Tuesday, February 27, 2024

በአገራዊ ጉዳይ ሆድና ጀርባ የሆኑት መንግሥትና ምሁራን

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት መንግሥትና ምሁራንን የማያግባቡ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች በተለያዩ መንግሥታት ዘመን ተነስተዋል፡፡ ባለፉት ሰላሳ ዓመታትም በመንግሥትና በምሁራን መካከል የማያግባቡ በርካታ ክስተቶችም ተስተውለዋል፡፡ መንግሥት ለምሁራን ካለው ምልከታ ጀምሮ፣ ምሁራን በአብዛኛው የመንግሥት ተቀጣሪ በመሆናቸው ምክንያት የሚደረጉ ጫናዎች በሁለቱ መካከል ቅራኔ ሲፈጥሩ ኖረዋል፡፡ አሁንም ቅራኔው አንዳንዴ ለዘብ ቢልም፣ ተመልሶ እያገረሸ የልዩነት ስንጥቆች ይስተዋላሉ፡፡

በአንድ አገር ውስጥ ለአገረ መንግሥትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና  ትርጉም ያለው የማኅበረሰብ ለውጥ ለማምጣት የምሁራን ዕሳቤ፣ ዕይታ፣ መርህን መሠረት ያደረጉ የምርምር ሥራዎች፣ እንዲሁም ሳይንሳዊ የፈጠራ አበርክቶዎች ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታቸውና መንግሥታዊ አወቃቀራቸው በግልጽ መርህ ያልታገዘና ከቡድን ወገንተኝነትና ከመንጋ ፖለቲካ ላልተላቀቁ አገሮች ደግሞ፣ ይህ የላቀ የምሁራን ሚና በእጅጉ አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ አማራጭ የሌለው ፍቱን የመፍትሔ አማራጭ መሆኑ ይነገራል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ባለፉት አምስት አሥርት ዓመታት ከንጉሣውያን ሥርዓተ መንግሥት አገዛዝ አገሪቱን ወደ ሕዝባዊና አሳታፊ ወደ ሆነ የመንግሥት ሥርዓት ለማስገባት በተደረጉ ጥረቶች፣ የፖለቲካውን ዓለም የተቀላቀሉ ምሁራን ሥልጣን በተለያዩ አጋጣሚዎች በተቆናጠጡ የፖለቲካ ልሂቃንና የመሀል ፖለቲካ ዘዋሪዎች ከሜዳው እየተገፉ ማበርከት የሚጠበቅባቸውን ምሁራዊ ዕይታ ከማበርከት ይልቅ፣ የዳር ተመልካች እንዲሆኑና ከአገር እንዲሰደዱ ተደርገዋል፡፡ የተወሰኑ ምሁራን ደግሞ አገርን ሊያቀራርብ ከሚችል ሐሳብ ይልቅ የሚያራርቅና አገርን ከሚገነባ ይልቅ የሚያፈርሰውን ትርክት ወደ ሕዝቡ እየረጩ የዴሞክራሲያዊ ጽንፈ ሐሳቦችን በማዳፈን በታኝና ጎጠኛ ትልሞችን እንደሚያቀርቡ ዘወትር የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡

በዚህ ሁሉ መሀል ደግሞ አርቆ አሳቢዎች፣ አገርን የሚያስቀድሙና አሻጋሪ የሆኑ ዕሳቤዎችን የሚያቀርቡ በአገር ጉዳይ ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩና ትንታኔ ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገር ውስጥ በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሉ ተብለው የሚታሰቡ ተመራማሪዎችና ምሁራን፣ ከመንግሥትና ከተለያዩ አካላት የሚሰነዘሩ ጫናዎችንና ግፊቶችን በአመዛኙ እንደ ምክንያት በማቅረብ ተሳትፏቸው ቁጥብ እየሆነ፣ በአገር ጉዳይ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እምብዛም ጎልቶ አለመታየቱ ብዙዎችን ያሳስባል፡፡

ይህንኑን የምሁራንን ሚና በተመለከተ ኅዳር 26 ቀን 2015 ዓ.ም. በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲና በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ ‹‹ለኢትዮጵያ ልዕልና የምሁራን ሚና›› በሚል መሪ ቃል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ኃላፊዎችና አመራሮች፣ እንዲሁም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን በተገኙበት በአዲስ አበባ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና እስያ ጥናት ትምህርት ክፍል ተመራማሪ ሳሙኤል ተፈራ (ዶ/ር)የዳሰሳ ጥናት አድርገው ባቀረቡት የመነሻ ጽሑፍ፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በአገር ሉዓላዊነት ዙሪያ የሚያደርጉት ጥናት ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከዓለም አቀፍ የትምህርት ተቋማት ጋር በመሆን ሉዓላዊነትን፣ አገራዊ መግባባትንና የሰላም ግንባታን በተመለከተ ለሚያቀርቡት የጥናት ፕሮጀክት የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ የጥናቱን ተቀባይነት መሠረት ያደረገ አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በተመሳሳይ ምሁራን በመገናኛ ብዘኃን ቀርበው ስለአገራዊ ጉዳይ ሐሳብ እንዲሰጡ ሲጠየቁ ፈቃደኛ አለመሆናቸውና ፍላጎት አለማሳየታቸው፣ አገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ለውጭ ሚዲያ ማብራሪያ ለመስጠት ሲሞክሩ መጀመርያ ከመንግሥት አለፍ ሲል ደግሞ ከሌሎች አካላት ዛቻና ማስፈራሪ ይመጣብናል ብለው በሥጋትና በፍራቻ በነፃነት ሐሳባቸውን ለማቅረብ ፍላጎት እንደሌላቸው አስረድተዋል፡፡

ምሁራን በሚዲያ ቀርበው ሐሳባቸውን በውጭ ቋንቋ በነፃነትና በሙሉ እምነት የሚሰማቸውን ሲናገሩና አስተያየት ሲሰጡ ለሚደርስባቸው ጥቃት ከመንግሥት ከለላ ማጣት፣ የተወሰኑ ሚዲያዎች ቀድመው በተቀረፁ አጀንዳዎች ‹‹ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ›› በሆነ ፍጥነት ጋዜጠኞች የፈለጉትን ብቻ እንዲነገርላቸው የሚያደርጉት ግፊት መኖሩን፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ሐሳባቸውን እንዲያስተላልፉና ውይይት እንዲያደርጉ የሚረዱ በቴክኖሎጂ የታገዙ መድረኮች አለመኖርን ሳሙኤል (ዶ/ር) በዳሰሳ ጥናቱ ከምሁራን ሰምቻለሁ በማለት የጠቃቀሷቸው ናቸው፡፡

በሌላ በኩል የአገረ መንግሥትና የፖለቲካ ዕሳቤ ቅይጥ መሆን፣ የነፃና ገለልተኛ ሚዲያ አለመኖር፣ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በቂ ጥናት አለመኖር፣ የመገናኛ ብዙኃን በመንግሥት ዛቻና ማስፈራሪያ አለፍ ሲልም ዕርምጃ ይወሰድብናል በሚል በተመረጡ አጀንዳዎች ብቻ ምሁራንን ማሳተፍ፣ ምሁራን አስተያየት ሲሰጡ ጋዜጠኞች ከዓውዱ ውጪ አስተያየታቸውን መጠቀም የሚሉትም ከምሁራኑ መነሳታቸውን አክለው አብራርተዋል፡፡

ከምሁራን የተነሱትን ቅሬታዎች፣ ፍራቻዎችና ሥጋቶች ለማስተካከል በመንግሥት ዘንድ ለምሁራንና ለአካዴሚክ ነፃነት ያለው ግንዛቤ መሻሻል እንዳለበት፣ የምሁራንን ኑሮ ለማሻሻል መንግሥት መትጋት እንደሚኖርበት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራር ከፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ ሙሉ ጊዜውን  ለትምህርትና ለአገራዊ ጉዳዮች ትኩረቱን እንዲያደርግ ቢደረግ የሚል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም የትምህርት ተቋማት ለትምህርት ነፃነትና ለማኅበረሰብ አገልግሎት እንዲሠሩ ከመንግሥት ድጋፍ ቢደረግ፣ የመንግሥት የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ገለልተኛ የሆነ የኮሙዩኒኬሽን ስትራቴጂ አዘጋጅቶ ምሁራንን አሳታፊ ያደረገ ወቅታዊ አገራዊ ውይይት ቢኖር፣ ምሁራን ስለአገራቸው ጉዳይ በውጭ አገር ላሉ የሚዲያ ተቋማትና ለውጭ ማኅበረሰብ ወቅቱን የጠበቀ ሐሳብ እንዲያቀርቡ የሚያግዝ አመቺ ሁኔታና የቴክኖሎጂ ምኅዳር ቢፈጠር፣ ለምሁራን ነፃ ሐሳብ ከለላና አልፎ አልፎም ማበረታቻ ቢሰጥ፣ ሚዲያዎች ከቆርጦ ቀጥልነት ቢወጡ፣ አካዴሚክ ነፃነት ቢከበርና በተለያዩ አጋጣሚዎች ለአገራቸው መልካም አስተዋጽኦ ላበረከቱ ምሁራን በመንግሥት ዕውቅና ቢሰጥ የሚሉ የመፍትሔ ሐሳቦች ከምሁራኑ መነሳታቸውን አስረድተዋል፡፡

ሳሙኤል (ዶ/ር) በማጠቃለያ ንግግራቸው ኢትዮጵያ ከእንግዲህ ትከበር ዘንድ ምሁራን በአገራቸውና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ምን ይጠበቅባቸዋል? የሚል ጥያቄ መነሳት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ መንግሥት ምሁራንን እንደ ድንገተኛ እሳት አደጋ አጥፊነት ማየቱን አቁሞ፣ በረዥም ጊዜ ዕይታ ምሁራን እንዴትና በአገር ላይ ምን ዓይነት ሚና ሊወጡ ይችላሉ የሚለው ዕሳቤ ሊጤን ይገባል ብለዋል፡፡

በመድረኩ ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የተወከሉ ተሳታፊ፣ ምሁራን በአገር ግንባታ  የሚስተዋሉ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ችግሮች ላይ የሚታያቸውንና የሚሰማቸውን ሐሳብ መስጠትና ትችት ማቅረብ ትልቁ ሥራቸው ቢሆንም፣ ለዚህ የምሁራን ሚናና አበርክቷቸው ዕውቅና የሚጥ የመንግሥት አካል አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ ይባስ ብሎም፣ ‹‹ብዙዎቻችን በሚዲያ ቀርበን ሐሳብና አስተያየት ስንሰጥ ትችት፣ ማስፈራሪያና ዛቻ ይደርስብናል፡፡ ለሚደርስብን ጥቃት ደግሞ ከለላ የለንም፤›› ብለዋል፡፡  በዚህ ሥጋት የተነሳ ደግሞ በርካታ ምሁራን አደባባይ ወጥተው ሐሳባቸውን ከማካፈል እንደሚቆጠቡ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ብዙ ምሁራን በፍርኃት ቆፈን ውስጥ ሆነው በአገር ጉዳይ ሐሳባቸውን እንዳይሰጡ መደረግ የለበትም፤›› በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ይሁን እንጂ ቀን ከሌሊት ደፋ ቀና ብለው አገራቸውን ማገልገል የሚፈልጉትን ምሁራን ያህል አገር፣ ማፍረስን ሥራቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱ በመኖራቸው ይህንን ሊያርምና ሊያስተካከል የሚችል ዕርምጃ መወሰድ እንዳለበት አስተያየት ሰጪው አሳስበዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የተወከሉት አቶ ተስፋዬ ተሾመ በበኩላቸው፣ ‹‹የምሁራን ሚና ለምን ደከመ? በጋራ ለመሥራት ምን ተሳነን? ለእናት አገር ይህ ይገባታል ወይ?›› የሚሉ ጥያቄዎች ለመድረኩ ሰንዝረዋል፡፡ በጣሊያን ወረራ ወቅት የአፄ ምኒልክን የክተት ጥሪ ዘመቻ ተቀብለው በአራቱም አቅጣጫ ወደ አንድ ቦታ የዘመቱ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ያደረጉት ዘመቻ የአገር ፍቅር ጥግ መገለጫ መሆኑን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ፣ ‹‹ቅድመ አያቶቻችን ደምና አጥንታቸውን ያልሳሱላትን ኢትዮጵያ እኛ ዕውቀታችን ለመለገስ ለምን ሳሳን?›› ሲሉ አክለው ጠይቀዋል፡፡

የአርመር ሃንሰን የጥናትና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አፈወርቅ ካሱ (ፕሮፌሰር)፣ መንግሥት በኢትዮጵያ ሀብት የተማሩ ምሁራን የት ናቸው ብሎ መፈለግ እንዳለበትና ምሁራኑም ኢትዮጵያ ስትፈልጋቸው እዚህ ነን ማለት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ መምህሩ አቶ ሲሳይ ደመቀ መድረኩ ላይ በሰነዘሩት ሐሳብ፣ ምሁራዊ ዕሳቤ አሁን እንዳለው ምሁርነት በዲግሪ ሳይታጀብ በቀደመው ጊዜ በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በመስጊድ የነበሩ ሊቃውንቶች ተከብረው ቦታ ይሰጣቸውና ገዥዎች ችግር ሲገጥማቸው ያማክሯቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በንጉሡ ጊዜ  ‹‹በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ›› እየተባለ ሊቃውንቶች ሸንቆጥ የሚያደርግ ንግግር እንዲያደርጉ ይፈቅደላቸው እንደነበር፣ ነገር ግን በዚያው ልክ ደግሞ ለሚሰነዝሩት ንግግር ከላላ ይደረግላቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

የምሁርነትን ምኅዳር አስመልክተው፣ ‹‹አሁን ምሁራኑ አንድ ምርምር ለማድረግ ሲፈልጉ ለቁርስ፣ ለምሣ፣ ለእራትና ለመኝታ ተብሎ የሚሰጣቸው የቀን አበል እውነት ምርምሩን ያሠራቸዋል ወይ የሚል ጥያቄ ያጭርብኛል፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ውሳኔ ሰጪ አካላት የምሁራኑን ሚና በአግባቡ እንዲረዱትና የአካዴሚክ ምኅዳሩ ለቀቅ የሚልበት መንገድ መፈጠር እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

የመድረክ አወያይ የነበሩት ማናየ ዘገየ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ አገር የማን ነው በሚለው ላይ ስምምነት አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡

በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ሊባል በሚችል ደረጃ በርከት ያለው ምሁር ዕጣ ፈንታው ከእሱ የዕውቀት ደረጃ የሚያንሱ ሰዎች ላይ እንደወደቀ የሚሰማው፣ የተገፊነት ስሜቱ ከፍተኛ የሆነ፣ ተጠራጣሪ፣ በቡድን ሆኖ በጋራ መወያየት የሚችል የማይመስለው የሚናናቅ፣ የሚጠላላ፣ የሚተማማና አብሮ መሥራት የሚቻል የማይመስለውና ብሶተኛ መሆኑን የገለጹት ሌላው የውይይት መነሻ ጽሑፍ አቅራቢ ደቻሳ አበበ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

በተቃራኒ ጥቂት የሚባሉ ደግሞ የማይጠረቃውን ቁሳዊ ፍላጎት ለማርካት የሚባዝኑ፣ ለአገር የሚረባ ሥራ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ድርጅቶች በመረጃ ሰብሳቢነትና አቀባይነት የተጠመዱ፣ በጥናት ትንተና ላይ የረባ ሐሳብ የማይሰጡ፣ ነገር ግን ኅትመቱ ላይ የሚጨመርና ትልልቅ የአካዴሚ ማዕረግ የተሰጣቸው፣ ስለአገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ለመነጋገር ጊዜ የሌላቸው ስለመኖራቸው ተናግረዋል፡፡

የተወሰኑት ደግሞ መንግሥት የሚወደውን ሐሳብ በማስተጋባትና ፖለቲካውን በመጠጋት የአማካሪነት ሥራ የሚሰጣቸው፣ ወይም በዩኒቨርሲቲ ኃላፊነት ቦታዎች የተሾሙ ናቸው ብለዋል፡፡

ስለዚህ ዝምተኛው፣ ብሶተኛውም ይሁን ለቁሳዊ ፍላጎት ማሟያ የሚባክነው የዩኒቨርስቲ ምሁር የሚጠበቅበትን አገራዊ ሚና እየተወጣ ነው ብሎ መናገር እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም ምሁራን የማይራደሩባቸው አገራዊ ጉዳዮች ሊኖሩት እንደሚገባ፣ ከጆሮአቸው በላይ ዓይናቸውን የሚያምኑና ፖለቲከኞቹ አገሪቱን በእጃቸው ይዘው ቢደነቃቀፉ እንኳን አገር የሚሠሩት ምሁራን መሆናቸውን መገንዝብ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዕውቀት ላይ ያልተመሠረተ መንግሥት ጠንካራ መሠረት ስለማይኖረው፣ መንግሥት ከዕውቀት ጠል አሠራርና ትርክት ሊላቀቅ እንደሚገባ በመግለጽ ከኢትዮጵያ ምሁራን ውስጥ የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ ሊወስን የሚችል በጎና ምጡቅ ሐሳብ ሊኖር ይችላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በመድረኩ መዝጊያ ምሁራን ዕውቀታቸውን ተጠቅመው የሚያሳምን አቅም ሊኖራቸው እንደሚገባ የተናገሩት፣ በቅርቡ የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ናቸው፡፡

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ለምሁራኑን በሰነዘሩት ሐሳብ ‹‹የተዘራ ነገር ጊዜውን ጠብቆ ይደርሳል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን አብረን ብንሠራ የእኛ ሕይወት ባይቀር ልጆቻችን የተሻለ አገር እንዲኖራቸው ማድረግ እንችላለን፡፡ እኛም ከምሁራን የሚመጣ ማንኛውንም ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆን ጠቃሚ ሐሳብ ለመቀበል ዝግጁ ነን፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -