Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አሁንስ በዛ!

ሰላም! ሰላም! ዘንድሮ ሰላም መባባልም ብርቅ ሆኖብናል፡፡ በነጋ በጠባ የምንሰማው ዜና ግድያና ማፈናቀል ሆኖ ምን ሰላም አለና ነው ሰላም የምንባባለው ያሰኛል፡፡ ‹‹ኧረ እኔስ ፈራሁ…›› ያለው አዝማሪ ወዶ አይደለም ለካ። ዛሬ ከትናንት ብሶ ነገ ደግሞ ከዛሬ የበለጠ እንደሚብስ እንዴት አንፈራ፡፡ አገር ሰላም ብለው እንደ ዋዛ እንደወጡ የሚቀሩ በበዙበት በዚህ ዘመን ለምን አንፈራ፡፡ አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንዴት! እንዴት! ምን ለማለት ነው እኔ እዚህ ተቀምጨ ፈራሁ ማለት?›› ይላል። ጀግንነት የፈታንበት መዝገበ ቃላችን ከተፈጥሮም ከፈጣሪም አራርቆን የለ? እንዲያው እኮ። ሌላው ነገሩ ወዴት እንደሄደ ገብቶት፣ ‹‹እህ ሰው አይፈራም? ይፈራል እኮ…›› ብሎ ሰውየውን በሙሉ ዓይኑ ሳያየው መለሰለት። ሰውየው ቱግ ብሎ በአሽሙር፣ ‹‹ለነገሩ የፈሪ ወጉ ነው መፍራት…›› ብሎ ላይ ታች ሲገላመጥ ያኛው ቀበል አድርጎ፣ ‹‹ታዲያ ጀግንነትስ ከየት የመጣ ይመስልሃል?›› አለው አሉ። በአሉ እንጀምረው ብዬ እኮ ነው፡፡ በነገር የሚተጋተግ ልብ ለልብ ይተዋወቃል ይባላል። እኛን ያስቸገረን ግን ራስን ማወቅ ሳይሆን አይቀርም። እውነቴን እኮ ነው። ደርሶ ግንፍልተኛው አልበዛባችሁም? በበኩሌ ጦር ጠማኝ ባለፍ ባገደምኩበት እየተከተለ እየለከፈኝ ተቸግሬላችኋለሁ፡፡ ለነገሩ እኔም ሆንኩ እናንተ የሰለቸን አጉል ጀብደኝነትና ሴረኝነት እንደሆነ ባልናገር ትታዘቡኛላችሁ፡፡ ታዛቢ ጥሩ ነው!

የክፍለ ከተማ ጣጣ፣ የአገር ውስጥ ገቢ እንግልቱ፣ የተበጠበጠ ትዳሩ… ብቻ አንዱ ትዝ ብሎት፣ ‹‹ምን እዚህ አቧራ ታቦናላችሁ? አንተ ፑቲን ነህ? ወይስ ባይደን ነህ?›› እያለ ለዱላ የሚጋበዘውን እንኳን እኛ መንግሥትም አልቻለውም አሉ። ‹‹እንዴት ያለ ነገር ነው ጃል? የሚያማርረን ነገር በዝቶ ኑሮ መረረን ይሆን?›› ብዬ ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር ሳወራ ልጅ ከት ብሎ ስቆ፣ ‹‹ኮንዶሚኒየም ሳይደርሰን ጭራሽ በኑሮ ምሬት እንለቅ…›› ብሎ አላገጠብኝ። ቆይ ግን እኔ መቼ ይሰጠን አልኩ? ይኼን እኮ ነው የምላችሁ። ክብደት እንጂ መደማመጥ ቀንሰናል። እህ? ሰውዬው፣ ‹‹እኔ እያለሁ ፈራሁ ምንድነው?›› እንዳለው ሰው እያደር ተፈጥሯዊ የሆነውን ዑደት ሳይቀር በራሱ ምልከታ ብቻ እየተረጎመ፣ መንገዱን ‹ዋን ዌይ› ብቻ አድርጎ መድረሻ አጣን። እሱም ባልከፋ፣ ነገር ግን የሐሳብ ሙግት ጠፍቶ የገዛ ወገንን መጨፍጨፍ ሙያ የሆነበት ጊዜ ላይ መድረሳችን ያስከፋል፡፡ እኔ በበኩሌ እንዲህ ያለው ነውረኛ ድርጊት ከመብዛቱ የተነሳ ሥራም እያስጠላኝ ነው፡፡ ወገኖቻችን ያለ ጥፋታቸው ሲጨፈጨፉ የሚያስጥል ጠፍቶ አገር ስታነባ ሁሉም ነገር ያስጠላል፡፡ ይመራል! 

የቀጠሮዬ ሰዓት ደረሰ። ደንበኛዬ ከአውሮፓ የመጣች ጠና ያለች ወይዘሮ ነች። አገሩ ስለተቀያየረባት አንድም ከተማውን እያያዟዟርኩ ላሳያት፣ አንድም እጄ ላይ የነበረ ባለሦስት ፎቅ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት መግዛት ስለፈለገች ላገበያያት ተነስቻለሁ። በቤቱ ጉዳይ ወስና ስለነበር ብዙ አልተንከራተትኩም። በዕድገት ጎዳና ላይ ያለችውን አገራችንን (አዲስ አበባም ያው አገራችን ውስጥ ያለች አገራችን ናት) ማስቃኘቱ ግን አድካሚ ነበር። በራይድ ወዲህ ስወስዳት ወዲያ ሳመጣት በሲኤምሲ፣ በመገናኛ፣ በቦሌ፣ በሜክሲኮ፣ በሳር ቤት… ሳዞራት ዋልኩ። ‹‹ውጭ አገር ነው ያለሁት ኢትዮጵያ?›› ስትለኝ እኔ ደግሞ ዕድገቱን እያሞካሸች መስሎኝ፣ ‹‹ይኼውልሽ እንግዲህ የሚፈርስበት እየፈረሰበት፣ የሆነለት ደግሞ እያለማበት ያደግንበት ሠፈር ጠፍቶናል…›› እያልኩ እለፈልፋለሁ። ለካ ሴትዮዋ ባለፍን ባገደምንበት ሁሉ በእንግሊዝኛ ፊደል ፈረንጅኛ መጠሪያዎችን እያነበበች በሽቃ ነው። ‹‹የት ሄዶ ነው ኢትዮጵያዊው ፊደል?›› ስትለኝ ነው ነገሩ የገባኝ (ምን አውቃለሁ ቋንቋችንም እንደ ቡናችን ኤክስፖርት መደረግ ጀምሮ ይሆናላ)፡፡ ለነገሩ እንኳን እሷ እኛም ተቀዣብረን የለም እንዴ፡፡ ይደንቃል!

ነገርን ነገር ያነሳዋል። ለነገረኛም ነገረኛ ያዝለታል። አላዝልን እያለ የተቸገርነው በበሽታ ልክ መድኃኒት ብቻ ነው። ‹‹በሽተኛው በዛ መድኃኒት አነሰው…›› ያለው ዘፋኙ ወዶ መሰላችሁ? ‹ማንም የወደደውን ያገባና የዘፈነ የለም› እንዳትሉኝና እንዳልስቅ። ማንጠግቦሽ ሰሞኑን በገባች በወጣች ቁጥር፣ ‹‹አሁንስ መረረኝ፡፡ በድህነታችን ላይ ጭራሽ ጭፍጨፋ ምን ብንበድል ነው…›› እያለች ለመርሳት የሞከርኩትን ነገር ስታስታውሰኝ ብሶቴ ተቀሰቀሰ፡፡ እኔ ደግሞ ሆደ ባሻ ስለሆንኩ ምርር ይለኛል፡፡ ሰው እንዴት የገዛ ወገኑን በዚህ ደረጃ ጠልቶ ይጨፈጭፋል እያልኩ ስቃጠል፣ ‹‹አንበርብር እዚህ አገር የጎደለን ነገር ምን እንደሆነ ታውቃለህ… ብስለትና ድፍረት ነው የጎደለን፡፡ ራሳችንን አንቅተን መብታችንን ለማስከበር ደፋር ብንሆን ኖሮ የማንም መጫወቻ አንሆንም ነበር፡፡ እኛ ግን ንቃተ ህሊናችንን ከማጎልበት ይልቅ የወሬ ሱሰኛ ሆነን ወገኖቻችን ተገደሉ ሲባል ስንት ሰዎች ሞቱ እያልን የሒሳብ ማወራረጃ እናደርጋቸዋለን፡፡ አንድ ሰው ለምን ከሕግ ውጪ ይገደላል ብለን ከመጠየቅ ይልቅ፣ የትናንቱን የጅምላ ጭፍጨፋ ረስተን ዛሬ ስለተገደሉ ሰዎች ብዛት ወሬ እንቆፍራለን፡፡ ያልነቃና ያልተደራጀ ሕዝብ የገዳዮቹ መጫወቻ ነው የሚሆነው…›› ብላ በንዴት ስትጦፍ እኔም ደሜ ከፍ አለ፡፡ ደሜ ተንተከተከ ማለት ይቀላል!

