Thursday, May 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

ቀን:

የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም ትምህርት ከጓደኞቻቸው ጋር ክፍል ውስጥ ቢቀመጡም፣ ልባቸው በናዝሬቱ አፄ ገላውዴዎስ ትምህርት ቤት የማርቺንግ (ማርች) ባንድ ሠልጣኞች በተለያየ የሙዚቃ መሣሪያ ያንቆረቁሩት ለነበረው ዜማ የተማረከ ነበር፡፡

‹‹ሁሌም ክፍል ውስጥ ሆኜ ለማርቺንግ ባንድ ዕድሜዬ ደርሶ የምማርበት ቀን ይናፍቀኝ ነበር›› ይላሉ ከልጅነታቸው ጀምሮ አብሯቸው ስላደረገው የሙዚቃ ፍቅር ሲገልጹ፡፡

ይህ ምኞታቸው ግን እሳቸው አንዳሰቡት ሳይሆን ቀርቶ በትምህርት ቤቱ ይሰጥ ከነበረው የማርቺንግ ባንድ ሥልጠና ብዙም ሳይቋደሱ ይቋረጣል፡፡ ገጠመኙ ቢያሳዝናቸውም ፍላጎታቸውን ከማሳካት አልቦዘኑም፡፡

- Advertisement -

ያ የልጅነት ልባቸውን ከቀለሙ ትምህርት ያሸፍት የነበረውን የማርች ሙዚቃ መክሊታቸው አድርገው ተነሱ፡፡ ያኔ በልጅነታቸው የተመኙት የሙዚቃ ትምህርት ተሳክቶላቸውም ኑሯቸው ሆነ፡፡

ሌተና ኮሎኔል ሲሳይ ፈቃዱ ይባላሉ፡፡ ካለፉት 35 ዓመታት ጀምሮ በሙዚቃ ሥራና መምህርነት እያገለገሉ ነው፡፡ የጡረታ ጊዜያቸውን ደግሞ እንዲሁ ማሳለፍም አልፈለጉም፡፡

በአንድ ወቅት በትምህርት ቤቶች ውስጥ ብልጭ ብሎና የተለያዩ ሙዚቀኞችን አፍርቶ የጠፋው ማርቺንግ ባንድ እንደገና እንዲያንሰራራ ገንዘባቸውንና ጊዜያቸውን ሰውተው እንዲሁም ለቤተሰባቸው መስጠት የሚገባቸውን ጊዜ ቀንሰው  ዳግም በትምህርት ቤቶች ይጀመር ዘንድ በ2014 ዓ.ም. የትምህርት ቤቶችን በር ማንኳኳት ጀመሩ፡፡

ለረዥም ዓመታት በአጠቃላይ የሙዚቃ መምህርነትና ኃላፊነት ያገለገሉት ሌተና ኮሎኔል፣ በአብዛኛው ለፕሮቶኮል ሥራዎች የሚውለውንና በሠልፍ ትርዒት መልክ የብራስ፣ ውድዊንድ፣ ሳክስፎን፣ ክላርኔት፣ ፍሉት፣ ትራምፔት፣ ዩፎኒየም፣ ሱዛፎንና ሌሎች የሙዚቃ መሣሪያዎች ጥቅም ላይ ውለውና በርካታ ባለሙያዎች ተቀናጅተው በጎዳና ላይ የሚሠሩትን የማርቺንግ ባንድ ትዕይንት በትምህርት ቤቶች ያንሰራራ ዘንድ በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የበጎ ፈቃድ ሥራቸውን ጀምረዋል፡፡

ማርቺንግ ባንድ በ17ኛው ክፍለ ዘመን እንደተጀመረ ታሪክ ያሳያል፡፡ ክወናውም በወታደሩ መንደር ውስጥ ነበር፡፡ ወታደራዊ እሴቶች የሚጎለብቱበት፣ የሠልፍ ትርዒቶች የሚደምቁበትም ነው፡፡ በእንግሊዝ፣ በአሜሪካና በሌሎችም የምዕራቡ ዓለም አገሮች ማርቺንግ ባንድ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰው በመከላከያ ተቋማት ውስጥ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ደግሞ ወደ ትምህርት ቤት እየተስፋፋ ሄደ፡፡ አሜሪካ እንደ አብነት ብትነሳ፣ በኮሌጆችና በዩኒቨርሲቲዎች ብቻ እስከ 800 ሰዎች በአንዴ የሚሳተፉበት በርካታ ማርቺንግ ባንዶች አሏት፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ፣ ማርቺንግ ባንድን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት አርመኖች እንዳመጡት ይነገራል፡፡ ንጉሡ በ1923 ዓ.ም. ለሚያከብሩት የንግሥ በዓላቸው ከቤንሻንጉል አካባቢ የመጡ ሰዎች ሥልጠና ተሰጥቷቸው የነበረ ቢሆንም፣ በጣልያን ወረራ ምክንያት ተቋረጠ፡፡

ከ1937 ዓ.ም. ወዲህ ግን በቀድሞ የክብር ዘበኛ በሚባለው ወታደራዊ ክፍል፣ በመቀጠልም በምድር ጦር፣ ፖሊስ ሠራዊት በኋላም ባህር ኃይልና አየር ኃይል እየተስፋፋ ሄደ፡፡ ሁሉም ወታደራዊ ክፍሎችም የማርቺንግ ባንድ ነበራቸው፡፡

የሰሜን ዕዝ፣ የምዕራብ ዕዝ፣ የምሥራቅ ዕዝ በሚባሉት ሁሉ ኦርኬስትራዎችና ማርቺንግ ባንዶች ተስፋፍተው ነበር፡፡ በተለይ ሰሜን ዕዝ ከማዕከላዊ ዕዝና ከምድር ጦር የማይተናነስ ማርቺንግ ባንድ ነበረው፡፡

በኋላም ወደ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ጀመረ፡፡ በተለይ ከ1960ዎቹ አጋማሽ እስከ 70ዎቹ አጋማሽ ድረስ ጠንካራ የማርች ባንዶች በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነበሩ፡፡

ሌተና ኮሎኔል ሲሳይ መረጃዎችን አገላብጠውና ታሪኩን የሚያውቁትን ጠይቀው እንደነገሩን፣ ማርቺንግ ባንድ በትምህርት ቤት ደረጃ ለመጀመርያ ጊዜ የተቋቋመው በ1950ዎቹ በደሴ ወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ነው፡፡

በኋላም ተስፋፍቶ በሐረር መድኃኔዓለም፣ በአዲስ አበባ ኮከበ ፅባህ፣ ዳግማዊ ምኒልክ፣ በናዝሬት አፄ ገላውዴዎስና በአርሲ ራስ ዳርጌ ትምህርት ቤቶችም ዘልቆ ነበር፡፡

የባህር ኃይል በርካታ ሙዚቀኞችም ከዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ማርቺንግ ባንድ የወጡ ነበሩ፡፡ የአሁኑን የኢትዮጵያን ሕዝብ መዝሙር ዜማ የደረሱት ሰለሞን ሉሉ፣ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህሩ አቶ በቀለ ደብሬ እና ዳይሬክተሩ አቶ ተክለዮሐንስ ዝቄ፣ መስፍን አበበ፣ ዓለማየሁ ወልደዮሐንስና ሌሎችም በርካታ ባለሙያዎች ከማርቺንግ ባንድና ከኦርኬስትራ የወጡ ነበሩ፡፡

የደሴው ወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤትና የናዝሬቱ አፄ ገላውዴዎስ የማርቺንግ ባንድ ሲቋቋም ከፍተኛ አበርክቶ የነበራቸው አቶ ብሥራት ታመነም የዚሁ ውጤት ናቸው፡፡

ይህ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በወታደራዊ ክፍሉ የተጀመረውና በኋላም በትምህርት ቤቶች ተስፋፍቶ የነበረው ማርቺንግ ባንድ፣ በ1970ዎቹ አጋማሽ ከትምህርት ቤት ቆይታው ተስተጓጎለ፡፡

‹‹የማርቺንግ ባንድ በትምህርት ቤቶች ውስጥ መኖር የሙዚቃውን ኢንዱስትሪ ያሳድጋል፣ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች በዘርፉ እንዲገቡ መሠረት ይሆናል፣ የሥራና የገቢ ምንጭም ነው›› የሚሉት ሌተና ኮሎኔል ሲሳይ፣ በትምህርት ቤቶች ላለፉት 40 ዓመታት ያህል ተቋርጦ የነበረው ማርቺንግ ባንድና ኦርኬስትራ እንዲያንሰራራ በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን መልምለው በነፃ ማሠልጠን ጀምረዋል፡፡

በ1975 ዓ.ም. አካባቢ በአፄ ገላውዴዎስ ተማሪ በነበሩበት ጊዜ የትምህርት ቤቱን ማርቺንግ ባንድ ተቀላቅለው ብዙም ሳይማሩ ሥልጠናው መቋረጡ ቁጭት እንደፈጠረባቸው ያስታወሱት የሙዚቃ ባለሙያው፣ የግል የሙዚቃ ትምህርት ቤትና የማርች ሙዚቃ ባንድ ለማቋቋም ያቀዱት ከአገር መከላከያ ሚኒስቴር በጡረታ ከመገለላቸው ከ2011 ዓ.ም. በፊት ነበር፡፡

ለሰላም ማስከበር ሥራ ወደ ውጪ የሄዱባቸው አጋጣሚዎች ደግሞ በርካታ የውጭ ዜጎች በተሳተፉበት ሥራዎቻቸውን አቅርበው፣ በዑጋንዳ ኢንቴቤ የሦስት ቀናት ጉብኝት ዋንጫ ከማስገኘቱም በላይ፣ ዓላማቸውን ለማሳካት መልካም ዕድል የፈጠረ ነበር፡፡ በወቅቱ ያፈሩትን ጥሪት ቤት ለመግዛት አሊያም ለሌሎች ነገሮችን አላዋሉትም፡፡ ይልቁንም የተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች ገዙበት፡፡

በመከላከያ ውስጥ በነበራቸው ከሦስት አሠርታት ያላነሰ የሙዚቃ መምህርነት ቆይታና ከበርካታ ጓደኞቻቸው ጋር ሆነው ያፈሩትን ዕውቀትና ልምድ ለተማሪዎች ለማካፈል አቀዱ፡፡ የግል የሙዚቃ መሣሪያዎቻቸውን ይዘውና የአንድ ዓመት የሥራ ዕቅድ ነድፈው ከዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ለመለመሏቸው 30 ተማሪዎች በ2014 ዓ.ም. ክረምት ለሦስት ወራት፣ እንዲሁም በበጋው የትምህርት ወቅት ከትምህርት ሰዓት ውጪ በማርሽ ባንድ ማሠልጠኑን ተያይዘውታል፡፡

ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች ከቀለም ትምህርታቸው ጎን ለጎን የተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች ሥልጠና እየወሰዱ ሲሆን፣ በቀጣይ የድምፅ ሥልጠና ለመስጠትም አቅደዋል፡፡

ቀጥታ በባንድ የታጀበ የሙዚቃ ዝግጅት እየጠፋና በኤሌክትሮኒክስ እየተተካ መሆኑ በርካታ ሙያተኛ በብቃትና በብዛት እንዳይወጣ የሚያደርግ መሆኑን የጠቆሙት ሌተና ኮሎኔል ሲሳይ፣ በትወና፣ በሥዕልና በሙዚቃ ፍላጎት ያላቸውን ልጆች ለማውጣት መሠረቱ ትምህርት ቤቶች በመሆናቸው፣ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በብቁ ባለሙያ የታገዘ ሥልጠና ቢሰጥ የሚል ምክረ ሐሳብም አላቸው፡፡

ለኪነ ጥበቡ ዋጋ ከፍለው በሚሠሩት ልክ ሥራው ገቢ ባያስገኝም፣ ወደፊት የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮና ሌሎች ተቋማት ይደግፉታል፣ ተቋማዊም ያደርጉታል የሚል እምነትም አላቸው፡፡

ተማሪዎቹ ሠልጥነው ገቢ የማያገኙበት ከሆነ ትርጉም እንደማይሰጥ በመጠቆምም፣ የሠለጠኑ ተማሪዎች በየፓርኮቹ፣ በየበዓላትና በየዕረፍት ቀናት በጎዳና የማርሽ ባንድ ትርዒት እያሳዩ ገቢ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋልም ይላሉ፡፡

በ1976 ዓ.ም. በባህር ኃይል በመርከበኝነት ለአንድ ዓመት የሰለጠኑት ሌተና ኮሎኔል ሲሳይ፣ በውድድር ባገኙት ዕድል በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት በመማር ከተመረቁ በኋላ አንድ ዓመት በባህር ኃይል በሙዚቃ መምህርነት አገልግለው በ1983 ዓ.ም. በነበረው የመንግሥት ለውጥ ሥራቸውን አቋርጠው እንደነበር ነግረውናል፡፡

ሆኖም ከሁለት ዓመታት በኋላ መከላከያ ሚኒስቴር በመምህርነት ያወጣው ማስታወቂያ ለእሳቸው መልካም ዕድልን የፈጠረ ነበር፡፡ ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ በሚኒስቴሩ በሙዚቃ መምህርነት በመቀጠር ከ25 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡

በመከላከያ ሚኒስቴር የነበራቸውን የሥራ ቆይታ አስመልክቶ ከሚኒስቴሩ የተሰጣቸው የአገልግሎት ማስረጃ እንደሚያሳየው፣ ከ1977 ዓ.ም. እስከ 2011 ዓ.ም. ድረስ ከባህር ኃይል የክላርኔት ተጫዋችነት እስከ የመከላከያ የሙዚቃ ትምህርት ክፍል መምህርነትና ኃላፊነት አገልግለዋል፡፡

የሙዚቃ ትምህርት ቤቱን ደረጃ ወደ ዲፕሎማ ለማሳደግ በተከናወኑ ሥራዎች አዳዲስ ሐሳቦችን በማቅረብና በጥናት ኮሚቴዎች ውስጥ በመሳተፍ፣ ለማርሽ ባንድ ወጥ የፈጠራ ሥራዎችና የኢምቴሽን (ቅጂ) የሙዚቃ ሥራዎችን አቀናብሮ በማሠራት፣ በ2007 ዓ.ም. የተከበረውን ሦስተኛው የሠራዊት ቀን የኪነ ጥበብ ፌስቲቫል በማስተባበር እንዲሁም ለመከላከያ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ አድርገው ለበላይ አካል በማቅረብ፣ ቡድኑን በመምራትና ጥናት በማድረግ መሳተፋቸውንም ማስረጃቸው ያሳያል፡፡

በአገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ የካበተ የሙዚቃ መምህርነት ልምዳቸውን ይዘው ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያቀኑት ሌተና ኮሎኔል ሲሳይ፣ በራሳቸው ወጪ ተማሪዎችን በማርሽ ባንድ ማሠልጠን ቢጀምሩም፣ ተግዳሮት መግጠሙ አልቀረም፡፡

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህራንና ሌሎችም ሥልጠናውን የሚሰጡበት አዳራሽ ሰጥተው እያበረታቷቸው ቢሆንም፣ ሥራው ገቢ እያስገኘ አለመሆኑ ለእሳቸው ሥጋት ለሚያሠለጥኗቸው ተማሪዎች ደግሞ የማይጨበጥ ተስፋ እንዳይሆን አሳስቧቸዋል፡፡

በሙዚቃው ዘርፍ የበጎ ፈቃድ ሥልጠና የመስጠት ልምድ አለመዳበሩ፣ ብቁ መምህራን አለመኖር፣ አላቂ የሙዚቃ ዕቃዎች መኖራቸው፣ የሙዚቃ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ በጀት መጠየቁና አጠቃላይ የዘርፉ እንዲሁም እሳቸው ያስተዋሉት ተግዳሮት ሲሆን፣ በግላቸው ደግሞ ችግሮቹን ተቋቁሞ ለመውጣት የሚያስችል የገንዘብ አቅም አለመኖሩ ፈትኗቸዋል፡፡፡

የቀድሞ የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ማኅበር እሳቸው ለሚያሠለጥኗቸው ተማሪዎች ሙሉ ዩኒፎርም እንዳለበሱ ያስታወሱት ሌተና ኮሎኔል ሲሳይ፣ ከጎናቸው ከሚያግዟቸው የሙያ አጋሮቻቸው በተጨማሪ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ትምህርት ቢሮና ሌሎች ተቋማት በግላቸው የጀመሩትን የበጎ ፈቃድ ሥራ ወደ ተቋምነት እንዲቀይሩትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...