Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልበስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

ቀን:

በአንዋር አባቢ

ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡ ገና ታዳጊ እያለች ነበር በእጅ ሥራዎች ፍቅር የወደቀችው፡፡ አራራት ታምራት ከልጅነት ዕድሜዋ አንስታ ለእጅ ሥራዎች ለየት ያለ ስሜት አላት፡፡ መሥራት ያስደስታታል። በቤታቸውና በዘመድ አዝማዱ የነበሩ የተለያዩ የስፌት ዓይነቶች ቀልቧን ይስቡት እንደነበር ታስታውሳለች። ውስጣዊ ፍላጎቷ የሆነውን የእጅ ሥራ ለመልመድና ለመሥራት የተነሳሳችውም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረችበት ወቅት ነው፡፡ ወጣቷ ሥራ ፈጣሪ የኪነ ሕንፃ ባለሙያም ብትሆንም እንዲያግዛት የአካውንቲንግና ማኔጅመንት ትምህርቶችን ቀስማለች። የመጀመርያ ዲግሪዋን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በምትማርበት ጊዜ ነበር ውስጣዊ ፍላጎቷን ዕውን ለማድረግ በጎንደር ገበያ ጥጥ ከሚፈትሉ፣ የስፌትና ሌሎች የእጅ ሥራዎችን ከሚሠሩ ሰዎች ጋር ወዳጀነት የመሠረተችው፡፡

ወጣቷ ስንደዶን ከመርፌ፣ ከክርና ከወርቀ ዘቦ እያዋሃደች ኢትዮጵያዊ መገለጫ የሆኑ ቁሳቁሶችን በዓይነት በዓይነቱ አዘጋጅታ ለገበያ ታቀርባለች።

- Advertisement -

አራራት ዛሬ ላይ የስፌት ሥራዎችን ከጎንደር ገበያ በተማረችው መሠረት በተለያየ ዲዛይን እያሳመረች ለገበያ ታቀርባለች። የዲዛይንና የቀለም ሥራው ኮምፒዩተር ላይ ከተጠናቀቀ በኋላ በሰዎች እጅ የሚሠራ እንደሆነም ከሪፖርተር ጋር በነበራት ቆይታ ተናግራለች።

ወጣቷ ሥራ ፈጣሪ ወደ ሥራው ያኔ ገና ስትገባ አምስት ሺሕ ብር ብቻ በመያዝ ነበር ስንደዶ፣ ሰበዝና ክር የገዛችው፡፡ በቤቷ ውስጥ ተቀምጣ ከጀመረችው ሥራዎቿ መካከል በስፌትና በክር የተሠሩ የአበባ ማስቀመጫ ገንቦዎች ቀዳሚዎች ነበሩ። ገንቦዎቹን ለደንበኞቿ ማቅረብ ጀመረች፣ ሥራዎቿ ተቀባይነት እያገኙ ቀስ በቀስ እያደጉ መምጣት ሲጀምሩ ሥራዋን በማስፋት አንድ ሁለት በማለት ሠራተኞችን በመቅጠር ‹‹ቱባ ባይ አራራት›› በሚል ስያሜ ድርጅቷን ማቋቋም ችላለች። በአምስት ሺሕ ብር  የተጀመረው የስፌት ሥራም አሁን ላይ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ደረጃ ላይ ደርሷል። በስፌት ሥራዎቿ የተለያዩ የመገልገያ ቁሳቁሶችን፣ የቤት ውስጥና የቢሮ ጌጣ ጌጦችን በመሥራት ለገበያ እያቀረበች ትገኛለች፡፡ ሥራዎቿን በተለያዩ አገሮች ኤምባሲዎች፣ በታዋቂ ሰዎች ቢሮና መኖሪያ ቤት፣ በሒልተን አዲስ አበባ፣ በኢንቨስትመንት ኮሚሽንና በተለያዩ ሎጆች ውስጥ የሚገኙ እንደሆነ አጨዋውታናለች።

አራራት ከምትሠራቸው የስፌት ሥራዎች መካከል አንደኛው እርቦ የሚባለው የሰፌድ ዓይነት ሲሆን፣ ሰፌዶቹ የተለያየ ዓይነትና መጠን ያላቸውና ለግድግዳ ጌጥ መሆን የሚችሉ ናቸው። ከሰፌዶቹ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ የአበባ ማስቀመጫ ገንቦዎችንም እንዲሁ በዲዛይንና መቀለማቸው በማመሳሰል የምትሠራ ሲሆን፣ በሽመና የሚሠሩ የሶፋ ትራሶች፣ ከምንጣፍና ከመጋረጃዎች ጋር በማመሳሰል ዘመናዊ በሆነ መንገድ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችን በዲዛይንና በቀለም አመሳስላ ታዘጋጃለች፡፡

ሥራው በእጅ የሚሠራ እንደመሆኑ በአሁን ወቅት 40 ሴቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ችላለች። የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ሴቶችም የቤት እመቤትና በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ የጎንደር ሴቶች እንደሆኑ ትናገራለች። ከእግራቸው ሥር ተቀምጣ የስፌትና ጥጥ የመፍተል ሙያን የተማረችው አራራት፣ የሥራ ዕድሉንም ለእነዚሁ ሴቶች ፈጥራለች። ሴቶቹ የተሰማሩበት የስፌት ሥራ በቋሚነት ገቢ እንዲያገኙበት አድርጓቸዋል።

 ሥራውን የሚሠሩት ሴቶች በተለያየ ምክንያት ሙሉ ጊዜያቸውን በቤት ውስጥ የሚያሳልፉ እናቶች እንደሆኑ ያወጋችን አራራት፣ በተለያዩ ጫናዎች ከቤት መውጣት ያልቻሉ እናቶች ከቤት ሳይወጡ ሠርተው ገቢ ማግኘት የቻሉበት መንገድ በመፈጠሩ እጅግ ደስተኛ እንደሆነች ትናገራለች። ሥራውን ለመሥራት የሚያስችሉ ስንደዶ፣ ሰበዝ፣ የተለያዩ ክሮች፣ መስፊያና ሌሎች ግብዓቶች ጭምር ባሉበት የሚቀርብላቸው ሲሆን በኮምፒዩተር የተዘጋጀው ዲዛይንም በወረቀት ይቀርብላቸውና ዲዛይኑን መሠረት አድርገው ይሠራሉ።

የስፌት ሥራዎቹ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተለመዱ ቢሆንም እንደየአካባቢውና አሠራሩ የሚለያይ እንደሆነ ያስረዳችው አራራት፣ ሙያውን የለመደችው በሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢ እንደመሆኑ በአካባቢው የተለመደውን በክር የሚሠራውን ስፌት ትሠራለች። የስፌት ሥራውም በስንደዶው ላይ የተለያዩ ቀለማት ያላቸው ክሮች በተቀመጠው ዲዛይን መሠረት የተጠለፉ የተንቆጠቆጡ የስፌትና የአበባ ማስቀመጫ ገንቦዎች ናቸው። ከአካባቢው ባገኘችው ልምድና ዕውቀት በመነሳት ወደ ሥራ የገባቸው አራራት ቁሳቁሶቹን የምታሠራው በጎንደርና ባህር ዳር አካባቢ ነው። ለስፌት ሙያና ለጥጥ መፍተል ባላት ተነሳሽነት ሙያውን ተምራ ወደ ሥራ መቀየር ችላለች፡፡

ተዘንግቶ የቆየውን ቱባ ባህል በዘመናዊ መንገድ ከማስተዋወቅ ባለፈ ምርቶቿን ለውጭ ገበያ በማቅረብም የኢትዮጵያን ባህል የማስተዋወቅ ሥራ እየሠራች ትገኛለች። ኢትዮጵያዊ ማንነትን አንፀባርቆ የሚያሳይ ሥዕል በመፍጠር ሰዎች ወደ ቱባ ባህላቸው መመለስ እንዲችሉ ከማድረግ ባለፈም የስፌት ሥራ ዓለም አቀፍ እንዲሆን እያደረገች ትገኛለች፡፡

አራራት በስፌት ሥራዎቿ ተወዳድራ ኢትዮጵያን በመወከል በተለያዩ አገሮች ተጉዛለች፡፡ በቅርቡ የኔዘርላንድ ኤምባሲ ባዘጋጀው ውድድር ላይ ተሳትፋ አሸናፊ ለመሆን ችላለች፡፡

በኢትዮጵያ ባህላዊ የስንደዶ ሥፌትና የክር ጥልፍ ሥራዎች ለኢትዮጵያውያን ሴቶች ሥራ መፍጠር የቻለች ሴት በሚል ‹‹ላዮነሲስ ኦፍ አፍሪካ››  የፊት ገጹ ላይ ይዟት ወጥቶ ነበር፡፡

‹‹ላዮነሲስ ኦፍ አፍሪካ›› በሜላኒ ሀውኬን አማካይነት በደቡብ አፍሪካ የተመሠረተ ጀማሪ የአፍሪካ ሴት ሥራ ፈጣሪዎችን የሚያበረታታ ኮርፖሬሽን ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኪነ ሕንፃ ሙያ የተመረቀችውን አራራት ታምራት ‹‹ምርጥ ሴት ሥራ ፈጣሪ›› በሚል አሞካሽቷታል፡፡

አራራት በኢትዮጵያ የ‹‹ቱባ ባይ አራራት›› የንግድ ምልክት ባለቤትና የሥራ ፈጠራው መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንደሆነችም አትቷል፡፡

የኪነ ሕንፃ ባለሙያዋ ሥራ ፈጣሪ የዓመቱ ምርጥ ሥራ ፈጣሪ የሚለውን ዕውቅናም እንዳገኘች አትቷል፡፡

ሥራ ፈጣሪዋ ወጣት የኢትዮጵያ ሴቶች ባላቸው ሙያና ጥበብ ግድግዳዎች ላይ የሚሰቀሉና ወለል ላይ ለአበባ ማስቀመጫነት የሚያገለግሉ በስንደዶ የተሠሩ ስፌቶችንና የአበባ ማስቀመጫዎችን፣ በጨርቅ ላይ የተጠለፉ የትራስና የአልጋ ልብሶችን በማምረት ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ እያገዘች መሆኗንም ጠቅሷል፡፡

ሥራ ፈጣሪዋ ወጣት እ.ኤ.አ. በ2030 እስከ 500 ለሚደርሱ ሴቶች ሥራ የመፍጠር ራዕይ እንዳላትም ኮርፖሬሽኑ በመረጃው ያመላክታል፡፡ አሁን ደግሞ በቅርቡ በናይጀሪያ ሌጎስ በሚካሄደው የአፍሪካ ምርጥ ሥራ ፈጣሪዎች ውድድር ዕጩ መሆን ችላለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...