ኋላ ታዲያ አስቤ አስቤ ሲደክመኝ ምሁሩን የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ውዴ ማንጠግቦሽ ስለከፋት ምን አባቴ ባደርግ ይሻለኛል?›› ብዬ ማማከር። ምን ይለኛል፣ ‹‹ቆይ ትንሽ ታገስ፣ ማንጠግቦሽ ብቻ አይደለችም መላ ሕዝቡ በቁጣ ተነስቶ ገዳዮች ለፍርድ ካልቀረቡ እንተያያለን ማለቱ አይቀርም…›› አለኝ። ‹‹እንዴት ሁሉም ሰው?›› ስለው፣ ‹‹የዛሬ 49 ዓመት የየካቲት 66 አብዮት ሲቀጣጠል እኮ ተማሪ ብቻ ሳይሆን፣ መላው ሕዝብ ነበር እኮ ጎዳናዎችን በሠልፍ ያንቀጠቀጠው…›› አለኝ። ያንን ታላቅ ሕዝባዊ አብዮት በዕዝነ ልቦና እያስታወስኩ፣ አሁን ያለንበትን ማስተዋል የጎደለው የሴረኝነት መንገድ ስታዘብ ምን ያህል ወደኋላ እንደቀረን እያሰላሰልኩ ነበር፡፡ ያ ታላቅ ሕዝባዊ ማዕበል የቀሰቀሰው ሕዝባዊ አብዮትም ለካ አርቆ ማሰብ በተሳናቸው ግንፍልተኞች እንዳይሆኑ ሆኖ ስንቶች እንዳለቁበት ሳስታውስ፣ ከትናንት የመጣ ውርስ ቅርፅና ይዘቱን ሳይቀይር የሴረኞች ሰለባ መሆኑ አልረሳህ አለኝ፡፡ የትናንት ዘመን ትራፊዎችና የዛሬ ተግደርዳሪዎች አንድ ላይ ተሸራርበው የሚያወራርዱት የበቀል ሒሳብ ሲታወሰኝ፣ ራሱ ፈጣሪ ጣልቃ ገብቶ እንዲገላግለን እየተመኘሁ ነበር፡፡ ዕድሜ ልክ በቀል፣ ጥላቻ፣ ክፋትና አሉባልታ ወረውን እኮ ነው ሰቆቃው የበዛው፡፡ ምርር ይላል!

ወደ ሥራዬ ስመለስ ከዳያስፖራዋ ጋር እየዞርኩ ነው፡፡ በዙረቴ ደግሞ ልማታዊ ባለሀብት ሆኜ ሕንፃ ገንብቼ በእንግሊዝኛ ስሰይመው በምኞት ይታየኝ ነበር። ነገር ግን እንኳንም አንዳንዱ ምኞት በነበር የሚቀር ሆነ። ዳያስፖራዋ ደንበኛዬ ነገሩን ችላ ብላ ማለፍ አቃታት። ጭራሽ ‹ፍሬንች ኪስ› የሚል ስያሜ ያለው ሕንፃ ስታይማ ራሷን ስታ እጄ ላይ ወደቀች። እኔ ያቀረብኩት ጥያቄ አንድ ነው።  ‹ከዚህች ሴትዮና ከእኔ ጤነኛው ማን ነው? አጥወልውሏት ራሷን ስታ እስክትወድቅ መያዣ መመለሻ ያጣው የማንነት ቀውስ፣ ለእኔ ምንም ያልመሰለኝ ምን ሆኜ ነው?› ብዬ ውሎ አድሮ አዛውንቱን ባሻዬን ስጠይቃቸው፣ ‹‹ዓይን እኮ ራሱን ዓያይም። አንተ ለችግሩ ቅርብ ነሃ። ተላምደኸው እየኖርክ ነው። ገና ብዙ ጉድ የሚሠራን ይኼው መላመድ ነው። ጠብቅ ባሻዬ ምን አሉ ትላለህ…›› ብለውኛል። እናም ከመልመድ ለመሸሽ መሰደድ አለብን? ሳይቃጠል በቅጠል እያለ? ለስደትስ የሚገፋፋን ይኼ እንደሆን ተጠንቷል? ወይስ ስደትን በተመለከተ ሕገወጥ ደላሎች ብቻ ናቸው ተጠያቂዎቹ? ለመሆኑ እኛ ግን ምን ሆነን ነው የማንነት ቀውስ ውስጥ የገባነው ያስብላል፡፡ ከማስባል አልፎም ማነጋገር አለበት!

እስኪ እንሰነባበት። አልፎ አልፎ ቢሆንም የምርጫ ቦርድ የድጎማ በጀት እንደበላ የፖለቲካ ፓርቲ ዕቁብ ከተበላ የምጣደፈው ነገር አለኝ። ማንጠግቦሽ ይኼን አዝጋሚነት እንዳሻሽል ደጋግማ ብትነግረኝም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ድጎማ ከሌለ በስተቀር ዘገምተኛ ልምዳቸውን እንዲተው ስንነግራቸው፣ የማይሰሙንን ፖለቲከኞች ይመስል አልሰማኋትም። በረባ ባረባው በጭቅጭቅና በአጉል ጥርጣሬ የጠፋውን ጊዜ የሚክስ ‹ኮሚሽን› አስገኝቶልኝ አንድ ቅጥቅጥ ሲሸጥ ስልኬ ጠራ። የጠፋ የሃምሳ ብር ካርዴን አግኝተውልኝ መስሎኝ ሳነሳው፣ በቀደም ዕለት አንድ የጎረቤታችን ሰው የቁጠባ ቤት ዕጣ ደርሶት ስለነበር ፌሽታ መደረጉን ሰማሁ። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ዛሬ ቢራ በነፃ የምንራጭበት ቦታ ተገኝቷል…›› ሲለኝ ወደ ሠፈሬ ከነፍኩ። እኔ ስደርስ ዕድለኛው ሰው ከሥራ ሲመለስ አንድ ሆነ። ቤቱ እስኪገባ እንደ መሲሁ ዘንባባ ተነጠፈለት። በዕልልታው ድምቀት መንደራችን በፌዴራል ፖሊስና እሳት አደጋ ተከበበች። ይኼን ያየ አንድ ነገረኛ ተናጋሪ፣ ‹‹ይኼኔ የአንዳችን ቤት እሳት ይዞት ቢሆን ነገም አይመጡ…›› አለ። ሌላው ቀበል አድርጎ፣ ‹‹ምን ታውቃለህ በቅናት ለሚቃጠሉት ከሆነስ የመጡት?›› ይለዋል። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ስማ! ዝም ብለህ አዳምጥ!›› ይለኛል። ነገሩ ሌላ መስሏቸው ሠግተው የነበሩ ሰላም አስከባሪዎች ጫጫታው በሌላ ጎኑ ጥሩ ቅስቀሳ መሆኑ ስለገባቸው፣ የደስታው አድማቂ ወደ መሆን ተገልብጠዋል። ‹አትገለባበጡና ዝም ብላችሁ ከንፈር ንከሱ…› ያለው ማን ነበር? እንጃ!

ሥነ ሥርዓቱን ለማደፍረስ የሚያስቡ እኩዮችን ከአፍራሽ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ የሚያስጠነቅቁም አሉ፡፡ ጭብጨባውና ዕልልታው የቀዘቀዘ የመሰላቸው አንዲት ወይዘሮ ደግሞ፣ ‹‹አዳሜ በደንብ አታጨበጭቢም? ነግሬያለሁ የዛሬ አምስት ዓመት እንኳን ለቤት ለጭብጨባውም ላትቆሚ ትችያለሽ…›› ይላሉ። ‹‹ምንድነው እርስዎ ደግሞ የሚያስፈራሩን? ከዚህ በላይ እጃችን ይቆረጥ?››› ሲል የፈራቸው ያመናቸው ደግሞ፣ ‹‹እንዴ ሌላው ዙር ዕጣ የሚወጣው የዛሬ አምስት ዓመት  ነው ማለት?›› ሲል ግራ ተጋብቶ ግራ ያጋባል። እንዲያው በአጠቃላይ በትንሽ ትልቁ ነገሩን ፖለቲካዊ አንድምታ ሊሰጠው የማይጥር የለም። ግርግሩ በረድ ብሎ እኔና የባሻዬ ልጅ ወደ ዕድለኛው ቤተሰብ ቤት ስንገባ ከየት መጡ ሳንላቸው ባሻዬ ከኋላችን ከች ብለው፣ ‹‹ትሰማላችሁ ሰው የሚለውን? ወይ ዕጣና ቁጠባ! የማያናግረን የለም እኮ…›› ብለውን ወደ ጓደኞቻቸው ተቀላቀሉ። እኛም ተገኘ ብለን ሁለተኛውን ቢራ ማጋባት ስንጀምር፣ ‹‹እኛ እዚህ ነገር ስንበላ ሌላው ወገናችን በጭካኔ ጥይት እየተደበደበ ምን ኑሮ ይባላል?›› የሚል ድምፅ ሲሰማኝ የበለጠ ራስ ምታት ለቀቀብኝ፡፡ ሌላው እየተንገፈገፈ፣ ‹‹አሁንስ በዛ፣ ከዚህ በላይ ትዕግሥት የሚሉት ቃል ራሱ ያስጠላል፣ አሁንስ ከመጠን በላይ በዛ ተንዛዛ…›› እያለን ምሬቱን ሲለቅብን ቢራውም አስጠላን፡፡ ሕይወትም አስከፊ መልኳ ብቻ እየታየን ጥርሳችን ተንቀጫቀጨ፡፡ አሁንስ በዛ! መልካም ሰንበት!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት