Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊምስርን የተካው የተቀናጀ የስንዴ ልማት በጊንቢቹ

ምስርን የተካው የተቀናጀ የስንዴ ልማት በጊንቢቹ

ቀን:

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን በምትገኘው ጊንቢቹ ወረዳ ለእርሻ የሚውለው ጥቁር አፈር የሰጡትን የሚቀበልና ፍሬያማ የሚያደርግ በርከት እንዳለው የአካበቢው ማኅበረሰብ ይናገራል፡፡ ከቢሾፍቱ በስተምሥራቅ 27 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ጊንቢቹ ወረዳ በምስር፣ በጓያ፣ በአተር፣ በባቄላና በተለያዩ የአትክልት ምርቶች የሚታወቅም ነው፡፡

አካባቢውን ከሳምንት በፊት በጎበኘንበት ወቅትም ምድሩ ሊታጨድ ሳምንታት በቀሩትና በተቀናጀ የዘር ብዜት በለማ የስንዴ ምርት ተሸፍኖ ዓይተናል፡፡

ቀድሞ በምስር ምርት የሚታወቀው አካባቢው፣ በአንድ ሔክታር መሬት እስከ 33 ኩንታል ምርት ይገኝበት የነበረ ቢሆንም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የምስር ልማት ምርት መስጠት ማቆሙንም አርሶ አደሩን ሐሳብ ውስጥ ከትቶ መሰንበቱን ከአካባቢው አርሶ አደር ሰምተናል፡፡ ሆኖም ለማንኛውም ምርት ምቹ እንደሆነ የሚነገርለት መሬት፣ የወረዳው አርሶ አደር አማራጭ አላሳጣውም፡፡

- Advertisement -

ወ/ሮ ዘርፌ ጌታቸው የጊንቢቹ ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ ለዓመታት ምስርና አትክልት እያለሙ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም 2008 ዓ.ም. በመንግሥትና የነባር ዘሮች ጥበቃ ‹‹አሊያንስ ባዮቨርሲቲ ኤንድ ሲአይኤቲ›› በተሰኘ ተቋም ትብብር የመጣው ፕሮጀክት የተሻሻሉ የስንዴ ዝርያዎች ለአርሶ አደሮቹ ማቅረብ መጀመሩ የምስር ምርቱ እያሽቆለቆለ ለሄደበት አርሶ አደር መልካም አጋጣሚ ነበር፡፡ ሆኖም አርሶ አደሩ ዘሩን ተቀብሎ በስፋት ወደ ምርት የገባው ዘንድሮ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ የተሻሻሉ የስንዴ ዝርያዎችን በተለይም ለፓስታና ለመኮሮኒ የሚሆኑትን በማቅረቡም ወ/ሮ ዘርፌን ጨምሮ በርካታ የአካባቢው አርሶ አደሮች በተቀናጀ የዘር ብዜት ዘዴ ምርታማነታቸውን ማሳደግ የሚችሉበትን አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡

ዓምና ባገኙት አሥር ኪሎ ግራም የፓስታና የመኮሮኒ ምርጥ የስንዴ ዘር በግማሽ ሔክታር መሬት ላይ ማልማት የቻሉት ወ/ሮ ዘርፌ፣ አዲስ ተስፋ የሰነቁበትን የስንዴ ምርት ማግኘታቸውን ይገልጻሉ፡፡

ወ/ር ዘርፌ ‹‹ቀድሞ የተሻሻሉ የስንዴ ዝርያዎች ባለመኖራቸው የምስርና የአትክልት ምርቶች ላይ ተሰማርተን ስናለማ ነበር፡፡ ሆኖም ልፋታችንና ውጤቱ የማይገናኝ ነው፤›› ይላሉ፡፡

በተለይ አካባቢው ምስርና ሌሎችን በማምረት ስለሚታወቅ፣ በእህል ምርት ላይ ደፍሮ የማልማት ልምድ እምብዛም በመሆኑና የስንዴ ምርትን የሚረከቧቸው ነጋዴዎች ምርቱን ስለሚያራክሱ ትኩረት ሳይሰጡት ቆይተዋል፡፡

የአካባቢው አርሶ አደር በተለምዶ በተሰየሙ የስንዴ ዓይነቶች ‹‹ሴት አኩሪ›› የስንዴ ዘር፣ የፓስታና የመኮሮኒ እንዲሁም የዳቦ ሲያለማ ነበር፡፡ ሆኖም ምርቱን ለነጋዴው በተመሳሳይ ዋጋ ሲያስረክብ የፓስታና የመኮሮኒ የስንዴ ዋጋ ከሌሎቹ ከፍ ያለ ነበር፡፡

አቶ አቤቤ ወንድሙ በዘር ብዜት በአንድ ቀርጥ መሬት ላይ የፓስታና የመኮሮኒ ስንዴን ካለሙት አርሶ አደሮች አንዱ ናቸው፡፡ እንደ አቶ አቤቤ አስተያየት፣ ቀድሞ ስንዴ አልምተው ለገበያ ሲያቀርቡ፣ ነጋዴው የፓስታና የመኮሮኒ ምርቱን ‹ለቅንጬ የሚሆን ስንዴ ነው› በማለት ዋጋ ሲያራክስባቸው እንደነበር ለሪፖርተር ያስረዳሉ፡፡

በዘር ብዜት ፕሮጀክት በቀረበው የዱረም ስንዴ ዝርያ በአንድ ቀርጥ መሬት ያለሙት አቶ አቤቤ፣ አራት ኩንታል የፓስታና የመኮሮኒ ምርጥ ዘር ማግኘታቸውን ገልጸው፣ በቀጣይ ዓመት ሰፊ መሬት ላይ ለማልማት ከወዲሁ መሰናዳታቸውን አብራርተዋል፡፡

‹‹ባለማወቅ በነጋዴው የቅንቼ ስንዴ እንደነበር፣ ሲራከስብን የነበረው የተሻሻለው የስንዴ ዝርያ አዲስ ተስፋ አምጥቶልናል፤›› በማለት ሐሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

በወረዳው 15,545 አርሶ አደሮች፣ በ48,889 ሔክታር መሬትን ለዘር አውለዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 36,500 ሔክታር መሬት ስንዴ ተዘርቶበታል፡፡ መሬቱ በዳቦ፣ በፓስታና በመኮሮኒ ስንዴ የተሸፈነ ነው፡፡

ከ85 በመቶ በላይ የሆነው መሬት በሞዴል ክላስተር የለማ ሲሆን፣ ከ300 ሔክታር እስከ 600 ሔክታር የሚደርሱ ስምንት ክላስተሮች መልማታቸውን የጊንቢቹ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አቡሽ አራጌ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ አቡሽ አስተያየት፣ የአርሶ አደሩን ግንዛቤ በመቀየርና በተመሳሳይ መሬት፣ ዝርያና ሜካናይዜሽን መሬት ከማሰናዳት ጀምሮ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸው፣ መሬቱን በክላስተር በማልማት፣ መድኃኒት፣ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ፣ መንግሥት ማቅረቡን ጠቅሰዋል፡፡

‹‹የፓስታና የመኮሮኒ ስንዴ ለማልማት፣ 80 ሴንቲ ሜትር ውኃን አጥልሎ የሚይዝ መንገድ በመጠቀም ምርቱ እንዲለማ ተደርጓል፤›› ሲሉም አቶ አቡሽ አስረድተዋል፡፡

በአካባቢው የአትክልት ምርት ብቻ በመስኖ ሲለማ የቆየ ቢሆንም፣ አምና 1,930 ሔክታር መሬት ላይ የመስኖ ስንዴ መልማቱን የሚያስረዱት አቶ አቡሽ፣ ዘንድሮ ግንዛቤውና ልምዱ አርሶ አደሩ ዘንድ በመኖሩ፣  9,616 ሔክታር መሬት በመስኖ ስንዴ ለማልማት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

በአካባቢው የከሰምንና የሞጆን ወንዞች እንዲሁም በአካባቢው ያሉትን የጉድጓድና የኩሬ ውኃዎችን በመጠቀም ውኃ የማይደርስባቸውን ቦታዎች በፓምፕ በመሳብ ለማልማት መታቀዱንም ጠቅሰዋል፡፡

መንግሥት የፓምፕ፣ የማዳበሪያና የምርጥ ዘር ግዥ ብድር ማመቻቸቱን የሚያስረዱት የጽሕፈት ቤት ኃላፊው፣ ከ58 ሔክታር በላይ ፆም ያደሩ መሬቶች እንዲለሙ መደረጋቸውን አክለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ምርጥ ዘር ለማግኘት ረዥም ርቀት ተጉዘው እንደሚሸምቱ የሚጠቁሙት የአካባቢው አርሶ አደሮች፣ ለአንድ ኩንታል ምርጥ ዘር እስከ 10 ሺሕ ብር ድረስ እንደሚያወጡ፣ ነገር ግን ዘንድሮ በተሰጣቸው የተሻሻለ የስንዴ ዝርያ በሔክታር እስከ 110 ኩንታል ውጤት ማግኘታቸው ተነግሯል፡፡

በጊንቢቹ ወረዳ በፕሮጄክቱ ታቅፈው የፓስታና የመኮሮኒ ስንዴ ምርት ላይ ውጤታማ የሆኑ አርሶ አደሮች የስንዴ ማሳ ጉብኝት የተደረገ ሲሆን፣ በፕሮጀክቱ 203 ሺሕ አርሶ አደሮችን ተደራሽ ለማድረግ ዕቅድ መያዙንና እስካሁን 180 ሺሕ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን የባዮቨርሲቲ ኢንተርናሽናል ሲያት ፕሮጀክት አስተባባሪ ደጀኔ ካሳሁን (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡

የባዮቨርሲቲ ኢንተርናሽናል ሲያት የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ የሚያደርግ ሲሆን፣ የፓስታና መኮሮኒ ስንዴ፣ እንዲሁም የሽንብራ፣ የባቄላ፣ የማሽላና የዳጉሳ ምርቶችም በኦሮሚያ፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች እንዲለሙ ሲሠራ መቆየቱ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...