Sunday, April 14, 2024

በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመው ጭፍጨፋና ሥጋቱ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኦሮሚያ ክልል ከቀውስ አዙሪት መላቀቅ ያቃተው ይመስላል፡፡ ከ200 በላይ ንፁኃን በምሥራቅ ወለጋ መገደላቸው ተሰምቷል፡፡ በኦሮሚያ ባሉ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎችና ከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ተቃውሞ ተቀጣጠለ፡፡ ከፀጥታ ሥጋት ተላቆ የማያውቀው ክልል፣ አሁን ደግሞ ውሉ ወዳልተፈለገ ነውጥና ተቃውሞ እየገባ ያለ ይመስላል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ባሉ ትምህርት ቤቶች ‹‹የኦሮሚያ ክልል መዝሙር ካልተዘመረ››፣ እንዲሁም ‹‹የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ ካልተሰቀለ›› በሚል ባለፈው ሳምንት ረብሻና ሁከት ነበር፡፡ ይህንን ተገን በማድረግ ደግሞ የኦሮሞ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ከሌሎች ማኅበረሰቦች ወኪል ነን ከሚሉ ኃይሎች ጋር በማኅበራዊ ሚዲያዎች የቃላት ውርወራ ሲያደርጉ ነው የከረሙት፡፡ በዚህ ጉዳይ ከረር ያሉ የዩቲዩብ እንካ ሰላንቲያዎችም ሲስተናገዱ ከርመዋል፡፡

ይህ ሁኔታ ሳይበርድ ደግሞ በሳምንቱ መገባደጃ ከወለጋ አሰቃቂ የጭፍጨፋ ዜና ተሰማ፡፡ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳና በኪራሙ ወረዳ፣ እንዲሁም በሆሮ ጉዱሩ ዞን ሆሮ ቡሉቅ፣ እንዲሁም ጃርዴጋ ጃርቲ ወረዳዎች በአማራ ተወላጆች ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ መፈጸሙ በስፋት ተሰምቷል፡፡

ከዚሁ ጥቃት ጋር በተገናኘ የኪራሙ ወረዳ ፍርድ ቤት ዳኛን ጨምሮ ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸው በአንዳንድ ሚዲያዎች ተዘግቧል፡፡ እነዚህ ሚዲያዎች ከአማራ ክልል የመጡ ፋኖዎች ናቸው የጭፍጨፋው ፈጻሚዎች ሲሉ ዘግበዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በምዕራብ ወለጋና በሌሎችም የኦሮሚያ አካባቢዎች ጥቃት ሲፈጸም ኦነግ ሸኔ ነበር ዋና ተጠያቂ ሆኖ የሚቀርበው፡፡ የአሁኑ ጥቃትም የኦነግ ሸኔ እጅ እንዳለበት ቢነገርም፣ ነገር ግን ከአማራ ክልል የተነሱ ፋኖዎች ናቸው ጥቃት አድራሾቹ የሚል የሚዲያ ዘገባ ተደጋግሞ እየተሰማ ነው፡፡

‹‹የምሥራቅ ወለጋውን ሰሞነኛ ጭፍጨፋ ፈጻሚ ፋኖ ነው›› የሚለው ውንጀላ ደግሞ በየዩኒቨርሲቲዎቹና በየከፍተኛ ትምህርት ቤቶቹ በተካሄዱ ሠልፎች ላይ መፈክሮች ተደጋግሞ ተስተጋብተዋል፡፡ ‹‹ፋኖ አሸባሪ ነው›› የሚለው የተማሪዎች መፈክር፣ በምሥራቅ ወለጋ ጥቃት አድራሾቹ ፋኖዎች ናቸው ከሚለው ትርክት ጋር በቀጥታ የተገናኘ መሆኑ ነው የተነገረው፡፡

ዓለም አቀፍ ሚዲያዎቸ ጭምር ኦነግ ሸኔ ከ200 በላይ አማራዎችን መግደሉን ሲዘግቡ ሰንብተዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል መንግሥትም ባለፈው ሳምንት በሰጠው መግለጫ ወለጋን ጨምሮ በየአካባቢው አርሶ አደሮችንና ንፁኃን ሲቪሎችን የሚጨፈጭፍ ያለውን የኦነግ ሸኔ ቡድን እንደሚዋጋው ተናግሯል፡፡

ለጉዳት የተዳረጉና ጥቃት የደረሰባቸው ነዋሪዎችም ቢሆኑ የኦነግ ሸኔ አባላት ጥቃት እንዳደረሱባቸው ሲመሰክሩ ይታያል፡፡ ከሰሞኑ በኦነግ ሸኔ ደጋፊዎች ማኅበራዊ ገጽ ከተሠራጩና ብዙዎች ከተቀባበሏቸው ቪዲዮዎች መካከል፣ ‹‹የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ሰው የሚበላ አውሬ አይደለም፤›› እያሉ የሚናገሩ ፀጉር የቆጣጠሩ ታጣቂዎች የማረኳቸውን ሰዎች እንጀራ በወጥ ሲያጎርሱ የሚያሳይ ነበር፡፡

ሰሞኑን የምሥራቅ ወለጋው ጥቃት በደረሰ ማግሥት ግን አጥቂዎቹ እኛ ሳንሆን፣ የአማራ ፋኖዎች ናቸው የሚል መረጃ ነው ከኦነግ ሸኔና ከደጋፊዎቹ በኩል እየተስተጋባ የሚገኘው፡፡ ለረዥም ጊዜ በወለጋ የሚንቀሳቀሰውና ጭፍጨፋ የሚፈጽመው ኦነግ ሸኔ እንደሆነ ሲነገርና ማስረጃ ሲቀርብበት የነበረ ቢሆንም፣ አሁን በድንገት አክራሪ የፋኖ ኃይሎች ከአማራ ክልል ወደ ወለጋ ገብተው ነው ጥቃቱን የፈጸሙት የሚል ውንጀላ ተፈጥሯል፡፡ ይህ ደግሞ በኦሮሚያ በሚካሄዱ ተቃውሞዎች እየተስተጋባ ነው፡፡

ይህ ውንጀላ ደግሞ ወደ አማራና ኦሮሞ የፖለቲካ ልሒቆች ተዛምቶ ክልላዊ፣ እንዲሁም የብሔር ይዘት ወዳለው ግጭት እንዳያመራ እየተሠጋ ይገኛል፡፡ ወደ ኦሮሚያ ክልል ተሻግሮ ፋኖ ጥቃት ፈጻሚ እንዴት ሆነ የሚለው ብዥታን እየፈጠረ እንዳለው ሁሉ፣ የሰሞኑን የምሥራቅ ወለጋ ጥቃትን በተመለከተም ኃላፊነትና ተጠያቂነት የወሰደ አካል የለም፡፡

ከሳምንት በፊት መግለጫ የሰጡት የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሸን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ፣ አሸባሪውን የሸኔ ኃይል ለመዋጋት ክልሉ ዕቅድ አውጥቶ እየሠራ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡

አንዱ ዕቅድ በአባገዳዎችና በአገር ሽማግሌዎች አስለምኖ ወደ ሽምቅ ውጊያ የገቡ ወጣቶችን መመለስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሁለተኛው ዕቅድም ኅብረተሰቡ ተደራጅቶ ራሱን ከጥቃት እንዲከላከል ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን፣ ሦስተኛው ዕቅድም በመንግሥት በኩል  በተጠናከረ መንገድ በአሸባሪ ኃይል ላይ ዕርምጃ ይወሰዳል ነበር ያሉት፡፡

‹‹የኦሮሚያ ክልል ትናንት እንዳደረገው ለሰላም እጁን ይዘረጋል፤›› ያሉት አቶ ኃይሉ፣ ‹‹ሆኖም ቡድኑ ለንግግርም ሆነ በሰላም ችግሮችን ለመፍታት አመቺ አይደለም፤›› ነው ያሉት፡፡

‹‹ኦነግ ሸኔ አርሶ አደሮችን እየገደለ፣ ንብረታቸውን እየዘረፈና ልጆቻቸውን እየደፈረ ነው፡፡ ኦነግ ሸኔ የሽምቅ ውጊያ የሚከተል፣ አንድ ዕዝ የሌለው፣ በአካባቢ የተከፋፈለ፣ እርስ በርሱ የሚባላ፣ ወለጋ፣ ሸዋና ጉጂ እያለ እርስ በእርሱ የሚታኮስ፣ ዓላማም ሆነ መሪ ድርጅት የሌለው፣ የሕዝብ ወገንተኝነት የሌለው፣ የሚያታግል የፖለቲከ አጀንዳ የሌለው፣ ሰላማዊ ሰዎችን በማገት ገንዘብ የሚቀበል ቡድን ነው፡፡ መንግሥት ከእንደዚህ ዓይነት ሽፍታ ጋር የሚነጋገርበት ሁኔታ የለም፤›› ብለዋል

በአሻባሪነት የተፈረጀው የኦነግ ሸኔ ዓለም አቀፍ ቃል አቀባዩ አቶ ኦዳ ተርቢ ግን ይህንን የክልሉን መግለጫ አጣጥለዋል፡፡ ‹‹ዓላማም ሆነ ግብ አለን፡፡ አመራርም ሆነ የምንመራበት ሥርዓት አለን፡፡ በሽብር ፈርጀው መልሰው ለድርድር መቀመጥ ከብዷቸዋል፡፡ በተለይ ከሕወሓት ጋር ከተደራደሩ በኋላ ከእኛ ጋር ለድርድር የማይቀመጡበት ዕድል አጡ፤›› በማለት ነበር የተናገሩት፡፡ አቶ ኦዳ ተርቢ ከዚህ ቀደም በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ ከመንግሥት ጋር አልተደራደርንም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኦዳ ተርቢ ከመንግሥት ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከዚህ ቀደም ተዳራድረን እናውቅም ቢሉም፣ በማግሥቱ ግን ድርጅታቸው ባወጣው መግለጫ የአስመራው ስምምነታችን ፈረሰ ሲል ነበር የሚጋጭ መረጃ ያወጣው፡፡

ኅዳር 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል እየተፈጸመ ስላለው ሰቆቃ ሰፊ መግለጫ ያወጣው ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)፣ የፌዴራልም ሆነ የክልሉ መንግሥት በኦነግ ሸኔ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ማስቆም እንዳቃታቸው አስታውቋል፡፡

ኅዳር 20 ቀን 2015 በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ማምረቻ ንብረት የሆነ አውቶቡስ በማስቆም፣ በሠራተኞች ላይ ዕገታ መፈጸሙን መግለጫው ይጠቅሳል፡፡

በምዕራብ ወለጋ ዞን ደግሞ ጉተን፣ ቱሉጋራ፣ ጃርዳጋ፣ ኦሞሮና ሌሎች ወረዳዎች ኦነግ ሸኔ ተደጋጋሚ ጥቃት እየፈጸመ ነው፡፡

ምሥራቅ ወለጋ ደግሞ በኪረሙ ወረዳ ሀሩ ቀበሌና ሌሎች አካባቢዎች ቡድኑ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እያደረሰ ነው፡፡

በምሥራቅ ሸዋ ደግሞ በጀጁ ወረዳና በሌሎች አካባቢዎች ኦነግ ሸኔ ጥቃት እየፈጸመ ነው በማለት መግለጫው ዝርዝር ጉዳዮችን ይጠቃቅሳል፡፡

ከዚህ በመነሳትም የኦሮሚያ ክልልንና የፌዴራል መንግሥት መቆሚያ ላጣው ለዚህ ጥቃት በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጡ ነው ኢሰመጉ የጠየቀው፡፡

የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አቶ ለሚ ስሜ ከሪፖርተር እንግሊዝኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ‹‹የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት›› ኦነግ ሸኔ በሚል የወል ስም መጠራቱ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረው ነበር፡፡ ‹‹የፖለቲካም፣ የሚሊታሪም አመራሩን በራሱ መያዙንና ከተማ ገብቶ በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ ከሚንቀሳቀሰው ኦነግ ጋር ግንኙነት ማቋረጡን ቡድኑ ካስታወቀ ቆይቷል፤›› ይላሉ፡፡

‹‹የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት›› የሚባለው ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ ቡድን መሆኑን ቢያውጅም፣ ነገር ግን አንድ ወይም ወጥ አመራር እንደሌለው አቶ ለሚ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ምዕራብ ኦሮሚያ በጃል መሮ የሚመራ፣ ደቡብ ኦሮሚያ ገመቹ አቦዬ፣ መሀል ኦሮሚያ ደግሞ ጃል ሰኚ የሚባል፣ እንዲሁም አባቢያ የሚባለው በሐረርጌና አርሲ አካባቢ የሚንቀሳቀስ አመራር ተፈጠረ፤›› ሲሉም ያስረዳሉ፡፡ ይህ ደግሞ ቡድኑ ማዕከላዊ አመራር ኖሮት በዲሲፕሊንና ወጥ በሆነ መንገድ እንዳይታዘዝ አድርጎታል ይላሉ፡፡

ቡድኑ የአመራር ቀውስ ካለበት ደግሞ በመካከሉ ግጭት እንደሚፈጠር፣ እንዲሁም ብዙ ቀውስ በቡድኑ ዙሪያ መፈጠሩ የሚጠበቅ መሆኑን ነው የፖለቲካ ተንታኙ የሚነገሩት፡፡ አቶ ሰኚ ይህንን ቢሉም ከታታቂዎቹ ጋር ችግርን በሰላም ለመፍታት ቅድሚያ እንዲሰጥ ነው የሚያሳስቡት፡፡

እሳቸው ብቻ ሳይሆን በርካታ የኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን በድርድርና በንግግር ኦነግ ሸኔ ወደ ሰላም መመለስ ይቻላል ሲሉ ይደመጣል፡፡ መንግሥት ከሕወሓት ጋር እንዳደረገው ሁሉ ከኦነግ ሸኔ ጋርም ተቀምጦ ይደራደር የሚል ግፊትና ጫናም ሲያሳድሩ ይታያል፡፡

ይሁን እንጂ ኦነግ ሸኔ በሚባለው ቡድን ላይ እንኳ የጋራ መግባባት ሳይኖር ድርድሩ እንዴት ሊካሄድ ይችላል ስለሚለው መልስ የሚሰጥ ብዙም የለም፡፡ በኦሮሚያ እየደረሰ ላለው ዕልቂትና ጭፍጨፋ ኦነግ ሸኔ ዋና ተጠያቂ መሆኑን መንግሥትና በርካቶች ይጋሩታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -