Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በወጣቶች ኑሮ ላይ ተስፋ የፈነጠቀው የማር ምርት

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማር ሀብት ልማት ብዙ መሬትና በርካታ ጉልበትን የማይጠይቅ ነገር ግን ትኩረት ተሰጥቶበት  ቢሠራ ከአንድ፣ ሁለትና ሦስት በላይ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ በዘርፉ ላይ ጥናት ያደረጉም ሆነ ጥናቱን መሠረት አድርገው ሠርተው የተለወጡ ሁሉ ይመሰክራሉ፡፡

በቀላል ምሳሌ ለመግለጽ፣ ንቦች ለሚቀስሙት ዕፅዋቶች ተብለው የሚተከሉ ዕፅዋት የመጀመርያ ገቢ ሲያስገኙ፣ ኅብረ ንብን (የንብ መንጋን) መሸጥ ቀጣዩ የገቢ ምንጭ ነው፡፡ ንቦችን በማዳቀልና ሠራተኛ ንቦችን በማብዛት ምርቱ ከፍ እንዲል በማድረግ የሚገኘው ገቢ ሦስተኛው ሲሆን፣ ምርቱን በማጣራት ሒደት የተገኘውን ተረፈ ምርት ማለትም እንደ ሰም ያለውን በመሸጥም ሆነ ለጧፍ ምርት በማቅረብ የሚገኘው ገቢ አራተኛው ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ምርቶች በማምረት ሒደት ውስጥ የቀፎ ሚና ወሳኝ በመሆኑ በአንድ አካባቢ የሚገኙ በእንጨት ሥራ ላይ ለተሰማሩ ግለሰቦች ሥልጠና በመስጠት ተሸጋጋሪ የሚባለውን የቀፎ ዓይነት ሠርተው ለገበያ እንዲያቀርቡና እንዲጠቀሙ ማድረግ አምስተኛው ተግባር መሆኑ በተግባር ታይቷል፡፡ የንብ አልባሳትን አምርተው ለአናቢዎቹ በማቅረብ ገቢ የሚያገኙ የስፌት ባለሙያዎችን መጥቀም ሌላኛው ዘርፉ ያመጣው ትሩፋት መሆኑ እንዲሁ ይገልጻል፡፡

በኢትዮጵያ ከባህር ጠለል በላይ ከ1,000-2,400 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኙ ክልሎች ለንብ ማነብ በጣም ተስማሚ መሆናቸው ይነገራል። በእነዚህ አካባቢዎች ዝናብ ዘንቦ አብቅቶ በደረቅና ፀሐያማ የአየር ሁኔታ ከተተካ በኋላ በተስማሚ አየር ሁኔታው ምክንያት የሚያብቡት ተክሎች ለንቦች ምቹ የመቅሰሚያና የመመገቢያ ግብዓትነት መሆናቸው እንዲሁ ባስረጅነት ይቀርባል፡፡

በኢትዮጵያ በርካታ የንብ ዝርያዎችና በሚሊዮን የሚቆጠሩ አናቢዎች ቢኖሩም በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እያገኘች እንዳልሆነ የሚናገሩት የዘርፉ ባለሙያዎች፣ በአገሪቱ ማርን በብዛትና በጥራት ለማምረት የንብ ዕርባታ ኢንዱስትሪ መቋቋም እንዳለበት፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂ ማላመድ፣ ዛፎችን በብዛት መትከል፣ የገበያ ትሰስር መፍጠር፣ አመራረቱን ዘመናዊ ማድረግ እንደሚገባ ያትታሉ፡፡ 

መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከሆነ ኢትዮጵያ በዓመት እስከ 550,000 ቶን የማር ምርት የማቅረብ አቅም አላት፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ በዓመት እየተመረተ ያለው  ዘጠኝ በመቶ ያህሉን ማለትም 50,000 ቶን ብቻ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት መረጃ ያመለክታል፡፡

የ2013 በጀት ዓመት የአገሪቱ የማር ምርት መጠን 129 ሺሕ ቶን ሲሆን፣ የሰም ምርት ደግሞ 6.3 ሺሕ ቶን እንደነበር በግብርና ሚኒስቴር የቀረበ መረጃ ያስረዳል፡፡ በኢትዮጵያ 1.8 ሚሊዮን የሚሆኑ አርሶ አደር፣ ከፊል አርብቶ አደር፣ ባለ-ኃብቶችና የከተማ ነዋሪዎች የንብ ኤክስቴንሽን ምርት አናቢዎች እንደሚገኙ ይገለጻል።

በኢትዮጵያ የንብ ማነብ ሥራ በምርቱም ሆነ በአሠራሩ ሒደት ለብዙዎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል መሆኑን ካሳዩ ተቋማት መካከል፣ ዋና መሥሪያ ቤቱን ካናዳ ካደረገው ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን (Master Card Foundation) ጋር በመተባበር የሚንቀሳቀሰው የዓለም አቀፍ የሥነ ነፍሳትና ሥነ ምኅዳር ማዕከል (International Center of Insect Physiology and Ecology – Icipe)  ተጠቃሹ ነው፡፡

ይህ ማዕከል ከአካባቢ ጥበቃና ነፍሳት ምርምር ጋር የተገናኙ ምርምሮችን ለማከናወን የተቋቋመ ተቋም ነው፡፡ ተቋሙ የንብ ልማት በዋናነት በገጠር የሚኖሩና የምጣኔ ሀብት እጥረት ያለባቸው ማኅበረሰቦችን ኑሮ ለማሻሻል ፕሮጀክት ቀርፆ በኢትዮጵያ በተለይም በአማራ ክልል መጠነ ሰፊ ሥራ መሥራት ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡

ማዕከሉ ለኢትዮጵያ ወጣቶች የንብ ማነብ ዕውቀትና ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ የሥራ ዕድል ፈጠራ በሚል በቀረፀው ፕሮጀክት፣ በተለይም ከፍተኛ የማር ሀብት አለባቸው በሚባሉት በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብና በትግራይ ክልሎች 70ሺ ወጣቶችን በንብ ማነብ እንዲሁም ሐር ትል ልማት በማሠልጠን ወደ ሥራ አስገብቷል። በጠቅላላው በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ 100 ሺሕ ወጣቶችን በልማቱ ውስጥ ለማስገባት እየሠራም ይገኛል።

በአገር ዓቀፍ ደረጃ እስካሁን የ25 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት እንዳወጣ የሚገልጸው የምርምር ማዕከሉ፣ በዚህ ወቅት በጠቅላላው እየሠራበት የሚገኘው ፕሮጀክት 55 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን በኩል የሚደረግበት እንዲሁም በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ 100 ሺሕ ወጣቶችን የሚያግዝ እንደሆነ ይነገራል፡፡ እስካሁን ድረስ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ የፈሰሰበት ፕሮጀክት ውጤት የተገኘበት መሆኑን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ወርቅነህ አያሌው (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡

ወርቅነህ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ እስካሁን በቀጥታ የማር ማምረቱ ላይ 65 ሺሕ ወጣቶች የሚሠሩ ሲሆን፣ እነዚህ ወጣቶች የሥራ ንግድ ክህሎት ሥልጠና፣ የሕይወት ክህሎት ሥልጠና፣ የዕቅድ፣ የገንዘብ ቁጠባ፣ የትርፋማነት ጽንሰ ሐሳብ የማስጨበጥ ሥልጠናዎች ያገኛሉ፡፡ የንብ ማነብ መሠረታዊ ሥልጠና ሌላው ለብቻው ለወጣቶቹ የሚሰጥ ሥልጠና ነው፡፡ ከሥልጠና በኋላ ለወጣቶቹ መሬት በሚመለከተው የመንግሥት መዋቅር ተመድቦላቸው ጋጣ የሚሠሩ ይሆናል፡፡ ለዚህም የሚሆነውን ቁሳቁስ በተቋሙና በራሳቸው የሚሟላ ነው፡፡ ተቋሙ የማስጀመር ሥራ ትልቁ የተልዕኮው አእማድ ሲሆን፣ በዚህ ሒደት እስከ መጨረሻው መሄድ የሚችል ስብስብ (ቡድን) ወደ ቀጣዩ ሒደት ይሸጋገራል፡፡ 

ፕሮጀክቱ በአገር ዓቀፍ ደረጃ የአማራ ክልልን ጨምሮ በኦሮሚያ በደቡብ ኢትዮጵያ እንዲሁም በዚህ ወቅት በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ ክልል ያለው እንቅስቃሴ ቢቋረጥም 70 ሺሕ የሚሆኑ ወጣቶችን  በንብ የማነብ ሥራ አሠልጥኖ ወደ ሥራ አስገብቷል፡፡ በፕሮጀክቱ ከሞላ ጎደል ያለው ተነጻጽሮ ቢያንስ 50 ሺሕ ወጣት በትኩረት እየሠሩበት ይገኛሉ፡፡

በባህላዊ፣ በሽግግር እንዲሁም በዘመናዊ ቀፎ የሚሠራው የንብ ማነብ ሥራ መረጃ ተሠርቶ ሲታይ ከባህላዊ ቀፎ አንፃር በተለምዶ ስድስት ኪሎ የሚገኝበትን አሠራር፣ ሥልጠና የወሰዱት ወጣቶች የተሻለ እንክብካቤ አድርገው ዘጠኝ ኪሎ ሲያገኙበት፣ በባህላዊ (ሽግግር) ቀፎ የሚፈለገውን ያህል ቁጥር ባይገኝም ከ20 እስከ 30 ኪሎ ያገኙም ወጣቶች አሉ፡፡ በሽግግር ቀፎ በደንብ አውቀው የሠሩ ደግሞ ከ35 እስከ 40 ኪሎ ያገኙ እንዳሉ ይገለጻል፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ የማር ዓይነቶች የሚገኙ ሲሆን፣ ዓይነቶቹ እንደሚገኙበት አካባቢና የብዝኃ ሕይወት ስብጥር በማሮቹ ላይ የይዘትና የቀለም ልዩነት አላቸው፡፡ ሰቆጣና ዋግኽምራ በተባሉት የአማራ ክልል አካባቢዎች የሚመረተው ማር እንደ ወተት ነጭ ቀለም ያለው ነው፡፡ በመካከለኛው የኢትዮጵያ ክፍል የሚመረተው ማር የቢጫና ወርቃማነት ቀለም ያለው ነው፡፡ ዝቅተኛ በሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች ደግሞ ነጣ ያለ ማር እንዲሁ ይመረታል፡፡

ጌትነት ያለው ከዋግሕምራ ዞን ጋዝግቢላ ወረዳ 02 ቀበሌ የመጣ ወጣት ነው፡፡ አሥር ሆነው ተደራጅተው በማዕከሉና በራሳቸው በቀረበላቸው ቀፎ የንብ ምርት ማምረት ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ የንብ ማነብና ተዛማጅ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ምንም ዓይነት ሥራ አልነበራቸውም፣ ንብ ማነብ እንደ ሥራ የማይታይ ለመሥራትም አስፈሪ መሆኑን ይገምቱ የነበሩት ወጣቶች፣ በተቋሙ የሚሰጠውን ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ ግን ውጤትና ጥሩ ተሞክሮ ያለው ዘርፍ መሆኑን መረዳታቸውን ይናገራሉ፡፡ በዚህ ወቅት ከዘመናዊ ቀፎ እስከ 20 ኪሎ ማር፣ እንደ ወቅቱ ቢለያይም ከባህላዊ ቀፎም እስከ ስድስት ኪሎና ከዘያም በላይ ምርት እንደሚያገኙ ይናገራሉ፡፡ በቂ ገበያ በአካቢያቸው እንዳለ የሚናገሩት ወጣቶቹ ነገር ግን የበለጠ ሥራውን ለማስፋት የገንዘብ ድጋፍ እንደሚስፈልጋቸው ያስረዳሉ፡፡ 

በሌላ በኩል ከአዊ ዞን ጓጉሳ ሹክዳን ወረዳ እንደመጡ የሚናገሩት ግዛት በላይና ጓደኞቹ በ2012 ዓ.ም. አሥር ሆነው የተደራጁ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ስድሰት የሚሆኑት ሴቶች፣ ቀሪዎቹ ወንዶች ናቸው፡፡ በአይሲአይፒኢ (icipe) የሞይሽ ፕሮግራም (More Young Entrepreneurs in Silk and Honey (MOYESH) Programme) ሥር በሌሎች አካባቢዎች የተደረገው ዓይነት ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡ በ2013 ዓ.ም. 180 ኪሎ ግራም ማር አግኝተው በመሸጥ ካፒታላቸውን እንዳሳደጉ፣ በ2014 ዓ.ም. ተጨማሪ ሥልጠና ወስደው ሥራውን በማሻሻል ጥሩ ውጤት እያገኙ እንደሆነ ወጣቶቹ ይገልጻሉ፡፡

እሱን ጨምሮ ብዙኃን የማኅበሩ አባላት በስደት ከክልል ክልል ሲዘዋወሩ መቆየታቸውን የሚናገረው ወጣት ግዛት፣ የሚኖሩበት ወረዳ ሦስት ሄክታር መሬት ከሰጣቸው በኋላ በመሬቱ ላይ የሰብል ምርት የሆኑትን በቆሎና ስንዴ እንዲሁም በተጨማሪነት የጀመሩት የንብ ማነብ ሥራ ውጤታማ እንዳደረጋቸው አስረድቷል፡፡ በግሉ የሚሠራቸው ሥራዎች የራሱን ቤት ገንብቶ እንዲኖር፣ ልጆቹን በትልቅ ደረጃ እንዲያስተምር እንዲሁም የእንስሳት ዕርባታ ላይ እንዲበረታ እንዳደረገው ግዛት ተናግሯል፡፡

አቶ ሞዓ መንግሥቱ የኦዳ አክሲዮን ማኅበር ማርኬቲንግ ኃላፊ ነው፡፡ ድርጅቱ ከአንድ ዓመት ወዲህ ወደ ማር ምርት የገባ ድርጅት ነው፡፡ የማር አቅርቦት ላይ የሚሠራ ተቋም ሲያፈላልጉ የአይሲአይፒኢ የሞይሽ ፕሮጀከትን እንዳገኙና አብረው መሥራት እንደጀመሩ አቶ ሞዓ ያስረዳል፡፡ ድርጅቱ ከማኅበራቱ ድፍድፍ ማር የሚገዛ ሲሆን፣ አጣርቶ በማሸግ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ያቀርባል፡፡

ቀጣይነት ያለውና ያልተቋረጠ ምርት ማቅረብ በተለይም ኤክስፖርት ሲታሰብ ወሳኙ ጉዳይ መሆኑን የሚስረዳው አቶ ሞዓ፣ ይህን እንዲሆን የአቅራቢዎችን አቅም በሥልጠናና በዓይነት ድጋፍ መጠናከር አለበት ይላል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2023 60 ቶን ወይም 60 ሺሕ ኪሎ ማር በአማራ ክልል ከሚገኙ ማር አቅራቢዎች እንዲሁም 40 ሺሕ ኪሎ ግራም ከኦሮሚያ ክልል ለመረከብ (ለመግዛት) ያቀደው ኦዳ፣ የዓለም አቀፍ ዋጋ በመመልከት ኤክስፖርት እደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ በተለይም የሞይሽ ፕሮጀክት ተግባራዊ በሚደረግባቸው ክልሎች ከላይ አንስቶ እስከ ታችኛው መዋቅር የሚገኘው አመራር ጉዳዩ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠበትን የሥራ አጥ ችግር የሚፈታ ስለሆነ በከፍተኛ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት እየደገፉት እንደሚገኙ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ወርቅነህ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለሴክተሩ የተሰጠው ግምት አነስተኛ ስለነበረ ‹‹ብድር መስጠት አደጋ አለው›› በሚል ዕሳቤ የባንኮችም ትኩረት አናሳ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ግን የሚገላበጠው የገንዘብ ብዛት ብድሩ እንደሚመለስ ባንኮችን ስላሳመነ፣ ወደ ኤክስፖርት ሊሰማራ ያሰበ ባለሀብት እየጨመረ ስለሆነ፣ ተሰብስቦ ምርቱ ወደ ውጭ ተልኮ የሚመጣው ምንዛሬ ቀላል ስላልሆነ በእነዚህ የተነሳ ባንኮችም ትኩረት ማድረግ መጀመራቸው ተነግሯል፡፡ የምርምር ተቋሙም ይዞ የሚመጣው ገንዘብ ከፍተኛ ገንዘብ በመሆኑ በውጭ ምንዛሬ መልክ የሚመጣውን ገንዘብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አግኝተው ለመሥራትና ለመጠቀም ባንኮች ፍላጎት አላቸው፡፡

‹‹ለፕሮግራሙ የተሰጠው በጠቅላላው 100 ሺሕ የሚሆኑ ወጣቶችን አብዛኛውን በንብ ማነብ የቀረውን ደግሞ በሐር ትል ልማትና ግብዓት አቅራቢነት እያደረጁ መደገፍ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ ከሞላ ጎደል ከ86 እስከ 90 ሺሕ ደርሷል፤›› የሚሉት ወርቅነህ (ዶ/ር)፣ አሁን ባለው አሠራር ተነሳሽነቱ ጥሩ ስለሆነ ከ130 እስከ 150 ሺሕ መድረስ ይቻላል ይላሉ፡፡

 ሥራ አጥነት ክፉኛ አጥቅቶት ለቆየው የገጠር ወጣት ከአማራጭ ወደ መሠረታዊ የሥራ መስክ የተቀየረለት የማር ማነብ ሥራ በተለይም በዚህ ወቅት ደግሞ በረከት የተወለደለት ይመስላል ‹‹የሌማት ትሩፋት›› በሚል ስያሜ የተጀመረው እንቅስቃሴ፡፡

ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በአርባ ምንጭ ከተማ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረገው ‹‹የሌማት ትሩፋት›› መርሐ ግብር፣ በምግብ ሉዓላዊነት ማስከበርንና የአገርን ጓዳ በእንስሳት፣ በዶሮና በማር  ምርቶች በማትረፍረፍ፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በስንዴ፣ አትክልትና ፍራፍሬ የተገኘውን ስኬት መድገም መሆኑ በመንግሥት እየተገለጸ ይገኛል፡፡

ለቀጣይ አራት ዓመታት በሚተገበረው የ‹‹ሌማት ትሩፋት›› መርሐ ግብር ዓመታዊ የወተት ምርትን አሁን ካለበት 6.9 ቢሊዮን ሊትር ወደ 11.7 ቢሊዮን ሊትር የማድረስ ግብ ተይዟል፡፡ በተጨማሪም የዶሮ ሥጋ ዓመታዊ ምርትን አሁን ካላበት 90 ሺሕ ወደ 240 ሺሕ ቶን እንዲሁም የማር ምርትን ከ147 ሺሕ ወደ 296 ሺሕ ቶን ከፍ ለማድረግ ግብ ጥሏል፡፡

በተለይም ከከተማ ውጪ በገጠሪቱ የአገሪቱ አካባቢዎች ለሚገኘው ወጣት የሥራ አጥነት ችግር ቁልፍ መፍትሄ እየሆነ የመጣውን የማር ምርት ከሥልጠና እስከ ግብዓት ድጋፍ በማድረግ ከዘርፉ የሚገኘውን ትሩፋት በአገር ደረጃ መቋደስ እንደሚቻል የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

‹‹በተሻለ አሠራር ፕሮግራሙን ለማስቀጠል ተነሳሽነቱ አለ፣ መንግሥትም ሆነ  የገንዘብ ድጋፉን የሚሰጠው ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን እንዲሁም የግብርና ሚኒስቴር ‹‹የሌማት ትሩፋት›› በሚለው ላይ መሥራት ስለሚፈልግ እንቅሰቃሴው ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል፤›› ሲሉ ወርቅነህ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች