Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊያልተነገረው ሥራ ተስፋዎች

ያልተነገረው ሥራ ተስፋዎች

ቀን:

በአበበ ፍቅር

ከየቤቱ የሚወጡ ተረፈ ምግቦችና ሌሎች የቆሻሻ ጥርቅሞች በትልልቅ ሕንፃዎች ሥር ሳይቀር በየጥጋጥጉ ተኮይሰው ማየት በመዲናችን የተለመደ ነው። ቆሻሻው ባለበት ከመቆየቱ የተነሳ በአካባቢው ለማለፍ አፍንጫን ይሰነፍጣል፡፡ በተለምዶ ቆሼ ሠፈር እስከ መባልም ደርሰው በስማቸው የሚጠሩ ቦታዎች እንዳሉ ይነገራል።

ይሁን እንጂ ሽታውንም ሆነ በሽታውን ከቁብ ሳይቆጥሩ ድህነትን ለማሸነፍ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች የዕለትም የዓመትም ጉርሳቸውን ያገኙበታል፡፡ ሌላ የሥራ ዕድልንም ሲፈጥሩበት ይስተዋላል።

- Advertisement -

እነዚህ ለአላፊ አግዳሚ ቀላል የሚመስሉ ሥራዎች ፆም ለማደር የተዘጋጁ ጉሮሮዎችን ይታደጋሉ፣ ወደ ጎዳና ሊወጡ የሚያመሩ እግሮችን ያስቀራሉ፣ ለልመና የተዘረጉ እጆችን ይሰበስባሉ።

ከተጠቀሱት ሥፍራዎች መካከል ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 አካባቢ በጅምር ላይ ያለው የአደይ አበባ ስታዲየም ነው። በዙሪያው የስታዲየሙን አጥር ተመርኩዘው በቆሙ እንጨቶች ላይ ዝናብና ፀሐይን በከፊል የሚከላከሉ ሸራዎች ጣል ጣል ብለው ይታያሉ። በውስጥም የተስፋ መቁረጥ ስሜት የሚታይባቸው ወጣቶች፣ ሕፃናትና ሴቶች እንዲሁም ሽማግሌዎች በአንድነት የታጨቁበት ሸራ አለ፡፡

በአንድ እጃቸው ሲጋራ በሌላው ጫት ይዘው፣ ቡናውን አስቀምጠው ስለኑሮ ውድነቱ፣ ስለፖለቲካው፣ ስለስፖርቱም ያወራሉ። ‹‹ሲታመሙ ካገኙ ጤናዳም ካልተገኘ ጋደም እንጂ ሕክምና የሚባል ነገር አናውቅም፤›› ሲሉም ቆሻሻን በመሰብሰብና በማስወገድ ሥራ የተሰማሩት የወ/ሮ ምሰሶ በላይ (ስማቸው ተለውጧል) የቡናና ሻይ ደንበኞች ይገልጻሉ።

ምሰሶ ከእነዚህ ሸራ ቤቶች መካከል በአንዷ ውስጥ ሆና ሻይ ቡና በመሸጥ የእሷንና የሁለት ልጆቿን ኑሮ የምትመራ እናት እንደሆነች ደንበኞቿ ይመሰክራሉ። የተለያየ አመል፣ ሱስና ባህሪ ያለባቸውን ደንበኞች እንደ ፀባያቸው በማስተናገድ በምታገኘው ገንዘብ ቀለብ፣ የቤት ኪራይ፣ ልብስ፣ ትራንስፖርትና ሌሎች ወጪዎችን በመቻል ልጆቿን እንደምታስተምር ትገልጻለች፡፡

የሥራ ቦታ ተከራይቶ ለመሥራት አቅም የሚጠይቅ ጉዳይ በመሆኑ፣ ከቆሻሻ ማከማቻ አካባቢ በመሆን ለመሥራት እንደተገደደች፣ ይሁን እንጂ ያለችበትንና የምትውልበትን የሥራ ቦታ ለልጆቿ አንድም ቀን አሳይታቸው እንደማታውቅና ነገም እንደማታሳያቸው ታስረዳለች።

ምክንያቷ ደግሞ ‹‹ነገ ተምረው ትልቅ ደረጃ ላይ አያቸዋለሁ የምላቸውን ልጆቼን የእኔን ጭቅጭቅ የሞላበትን ሥራ፣ የሚቅሙ፣ የሚያጨሱ ደንበኞችን፣ በልተው አልከፍልም የሚሉና ፀያፍና ለእናት የማይገቡ ስድቦችን ልጆቼ እንዲያዩና እንዲሰሙ አልፈቅድም፤›› የሚለው እንደሆነ ታክላለች፡፡ ‹‹ከአህያ ጋር የዋለች ጊደር ምን ተምራ ትመጣለች›› እንደሚባለው፣ አብረው ሲውሉ የእነሱን ባህሪ እንዳይላበሱና የእኔን ዝቅ ብሎ መሥራት ሲመለከቱ ውስጣቸው ተጎድቶ በትምህርታችው ላይ ጫና እንዳያሳድር ከሚል የመነጨ መሆኑንም ታስረዳለች። 

ከባለቤቷ ጋር ከተለያየች ከሁለት ዓመታት በላይ እንደሆናትና አባታቸውም በአግባቡ እንደማይረዳቸው፣ ልጆቿ ጎዳና ላይ እንዳይወድቁ ቀን ከሌት በመሥራት ከቤት ኪራይና ከምግብ በዘለለ በቻለችው፣ አቅም የሚጠይቃትን ለማሟላት ከፈጣሪ ጋር እየጣረች መሆኗን ተስፋም ቁጭትም በተቀላቀለበት መንፈስ ትናገራለች።

የ8ኛና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የሆኑት ልጆቿ እስካሁን በክፍል ውስጥ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ከክፍል ወደ ክፍል እንደሚሸጋገሩ ነግራናለች፡፡

ከዚች የሸራ ጎጆ ሥር የነገ ኢንጂነርና ዶክተር፣ ለነገ የአገር ችግር ፈጣሪ ሳይሆን፣ ችግር ፈች ሊሆኑ የሚችሉ ዜጎች ሊወጡ እንደሚችሉ መገንዘብ አስፈላጊ እንደሆነና ችግርን ፊት ለፊት ተጋፍጦ ማሸነፍ እንደሚቻል የምትናገረው ምሰሶ፣ ቀን ለደንበኞቿ ማታ ለልጆቿ ደፋ ቀና ስትል ታሳልፋለች፡፡

ከቀዳዳዋ ሸራ ይብስ የአካባቢው ሽታ ቢከብድም ለልጆቿ ስትል የማትከፍለው መስዋዕትነት እንደሌለ የምትገልጸው ምሰሶ፣ ከሁሉም በላይ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ…›› የሆነባት በየቀኑ የሚመጡት ደንቦች፣ ‹ቦታው የመንግሥት ነው› በማለት፣ እያፈረሱባት መሄዳቸው ነው፡፡ መልሰው ቢጠግኑም ለሳምንት ተጠቅመው ሳይዘልቁ መጥተው ያፈርሱባቸዋል፡፡ በዚህ ድብቅብቆሽ ውስጥ ማለፍም በጣም ከባድ ሆኖባታል፡፡

‹‹በዚህች ጠባብ ጎጆ ውስጥ አንዳችን ያለ አንዳችን መኖር አንችልም፡፡ እዚህ እኛ ካልመጣን ሌላ ሰው ብዙም አይመጣም፤›› ያለው በሥፍራው ያገኘነው ወጣት ዮናስ ነው። ዮናስ ቁርስ፣ ምሳና እራት የሚጠቀመው እዚህች ቤት እንደሆነ ይናገራል። ምሰሶ ጠንካራና ሁሉን ቻይ ለልጆቿ ስትል ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁማ የምትሠራ የጠንካራ እናት ምሳሌ ናትም ይላል፡፡

‹‹እዚህ ሠፈር ያሉ ሁሉ ወጣት ይሁን ሽማግሌ በብዛት ያጨሳሉ፣ ይቅማሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የፈለጉትን ተናግረው፣ የተጠቀሙበትን ሲያገኙ ከፍለው፣ ሲያጡ ለነገ ብለው የሚሄዱ ናቸው፤›› የሚለው ወጣቱ፣ ከችግር ጋር ፊት ለፊት መጋፈጥና ችግርን ለማሸነፍም ሆነ በችግር ላለመሸነፍ መታገል፣ ጠንክሮ መሥራት፣ ራስን፣ ወገንንና አገርን ለመቀየር ትልቅ ሚና አለው ሲል ያክላል።

‹‹ልጆችን አስቀያሚ ወደ ሆነው የጎዳና ላይ ኑሮ ከመውጣት መታደግ ትውልድን መታደግ ነው፤›› የምትለው ምሰሶ፣ ልጆች እንደፈለጉ ይሁኑ ብሎ መረን ከመልቀቅ መታደግ፣ የሚውሉበትን ቦታ መከታተል፣ ነገ የተሻለች አገርን ለመፍጠር አሁን ላይ በርትቶ መማር እንዳለባቸው መምከርና አቅም በፈቀደ መጠን ፍላጎታቸውን ማሟላት፣ በቁሳዊ ነገር እንዳይታለሉ አስፈላጊውን ክትትል ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ታስረዳለች።

ይህች እናት የዛሬን ብቻ ሳይሆን፣ ነገ ምን ይመጣ ይሆን? በማለትም ለልጆቿ በስማቸው የባንክ ደብተር በመክፈት ከምታገኛት ከቤት ኪራይና ከዕለት ጉርስ፣ ከልብስና ከትራንስፖርት ተሸራርፋ የምትቀር ሳንቲም ትቆጥባለች፡፡ ገንዘቡን ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲሄዱ ብቻ መጠቀም እንደሚችሉም ነግራናለች፡፡

በመዲናዋ ብዙ ምሰሶዎች እንዳሉ የማንም ምስክርነት አያስፈልገውም፡፡ በየጥጋጥጉ ቡና ሽጠው፣ የሰው ቤት ሥራን ሠርተው፣ በብዙዎች ዘንድ አይቻልም የሚባለውን ችለው፣ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ሥራን ሳያማርጡ የነገን ትውልድ የሚገነቡ እናቶች ብዙ ናቸው።

በአንፃሩ ‹‹እኔ ምን ሠርቼ ልጆቼን አሳድጋለሁ፣ ምን አበላቸዋለሁ ምንስ አለብሳቸዋለሁ›› በማለት በጉልበት ከመሥራት ይልቅ ምንም ሳይሞክሩ ከመንግሥትና ከሌላ አካል ዕርዳታ በመጠበቅ ልጆችን ለረሃብና ለእንግልት የሚያጋልጡ አሉ፡፡

ከዚህም ከፍ ሲል ሕፃናትን ለልመና ጎዳና ላይ በማሰማራት ያለ ዕድሜያቸው እንዲኖሩ የሚያደርጉ እናቶችም አሉ።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...