Thursday, February 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትአምስት አሠርታትን የተሻገረው የካዛንቺስ የጤና ስፖርት ማኅበር

አምስት አሠርታትን የተሻገረው የካዛንቺስ የጤና ስፖርት ማኅበር

ቀን:

በስፖርት ውድድር ላይ ከመካፈል በዘለለ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለጤና ጥቅምን እንደሚያስገኝ በጥናት የተረጋገጠው እ.ኤ.አ. 1980ዎቹ እና 90ዎቹ መሆኑ ይወሳል፡፡ በመደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍ ያለው ጠቀሜታ እንዳለው፣ በተለይ የልብና የደም ቧንቧ፣ የስኳር በሽታ፣ ካንሰር፣ የደም ግፊትና ውፍረትን ጨምሮ የተለያዩ በሽታዎችን መከላከል እንደሚያስችል ይታመናል፡፡

ከዚያም ባሻገር በተለይ በጤና ስፖርቶች ላይ መሳተፍ ማኅበራዊ ፋይዳው የጎላ እንደሆነና ማኅበረሰቡ እርስ በርስ ያለውን  ትስስር እንደሚያጠናክር ይነገራል፡፡ በአዲስ አበባ በተለይ በመስቀል አደባባይ የሳምንቱን የመጨረሻ ቀናት ወይም የዕረፍት ጊዜያቸውን ጠብቀው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ በርካቶች ነበሩ፡፡ ዘግይቶም ቢሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የብዙኃን (ማስ) ስፖርት በኅብረተሰቡ ዘንድ መዘውተር ከጀመረ ሰንባብቷል፡፡

በአንፃሩ የጤና ስፖርት ፋይዳን ቀድመው ተገነዝበው ከአምስት አሠርታት በላይ ማቆየት የቻሉ ጠንካራ ማኅበሮች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በአዲስ አበባ ካዛንቺስ አካባቢ በ1960ዎቹ እንደተመሠረተ የሚነገርለት ‹‹መብረቅ የጤና ስፖርት ማኅበር›› አንደኛው ሲሆን፣ በጊዜው ማኅበሩ ሲቋቋም ካዛንቺስ ቶታል አካባቢ እንዲሁም በተለምዶ ሽሜ ጫካና መላጣ ሜዳ በሚባሉ ሥፍራዎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ በነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደተመሠረተ ይነገራል፡፡ በታሪክ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ የደረሰው ማኅበሩ ጫንያለው ጀምበሬ፣ ዮሐንስ ሥዩምና ግርማ ክፍሉ በሚባሉ ግለሰቦች አማካይነት እንደተመሠረተ ይነገራል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ማኅበሩ በዋነኛነት የተቋቋመበት ዓላማ ዕድሜን አስታኮ የሚመጣ በሽታን፣ ማለትም እንደ ስኳርና ደም ግፊትን በአባላቱ ላይ እንዳያጋጥም ግንዛቤ በመፍጠር ለመከላከል ግቡ አድርጎ መመሥረቱን የካዛንቺስ መብረቅ ጤና ስፖርት ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ብርሃኑ ሳህሉ ለሪፖርተር ያስረዳሉ።

በማኅበሩ ውስጥ በርካታ የቀድሞ የክለብ እንዲሁም የብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች የሚገኙ ሲሆን በተለያዩ ውድድሮች ላይ ይካፈላሉ፡፡ ማኅበሩ በ1991 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ጤና ስፖርት ማኅበር ክረምትን ጠብቆ ቢሾፍቱ ላይ በሚሰናዳው ዓመታዊ ውድድር ላይ መካፈል ጀመረ፡፡ በውድድሩ መካፈል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ በ1994 እና 2012 ዓ.ም. ሻምፒዮን መሆን ሲችል፣ አብዛኛውን ውድድር ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን ማጠናቀቁን ሊቀመንበሩ ያስታውሳሉ፡፡

ከዚህም ባሻገር በተለያዩ ውድድሮች ላይ የፀባይ ዋንጫን ከማንሳት በዘለለ፣ የቡድኑ ተጫዋቾች ኢሳይያስ አረጋ ለሦስት ዓመታት በተከታታይ ኮከብ ግብ አግቢ በመሆኑ ልዩ ተሸላሚ ለመሆን ችሏል። ማኅበሩ በቢሾፍቱ ከሚሳተፉ ከ40 በላይ የጤና ስፖርት ማኅበራት በአደረጃጀቱና መዋቅራዊ ይዘቱ ልዩ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ 

ማኅበሩ ከስፖርታዊ ክንውኖች በዘለለ የእርስ በርስ መረዳጃ ማኅበር እንደሆነ የሚገልጹት አቶ ብርሃኑ፣ መረዳጃ ሲባል የማኅበሩ አባል ሐዘን ወይም ደስታ ሲገጥመው ብቻ ከማገዝ በዘለለ፣ ሰው በቁሙ እያለ ጤናውን እንዲጠብቅ የሚያበረታታ ማኅበር እንደሆነ ያብራራሉ። 

‹‹የማኅበሩ አባል የሆነ እንዲሁም ያልሆነ ሰው ቤቱ ተቀምጦ ተረጂ ከመሆን ወደ ማኅበሩ እንዲቀላቀል በማድረግ በትጥቅ፣ በምክር እንዲሁም የትራንስፖርት ድጋፍ ይደረግለታል፤›› በማለት አቶ ብርሃኑ ያስረዳሉ፡፡

አቶ ሞገስ ዳኛቸው በአካባቢው በተለያዩ የእግር ኳስ ቡድኖች ውስጥ ሲጫወት የቆየ ሲሆን፣ ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ የማኅበሩ አባል መሆኑን ይናገራል፡፡ እንደ አቶ ሞገስ አስተያየት ከሆነ ማኅበሩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግም ባሻገር፣ በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በመደገፍ ይታወቃል። 

‹‹ማኅበሩ በደስታ፣ በሐዘን እንዲሁም በችግር ጊዜም ከአባላቱ እንዲሁም ከአባላቱ ቤተሰብ ጎን በቀዳሚነት ቆሞ ድጋፍ ያደርጋል፤›› በማለት አቶ ሞገስ አስተያየታቸውን ይገልጻሉ፡፡ 

በሌላ በኩል ማኅበሩ በአካባቢው  የተለያዩ የልማት ተግባሮች ላይ በመሳተፍ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑ ይነገራል።

በዚህም በ2014 ዓ.ም. ማኅበሩ የተቆረቆረበት አስፋ ወሰን ትምህርት ቤት (ምሥራቅ ጎህ)፣ የተሰባበሩ የመማሪያ ወንበሮችን ከመጠገን ባለፈ፣ ከ300 ሺሕ ብር በላይ ወጪ በማድረግ የእጅ ኳስና ቅርጫት ኳስ መጫወቻ ሜዳን ማስገንባታቸውን አቶ ብርሃኑ አስታውሰዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ማኅበሩ በዓመታዊ የችግኝ ተከላና የደም ልገሳ  ተግባሮች ላይ መሳተፉንም  ያስረዳሉ።

ማኅበሩ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት ማኅበራዊ ግዴታውን ለመወጣት፣ 300 ሺሕ ብር በሚገመት ወጪ በአካባቢው ለሚገኙ ከ200 በላይ አቅመ ደካሞች፣ የዘይት፣ የሩዝ፣ የሳሙና፣ የመኮሮኒና የፓስታ ድጋፍ ማድረጉን ሊቀመንበሩ አስረድተዋል። 

ማኅበሩ ከ100 በላይ ቋሚ አባላትና 30 የክብር አባላት  አሉት። አባላቱ የአባልነት ክፍያ በየወሩ 50 ብር ብቻ የሚከፍሉ ሲሆን፣ በአንፃሩ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት ገንዘብ ሲያስፈልግ፣ በአገር ውስጥ እንዲሁም በውጭ አገር የሚኖሩ የማኅበሩ አባላት ንቁ ተሳትፎ እንደሚከናወን አቶ ብርሃኑ ያስታውሳሉ። 

በተለይ በአሜሪካ የሚኖሩ የካዛንቺስ ልጆችን በማሰባሰብ ድጋፍ የሚያደርገው ተሾመ መኮንን፣ ኑሯቸውን በአገር ውስጥ ያደረጉት ተድላ ጫንያለው (ኢንጂነር) እና አየነው ዘውዴ (ኢንጂነር) ማኅበሩ በአደረጃጀትም እንዲሁም የፋይናንስ አቅሙ እንዲጎለብት፣ በተጨማሪም ማኅበራዊ ግዴታውን እንዲወጣ የጎላ አስተዋጽኦ እያደረጉ የሚገኙ ስማቸው በቀዳሚነት የሚነሳ  መሆናቸው ይጠቀሳል። 

መሠረታዊ ገቢ የሌለው ማኅበሩን ከወርኃዊ መዋጮ በገንዘብ ከሚደግፉት አባላቱ፣ እንዲሁም ከተወሰኑ ካምፓኒዎች ድጋፍ ባሻገር፣ ‹‹የማነቃቂያ ልዩ መዋጮ መርሐ ግብር›› የሚል የሀብት ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር እንደሚያከናውን አቶ ብርሃኑ ለሪፖርተር አብራርተዋል።

‹‹የማነቃቂያ ልዩ መዋጮ መርሐ ግብር በሁለት ዓመት አንዴ ይጠራል። በዕለቱም የማኅበሩ አባላት የተለያዩ የገንዘብ መጠኖችን ቃል ይገቡና፣ የአቅማቸውን ድጋፍ ያደርጋሉ፤›› ሲሉ፣ አቶ ብርሃኑ የገንዘብ ምንጫቸውን መላ ያስረዳሉ፡፡

አምስት አሠርታትን የተሻገረው የካዛንቺስ ጤና ስፖርት ማኅበር፣ የገቢ ምንጩ በበጎ አድራጊ ግለሰቦችና በተለያዩ ስፖንሰሮች ላይ ተንጠልጥሎ የቆይ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ በተመሳሳይ መንገድ መቀጠል እንደሌለበትና የራሱን የገቢ ምንጭ መፍጠር እንደሚገባው ውሳኔ ላይ መድረሱ ተገልጿል።

በዚህም መሠረት የሥራ አመራሩ ማኅበሩ የገቢ ምንጭ ይፈጥሩልኛል ያላቸውን ሁለት የሥራ ዘርፍ መርጦ ውሳኔ ላይ መድረሱን ሊቀመንበሩ ያስረዳሉ። አንደኛው የመዝናኛ ሥፍራ ሲሆን፣ በውስጡ የእግር ኳስ ጨዋታ ማስተላለፊያ፣ የቤት ውስጥ ውድድሮች፣ ፑል፣ ከረምቡላ፣ ለስላሳና የተለያዩ መጠጦች ማቅረብ የሚያስችል ድርጅት ማቋቋም ሲሆን፣ ሁለተኛው የራሱን አርቴፊሻል ሜዳ አሰናድቶ የገቢ ምንጩን ለመፍጠር መወጠኑ ተገልጿል።

‹‹ድርጅቱን ለማቋቋም የሚያስፈልጉ ጥናቶች አጠናቀን  ቦታ ለማግኘት ከሚመለከተው አካል ጋር ቀርበን ተወያይተናል። ‹ጠብቁ› የሚል ምላሽ አግኝተናል። በአንፃሩ ሜዳውን በተመለከተ ጥናት እያስጠናን እንገኛለን፤›› በማለት አቶ ብርሃኑ ሁኔታውን ያስረዳሉ።

በየዓመቱ ጠቅላላ ጉባዔ የሚጠራው ማኅበሩ የተከናወኑ ሥራዎችን ገምግሞ የኦዲት ሪፖርት ለጉባዔተኛው ያቀርባል። በሪፖርቱም መሠረት ውሳኔዎቹን ያስተላልፋል። ማኅበሩ በአዲስ አበባ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ወደ ክልሎች አምርቶ ቆይታ በማድረግ የማኅበረሰብ መስተጋብር የመፍጠር ልምድ አለው፡፡

ማኅበሩ ተተኪዎች እንዲኖሩት በርካቶችን ከመጋበዝም በላይ፣ ለማኅበሩ አባላት ልጆች አሠልጣኝ በመቅጠር የእግር ኳስ ሥልጠና እንዲወስዱ አድርጓል፡፡ 

ዘመናትን መሻገር የቻለው ማኅበሩ በመቻቻል እንደሆነ የሚያስረዱት አቶ ብርሃኑ፣ ተተኪዎችም በተመሳሳይ መንፈስ ሌላ ሃምሳ ዓመታትን መሻገር እንዲችሉ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ያስረዳሉ። በአንፃሩ የመጫወቻ ሜዳ ማግኘት አዳጋች እንደሆነና ማኅበሩ ከጀርባው በርካታ ማኅበረሰቦች መኖራቸው ተገንዝቦ፣ ማኅበሩ ሊያቋቁመው ላቀደው የገቢ ምንጭ ድርጅት መንግሥት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ አቶ ብርሃኑ ተማጽነዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...