Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየአካል ጉዳተኞች የሥራ ሥምሪት አካታችነት ሁለት በመቶ ብቻ መሆኑ ተገለጸ

የአካል ጉዳተኞች የሥራ ሥምሪት አካታችነት ሁለት በመቶ ብቻ መሆኑ ተገለጸ

ቀን:

በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች በሥራ ሥምሪት መካተት እንዳለባቸው የሚገልጽ አዋጅ ቢኖርም፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የግል ድርጅቶች የሥራ ቅጥር መሥፈርቶች አካል ጉዳተኞችን በዝቅተኛ ደረጃ እንደሚያሳትፉና አካታችነቱም ሁለት በመቶ ብቻ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው ‹‹አካታች የፈጠራ ሥራና ሽግግራዊ መፍትሔ ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተደራሽነት›› በሚል መሪ ቃል፣ በኢትዮጵያ የተከበረውን 30ኛው የአካል ጉዳተኞች ቀንን በማስመልከት በተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ ነው፡፡

በመድረኩ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች የአካል ጉዳተኞች ማኅበር፣ የአሜሪካ ኤምባሲ፣ እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት የተወከሉ አካል ጉዳተኞችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

- Advertisement -

የአካል ጉዳተኞች የሥራ ሥምሪት መብት በአዋጅ በቁጥር 568/2000 ላይ የተደነገገ ሲሆን፣ አዋጁ ፀድቆ ወደ ሥራ ቢገባም ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የቅጥር ሒደት የሚፈጥር አለመሆኑ በመድረኩ ተነስቷል፡፡ በመሆኑም ለአካል ጉዳተኞች የሚመቹ የቅጥር መሥፈርቶችን አዋጁ በማካተት መሻሻል አለበት ተብሏል፡፡

‹‹በተለያዩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አካል ጉዳተኞችን በማሳተፍ ከችሎታቸው መጠቀም፣ እንዲሁም አካል ጉዳተኞች አኗኗሪ ብቻ ሳይሆኑ ነዋሪ ማድረግ ያስፈልጋል፤›› ሲሉ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች የአካል ጉዳተኞች ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሴ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች በድሎት ውስጥ ሳይሆን በከፍተኛ የኑሮ ውጣ ውረድ ውስጥ የሚኖሩ ናቸው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ 95 በመቶ የሚሆኑ የአካል ጉዳተኞች ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ መሆናቸውን፣ 98 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሥራ መቀጠር አለመቻላቸው በጥናት መረጋገጡን አቶ ሙሴ ገልጸዋል፡፡

አብዛኞቹ ‹‹በሥራ ሥምሪት፣ በተሳትፎ፣ በትምህርት፣ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ጭምር የተካተቱ አይደሉም›› ያሉት አቶ ሙሴ፣ ‹‹በአገራችን አካል ጉዳተኞች በሁሉም የልማት መስኮች ማካተት ያልተለመደና መለመድ ያለበት ወቅታዊ ተግባር ነው፡፡ ይህ ሲሆን ብቻ ነው የሠለጠነና ዘመናዊ ኅብረተሰብ የሚለው ስያሜ ባለቤት መሆን የምንችለው፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የአካል ጉዳተኞችን ቅሬታዎች ለማስተናገድ ባዋቀረው የአካል ጉዳተኞች ምርመራና ክትትል ቡድን አማካይነት፣ በርካታ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል፡፡

ወደ ኮሚሽኑ አካል ጉዳተኞች በሚመጡበት ወቅት አገልግሎት አሰጣጡን አመቺ በማድረግ፣ ደርሶብናል የሚሉትን በደልና ቅሬታ በመከታተል መፍትሔ እንዲያገኙ ያግዛል ተብሏል፡፡

የአካል ጉዳተኞችን ቅሬታ በማስተናገድ ሥራዎችን ማከናወን ከኃላፊነት በዘለለ እንደ ሥራ ጫና መታየት የለበትም ሲሉ አቶ ሙሴ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የሥራ ሥምሪቶች አካል ጉዳተኞችን በልዩ ሁኔታ የሚያስተናገዱበት አመቺ ሁኔታ እንደሌላቸው በመድረኩ የተገለጸ ሲሆን፣ የቅጥር መሥፈርቶቹ ‹‹ዝሆንና ጦጣን እኩል ዛፍ ላይ እንዲወጡ የማዘዝ ያህል ነው›› ሲሉ በውይይት ላይ የተገኙ አንድ ተሳታፊ ተናግረዋል፡፡

በየተቋማቱ ያሉ የሥራ ድርሻዎችን በመለየት ለአካል ጉዳተኛ ምቹ በሆኑ ሥራዎች እንዲሰማሩ መደረግ አለበት ያሉት አቶ ሙሴ፣ አካል ጉዳተኞችን ማሳተፍ የመንግሥትና የበጎ አድራጎት ተቋማት ኃላፊነት ብቻ ማድረግ የተሳሳተ ግንዛቤ በመሆኑ፣ በግል ቢዝነስ ተቋማት፣ በሆቴሎች፣ በባንኮችና በፋብሪካዎች መቅጠርና ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

አካል ጉዳተኞች ሥራ ሲቀጠሩ የተገኘው ዕድል በጠባብ መንገድ በመሆኑ፣ ጠንክረው በመሥራት ከሌሎች ጋር እኩል ለመሆን በትጋት ስለሚሠሩ፣ በግል ዘርፎች ማሳተፍ ምርታማነት እንዲጨምር ያደርጋል ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ለ30ኛ ጊዜ በዓለም ደግሞ ለ31ኛ ጊዜ ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን ኅዳር 24 ቀን 2015 ዓ.ም. በድሬደዋ ከተማ ተከብሯል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ኮንቬንሽንን ከ12 ዓመታት በፊት ተቀብላ የፈረመች ሲሆን፣ የአካል ጉዳተኞች የሥራ ሥምሪት አዋጅ፣ የሕንፃ አዋጅ፣ የቀረጥ ነፃ መመርያና አካል ጉዳተኞችን ከ60 በመቶ በላይ የቀጠረ ድርጅት ከታክስና ቀረጥ ነፃ መሆን አለበት የሚሉት በአገር ውስጥ መውጣታቸው ይጠቀሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...