥ ልጆች ተጋድሎ ታሪክ ላይ በጉልህ የሚነሳ የትግል ዓውድ ነው፡፡ ፍልሚያውን የመሩት ልጅ አበበ ሸንቁጥ ናቸው፡፡ ሠራዊታቸው የጠላትን ጦር እንደ እህል እያበራየ ለአርበኝነቱ ትግል ወሳኝነት ያለውንና ገዥ መሬት የሆነውን ኮላሽ ምሽግን ተቆጣጠረ፡፡ የአበበ ሸንቁጥ ሠራዊት ኮላሽ ምሽግን ሲቆጣጠር በጠላት ሠራዊት ዘንድ የደረሰው ኪሳራ ከቁጥር በላይ ነበር፡፡ በእዚህም ምክንያት በጠላት ካምፕ ዘንድ የሸንቁጥ ልጆች ዝና ይበልጥ ናኘ፡፡ በድሉ ደስታውን መቆጣጠር የተሳነው አገሬው ይህንን ስንኝ ለጀብዳቸው ገጠመላቸው፣

             መውዜሩን ነዳፊ የበረሃ ጊንጥ

             ኮላሽ ላይ ብቅ አለ አበበ ሸንቁጥ

             መከራ አረገዘ ጣሊያን ያዘው ምጥ

             በየምሽጉ ሥር ዋለ ሲራወጥ፡፡

ይህን ቤተሰብ ማውሳት ዛሬ ላይ አንድነት ላጣን ኢትዮጵያውያን አገራችን በምን ዓይነት መልኩ እኛ እጅ ላይ እንደደረሰች በተጨባጭ ምስክር ማቅረብ እንደ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ግራዝማች ተሾመ ሸንቁጥ (በጦር ሜዳ በጠላት ጥይት ሰውነታቸው እንደ ወንፊት የተበሳሳ (በኋላ ደጅዝማች)፣ ልጅ ኃይሌ ሸንቁጥ (በጦር ሜዳ በጀግንነት ሲዋጉ ከባድ የመቁሰል አደጋ ስለደረሰባቸው በጠላት ኃይል አንገታቸው ተቀልቶ የተወሰደ)፣ ልጅ አበበ ሸንቁጥ (እጅግ በርካታ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸው በተዓምር የተረፉ (በኋላ ደጃ ገዝማች)፣ ልጅ ይነሱ ሸንቁጥ (በጦር ሜዳ ተሰተው ከአረመኔው የፋሺስት ጦር ጋር ተባባሪ የነበረ አንድ የአገሬው ዘማች አማካይነት ሰውነታቸው ተቆራርጦ የተወሰደ)፡፡ ልጅ ጥላሁን ሸንቁጥ (በጦር ሜዳ ተሰውተው አንገታቸው በጠላት ተቆልቶ ሬሳቸው የተወሰደ) በመሆናቸው፡፡

ሶሊቱድ 

ከሄይቲ የባሪያ አመፅ በኋላ በ1794 በካሪቢያን ባሉ የፈረንሣይ ቅኝ ግዛቶች ባርነት ተወገደ፡፡ የፈረንሣይ መንግሥት ሥፍራውን የለቀቀው በቅኝ ግዛቶቹ የተነሱትን አጠቃላይ የባሪያ ዓመፅ ለመቋቋም አቅም እያጣ በመምጣቱ ነበር። ነገር ግን ከስምንት ዓመታት በኋላ ናፖሊዮን ቦናፓርት በፈረንሣይ ሥር የነበሩት ቅኝ ግዛቶች መልሶ ለመያዝ ወታደሮቹን ወደካሪቢያን ሲልክ 3,500ቱ በጄኔራል አንቶኒ ሪችፓንስ እየተመሩ ወደ ጓዴሎፕ (ምሥራቅ ካሪቢያን) ተጓዙ። በትግላቸው ነፃነታቸውን ተቀዳጅተው የነበሩት ጓዴሎፕአውያን ነገሩን በፀጋ የሚቀበሉት ሆኖ ባለመገኘቱ ተቃውሟቸውን ለማሰማት ‹‹ጆሴፍ ኢግናስ›› በተባለ ሰው መሪነት ወደ ትግል ገቡ። በሉዊስ ዴልግሬስ ዙሪያ ለተቃውሞ ከተሰባሰቡና ለነፃነት ከተዋደቁ ታጋዮች መካከል ሶሊቱድ አንዷ ነበረች፡፡ በጥቁሮች የነፃነት ትግል ውስጥ አያሌ እንስቶች ቢኖሩም ሶሊቱድ በልዩነት መነሳቷ የእንስቶቹን የተጋድሎ መጠን የበለጠ ሊያስገነዝበን ስለሚችል ነው፡፡

እናቷ ከአፍሪካ ወደ ምዕራብ ህንድ በባርነት በምትጓዝበት ወቅት በመርከበኛ በመደፈሯ በጓዴሎፕ ደሴት ውስጥ ከደረሰች በኋላ በ1772 ሶሊቱድ ተወለደች፡፡ ሶሊቱድ ‹‹ሙልታሬሴ›› ተብላ ትጠራ ነበር፡፡ ይህም ማለት የነጭና ጥቁር ቅይጥ በመሆኗ ‹‹የነጣ የገረጣ ቆዳ ያላት›› እንደማለት ነው፡፡ በጊዜው በነበረው የኅብረተሰብ የዘር አድሎ ውስጥ የነጭ ዘር ያረፈባት መሆኗ የተወሰነ ጠቀሜታ ስለሰጣት በእርሻ ላይ ለመሥራት ከመገደድ ይልቅ የቤት ውስጥ ሥራን ብቻ እንድታከናውን ተደርጋ ነበር፡፡

በጓዴሎፔአውያን ትግል ወቅት ከሌሎች ሴቶች ልዩ የሚያደርጋት ነገር ቢኖር ነፍሰ ጡር ሆና የተሳተፈችበት መሆኑ ነበር፡፡ ሁኔታውን ለመግለጽ የፈለጉ በርካቶች ‹‹ራሷንና ልጇን ወደ ጦርነቱ ያዘመተች ደፋር ተዋጊ›› ብለዋታል፡፡ በግንቦት 28 ቀን 1802 በተካሄደው የነፃነት ትግል ጦርነት ላይ በጀግንነት ተዋድቀው በመጨረሻ በፈረንሣዮች ከተማረኩት የነፃነት ታጋዮች መካከል ሶሊቱድ አንዷ ብትሆንም ሁሉም በሞት ሲቀጡ እሷ ግን ‹‹ነፍሰ ጡር በመሆኗ›› የሚል የሕግ ከለላ አግኝታ በእስር እንድትቆይ ተደርጎ በኅዳር 29 ከወለደች ከአንድ ቀን በኋላ ልጇን ወስደው በማሰር በስቅላት ተቀጣች፡፡ የመጨረሻ ቃሏም ‹‹በነፃነት መኖር ወይም መሞት›› የሚል ነበር።

ከሞተች በኋላ በካሪቢያን ጥቁር ሕዝብ ትርክትና አፈ ታሪክ ውስጥ እኩልነት ለማስፈን እና ነፃነትን ለመጠበቅ የታገሉ ሴቶች ምልክት ተደርጋ ብትቀጥልም ከታሪክ መዛግብት እንድትሰወር በርካታ ጥረት ተደርጓል። ለእንዲህ ዓይነት መስዋዕትነት የሚመጥን ክፍያ ማግኘት ባይቻልም ከ1960ዎቹ በኋላ ታሪኳ ዳግም መነሳት ከጀመረ ወዲህ በሶሊቱድ ስም አደባባዮችን፣ መንገዶችን፣ ቤተ መጻሕፍትንና ሙዚየሞች ተሰይመዋል፡፡ እናትነትንና ጀግንነትን አስተባብረው የያዙ ዘፈኖችና ግጥሞች በስሟ በሰፊው ተደርሰዋል፡፡ በ1999 ለሶሊቱድ ክብር ጓዴሎፕ ውስጥ ሐውልት ተተክሏል፡፡  በ2014 ከፓሪስ በስተደቡብ ባለችው አይቭሪ ሱር ሴን (Ivry-sur-Seine) ከተማ ውስጥ አዲስ መንገድ በስሟ እንዲሰየም ተወስኗል። በጓዴሎፕ የሙላቶ ጎዳና በስሟ ተመርቋል፡፡ የናንተስ ክልላዊ አስተዳደር 46ኛ ግዛቱን በስሟ ሰይሞታል፡፡ በ2019 በፍሬዴሪክ በተዘጋጀው ‹‹ሌስግራንድስ-ቴሪየንስ›› በተባለው ልብ ወለድ ውስጥ ዋና ገፀ ባህሪ ሆና ቀርባለች። በመስከረም 26 ቀን 2020 የፓሪስ ከተማ ከንቲባ አን ሂዳልጎ ‹‹የጃርዲን ሶሊቱድ›› በሚል ፓርክ ሰይሞላታል፡፡ በተጨማሪም ሐውልቷን በዚህ ፓርክ ውስጥ እንደሚተክሉ አስታውቀዋል፡፡ ነገሩ እውነት ከሆነ በፓሪስ ውስጥ 40ኛ የታሪካዊ ሴቶችና የመጀመርያ የጥቁር ሴት ሐውልት ይሆናል፡፡

በአንደኛው የነፃነት ትግል ምዕራፍ ውስጥ ሁለተኛው የታሪክ ይዘት   አፍሪካውያን ከባርነት ይልቅ ሞትን በመምረጥ የገዛ ራሳቸውን ያጠፉበትን ሒደት የሚያሳይ ሲሆን የኢግቦ ሕዝብን ተምሳሌት አድርገን እናነሳለን።

የኢግቦ/ኢቦስ ማረፊያ

በአፍሪካውያን የባርነት ታሪክ ውስጥ በርካታ የነፃነት ትግል እንቅስቃሴዎች ተደርገው ተፅዕኖው አሁን ድረስ ያላቆመ ነውና ዛሬም ቢሆን ትግሉ እንደቀጠለ ነው፡፡  በጥቁር የነፃነት ትግል ታሪክ ውስጥ ታግሎ መሞት ወይም ታግሎ ጨቋኙን መግደል እንዳለ ሆነው በኢግቦ/ኢቦስ ማረፊያ የተደረገው የነፃነት ትግል ግን በልዩነት ይወሳል፡፡ በአሜሪካ፣ በካሪቢያን፣ በደቡብ አሜሪካና በአፍሪካ በተለይም ለታሪኩ ቅርብ እንደሆኑ በሚሰማቸው የምዕራብ አፍሪካ አካባቢዎች የኢቦስ ማረፊያ ታሪክ በተረታቸው ቀይጠው ለልጅ  የማይነግሩ፣ በተረትና ምሳሌያቸው በዘይቤ ቃኝተው ለተግባቦት ያላዋሉና መጽሐፍ ጽፈው፣ አልያም ፊልምና ቲያትር ደርሰው ያልዘከሩ የሉም፡፡

የኢቦስ ማረፊያው ተብሎ የሚጠራው አከባቢ በሴንት ሲሞን ደሴት ግሊን ካውንቲ፣ ጆርጂያ ላይ በዳንባር ክሪክ የሚገኝ ታሪካዊ ሥፍራ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ1803  ከምዕራብ አፍሪካ አከባቢዎች በጆን ኩፐርና ቶማስ ስፓልዲንግ ወኪሎች አማካይነት ለእርሻ አገልግሎት እንዲውሉ እያንዳንዳቸው 100 ዶላር ተገዝተው ዘ ስኩነህ ዮርክ (The Schooner York) በተባለች መርከብ ላይ ተጭነው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በመጓዝ ላይ ከነበሩ ጥቁሮች መካከል በአብዛኛው ወይም ወደ 75 የሚጠጉት በአሁኑ ጊዜ በናይጄሪያ ከሚገኙት የማኅበረሰብ ክፍል መካከል አንዱ ከሆነው የኢግቦ ጎሳ ተወላጆች የተውጣጡ ነበር። ባሪያዎቹ በድንገት መርከቧን ተቆጣጥረው  በዚህ ማረፊያ ላይ ካቆሙት በኋላ ከባርነት ይልቅ ሞትን በመምረጥ  በጅምላ ራሳቸውን አጠፉ፡፡

በሳቫናህ የባሪያ አከፋፋይ ዊልያም ሜይን እንደተጻፈ የሚነገረው ደብዳቤ   አፍሪካውያኑ ወደ ባህሩ ዳርቻ ሲደርሱ መርከቧን በመቆጣጠር ከፍተኛ የኢግቦ አለቃው ‹‹የውኃ መንፈስ አመጣን፣ የውኃው መንፈስ ወደ ቤት ይወስደናል፡፡ ከባርነት ይልቅ ሞትን ተቀበሉ፤›› የሚል ድምፅ አሰማ፡፡ ይህንን ተከትለው በአንድነት ወደ ጅረት እየዘለሉ ገቡ፡፡ ወደ ጅረቱ ከገቡ ኢግቦዎች መካከል ከ10 እስከ 12 የሚደርሱት ሰጥመው ሲሞቱ አንዳንዶቹ ደግሞ አሥር ዶላር በተከፈላቸው  ዋናተኞች  ተረፉ፡፡   ከኢግቦ አመፅ የተረፉ ሰዎች በሴንት ሲሞን ደሴትና በሳፔሎ ደሴት ወደሚገኘው መዳረሻዎች ተወስደዋል በሚል ክስተቱን ይገልጸዋል።

ታሪኩን ‹‹ትልቅ የተቃውሞ ዕርምጃ›› በሚል በመውሰድ በጥቁር አሜሪካውያን አፈ ታሪክና ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ተምሳሌታዊ ጠቀሜታውን በማጉላት ‹‹የመጀመርያው የነፃነት ጉዞ›› ብለው ሲጠሩት በተቃራኒው ከሁለት መቶ ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ  በነጮቹ ባለሥልጣናት ዘንድ ታሪኩን እንደ አፍሮ አሜሪካዊ የውሸት ተረት አድርገው ይቆጥሩ የነበረ ቢሆንም፣ ከ1980 ጀምሮ የተደረጉ ጥናቶች ታሪካዊ ይዘቱን በተጨባጭ አረጋግጠዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጆርጂያ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የታሪክ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ ቦታው አሁንም በመደበኛነት በታሪክ ተመራማሪዎችና ቱሪስቶች ይጎበኛል።

ይህንን የጥቁር ሕዝብ የነፃነት ትግል ታሪክ ለመዘከር በቂ ነው ባይባልም የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ በሴፕቴምበር 2002 የቅዱስ ሲሞን የአፍሪካ አሜሪካዊ ቅርስ ጥምረት ከኢግቦ ታሪክ ጋር በተያያዘ ወደ ሥፍራው የሁለት ቀን መታሰቢያ የእግር ጉዞ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ዝግጅቱ የነፃነት አርበኞቹን ለመዘከር በቁጥራቸው ልክ  75 ተሰብሳቢዎችን ከናይጄሪያ፣ ቤሊዝ፣ ሔይቲና ከሌሎች ሥፍራዎች መጥተው የተሳተፉበት ሲሆን፣ ዓላማውም ቦታውን በሰማዕቶቹ የተቀደሰ መሬት አድርገው ለመሰየም የታሰበበት ነበር።

በመጽሐፍ መልክ ከዘከሩት መካከል የኖቤል ተሸላሚዋ ቶኒ ሞሪሰን  ‹‹የመብረሪያ አፍሪቃውያንን አፈ ታሪክ›› በሚል ያዘጋጀችው ልብወለድና  አሌክስ ኃሌይ ‹‹ሩትስ›› በሚል ታሪኩን ያነሳበት መጽሐፉ ተጠቃሽ ናቸው፡፡  በጁሊ ዳሽ ዳይሬክት በተደረገው ‹‹ዳውተርስ ኦቭ ዘ አቡራ›› በተሰኘው ፊልም  ላይም ታሪኩ ተነስቷል፡፡ ጆሴፍ ዞቤል፣ ሜሪሴ ኮንዴ፣ ቶኒ ካዴ ባምባራና ጃማይካ ኪንካይድ የተባሉ የዘመኑ አርቲስቶችም በሥራቸው ዘክረውታል፡፡ የቢዮንሴ የ‹‹ፍቅር ድርቅ›› በሚል የተነሳው ምስሏ በኢግቦ ማረፊያ ታሪክ የተቀናበረ ነው ተብሏል።

እ.ኤ.አ. በ 2018 ማርቭል ፊልም ባዘጋጀው ‹‹ብላክ ፓንተር›› በተሰኘው ፊልም ላይ ኢግቦ ማረፊያ ዋቢ አድርጎ ‹‹ከመርከቦች ከዘለሉ ቅድመ አያቶቼ ጋር በውቅያኖስ ውስጥ ቅበሩኝ፣ ምክንያቱም ሞት ከባርነት ስለሚሻል፤›› ይላል ማይክል ቢ. ጆርዳን  በትዕይንቱ ላይ። ወደ አያቶቻችን መንፈስ እንመለስ።

ወደፊት ለምትኖረን ሴት ልጃችን ከዚህ ማኅበረሰብ የተቀዳ ስም ብናወጣላት  ዓለም ለሴት ልጅ አያሌ የጭቆና ቀንበር አዘጋጅታ የምትጠብቅ ናትና ‹‹እምቢ አልገዛም›› የማለት ጥግ ምን ድረስ ሊደርስ እንደሚችል ሊያስገነዝባትና ሰንሰለቱን በጣጥሳ ወደ ህልሟ እንድትገሰግስ ስንቅ ሊሆናት ይችላል፡፡

በአንደኛው የነፃነት ትግል ምዕራፍ ሦስተኛው የታሪክ ይዘት አፍሪካውያን በቅኝ ሊገዛ ከተነሳው አካል ጋር ለነፃነት በመዋደቅ ድል የነሱበትን ሲሆን ዓድዋን በብቸኝነት ምሳሌ አድርገን እናነሳለን፡፡

በአጠቃላይ የመጀመርያውን የታሪክ ምዕራፍ ከላይ ያየናቸውን ሦስት ይዘቶች የተላበሰ ነበር፡፡

ሆኖም በካሪቢያን፣ በሌሎች የአፍሪካ አገሮችና በኢትዮጵያ የጥቁሮች የነፃነት የትግል ወቅት ማብቂያ በሁለት ጽንፍ የተቀመጠ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡

በካሪቢያን ከነፃነት በፊት የቅኝ ግዛቱ አስተዳደር የነፃነት ሰማዕታቱ ስማቸው እንዳይነሳ አፈና ቢያደርግም ማኅበረሰቡ ስማቸውን ሳያነሳ አንዴ ንፋስ፣ ሌላ ጊዜ ዝናብ እየሆኑ በአፈ ታሪኩና በተረቱ እየቀየጠ ውለታቸውን ለልጆቹ ይተርካል፡፡ እንዲህ እየተነገረው ያደገ ዜጋ የሥነ ዜጋ ትምህርት ሳያስፈልገው በወታደር ሥነ ምግባር የታነፀ ነው፡፡ ነፍጥ አንግቦ አገሩን ለመጠበቅም ይሁን በተሰማራበት ዘርፍ ሊኖረው የሚገባውን ታማኝነት፣ ቆራጥነትንና መጨከንን ይማራል፡፡ ቤተ ሙከራ ይዞት የገባው ሥራ እስኪሳካ ድረስ ከ72 ሰዓታት በላይ ያለ እንቅልፍ የሚያሳልፍና  ከሦስት እስከ አራት ሳምንታት ላቦራቶሪውን እላዩ ላይ የሚቆልፍ ጨካኝ ዜጋ ይፈጠራል፡፡ በንግድ ዘርፍ ቢሰማራ ለአገሩና ለሕዝቡ እያደረገ እንኳን የሰጡኝን ያህል አልከፈልኳቸውም እያለ የሚቆጭ እንጂ አገሩን ግብር ለማሳጣትም ይሁን እቃን ከገበያ በመሰወር የማኅበረሰቡ ጉሮሮ መጠማቱንና መራቡን ሲገነዘብ የትርፍ ማጋበሻው ሰዓት እንደደረሰ የሚሰማው ለመሆን ሞራሉ የተገነባበት የነፃነት ሰማዕታት ታሪክ ዕድል የማይሰጠው ይሆናል፡፡

በካሪቢያን አገሮች የቅኝ ግዛቱ አስተዳደር ተወግዶ፣ አገሬው ነፃነቱን ተቀዳጅቶ በፓርላማ ሲሰባሰብ ተጨባብጦ ባንዲራና ሕገ መንግሥት ከመቀባበላቸው በፊት የሚቀድመውን ያደርጋሉ፡፡ እሱም ‹‹ቆጠራ ወይም ኢንቨንትሪ›› ነው፡፡ ‹‹ዛሬ በነፃነት በፓርላማው እንድንሰባሰብ ባስቻለን የነፃነት ትግል ውስጥ ማን ማን ተካፈለ? ረግጠነው ወደ ፓርላማ በመጣንበት መንገድ ላይ የማን የማን ደም ፈሰሰ? በዱር በገደሉ የማን ሕይወት አለፈ? የማን አካል ጎደለ?›› የሚለውን ይሰንዳል፡፡ አንድ የሽግግር መንግሥት በዚህ መልኩ ሰማዕታቱን ቢሰንድ ሕገ መንግሥትም አያስፈልገውም፡፡ የሥልጣን ወንበሩም ቢሆን ተደላድለው የሚቀመጡበት ምቹ ሥፍራ ከመሆን ይልቅ ዘወትር የሚቆረቁር፣ ምንሠራህ ብሎ የሚጠይቅ፣ ዘመንህ አብቅቷል ብሎ የሚያስታውስ ይሆናል፡፡

ፓርላማው ሰማዕታቱን ለይቶ ከሰነደ በኋላ ቅድም ማን ማን እንደሆኑ ስለማያውቅ ደማቸው የፈሰሰበትን ምድር በድፍረት በመርገጡ ይቅርታ በመጠየቅ  ተመልሶ በዚሁ መልኩ ወደ ውጭ መውጣት ተጨማሪ ድፍረት መሆኑን ተረድቶ  ደማቸው የፈሰሰበትን ሥፍራ፣ ከተማ፣ መንገድ፣ አደባባይ ሁሉ ዘላቂ የስማቸው መዘከሪያ እንዲሆን በስማቸው ይሰይማል፡፡ አደባባዮችን በግዙፍ ምስለ ሐውልታቸው ያስጌጣል፣ ይተክላል፡፡ እንዲሁ በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ተገቢውን ሥፍራ ይሰጣል፡፡ የሥነ ጽሑፉ፣ የሙዚቃው፣ የቴአትሩ፣ የሬዲዮው፣ የቴሌቪዥኑና ሌሎችም የሚዲያ ዘርፎች አያሌ ሥራዎችን በሰማዕታቱ ስም ያበረክታሉ፡፡

በአገራችን ያለው የነፃነት ሰማዕታት ዝክር ግን ከላይ ካየነው በጽንፍ የሚቀመጥ ነው፡፡ ሰማዕታቱ የተዘነጉ ናቸው፡፡ ከተዘነጉ አይቀር በክፉም ሆነ በደጉ መዘንጋት የሚሻል ቢሆንም የነፃነት አርበኞቹ በክፉ ሲነሱ መመልከት እጅጉን ይደንቃል፡፡ ብዙዎቻችን ወጣቶች የጥቂቶቹን ስም እንኳን ያወቅነው በግለሰቦች ጥረት ነው፡፡ የታሪኩ ጠቀሜታ ተገንዝቦ አገሪቱ እንዴት እዚህ እንደደረሰች ያስረዳን ባለመኖሩ ብዙዎቻችን አገር የምትሠራው ልጅ ሆነን ወራጅ ውኃ ላይ እንደሠራነው የጭቃ ግድብ ተጠፍጥፎ ይመስለናል (በልጅነታችን የጭቃ ግድብ ከመሥራቱ በላይ በመጨረሻ ግድቡን አፍርሰን የተጠራቀመውን ውኃ መልቀቅ ሁላችንንም ያጓጓ ነበር)፡፡ ለዚህም ነው በሕይወት አንድ ጊዜ የምናገኘውን የጉብዝና ወራት ጉልበታችንን እናታችንን ወይም አገራችንን ለመደብደብ የተጠቀምንበት፡፡

ሁለተኛው የነፃነት ትግል ታሪክ ምዕራፍ እንደዚሁ ሦስት ይዘቶችን የያዘና የፓን አፍሪካኒዝም (የጋራ ጥቅም ያላቸው አፍሪካውያን አንድ መሆን አለባቸው) ጽንሰ ሐሳብ የተሸከመ ነው።

በመጀመርያ የተመለከትነውን የታሪክ ምዕራፍ ውጤታማነት ከግብ ለማድረስ ከ1963 በኋላ ‹‹አፍሪካውያን ለችግሮቻቸው መፍትሔ ማፈላለጉን ከተናጠል ይልቅ በጋራ ሊረባረቡበት ይገባል፤›› ባሉ ንቁ አፍሪካውያን መሪዎች መቀንቀን የጀመረና የተዘየደ መላ ነበር፡፡

በዚህ ምዕራፍ የመጀመርያው የታሪክ ይዘት በ1963 ግርማዊነታቸው ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ ሐሰን ሪዳ (የሊቢያ ንጉሥ)፣ ኩዋሚ ኑኩሩማ (የጋና ፕሬዚዳንት)፣ አህመድ ቢን ቤላ (የአልጄሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር)፣ ኤል ፋሪኪ ኢብራሂም አብቦድ (የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር)፣ ጁሊየስ ኔሬሬ (የታንጋኒካ ፕሬዝደንት)፣ አጁማ ኦጊጋ ኦዲንጋ (ነፃ ያልወጣውን በመወከል)፣ ገማል አብድል ናስር (ግብፅ)፣ ምዋሚ ምዋምቡታ ስድስተኛ (የቡሩንዲ ንጉሥ)፣ አህማዱ አህጆ (የካሜሩን ጠቅላይ ሚኒስትር) እና ሌሎችም በአጠቃላይ ከ32 የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ መሪዎች፣ በተጨማሪም ከአመራሮቹ ሥር በነበሩ እንደ ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ፣ አቶ ከተማ ይፍሩ ዓይነት ፓንአፍሪካኒስት ሹማምንት አማካይነት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሠረተበት ወቅት ነበር።

በዕለቱ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ‹‹ይህ ለአፍሪካና ለመላው አፍሪካውያን ታላቅ ታሪካዊ ቀን ነው። እኛ ዛሬ በዓለም ጉዳዮች አቅጣጫ ላይ ያለንን ሚና ለማረጋገጥና ለመተባበር ተሰብስበናል፡፡ 250 ሚሊዮን ሕዝቦቿን የምንመራ መሪዎችም ለታላቋ አኅጉር ግዴታችንን እንወጣለን፡፡ ዛሬ አፍሪካ ከትናንት ወደ ነገው በሚያሸጋግር ድልድይ መካከለኛ ላይ ትገኛለች፡፡ ካለፈው ወደ ወደፊት እንሸጋገራለን፡፡ የጀመርንበት ተግባር የመጨረሻ ግቡን ዛሬ ይመታል ባንልም የወደፊቱን ጊዜ ለመቅረፅ በክስተቶች ላይ አሻራችንን መተው ያስችለናል፤›› የሚል ይዘት ያለው የመክፈቻ ንግግር አድርገው ነበር፡፡

የምዕራፉ ሁለተኛ የታሪክ ይዘት ቀድሞ የተመሠረተው የአንድነት ድርጅት ማጠናከርን መሠረት ባደረገ መልኩ 50 ዓመታት ያስቆጠረውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በ2013 ወደ አፍሪካ ኅብረት የተሸጋገረበትና ወደ ሥራ ተገብቶ አሁን እስከደረስንበት ያለው ወቅት ነው፡፡

የምዕራፉ ሦስተኛው የታሪክ ይዘት የአንድነት ጉዞው ማጠቃለያውና በአፍሪካ ኅብረት ምሥረታ ላይ በ2063 የተባበሩት አፍሪካን እንደ አንድ አገር ለመመሥረት በተቀመጠው ዕቅድ መሠረት ወደ እዚያ መንገድ የጀመርንበት ወቅት ነው፡፡ ሆኖም አፍሪካን እንደ አንድ አገር የመመሥረቱ መንገድ በብዙዎች ዘንድ ‹‹ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚደረግ ጉዞ›› ቢባልም በእኔ ዕይታ ወደ ቀደመ የአፍሪካውያንና የዓለም ሕዝብ የአኗኗር ዘመን መመለስ እንደሆነ አምናለሁ።

አፍሪካውያን ‹‹የአገራችሁ ድንበር የት አለ?›› ቢባሉ ወደ መሬት ከማየት ይልቅ ወደ ሰማይ የሚጠቁሙ ሕዝቦች ነበሩ፡፡ ይህም ማለት ድንበሩ ሰማይ የሆነለት ዓለም ሁሉ አገሩ፣ የዓለም ሕዝብ ሁሉ ወንድሙ ይሆናል፡፡ ለዚያም ነው በምሥራቅ አፍሪካ ኦሮሞ የሚባል ጎሳ ኢትዮጵያና ኬንያ፣ ሶማሌ የሚባል ጎሳ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ በሶማሊ ላንድና ኬንያ፣ አፋር የምንለው ጎሳ በኢትዮጵያ፣ በኤርትራና በጅቡቲና እንዲሁም በተቀረውም አካባቢም ቢሆን አንድ ጎሳ ከአሥር ባላነሱ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ መኖሩን ስናይ የመሬት መስመር ድንበራችን ሰው ሠራሽና ጥቅመኞች ያበጃጁት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በተጨማሪም በአገር አሳሽ የተደረሰባቸው የተለያዩ የዓለም ሥፍራዎች ላይ እንኳን ነባር ሕዝቦች ጥቁሮች እንደነበሩ ስንገነዘብ ነገሩን ያጠናክርልናል፡፡ የሰው ዘር ጥናት ደግሞ የሰው ልጅ መነሻ አፍሪካ መሆኗን ሲያረጋግጥልን ነገሩ እውነት ሆኖ እናገኘዋለን።

ለአፍሪካውያን ሁሉም የዓለም ሕዝብ ወንድሞቻቸው እንደነበሩ ለማረጋገጥ ደግሞ የዓድዋ ጦርነት ተጠናቆ የሞቱትን የጣልያን ጦር ጀነራሎች በመሰብሰብ  በመጀመርያ ይገለገሉበትን የነበረው ቁሳቁሶች ለቤተሰቦቻቸው ለማስታወሻነት እንዲሆናቸው የተመለሰበት፣ ሬሳቸው እንደየእምነታቸው ሥርዓት ተገንዞና እንደ ወታደራዊ ማዕረጋቸው መሣሪያ ተተኩሶ የተቀበሩበት፣ ምርኮኛው አሽከር ተቀጥሮለት ሲቀለብ ከርሞ ወደ አገሩ በሰላም እንዲመለስ የተደረገበት መንገድ የይቅርታውን ልክ መጠን የሚያስገነዝብ ሲሆን፣ በወቅቱ ከኢትዮጵያውያን የጦር መሪዎች መካከል ከኦሮሞ ጎሳ የሚገኙት አዛዥ ጢኖ በጣልያን ጦር ከተገደሉ በኋላ ጣልያኖቹ ሬሳቸውን ለጅብ እንዲሰጥ ስላደረጉ ቤተሰባቸው ወደ ኢትዮጵያ ንጉሥ በመምጣት  ‹‹የአባታችንን እሬሳ ለጅብ ሰጥተው እርሶ እንዴት በክብር ይቀብሯቸዋል?›› ቢሏቸው ንጉሡም ‹‹እኛ ከነሱ ተሽለን መገኘት ይገባናል፣ ባያውቁት እንጂ ወንድማማቾች ነበርን›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡  ‹‹አሁን ላይ  በታሪኩ ላይ የተሳተፈ ሰው በአካል ማግኘት ስለማይቻል የታሪክ ሰነዶቹ ውሸት ናቸው፤›› ብንል እንኳን በ1942 7,000 የፖላንድ ስደተኞችን ተቀብላ ያስተናገደችው ኡጋንዳ ምንም እንኳን ወቅቱ ከቅኝ ግዛት የግፍ ቀንበር ያልተላቀቀች ቢሆንም ከበቀል ይልቅ ለአውሮፓውያኑ ያሳዩትን ፍቅር ታሪኩ 80 ዓመታት አካባቢ ብቻ የሞላው በመሆኑ በሕይወት የሚገኙ ፖላንዳውያን ምስክር መሆን ይችላሉ፡፡

አብዛኞች ‹‹የጨለማ አኅጉር›› ብለው በጠሩት አፍሪካ ውስጥ የታየው ሥነ ምግባር ወይም እየሞቱ ይቅር ማለትን አብዛኞቹ ቅዱስ መጽሐፍ እጃቸው ላይ ከደረሰ ጀምሮ የሚያውቁት ሲሆን፣ በአፍሪካውያን ዘንድ ግን ከዚያ በፊት የሰው ዘር ጅማሮም እንደመሆናቸው መጠን በሕገ ልቦና ከመለኮት ጋር ከነበራቸው ተፈጥሯዊ ግንኙነት ጀምሮ የሚመነጭ ነበር፡፡ ታላቁ የሬጌ አቀንቃኝ ቦብ ማርሌ ‹‹ከጥቁርም፣ ከነጮችም በኩል ሳልሆን ከፈጣሪ በኩል ነኝ›› ያለውም የአባቶቹን መንፈስ ለመግለጽ ይመስለኛል፡፡ የሆነው ሆኖ በዚህ መልኩ የዓለም ሕዝብ ወንድማቸው እንደሆነ አስመስክረዋል፡፡

ስለዚህ አፍሪካን አንድ አገር የማድረጉ ጉዞ ወደ ኋላ የመመለስ እንጂ አዲስ መንገድ አይደለም፡፡ ይህ ጉዞ የመላው ጥቁር ይሁን የተቀረው የዓለም ሕዝብ ወደ ነባር ማንነቱ የመመለስ ጉዞና የአኅጉሩ ካርታም ይዘት አሁን ካለው ይልቅ የዓለም ሉል ተደርጎ መቆጠር የሚገባው ነው፡፡ ፈቃዳቸው ቢሆን በየዘርፉ ያሉ የዓለም ሕዝቦች  ካልሆነም በበላይነት ኃላፊነት ያለባቸው የጥቁር ሕዝቦችን ርብርብን የሚጠይቅ ነው፡፡

ሆኖም ችግሮቻችንን አቃለን በአንድ የመጠቃለላችን ጉዞ ዕውን እንዲሆን ግን በፖለቲከኞቹ አቅም ብቻ የሚሳካ አይደለም፡፡ ቢሳካም ዘመኑን እጅግ ያርቀዋል፡፡ ምክንያቱም ፖለቲከኞቹ ይህንን አጀንዳ ከማፅደቃቸው አሥርና ሃያ ዓመት ቀደም ብለው ሚሊዮኖችን በጎጥ በጎጥ እያቧደኑ፣ ስንቅ ሰፍረውና ትጥቅ አስታጥቀው በሌላ መንገድ ወደ ቀበሌው ሰደውታል፡፡ ለ2063 አኅጉርን እንደ አገር ለማዋቀር ይቅርና አውራጃ ለመመሥረት ቢፈልጉት ከየትም አይገኝም፡፡ በተለይ በግጭት አፈታቱ መስክ የፖለቲከኞቹ አማራጭ የሆነው መሣሪያ አስታጥቆ ሰላም ለማስከበር የሚደረገው ጥረት ዘላቂ መፍትሔ መሆን አይችልም፡፡ ንፁኃን ሕፃናትና አዛውንቶች በቤታቸው፣ በርካታ አምራች ኃይል ወጣት በጦር ሜዳ መሣሪያ ታቅፈው ሕይወታቸው አልፏል፡፡  ብዙኃን ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡ የሰው ልጅን የእጅ አሻራ፣ የእግር ዳናና ወዝ የታተመባቸው ከተሞች የያዙትን ቅርስ እንደታቀፉ ላይመለሱ ፈርሰዋል፡፡ በአፍሪካ የኢስላም ሥልጣኔ ተሸክመው የነበሩ የማሊ ከተሞች ላይ የደረሰውን መመልከት ይቻላል፡፡ ስለዚህ የአንድነት ጉዞውም ይሁን የሰላም ማፈላለጉና የማስፈኑ ሒደት አዲስ ዘዴን ሊያካትት ይገባል፡፡ በተለያዩ ዘርፍ ውስጥ ያሉና በርካታ ተከታይ ያላቸውን የፕሮፌሽናሎች ኅብረቶችን በአኅጉር ማኅበር ደረጃ እንዲዋቀሩና ድጋፋቸውን አማራጭ  አድርጎ ሊያካትት ይገባዋል፡፡ ከዚህም መሀል በርካታ ተከታይ ያላቸውን የእግር ኳስ ተጨዋቾች ኅብረት በተጨባጭ አማራጭ ሆኖ መቅረብ ይችላል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ተጨዋቾች ኅብረት በአንድ በሚመክሩበት ወቅት የተጨዋቾቹ ተከታዮች ቁጥር በእርግጠኝነት በዓለም ካሉ ትላልቆቹ እምነቶች ተከታዮች የሚተናነስ አይደለም፡፡

ሃይማኖቶች ለሚከተሏቸው ሰዎች በርካታ አበርክቶን ሰጥተዋል፡፡ የሰው ልጅ ከምንም የመጣ ሳይሆን ቅድመ ዓለም ጀምሮ ታሪክ የነበረው እንደሆነ፣ ከሞተም በኋላ ምንም ሆኖ እንደማይቀር ሰማይ ቤት ሕይወት እንደሚጠብቀው ተስፋን አሳድረውበታል፣ በሰላም መንገድ መርተውታል፣ እንዲተዛዘን አድርገውታል፣ ከአንድ ፈጣሪ የተገኘ አንድ ሕዝብ እንደሆነ አስገንዝበውታል፡፡ ታዲያ የአፍሪካ እግር ኳስ ተጨዋቾችም ያን ያህል ባይሆን እንኳን ተከታዮቻቸውን በሰላም መንገድ በመምራት፣  እንዲተዛዘን፣ እንዲተሳሰብና በኅብረት እንዲቆም የማድረግና አፍሪካን እንደ አንድ አገር የማዋቀሩ ሒደትን በታሰበው ጊዜ ዕውን ለማድረግ አቅሙ ይፈጥራል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles