Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ወጋገን ባንክ ከገጠመው ቀውስ በማገገም በ2014 የሒሳብ ዓመት የተሻለ ትርፍ አገኘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የቢዝነስ እንቅስቃሴያቸው ከተስተጓጎለባቸው የግል የፋይናስ ተቋማት መካከል ወጋገን ባንክ የበለጠ ጉዳት በማስተናገድ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ባንኩ በዚህ ጦርነት ምክንያት 112 የሚሆኑ ቅርጫፎቹ ከመዘጋታቸው ባለፈ በርከት ያለ ብርድ በዚህ አካባቢ ለሚገኙ ደንበኞቹ መስጠቱ ጉዳቱን አባብሶበታል። 

ባንኩ በይበልጥ ይንቀሳቀስበት የነበረው ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት የሥራ እንቅስቃሴው ላይ ተፅዕኖ ከማሳረፉም በላይ፣ ከዕድሜው አንፃር ሊደርስበት ይችል የነበረው የገቢና የትርፍ ምጣኔ ላይ ተፅዕኖ አሳርፎበት ቆይቷል፡፡ በተለይ በ2013 የሒሳብ ዓመት የባንኩ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ላይ ያሳረፈው ተፅዕኖ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ደርሶ የነበረውን የትርፍ ምጣኔውን ወደ 193 ሚሊዮን ብር እንዲያሽቆለቁል ምክንያት መሆኑ ጉልህ ማሳያ ነው፡፡ 

የተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብና ይሰጥ የነበረውም ብድር እንዲገደብ አድርጎት ነበር፡፡ ባንኩ በ2013 የሒሳብ ዓመት የነበረው አፈጻጸም ግን በ2014 መሻሻል አሳይቷል፡፡ ሁሉም ቅርጫፎቹ ባልተከፈቱበትና በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ለተለያዩ ደንበኞች  የሰጠው ብድር ባልተመለሰበት ሁኔታ ከ2013 የሒሳብ ዓመት የተሻለ የሚባል ትርፍ በ2014 የሒሳብ ዓመት ማትረፍ ችሏል፡፡ ባንኩ ባለፈው ቅዳሜ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔው ላይ እንዳስታወቀው፣ ከታክስ በፊት 572 ሚሊዮን ብር ማትረፍ ችሏል፡፡  

ይህም ክንውን ካለፈው በጀት ዓመት ከተመዘገበው ከታክስ በፊት 193 ሚሊዮን ብር ትርፍ ጋር ሲነፃፀር የ379 ሚሊዮን ብር ወይም የ196 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ በዚህም አንድ አክሲዮን ያስገኘው የትርፍ ድርሻ በ16.6 በመቶ መሆን አስችሏል። ባለፈው ዓመት በአንድ አክሲዮን የተገኘው የትርፍ ድርሻ 4.2 ከመሆኑ አንፃር በ2014 የሐሲብ ዓመት የተገኘው የትርፍ ድርሻ በ12.4 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። በዚህ መሠረት ባንኩ የሕጋዊ መጠባበቂያና ሌሎች ተቀናናሾችን ታሳቢ በማድረግ የቀረውን 224 ሚሊዮን ብር ለባለአክሲዮኖች የድርሻ እንዲከፋፈል አድርጓል፡፡ 

ወጋገን ባንክ የገጠመውን ከባድ ፈተና ተወጥቶ ወደ ተሻለ ደረጃ እየሄደ መሆኑን የገለጹት የባንኩ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አክሊሉ ውበት፣ በፋይናንስ ደረጃ ከተፈጠረው ጫና በላይ የባንኩን ስም በማጠልሸት ረገድ የገጠማቸው ፈተና የበለጠ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል።

‹‹ከሁሉ በላይ እኛን ጎድቶን የነበረው የባንኩን ስም ማጠልሸት ነው፡፡ ሠራተኛውን ለመያዝ እንኳን አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥሮብን ነበር፡፡ ይህ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ስለዚህ ይህንን ለማስተካከል የተሠራው ሥራ ውጤት አምጥቷል፡፡ ወጋገን የሚሠራው ቢዝነስ ነው ለካ እንዲባል ማድረግ ተችሏል፤›› ብለዋል።

ባለፉት አንድ ዓመት ተኩል ይህንን ብዥታ ለመቀየር የተደረገው ጥረት ብዙ ለውጥ ማምጣቱንና የነበረውን ጫና በመቋቋም ወደ ተሻለ መንገድ የሚወስደውን መንገድ ለመያዝ መቻሉን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል። 

የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብዱሽ ሁሴን ባለፈው ቅዳሜ የባንኩ ለባለአክሲዮኖች ባቀረቡት ሪፖርት፣ ‹‹ባንካችን ይህንን ውጤት ያስመዘገበው በስፋት በሚንቀሳቀስበት በሰሜኑ አገራችን ክፍል የሚገኙ 112 ቅርንጫፎች ተዘግተው፣ ከአካባቢ ይገኝ የነበረው ከፍተኛ መጠን ያለው ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰብና የሰጠውን ብድር ማስመለስ ባልቻለበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ነው። በዚህ (2015) የሒሳብ ዓመትም የበለጠ ውጤት ይጠበቃል፣ ለዚህ መልካም ዕድሉ ደግሞ የሰላም ስምምነቱ የተዘጉ ቅርጫፎቻችንን ለመክፈት ያስችለናል፤›› ብለዋል።

በተለይ ባንኩ በኢንዱስሪው ብቁና ተወዳዳሪ ሆኖ ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማስመዝገብ ይችል ዘንድ ጠንካራ ተቋም፣ አቅምና የቁጥጥር ሥርዓት የመፍጠር ወሳኝ በመሆኑ ግልጽና ተጠያቂነትን ያስፈለገበት አሠራር ተግራዊ በማድረግ ውጤታማ ሥራ መሥራቱን የገለጹት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ይህንን ተግባር ማጠናከር ዕድገቱን ያስቀጥላል ብለዋል፡፡ 

የባንኩ የ2014 የሒሳብ ዓመት ዋና ዋና የሥራ አፈጻጸምን ከሚያመላክቱት መረጃዎች መካከል አንዱ የባንኩ 112 ቅርንጫፎች ከሥራ ውጭ ሆነውም ቢሆን በሒሳብ ዓመቱ በአጠቃላይ 2.4 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉ ነው። በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ 33.9 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የስምንት በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ በተመሳሳይም የባንኩ ከወለድ ነፃ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ባለፈው ዓመት ከነበረው 1.5 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ4.6 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ 1.6 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተገልጿል፡፡

ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የተሰጠው አጠቃላይ የብድር መጠን ካለፈው ሒሳብ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር፣ የ11 በመቶ ወይም የ2.9 ቢሊዮን ብር ጭማሪ በማሳየት 30.3 ቢሊዮን ብር መድረሱን አብዱሽ ገልጸዋል፡፡ 

የሒሳብ ዓመቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት 195 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ይህም ባለፈው የሒሳብ ዓመት ከተገኘው 252 ሚሊዮን ዶላር አፈጻጸም ጋር ሲነፃፀር የ23 በመቶ ቅናሽ ያሳያል፡፡ 

የባንኩ ጠቅላላ ሀብት መጠን በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የ8.7 በመቶ ወይም የ3.5 ቢሊዮን ብር ዕድገት በማሳየት ወደ 43.1 ቢሊዮን ብር ማደጉንም የቦርድ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡ የባንኩ የካፒታል ዕድገት በተመለከተ የቀረበው ሪፖርት ደግሞ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ በ109.3 ሚሊዮን ብር ወይም ሦስት በመቶ ዕድገት በማሳየት 3.4 ቢሊዮን ብር መድረሱን የባንኩ መረጃ ያመለክታል። ይህንን አፈጻጸም የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ‹‹ባንኩ ሊደርስበት ከሚገባው የካፒታል ዕድገት አንፃር አጥጋቢ የሚባል ባለመሆኑ፣ የባንኩን ካፒታል በማሳደግ በኩል ባለአክሲዮኖች የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ፤›› ጠይቀዋል፡፡ በዚህም መሠረት ቅዳሜ ዕለት በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የባንኩን ካፒታል ወደ 20 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ተወስኗል፡፡ ይህንን የ15 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ካፒታል በአምስት ዓመት ለማሟላት የጠቅላላ ጉባዔው ወስኗዋል፡፡  

ወጋገን ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት 5.1 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘት የቻለ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው የሒሳብ ዓመት በ96.7 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው ነው፡፡ በዘንድሮ የባንኩ ሪፖርት ላይ መረዳት እንደሚቻለው ወጪውን ለመቀነስ የሠራው ሥራ የሳካለት መሆኑን ለመረዳት ይቻላል፡፡ ይህም ለመጀመርያ ጊዜ ዓመታዊ ወጪውን የቀነሰበት ሆኗል፡፡   

የባንኩ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ የ2014 የሒሳብ ዓመት አጠቃላይ ወጪው 4.5 ቢሊዮን ብር ሲሆን ይህም ካለፈው ሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ282.5 ሚሊዮን ብር ቅናሽ አሳይቷል። 

እንዲህ ባለው አፈጻጸም የ2014 የተሻገረው ወጋገን ባንክ፣ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የገጠመን ችግርና ሌሎች ተግዳሮቶችን በመውጣት ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሻገረ እንደሆነ የሚያመለክቱት የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች፣ በቀጣይ የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙን ላቅ ለማድረግ ትኩረት ከሚደረግባቸው ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች መካከል የባንኩን የውስጥ አቅም በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል ልማት፣ በአሠራር ሥርዓትና አደረጃጀት ማጠናከር የሚለው ቀዳሚ ሆኖ ተቀምጧል፡፡ ፕሬዚዳንቱም ይህንን የሚያጠናክር ሐሳብ የሰጡ ሲሆን፣ በተለይ የደንበኞችን ዕርካታ የበለጠ ሊያሳድጉ የሚችሉ አዳዲስ የባንክ አገልግሎቶችን ማቅረብ፣ የባንኩን የገቢ ምንጭና የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት ማስፋፋት፣ የሥጋት አስተዳደር ማጠናከርና የመሳሰሉ ተግባራት በሠራተኞች ውስጥ ተካተው የሚሠራባቸው ነው ተብሏል፡፡ ባንኩ ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ስትራቴጂ ግንኙነት ማጠናከር አዳዲስ ግንኙነቶችን መመሥረት፣ የፕሮጀክት አፈጻጸም አቅምን ማሳደግና የባንኩን ገጽታ ይበልጥ መገንባት ዋና ዋናዎቹ ተግባራቱ ስለመሆኑም አመልቷል፡፡

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተከስቶ የነበረውን ግጭት ለመፍታት ከተፈረመው የሰላም ስምምነት ጋር ተያይዞም፣ በትግራይ ክልል ተዘግተው የሚገኙ 112 ቅርጫፎቻችንን ብሔራዊ ባንክ በሚሰጠው መመርያ መሠረት ሥራ ለማስመር በዝግጅት ላይ የሚገኝ መሆኑን የቦርድ ሊቀመንበሩ ተናገረው፣ የእነዚህ ቅርንጫፎች መከፈት የባንኩን የ2015 እና ከዚያ በኋላ ያለውን አፈጻጸም በላቀ ደረጃ የሚያሳድግ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ቅርንጫፎቹን በተፋጠነ መልኩ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው መመርያ መሠረት ሥራ ለመሥራትም አስፈላጊውን ሁሉ የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ አቶ አክሊሉ፣ የባንኩን ቅርንጫፎች ሥራ ከማስጀመር አኳያ ባንኩ ሙሉ ዝግጅቱን አጠናቆ እየጠበቀ መሆኑን ጠቁመዋል። የመከላከያ ሠራዊቱ የሚገባባቸው ቦታዎችን በመከተል የተዘጉ ቅርቻፎችን ኦዲት በማድረግ ሥራ ለማስጀመር ባንኩ የሚጠበቀውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

የባንኩን ቀጣይ እንቅስቃሴን በተመለከተ አቶ አክሊሉ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ ጦርነቱን ተከትሎ የመጣው ብድር ያለ መክፈል ችግር እንዳለ ሆኖ፣ አዲስ ደንበኛ የማፍራት ሥራ ላይ ባንኩ አጠንክሮ እንደሚሠራ አመልክተዋል፡፡ ይህንን ውጥን ዕውን ለማድረግ ሁሉም የባንኩ ማኅበረሰብ በሙሉ ልብ የተሻለ ባንክ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ የነበረውን ተግዳሮት እንደ መልካም ዕድል ተጠቅሞ የመሥራቱ ሥራ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ ነገ የተሻለ መሆኑን በመገንዘብ እስካሁን የሠራነውም ሆነ ወደፊት የምንራው ሥራ ባንኩን ወደ ተሻለ ውጤት ይወስደዋል ብለው እንደሚያምኑ አቶ አክሊሉ ገልጸዋል፡፡  

ወጋገን ባንክ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊት ለነበሩት ተከታታይ ዓመታት ትርፉን እያሳደገ የመጣና በጥሩ እንቅስቃሴ ውስጥ የነበረ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። ለአብነትም ባንኩ በ2010 የሒሳብ ዓመት 1.05 ቢሊዮን ብር፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት 735 ሚሊዮን ብርና በ2012 ሒሳብ ዓመት 1.07 ቢሊዮን ብር ከታክስ በፊት ማትረፉን ለማወቅ ተችሏል።

ወጋገን ባንክ ከ298 በላይ የኤቲኤምና 429 የክፍያ መፈጸሚያ (ፖስ) ማሽኖች ተሠራጭው አገልግሎት በመስጠት ላይ ሲሆኑ፣ የኤቲኤም ካርድ ተጠቃሚ ደንበኞቻችን ቁጥርም 544,157 ደርሷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ 1,443,566 ደንበኞች የሞባይል ባንክ አገልግሎትና 11,762 ደንበኞች ደግሞ የኢንተርኔት ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ የወኪል ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር ደግሞ 2,712 ደርሷል፡፡ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የባንኩ ቅርንጫፎች ቁጥር 400 ደርሷል፡፡ 

 

 

   

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች