Sunday, January 29, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በሴራ ፖለቲካ ሕዝብን ማሰቃየት ይቁም!

ኢትዮጵያ አንፃራዊ ሰላም የምታገኝበት የተስፋ ውጋጋን መታየት ሲጀምር፣ ድምፃቸውን አጥፍተው የከረሙ ፋይዳ ቢሶች የሰለቹ አጀንዳዎችን ከየስርቻው እየመዘዙ ከየአቅጣጫው ነገር እየቆሰቆሱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ማናቸውም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተግዳሮቶችን በሰላማዊ ንግግሮች የመፍታት ልምድ ማዳበር እየተቻለ፣ ከአገር በላይ ራሳቸውን በቆለሉ ጥራዝ ነጠቆች ምክንያት አገር እየታመሰች ነው፡፡ በተለይ የፖለቲካው ሠፈር የሴረኞችና የራስ ወዳዶች መፈንጫ ስለሆነ የብሔርና የእምነት ማንነትን ከለላ በማድረግ፣ ለአገር ዕድገትና ለሕዝብ አብሮነት የማይጠቅሙ እኩይ ባህርያት እያገረሸባቸው ነው፡፡ ዜጎች በአገራቸው በፈለጉት ሥፍራ የመኖር፣ የመዘዋወር፣ የመሥራትና ጥሪት የማፍራት ተፈጥሯዊና ሕጋዊ መብቶቻቸው እየተጣሱ በማናለብኝነት እየተጨፈጨፉና እየተፈናቀሉ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች›› የሚል ሰሌዳ የተለጠፈለት የዘውግ ፌዴራሊዝም፣ የግለሰብን መብት አፍኖና ደፍጥጦ ዜጎችን አገር አልባ እያደረገ ነው፡፡ በፌዴራል ሥርዓት መልካም ተሞክሮ ካላቸው የሠለጠኑ አገሮች ልምድ በመቅሰም ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ከማጎልበት ይልቅ፣ ዩጎዝላቪያን አምስት ቦታዎች የከፋፈለ (Balkanization) ዓይነት ፌዴራሊዝም በመከተል የት እንደሚደረስ ግራ ያጋባል፡፡

እዚህ ላይ በቅጡ መጤን ያለበት ጉዳይ ቢኖር ለኢትዮጵያ የሚያዋጣው የፌዴራል ሥርዓት መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን የፌዴራል ሥርዓቱ ሕዝብን የሚለያይ፣ አገራዊ አንድነትን የሚንድና ከብዙኃኑ ይልቅ የጥቂቶችን ፍላጎት የሚያስተናግድ እንዳይሆን ነው ጥንቃቄ የሚያስፈልገው፡፡ የአንድን ግለሰብ መብት የማያከብር የፌዴራል ሥርዓት ‹‹የብሔር ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን መብት ያስከብራል›› ተብሎ ሲደሰኮር በጣም ነው የሚያስገርመው፡፡ እውነት እንነጋገር ከተባለ ዩጎዝላቪያን ያፈራረሰ የፌዴራል ሥርዓት ከመከተል ይልቅ ለምን የአሜሪካን፣ የጀርመንን፣ የፈረንሣይንና መሰል አርዓያነት ያላቸው የፌዴራል ሥርዓቶችን መከተል አልተመረጠም ሲባል መልሱ ግልጽ ነው፡፡ የሥርዓቱ አርቃቂዎችና አፅዳቂዎች ለአገር አሳቢዎችንና ተቆርቋሪዎችን ገሸሽ በማድረግ፣ እነሱ በፈለጉ ጊዜ ኢትዮጵያን እንደ ዶሮ ብልት ለመገነጣጠል የሚያስችል ዕቅድ በመያዛቸው ነው፡፡ ለዚህም ሲባል ከሕገ መንግሥት መግቢያ ጀምሮ ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን›› በማለት ፋንታ፣ ውሉ የማይታወቅ ‹‹እኛ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች›› ተብሎ የጊዜ ቦምብ የተጠመደው፡፡ የእዚህ ግራ አጋቢ ጽንሰ ሐሳብ አስከፊ ውጤት ደግሞ እየታየ ነው፡፡

የአገር ጉዳይ ሲነሳ በሁለት ጎራዎች ተሠልፈው ‹‹አሀዳዊ›› እና ‹‹ፌዴራሊስት›› እየተባባሉ ከሚነቃቀፉ ወገኖች በላይ፣ አገራቸውን ከትውልድ እስከ ትውልድ እየተቀባበሉ በመጠበቅ እዚህ ያደረሱ የመላ ኢትዮጵያውያን ሰላምና ደኅንነት ሊያሳስብ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ልሂቃን በተጣሉ ቁጥር የበቀል ሒሳብ ሲወራረድበት የኖረው ይህ ምስኪን ሕዝብ ነው፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በግንባር ተሠልፈው ከተፋለሙት የታጠቁ ኃይሎች ባልተናነሰ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ከባዱን መከራ የተቀበሉት ንፁኃን ወገኖቻችን ናቸው፡፡ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በሌሎችም ሥፍራዎች ፖለቲከኞች በቆሰቆሱት ፀብ የተጨፈጨፉትና የተፈናቀሉት ንፁኃን ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ማንም አይስተውም፡፡ ብሔርተኛ የፖለቲካ ልሂቃን ከተደጋጋሚ ስህተቶቻቸው ስለማይማሩ፣ አሁንም የብሔር ባርኔጣቸውን እያጠለቁ ደም መፋሰሱን ለማስቀጠል የፕሮፓጋንዳ ዘመቻቸውን በስፋት ከፍተዋል፡፡ ለረዥም ጊዜ ድምፃቸው ጠፍቶ የከረሙ ሳይቀሩ፣ የዕልቂቱን ፊሽካ በመንፋት ትኩረት ለመሳብ እየተጣደፉ ነው፡፡ ሕግ የማስከበር ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ደግሞ ምንም እንዳልተፈጠረ ድምፁን አጥፍቷል፡፡ የሰሜኑ አውዳሚ ጦርነት ቆሞ አንፃራዊ ሰላም ሊገኝ ነው ሲባል፣ በሌላ አቅጣጫ ዕልቂት ሲደገስ ያሳዝናል፡፡

ከዚህ ቀደም በተሳሳተ ዓላማቸው ምክንያት ለበርካቶች ሞት ምክንያት የነበሩ ግለሰቦች እንደገና ሌላ ዕልቂት ሲደግሱ፣ አይቻልም ብሎ የማስቆም ኃላፊነት የመንግሥት ቢሆንም መላው ሕዝብ ተባብሮ ግፊት ማድረግ አለበት፡፡ ደም የጠማቸው ፖለቲከኞች ጎራ ለይተው አገሪቱን በደም ሊያጨቀዩ ሲነሱ፣ የጉልበት መንገድ እንደማያዋጣ አስረግጦ በመንገር ወደ ሰላማዊ የንግግር ጠረጴዛ ጎትቶ ማምጣት የግድ መሆን ይኖርበታል፡፡ አልሆን ካለ ደግሞ የፍትሕ ሥርዓቱ ሕዝብና አገርን ከአደጋ ለመጠበቅ ሲል ሕግ ማስከበር ይጠበቅበታል፡፡ በመንግሥት መዋቅር ውስጥም ሆነ በተፎካካሪ ኃይሎች ውስጥ ተሰግስገው ከአገር በላይ እንሁን የሚሉ በሙሉ፣ በሕግና በሥርዓት ካልተዳኙ አገር ከማፍረስ ወደኋላ እንደማይሉ መታወቅ አለበት፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የኢትዮጵያን ሕዝብ እርስ በርሱ ደም ለማቃባት ያደፈጡ ኃይሎች፣ ከየስርቻው እየወጡ የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ ላይ ናቸው፡፡ ይህንን አደገኛ ፍላጎት ማስቆም ካልተቻለ ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን በንፁኃን ላይ የተፈጸመው ዘግናኝ ጭፍጨፋ፣ ወደ ሌሎች አካባቢዎች መዛመቱ አይቀሬ ነው፡፡

ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በተለያዩ ጎራዎች ውስጥ ሆነው በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርበው መነጋገር ፍላጎታቸው አይደለም፡፡ ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ አንድ እንዲሆንም አይፈልጉም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዓመታት በአርቆ አሳቢነቱ በገነባቸው የጋራ ማኅበራዊ እሴቶቹ አማካይነት ተስማምቶና ተግባብቶ ሲኖር እያዩ፣ እነሱ ግን ጥቃቅን ልዩነቶችን በአጉሊ መነፅር እየፈለጉ ግጭት ለመፍጠር ይዳክራሉ፡፡ ለልዩነቶች ዕውቅና ተሰጣጥቶና ተግባብቶ መኖር ብርቅ ባልሆነባት ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ጥንት የተፈጸሙ ስህተቶችን እያነፈነፉ የዘመኑን ትውልድ ለማፋጀት የሚሄዱበት ርቀት አስደንጋጭ ነው፡፡ በጣት ከሚቆጠሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በስተቀር ብዙዎቹ የዘውግ አቀንቃኞችም ሆኑ የእነሱ ተገዳዳሪዎች፣ የብሔርተኝነት ማጥ ውስጥ ተዘፍቀው ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይመጥን የጭካኔ ዓላማ እያራመዱ ነው፡፡ ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ዕውን መሆን ከመታገል ይልቅ፣ ኢትዮጵያውያንን በማንነት እየለያዩ ለማፋጀት የሚነዙት ፕሮፓጋንዳ አገር እንደሚያፈርስ መገንዘብ ይገባል፡፡ ልዩነትን አክብሮ በእኩልነት መንፈስ ኅብረ ብሔራዊ አገር መፍጠር እየተቻለ፣ አውዳሚ ድርጊት ውስጥ መዘፈቅ ያሳፍራል፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ አሳፋሪ ድርጊት ውስጥ መውጣት የግድ መሆን አለበት፡፡

አሁንም ደግመን ደጋግመን ማሳሰብ የምንፈልገው በየትኛውም ጎራ ውስጥ ሆናችሁ የፖለቲካ ዓላማ የምታራምዱ ፖለቲከኞችም ሆናችሁ ተከታዮች፣ ኢትዮጵያን ወደ ውድመትና ፍጅት ከሚወስድ ድርጊት እንድትታቀቡ ነው፡፡ በሕዝብ ስም እየቆመራችሁም ሆነ በተለያዩ ፍላጎቶች ውስጥ ተሸጉጣችሁ አገር ለማድማት የምትፈጽሙት ተንኮልም ሆነ ሴራ፣ ዞሮ ዞሮ የሚጎዳው ሕዝብና አገርን በመሆኑ ልዩነቶቻችሁን በሠለጠነ መንገድ ለማስተናገድ ጥረት አድርጉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አማራም ሆነ ኦሮሞ፣ ትግሬም ሆነ ጉራጌ፣ አፋርም ሆነ ወላይታ፣ ሶማሌም ሆነ ጋምቤላ፣ ወዘተ ከግጭትና ከአስመራሪው ድህነት የተላቀቀች ሰላማዊት አገር ይፈልጋል፡፡ በእናንተ ጥጋብና ድንቁርና ምክንያት አገር መድማት የለባትም፣ ሕዝብም ለመከራ መዳረግ አይኖርበትም፡፡ እናንተ እጃችሁ በደም እየተጨማለቀ፣ በሌብነት እየቆሸሸና በሰብዓዊነት ፋንታ በጭካኔ እየተበላሻችሁ አገር ስታፈርሱ ዝም መባል የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ ዘመናትን ተሻግራ እዚህ የደረሰችው በየዘመኑ ትውልድ በተከፈለ ታላቅ መስዋዕትነት ስለሆነ፣ ከየጎራው እየተጠራራችሁ የጀመራችሁትን አገር የማፍረስ ዘመቻ በሕግም ሆነ በኃይል ማስቆም የግድ መሆን አለበት፡፡ በሴራ ፖለቲካ አገርና ሕዝብን ማሰቃየት ይቁም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ከውጭ ይገቡ የነበሩ 38 ዓይነት ምርቶች እንዳይገቡ ዕግድ ተጣለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 38 ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ዕገዳ...

የአየር መንገድ ተጓዦች በሻንጣ የሚያስገቡትን የልብስና የጫማ ብዛት የሚገድብ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

ከቀረጥ ነፃ ይገቡ የነበሩ ዕቃዎች 87 በመቶ እንዲቀንሱ ተደርጓል መንገደኞች...

አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...

ለልማት ፕሮጀክቶች የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተፈቀደ

የገንዘብ ሚኒስቴር በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በሎጀስቲክስ፣ በኮንስትራክሽን፣ የባለኮከብ ሆቴሎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...

ፖለቲካና ሃይማኖትን እየቀላቀሉ በእሳት መጫወት አይቻልም!

ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከሚሹ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሃይማኖት ነው፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ ለተቋማቱና ለምዕመናኑ ብቻ የተተወ ነው፡፡ በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥትም መንግሥትና ሃይማኖት...

አገር የጥፋት ቤተ ሙከራ አትሁን!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የሚለዋወጡ ስትራቴጂዎች እንደሚኖሩት ዕውን ቢሆንም፣ በየጊዜው መዋቅሮችንና ፖሊሲዎችን መለዋወጥ ግን አይችልም፡፡ ‹‹ሁሉን መርምሩ የተሻለውን ያዙ›› የሚለው መጽሐፍ...