Saturday, May 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኦሲፒ አፍሪካ ጨዋማ መሬት ለማከም የሚረዳ ምርምር ይፋ አደረገ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለአርሶ አደሩ የሚሠራጨውን የአፈር ማዳበሪያ በማቅረብ የሚታወቀው ኦሲፒ ግሩፕ አካል የሆነው፣ ኦሲፒ አፍሪካ ጨዋማ መሬቶችን ለማከም የሚረዳ ምርምር ይፋ አደረገ፡፡

ኦሲፒ አፍሪካ ይህንን ጨዋማ መሬት ለማከም የሚረዳውን ምርምር በቤተ ሙከራና ግሪን ሃውሶች ላይ የመጀመሪያ ሙከራ አጠናቆ፣ በማሳ ላይ በሰባት የአዝዕርት ዓይነቶች ሙከራ እያደረገ መሆኑን፣ የኦሲፒ አፍሪካ የኢትዮጵያ ወኪል ጽሕፈት ቤት የአግሮኖሚና የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ቡድን መሪ ሰላምይሁን ኪዳኑ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የምርምር ጥናቱ ‹‹ኮስሞጂፕሰም›› በሚባልና ማዳበሪያ በሚሠራ ጊዜ የሚወጣ ቅሪትን በመጠቀም መሬቶች ወደ ነበሩበት ምርትና ምርታማነት ለመመለስ የሚያስችል መሆኑን ሰላምይሁን (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

በድርጅቱ ይፋ የተደረገው ምርምር እንዴት ተደርጎ ጨዋማ አፈር ማከም ይቻላል?፣ ምን ያህል ውኃ ያስፈልጋል?፣ የትኛው ዕፀዋት ከየትኛው ቢከተል የተሻለ ውጤት ያመጣል? የሚለውን በማቀናጀትና በማሳባጠር ከዚያ የተገኘውን ውጤት ተግባር ላይ የሚያውል መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በዚህ ወቅት በግሪን ሃውስ ውስጥ የተሞከረው ምርምር ውጤት ማስገኘቱን የገለጹት ቡድን መሪው፣ ያንን በመስክ ላይ ለመድገም የማረገገጫ ጥናት እየተሠራ እንደሚገኝ፣ በሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ በጨዋማነት የተጠቁ አፈሮችን በስፋት ወደ ምርትና ምርታማነት እንዲገቡ የሚያስችል ውጤት ላይ መደረሱ ተገልጿል፡፡

‹‹የመሬት ጨዋማነት በተፈጥሮ ያለና የሚመጣ ነው፡፡ በተለይም ወደ ቆላና በረሃማነት የተቀየሩ አካባቢዎች ከፍተኛ የትነት መጠን ስላለ ማንኛውም ውኃ ጥቅም ላይ ቢውል ከጊዜ ብዛት ጨው በአፈር ላይ ይጠራቀማል፤›› ያሉት የቡድን መሪው፣ ‹‹አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መሬቱ በራሱ በተፈጥሮ የጨው ይዘት ያላቸው በተለይም በስምጥ ሸለቆ አካባቢ ከፍልውኃ ጋር የተያያዘ ችግር ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

የምርምር ፕሮጀክቱን ከሁለት አገር በቀል ዩኒቨርሲቲዎች ሐዋሳና ሃሮማያ ጋር በጣምራ የሚሠራ ሲሆን፣ ስድስት የሁለተኛ ዲግሪና እንዲሁም አምስት የፒኤችዲ ተማሪዎች ድጋፍ ተደርጎላቸው እየሠሩበት መሆኑ ታውቋል፡፡

መንግሥት ከፍተኛ መዋለ ንዋይ አውጥቶ የመስኖ አውታር የዘረጋባቸው ነገር ግን በሥራ ሒደት ምክንያት ወደ ጨዋማነት በመቀየር ከምርት ውጭ የሆነ 90 ሺሕ ሔክታር መሬት እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ በመካከለኛው የስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙት ከሰም ተንዳሆ፣ ዱብቲ፣ ዝዋይ እንዲሁም ብላቴ ከፍተኛ ጨዋማ ችግር ያለበት መሬት የሚገኝባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን የቡድን መሪው ገልጸዋል፡፡

መንግሥት የመስኖ እርሻ በመጠቀም አገሪቱን በምግብ ዋስትና የማስቻል፣ ከውጭ የሚገባውን ሰብል ለመተካትና ኤክስፖርትን ለማስተዋወቅ የተነደፈው ስትራቴጂ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እግር በእግር የመስኖ ውኃ ልማትና አስተዳደር ላይ ትኩረት አድርጎ መንቀሳቀስና ለአፈር የሚያስፈልገው እንክብካቤባና ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር መሰል ችግሮች ሲከሰት ለመቆጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ በመስኖ ላይ የተመሠረተ እርሻ ያላቸው አገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳየው፣ ችግሩ ተፈጥሮአዊ ሲሆን፣ ነገር ግን የመቆጣጠር አቅማቸው ከፍተኛ እንደሆነና ችግሩ እንዳይፈጠር ከመከላከል ባለፈ ከተፈጠረ ደግሞ የተጎዳውን እንደሚያክሙ ሰላምይሁን (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በኦሲፒ አፍሪካ የሚደረገው ምርምር እንደጠበቀ ሆኖ በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በኩል በቀላሉ ከጨዋማ አፈር ጋር ሊላመዱ የሚችሉ ዕፀዋትን በማሳደግ፣ የውኃ አጠቃቀምን በማሻሻል እንዲሁም ችግሩ ተፈጥሮ ሲገኝ የማከም ሥራውን በቴክኖሎጂ እየተደገፈ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች