Thursday, February 29, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሒጂራ ባንክ የ143 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዘገበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት ወደ ሥራ ከገቡት ሁለት ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው ሒጅራ ባንክ፣ በመጀመርያው የሥራ ዓመት ከ1.34 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ቢችልም 143 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ማስመዝገቡ ተገለጸ፡፡

ባንኩ እሑድ ኅዳር 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በቀረበው ዓመታዊ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርቱ፣ በ2014 የሒሳብ ዓመት ኪሳራ ያስመዘገበው፣ በመጀመርያ ዓመቱ እንደ ጀማሪ ባንክ ሥራ ለማስጀመር ከፍተኛ ወጪ በማውጣቱ መሆኑን አስታውቋል፡፡

እንደ ባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት በ2014 የሒሳብ ዓመት አጠቃላይ ወጪው 170.6 ሚሊዮን ብር ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ ያገኘው ገቢ ደግሞ 27.57 ሚሊዮን ብር ብቻ ስለነበር ከወጪዎቹ አንፃር ገቢው አነስተኛ በመሆኑ ባንኩ በመጀመርያው የሥራ ዘመን 143 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ሊያስመዘግብ ችሏል፡፡

ከአጠቃላይ ገቢና ወጪ አንፃር ብዙ ጀማሪ ባንኮች በመጀመርያ የሥራ ዓመት የወጪ ከፍ ማለትና የገቢ ማነስ የሚያጋጥም በመሆኑ፣ የትርፍ ቅናሽ ሊታይ መቻሉንም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ከገቢ አንፃር ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ እንደመሆኑ መጠን ዋና ገቢ የሚመጣው ከፋይናንሲንግ (ብድር) ከመስጠት ከሚገኝ ትርፍ ስለሆነ፣ በሪፖርቱ ሀብት ማሰባሰቡ ቅድሚያ ሊሰጠው ስለሚገባ ባንኩ በዚሁ ተግባር ላይ ጠንከር ያለ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል ተብሏል፡፡ በመጀመርያዎቹ ስድስት ወራት የሥራ ጊዜው 30 ቅርንጫፎችን በመክፈት ተቀማጭ ገንዘብ የማባሰብ ሰፊ ሥራ ማከናወኑን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ በሒደትም የፋይናንሲንግ (የብድር) አቅርቦት ሥራ ውስጥ የገባው በመጨረሻው የሒሳብ ዓመቱ አራት ወራት ውስጥ በመሆኑ፣ የተመዘገበው ገቢ ሊገመት እንደሚችለው አነስተኛ ሊሆን መቻሉንም ሪፖርቱ ውስጥ ተካቷል፡፡ ካሉት እውነታዎች አንፃር በሒሳብ ዓመቱ ኪሳራ ማጋጠሙን ተጠባቂ እንደነበርም ከቀረበው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡

አንዳንድ ወጪዎች እንደ ረዥም ጊዜ ኢንቨስትመንት ሊታዩ የሚችሉ መሆናቸውን የሚያስረዳው የባንኩ ሪፖርት፣ ባንኩ የገዛው ሕንፃና ለቋሚ ንብረቶች የሚመዘገቡ የዕርጅና ወጪዎች በቀጥታ በገንዘብ የሚደረጉ ወጪዎች ሳይሆኑ ታሳቢ ስለሚደረጉ፣ ለተወሰነ ዓመት ብቻ ተመዝግበው የሚጠናቀቁ መሆናቸውን ይጠቅሳል፡፡ ለሕንፃውና ለተለያዩ ንብረቶች የተደረጉት ወጪዎች በኢትዮጵያ ሁኔታ ከተለመደው አሠራር ባለፈ ለረዥም ጊዜ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉና የወደፊት ትልልቅ ወጪዎችን የሚያስቀሩ ጭምር ስለሆኑ፣ በቀጣይ ዘላቂ ትርፉን ለማግኘት የሚያስችሉ እንደሆነም በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ባንኩ በመጀመርያ የሥራ ዓመቱ እንደ ጀማሪ ባንክ ሥራ ለማስጀመር ብዙ ወጪዎች እንዲያወጣ ያስገደዱት ዋና ዋና ወጪዎችም በሪፖርቱ ተካተዋል፡፡ እነዚህም ለሠራተኞች ደመወዝ፣ ለቅርንጫፎች ቢሮ ኪራይ፣ በመጀመርያው ዓመት ለተገዛው የዋናው መሥሪያ ቤት ሕንፃ ዕርጅና ወጪ፣ ለባንክ ቴክኖሎጂና ለዲጂታል ሲስተሞች ዕርጅና ወጪ፣ ለቢሮ ዕቃዎች ዕርጅና ወጪ፣ ለጽሕፈት መሣሪያዎች ወጪ፣ ከቅርንጫፎች ከፈታ ጋር በተያያዘ ለውሎ አበልና ለትራንስፖርት፣ እንዲሁም ለማስታወቂያና ለፕሮሞሽን ወጪዎች ናቸው ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል ውጤታማ የሆኑ የባንክ ሥራዎችን ለማከናወን የራሱ ሒደት ስላለውና ጊዜ የሚፈልግ በመሆኑ፣ በመጀመርያ የሥራ ዓመቱ ያስመዘገበው ገቢ 27.57 ሚሊዮን ብር እንደነበር ያመላከተው ሪፖርቱ፣ ይህ ገቢ ከወጪዎቹ አንፃር አነስተኛ ስለሆነ ባንኩ በመጀመርያ የሥራ ዘመኑ ኪሳራ ቢያጋጥመውም በቀጣዩ ዓመት ትርፍ የሚገኝበት መሠረት መጣሉን ያሳያል ተብሏል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ ባንኩ ለቀጣይ ትርፍ ሊያስገኝ ይችላል ብሎ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል፣ ለአጭር ጊዜ ኢንቨስትመንት የዋለው 400 ሚሊዮን ብር በዋናነት ተጠቅሷል፡፡ የፋይናንስ ቅድመ ክፍያ ብድር 370.8 ሚሊዮን ብር መሰጠቱንም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ ባንኩ ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርጎ ውጤታማ ከሆነባቸው ተግባራቱ መካከል አንዱ፣ በተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ ረገድ ያስመዘገበው ውጤት ነው፡፡ በዚህ እንቅስቃሴው በሒሳብ ዓመቱ 1.33 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ተችሏል ነው የተባለው፡፡

ባንኩ በቀጣይ ለውጤት የሚያበቁ ተጨማሪ ሥራዎችን የሠራ መሆኑን፣ በተለይ የባንኩን የአምስት ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ በተሳካ መንገድ በመተግበርና ሸሪዓን መሠረት ያደረገ የባንክ አገልግሎት በማሳለጥ ለደንበኞች ቀጣይነት ያለው ጠቀሜታ ማስገኘት የሚሉት ተጠቅሰዋል፡፡

ሒጅራ ባንክ አጠቃላይ የተከፈለ ካፒታሉን ከ862.5 ሚሊዮን ብር በላይ ያደረሰ መሆኑን፣ ባለአክሲዮኖቹ ከስምንት ሺሕ በላይ እንደሆኑና በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የከፈታቸው ቅርንጫፎች 40 ደርሰዋል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች