Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልከፈረንሣይ የተመለሱ የተለያዩ የአርኪዮሎጂ ቅሪተ አካላትና ዓውደ ርዕዩ

ከፈረንሣይ የተመለሱ የተለያዩ የአርኪዮሎጂ ቅሪተ አካላትና ዓውደ ርዕዩ

ቀን:

ከታሪክ በፊት የነበረውን ዘመን መርምሮ ለማወቅ የሚደረገው ጥናት ቅድመ ታሪክና ፓሌዎንቶሎዢ ይባላሉ። ለእነዚህ ጥበባት በተለየ የሚረዱ ወደ ድንጋይነት የተለወጡ አጥንቶችና ዕፀዋት ናቸው። በኢትዮጵያ ለዚህ የታሪክ ምርመራ የሚረዱ በሊቃውንት ዘንድ ከፍ ያለ ግምት የተሰጣቸው ሁለት ሥፍራዎች መልካ ቁንጡሬና የኦሞ ጅረት ሽለቆ ናቸው።

የቀድሞው የአርኬዎሎጂ መሥሪያ ቤት ያዘጋጀው ‹‹የጥንታዊ ታሪክ ቅርስ አጠባበቅ መግለጫ›› ብሎ ባሳተመው ጽሑፍ ላይ እንደተገለጸው፣ የፓሌዎንቶሎዢ ሊቃውንት በዘመን ብዛት መሬት ውስጥ ተቀብረው በመኖር ወደ ድንጋይነት የተለወጡ አጥንቶችና ዕፀዋትን በመመርመር እጅግ ሩቅ በሆነው ዘመን በመሬት ላይ ይኖሩ የነበሩት እንስሳትና ከሰው ሥነ ፍጥረት ጋር የሚቀራረቡ ፍጡሮችን ይመረምራሉ። 
በኢትዮጵያ የአርኪዮሎጂን መሥሪያ ቤት በ1950ዎቹ አጋማሽ በፈረንሣይ መንግሥት ድጋፍ ያቋቋሙት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሲሆኑ፣ የመጀመሪያው ኃላፊውም አቶ ከበደ ሚካኤል ነበሩ።

ከፈረንሣይ የተመለሱ የተለያዩ የአርኪዮሎጂ ቅሪተ አካላትና ዓውደ ርዕዩ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የዓውደ ርዕዩ ገጽታ

ዘርፉ በስድስት አሠርታት ጉዞው በርካታ ግኝቶች የተገኙበት ኢትዮጵያንም በዓለም ያስጠራ፣ ‹‹ምድረ ቀደምት›› ያሰኘ ነው።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በኢትዮጵያ የአርኪኦሎጂና የፓሌንቲዮሎጂ ጥናትና ምርምር ከፍ ያለ አስተዋፅኦ ካበረከቱት የውጭ ሊቃውንት አንዱ ዦን ሻቫዮን (ፕሮፌሰር) ናቸው። እኚህን ሳይንቲስት የሚዘክር የፎቶ ዓውደ ርዕይ የቅርስ ባለሥልጣን ኅዳር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ከፍቷል።

ባለሥልጣኑ እንዳስታወቀው፣ ዦን ሻቫዮን በመልካ ቁንጡሬ መካነ ቅርስ ላይ ለረዥም ጊዜ ምርመራ በማድረግ በርካታ ሳይንሳዊ የጥናት ውጤቶችን ከማቅረባቸውም በተጨማሪ ሥፍራው እንዲጠበቅ፣ መሠረተ ልማት እንዲኖሩትና እንዲከለል ሠርተዋል፡፡ በታችኛው ኦሞ ሸለቆ መካነ ቅርስም በተመሳሳይ የአርኪዮሎጂና ፓላንቶሎጂ ጥናትና ምርምር በማድረግ የቀደምት የሰው ልጅ መገልገያ የሆኑትን የድንጋይ መሣሪያዎች ቅሪተ አካላት ግኝቶችን በማውጣት በዘርፉ ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ ሀብት አሳይተዋል፡፡

በቅርስ ባለሥልጣን መግለጫ መሠረት፣ ዓውደ ርዕዩ ፕሮፌሰር ዦን ሻቫዮ በታችኛው ኦሞ ስምጥ ሸለቆ ከ1960-1970 ሲያካሂዱ የነበረውን የመስክ ቁፋሮ የሚያሳዩ ናቸው። ፎቶ ግራፎቹም በዦን ሻቫዮ መዛግብት የተገኙ መሆኑም ተገልጿል። ዓውደ ርዕዩ በኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣንና የፈረንሣይ የኢትዮጵያ ጥናት ማዕከል በጋራ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ከታችኛው ኦሞና መልካ ቆንጥሬ በቁፋሮ የተገኙ ቅርሶች ለዕይታ ቀርበውበታል፡፡

ከዓውደ ርዕዩ ጎን ለጎንም በ1960ዎቹ መጨረሻ ለጥናት ተብለው ወደ ፈረንሣይ የሄዱ 760 ጥንታዊ ሰው ይጠቀምባቸው የነበሩ የድንጋይ መሣሪያዎችና የተለያ የአርኪኦሎጂና የፓሌንቲዮሎጂ ቅሪተ አካላትን ባለሥልጣኑ ተረክቧል። ከመልካ  ቁንጡሬና ከኦሞ አካባቢ በቁፋሮ የተገኙ የአርኪኦሎጂና የፓሌንቲዮሎጂ ቅሬተ አካላትና የድንጋይ መሣሪያዎች ከፈረንሣይ መመለሳቸውን ያወደሱት የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው፣ ድርጊቱ የአገሮቹን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል፡፡

መልካ ቁንጡሬ ሲገለጽ የመልካ ቁንጡሬ የአርኪዮሎጂካል ሥፍራ ከአዲስ አበባ በስተደቡብ አቅጣጫ ቡታጅራ ሆሳዕና በሚወስደው አቅጣጫ የሚገኝ ነው፡፡ 

ከሥፍራው የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ መልካ ቁንጡሬ የቅድመ ታሪክ መካነ ቅርስ ብቸኛው በግልጽ የሚታይ (ኦፕን ኤር ሙዝየም) በመያዙ ይታወቃል፡፡ መካነ ቅርሱ ከሆሞኢሬክተከ ታሪክ ጋር የሚገናኝ ሲሆን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ መቆም የቻለውን የሰው ዝርያ ሆሞኢሬክተስ ቅሪተ አካል፣ የድንጋይ መሣሪያዎች፣ እሳት ያነደዱበት ቦታና የጉማሬ ቅሪተ አካል ይገኝበታል፡፡ ላለፉት አምስት አሠርታት የምርምር ውጤቶች መነሻ በመሆን የሚጠቀሰው መካነ ቅርሱ፣ 65 የቁፋሮ ቦታዎች አሉት፡፡

በአፍሪካ ከታንዛኒያው ኦልዱቫይ ጎርጅ ቀጥሎ የሚገኝ ኦፕን ኤር ሙዝየም ሲሆን፣ ከሌሎቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለየ የቅድመ ታሪክ ሙዚየም ነው፡፡ የድንጋይ መገልገያዎች፣ የእንስሳት፣ የሰዎችና የዕፀዋት ቅሪተ አካሎች የሚገኙበት በመሆኑ ከሌሎች የቁፋሮ ቦታዎች በበለጠ ለጥናትና ለምርምር የተመቸ መሆኑን ሊቃውንቱ ይናገራሉ።

የመልካ ቁንጡሬ ሙዚየም ከቀደሙ የድንጋይ መገልገያዎች ጀምሮ የመካከለኛው ዘመን የድንጋይ መገልገያዎችም ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ ስድስት በዘርፉ ተጠቃሸ የሆኑ የቁፋሮ ቦታዎች (አርኪዮሎጂካል ሳይትስ) ሐዳር፣ ኦሞ ስምጥ ሸለቆ፣ ባሌ ጋደብ፣ መካከለኛው አዋሽ፣ ሞጆና ድሬዳዋ የዋሻ ውስጥ ሥዕሎች የተገኙበት ለገ ኦዳን የሚያሳይም ነው፡፡

መልካ ቁንጥሬ ከሚገኝበት ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባልጩ ከሚባለው የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ የነበረበት አካባቢ የተሰበሰቡ ሹል መገልገያ ድንጋዮች የሚገኙበት ሲሆን፣ በመካነ ቅርሱ ካሉ የቁፋሮ ቦታዎች የተሰባሰቡ የእንስሳት ቅሪተ አካሎችና የእጅ መሣሪያዎችንም አካቶ ይዟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የወጪ ንግድ ፖሊሲያችን አገርን የሚጠቅምና ሕገወጥነትን የሚነቅል ሆኖ እንደ አዲስ ሊቀረጽ ይገባል!

ኢትዮጵያ ያልተቋረጠ የውጭ ምንዛሪ ችግር ውስጥ እንድትገባ ካደረጓት የተለያዩ...

የኢትዮጵያ ከአጎአ የገበያ ዕድል መታገድ በኢንዱስትሪዎች ላይ ያስከተለው ጉዳት

የአሜሪካ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ2000 መገባደጃ ላይ ያፀደቀው የአፍሪካ ዕድገትና...

የአብዮቱ ያልተዘጉ ዶሴዎች

‹ዳኛው ማነው› ሒሳዊ ንባብ - ሐሳብና ምክንያታዊነት በዚያ ትውልድ...