Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

ቀን:

‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ የጤና አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ  እያለ፣ ዓለም ለኤችአይቪ ተገቢውን ምላሽ አለመስጠቱ አደጋ ላይ ይገኛል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት የኤችአይቪ ግቦች ላይ የነበረው ትጋትና ግስጋሴ ቆሟል፣ ሀብቱ ቀንሷል፣ እናም በዚህ ምክንያት የሚሊዮኖች  ሕይወት ለአደጋ ተጋልጧል። ኤችአይቪ የዓለም የጤና ቀውስ ሆኖ እንዲቆይና እንዲቀጥል ካደረጉት ውድቀቶች መካከል መከፋፈል፣ ልዩነትና የሰብዓዊ መብት አለማክበር ይጠቀሳሉ፤››

ይህን ኃይለ ቃል የዓለም ጤና ድርጅት ያስተጋባው የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የኤድስ ቀን ምክንያት አድርጎ ነው። በየዓመቱ ኅዳር  22 ቀን (ዲሴምበር 1) የሚከበረው ቀኑ የዚህ ዓመት መሪ ቃል እኩል ማድረግ  (Equalize) ነው።

ይኸው የዓለም ኤድስ ቀን በኢትዮጵያ ከተሞች ‹‹ፍትሐዊና ተደራሽ የኤችአይቪ ኤድስ አገልግሎት!›› በሚል መሪ ቃል  ተከብሯል። በተለይ በአዲስ አበባ በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያ የኤችአይቪ የሥርጭት መጠን መቀነስ ቢቻልም አሁንም በየደረጃው ከፍተኛ መዘናጋትና ቸልተኝነት አለ፡፡ የኤችአይቪ የሥርጭት ምጣኔ 0.93 በመቶ ሲሆን በዚህ ሥሌት 617,921 (62 በመቶ ሴቶች) በላይ የሚሆኑ ወገኖች ኤችአይቪ በደማቸው እንደሚገኝ በ2013/14 የተሠራውን ግምታዊ ቀመር ያሳያል ብለዋል፡፡ በ2014 ብቻ በአገሪቱ አዲስ ኤችአይቪ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከ35 ሺሕ በላይ ነበር።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የሥርጭቱ ምጣኔ ለመቀነስ እ.ኤ.አ. በ2025 ከተቀመጠው የሦስቱ 95 ግቦች አንፃር ወረርሽኙን ለመግታት የጤና ሚኒስቴር፣ ክልሎችና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የመሪዎችን ትኩረትና አጀንዳ ማድረግ ውጤቱን ለማሻሻል እየተሠራ ነው፡፡

ኤችአይቪ ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የውጭ ሀብት እየቀነሰ መምጣቱን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠትና ዋና የትኩረት አቅጣጫው በማድረግ እየሠራ መሆኑን፣  ማጠናከርና የማኅበረሰቡን ተሳትፎና ባለቤትነት እንደገና በማደስ እ.ኤ.አ. በ2030 ኤድስ የማኅበረሰቡ የጤና ችግር እንዳይሆን የተቀመጠውን ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ራዕይ ዕውን ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሯ  መግለጫ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት የኮቪድ-19 ወረርሽኝና ሌሎች አገር አቀፍ ግጭቶችና መፈናቀሎች በኤችአይቪ መከላከልና ቁጥጥር ሥራ ላይ ጫና አሳድሯል። በተለይ አገራዊ የኤችአይቪ ሥርጭት ምጣኔ ከክልል ክልል፣ በክልል ውስጥ ከአንድ ቦታ ሌላ ቦታ፣ በተለያዩ ማኅበረሰብ ክፍሎች እንዲሁም በከተማና በገጠር ከፍተኛ መሆኑን ሳይጠቅሱ አላለፉም።

በአንዳንድ አካባቢዎች በግጭትና መፈናቀል ምክንያት የጤናውን ሽፋን በአግባቡ ለማከናወን አዳጋች ማድረጉን፣ የሕፃናትና የአፍላ ወጣቶች የኤችአይቪ ሕክምና ሽፋን አነስተኛ መሆን፣ ቫይረሱ በደማቸው በሚገኝ ወገኖች ላይ  አድሎና ማግለሎች በመኖራቸው ይህንን ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለማከናወን እየተጣረ ነው።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ያደታ በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ በትምህርት ቤትና ከዚያም ውጪ ለሚገኙ ልጃገረዶችና አፍላ ሴቶች ቀጣይነት ያለው የኤችአይቪ መከላከል ትምህርትና ምርመራ  እንዲያገኙ፣ ሥርዓተ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን የመከላከል አቅም እንዲኖራቸው መደረግ አለበት።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ  በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንደገለጸው፣ በከተማይቱ የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት 3.3 በመቶ ነው።  በመሆኑም ከተማዋ የአገሪቷ ዋና ከተማ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ  ሥርጭቱ ከፍተኛ በመሆኑ አሁንም ትኩረት በመስጠት መሥራት   እንደሚገባ የጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ  ሙሉጌታ እንዳለ (ዶ/ር)  ገልጸዋል።

እንደ ቢሮው መግለጫ፣ አዲስ አበባ  በቫይረሱ ሥርጭት ከጋምቤላ ቀጥላ  በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ በመሆኑ የመከላከልና የመቆጣጠር እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራው አሁንም ትኩረት ተደርጎ መሠራት አለበት። ኤድስን ለማስወገድ በሚደረግ ጥረት የዓለም መሪዎችና ዜጎች በንቃት እንዲገነዘቡና ለመፍትሔውም በጋራ እንዲቆሙ  የዓለም ጤና ድርጅት  ጥሪውን አቅርቧል። 

‹‹ኤችአይቪን ለማጥፋት ቃላችንን እናድስ›› ያለው ድርጅቱ፣  የኮቪድ-19 ወረርሽኝና ሌሎች ዓለም አቀፍ ችግሮች የሚያስከትሉትን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመቋቋም እንደሚደረገው ጥረት ሁሉ   የሕዝብ የጤና ጠንቅ የሆነውን ኤድስን ለማስወገድ አዲስ ጥረት ይጠይቃል ብሏል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...