አሥር ድምፃውያን የተሳተፉበት ‹‹ሻኩራ›› የተሰኘ አልበም በሰዋሰው መልቲ ሚዲያ ቀረበ፡፡
ጃሉድ አወል፣ ራስ ዳጊ፣ ኒና ግርማ፣ ዘቢባ ግርማ፣ ዳግማዊ ታምራትን ጨምሮ አሥር አርቲስቶች የተሳተፉበት አልበም ኅዳር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል ተመርቋል፡፡
በሙዚቃ አቀናባሪና ፕሮዲውሰር ካሙዙ ካሳ የተዘጋጀው ‹‹ሻኩራ›› አልበም በዕለቱ ተለቋል፡፡
ካሙዙ እንደተናገረው፣ አልበሙ ወጣት ድምፃውያን የተሳተፉበትና ዳንሶል፣ ሬጌና ሌሎችም የሙዚቃ ሥልቶች ያካተተ ነው፡፡
አልበሙ በሰዋስው መልቲ ሚዲያ በተዘጋጀው መተግበሪያ ላይ እንደሚለቀቅ፣ ይህም የኮፒ ራይት መብትን የሚጠብቅ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከ23 ዓመታት በኋላ ወደ አገሯ ትገባለች ተብሎ የምትጠበቀው አንጋፋዋ ድምፃዊት ማሪቱ ለገሠ በአራት ከተሞች ሥራዎቿን ልታቀርብ መሆኑንም ሰዋስው መልቲ ሚዲያ አስታውቋል፡፡
የሚዲያው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብቱ ነጋሽ እንደተናገሩት፣ አንጋፋዋ ድምፃዊ ከሳምንት በኋላ ወደ አገሯ ትገባለች፡፡
ከረዥም ዓመታት በኋላ በደሴ፣ በጎንደር፣ በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ከተሞች ሥራዎቿን እንደምታቀርብ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ የመድረክና ሌሎችም አስተዳደራዊ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል፡፡